በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ከተዘነጉና አገልግሎታቸውም ምንአልባት ተቋርጧል ከሚል ደረጃ ከደረሱ የጤና ዘርፎች ውስጥ አንዱ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ነው። ይህ አገልግሎት ከወረርሽኙ በፊት በተለያዩ የመንግሥት ጤና ተቋማት ውስጥ ሳይቆራረጥ ይሰጥ እንደነበርና በዚህም በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደነበሩ ይታወሳል። ይሁንና ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ለወረርሽኙና ለሌሎች የጤና ጉዳዮች ይበልጥ ትኩረት በመሰጠቱ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት በሚገባው ልክ ለተጠቃሚው ሲደርስ አልነበረም።
ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና የታዩ መልካም እድሎችን ለመዳሰስ የሚያስችል ሶስተኛው የስነ ተዋልዶ ጤና ሲምፖዚየም ከሰሞኑ ተካሂዷል። በዚህ ሲምፖዚየም የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ የሙያ ማህበራት፣ መምህራንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል።
እነዚሁ በሴቶችና በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚሰሩ አካላትም በነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ የነበሩ ተግዳሮቶችን ለመለየትና ላጋጠሙ ተግዳሮቶች ምን አይነት መፍትሄዎች እንደሚያስፈልጉ ካላቸው ልምድ በመነሳት ለመጠቆም ሞክረዋል። አዳዲስ የጥናት ውጤቶችም ቀርበዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የማህፀንና ፅንስ ሐኪም ዶክተር ተስፋዬ ሁሪሳ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር የቤተሰብ እቅድን ጨምሮ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ተስተጓጉሏል። ይህንንም ተከትሎ የእናቶች ሞት መጨመር፣ የእናቶች እርግዝና ክትትልና የቤተሰብ አቅድ አገልግሎት መቀነስ ተስተውሏል።
ይሁን እንጂ በመገናኛ ብዙሃን ህብረተሰቡን በማንቃት፣ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች ከሌሎች የጤና አገልግሎቶች ጋር በጥምረት እንዲሰጡ በማድረግ አገልግሎቱን ለማሳደግ ተችሏል። ጤና ሚኒስቴርም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ሲሰራቸው የነበሩ ሥራዎችን ሲያጋራ ቆይቷል።
የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በሚመለከት ባለፉት ሁለት ዓመታት የተሰሩ ሥራዎች አሉ። በዚህ ሲምፖዚየምም በሁለቱ ዓመታት ውስጥ ከስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ የነበሩ እድሎች ተለይተዋል። ለአብነትም ህብረተሰቡን በማንቃት የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን የት አካባቢዎች ላይ ማግኘት እንደሚችልና አገልግሎቶቹን በምን መልኩ መጨመር እንደሚቻል ሃሳቦች ተጋርተዋል።
የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶች አሁንም እየተሰጡ እንደሆነና ህብረተሰቡ በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች አገልግሎቶቹን ማግኘት እንደሚችል መረጃዎች ሲሰጡ ቆይተዋል። ይህንንም ተሞክሮ በማስፋትና በመቀጠል አገልግሎቶቹ ከዚህ በፊት ከነበረው ቁጥር በላይ እንዲሰጡ የመፍትሄ ሃሳቦች ተጠቁመዋል።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባሻገር ሀገሪቷ ያጋጠማትን ጦርነት ተከትሎ በተከሰተው የውስጥ መፈናቀልና ሰብአዊ ቀውስ ምክንያት የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቱን ለዜጎች ለማዳረስ አዳጋች አድርጎታል። እነዚህኑ ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባትም ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ጥናቶችን በማካሄድ በነዚሁ አካባቢዎች ላይ አገልግሎቱ ተደራሽ እንዲሆን ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ይሁንና ከዚህም በላይ ከፍተኛ ርብርብ ይጠይቃል። ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።
የኢትዮጵያ ፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው እንደ ሚሉት የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በሚመለከት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ሀገሪቱ ከገባ ወዲህ መረጃ ከመሰብሰብ ጀምሮ እስከማጋራት ድረስ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። በተለይ ደግሞ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ለሚፈልጉ ሴቶች አገልግሎቱ በነዚህ ወረርሽኝ ምክንያት እንዳልተቋረጠና አሁንም እንደሚቀጥል መረጃዎችን በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የመስጠት ሥራዎች ተሰርተዋል።
በዚህም ከጤና ሚኒስቴር ጋርና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በተለይ በትምህርት ቤቶችና የፅንስና ማህፀን ህክምና ዙሪያ የሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎችና ተማሪዎች ያላማቋረጥ በተለያዩ ጊዜያት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል።
በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ከስነ ተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ አብዛኛዎቹ ግብአቶች በተለይ ደግሞ በወሊድ ጊዜና ከወሊድ በኋላ ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብአቶች የሚመጡት ከውጭ ሀገር በመሆኑና አብዛኛዎቹ የጤና ባለሙያዎችም ሥራቸው በኮቪድ ላይ በማተኮሩ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል።
የጤና ባለሙያዎች ያልተቋረጡ የህክምና አገልግሎቶችን በሚሰጡበት ጊዜ ራሳቸውን ከኮቪድ-19 በመጠበቅ አገልግሎቱን እንዲቀጥሉ በሚደረጉበት ጊዜ በቂ የሆነ ራስን የመከላከያ መሳሪያዎች አለመኖርም በስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጫና አሳድሯል። ይሁንና የተለያዩ ሀገር በቀል ሃሳቦችን በመጠቀም፣ እዚሁ በሀገር ውስጥ እንዲሰሩ በማድረግና ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ችግሮቹን ለማስቀረት በርካታ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ወረርሽኙን ተከትሎ በተለይ ወጣቶች ትምህርት ቤቶች ተቋርጠው በቤት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ማለትም የእርግዝና መከላከያ አለማግኘት፣ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል በሚል ወደ ጤና ተቋማት ያለመምጣትና ወደ ጤና ተቋማት ለመሄድና የጤና ባለሙያዎችን ለማግኘት የመፍራት ችግሮች ይታይባቸው ነበር።
ከነዚህ ችግሮች በመነሳትም ወጣቶቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ወደ ጤና ተቋማት እንዲመጡ፣ ከጤና ባለሙያዎች ጋር እንደሚመካከሩ፣ የሚያስፈልጋቸውን የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ጤና ተቋማትንም ለወጣቶች ምቹ እንዲሆኑና አገልግሎቶቹም ቀጣይነት እንዲኖራቸው በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለፃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎትን በመስጠት ሂደት በርካታ ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙም ከነዚህ ተግዳሮቶች ትልቅ ትምህርት መውሰድ ተችሏል። በተለይ ደግሞ ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ዝንባሌ በመኖሩ የስነ ተዋልዶ ጤና ትምህርትን በጥራትና በአነስተኛ ክፍል ውስጥ ለበርካታ ሰዎች ማስተማር እንደሚቻል፣ ዲጂታላይዝ ማድረግ፣ ኮምፒዩተሮችን መጠቀም፣ በይነ መረቦችን በመጠቀም ከተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ትምህርቶችን መማር፣ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መውሰድ ተችሏል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አሁንም ያለና ወደፊትም የመቀጠል አዝማሚያ እያሳየ በመሆኑ በቀጣይ ባለመዘናጋት እናቶችን በመደገፍ፣ በስነ ተዋልዶ ጤና የሚሰሩ ሥራዎችን በማጠናከር የተጀመሩ ሥራዎችን ማስቀጠል ያስፈልጋል።
ከኮቪድ-19 በተጨማሪ ሀገሪቱ በጦርነቱ ምክንያት ጫና ውስጥ ያለች በመሆኑ በተለይ የዚህ ችግር ዋነኛ ተጋላጭ ህፃናት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና እናቶች በመሆናቸው የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ግብአቶችን ከማሟላት አንፃር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ግብዓቶችን የማሟላት ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በተጨማሪም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑና ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ግብአቶች በሀገር ውስጥ የሚመረቱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥናቶችን በመሰብሰብ ለፖሊሲ እንዲያግዙ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አሉ።
የእናቶችና የህፃናት ጤና አገልግሎት መቋረጥ የማይችል በመሆኑ በተቻለ አቀም ጤና ተቋማት አሁንም ክፍት ሆነው የሚሰሩበትን ሁኔታ ለመቀጠል ሙከራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለዚህም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል። አሁንም ቢሆን በተለይ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከጤና ባለሙያዎች፣ ከሌሎችም አጋር ድርጅቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቀው የተቻለውን ሁሉ ሀብት በማሰባሰብ ህፃናት፣ እናቶችና ሴቶች ብሎም ወጣቶች ማግኘት የሚገባቸውን የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዳይቋረጥባቸው በጋራ መስራት ነው።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014