“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል” እንዲሉ፤ ሊበሏት አይደለም አጥምደው ሊይዟት ያልቻሏትን፣ የማይችሏትንም ታላቋን አገር ኢትዮጵያ ላይ ዛሬ ለክፉ ምኞታቸው የሚውል ስሙር የዳቦ ስም ማፈላለግ ከጀመሩ ውለው አድረዋል።
ምንም እንኳን ለመብላት የሚያስችላቸውን ተስማሚ ስም ሰጥተው ግዳይ ልትሆናቸው፤ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ሕልምና ምኞትም እስካሁን ሊጨበጥላቸው ባይችልም፤ በእነ ኢራን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታንና ሌሎችም አያሌ አገራት ይሄን መሰል የዳቦ ሥም በመስጠት ግዳዮቻቸውን በወጉ አጣጥመው ሕልምና ምኞታቸውን ማሳካት ችለዋል።
ዛሬ ላይም በኢትዮጵያ ላይ የያዙት አቅጣጫ ከዚህ የተለየ አይደለም። ሆኖም ይህ የእነርሱ ምኞት የኢትዮጵያውያን እውነት አይደለም። ምክንያቱም የአሜሪካም ሆነች አጋሮቿ ሕልም እና በኢትዮጵያ ያለው እውነት ለየቅል ናቸው። ምኞትና ሕልማቸው ኢትዮጵያ ፈርሳ እና ለእነርሱ የሚታዘዝ አሻንጉሊት መንግሥት ኖሯት ማየት ነው። ለዚህም ነው በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በዲፕሎማሲው እና በሀሰት የፕሮፖጋዳ ዘመቻው ላይ በፊት አውራሪነት በመምራት በኢትዮጵያውያን ላይ የሥነልቡና ጫና በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማንበርከክ እንቅልፍ ያጡት።
እዚህ ጋር አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ሀቅ አለ። ይሄም አሜሪካም ሆነች ግብራበሮቿ፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እንቅልፍ የሌላቸው፤ ሰብዓዊ ጥሰትን ለመከላከል እና ዴሞክራሲን ለማስፈን እረፍት የማያውቁ ሆነው ለዓለም መታየታቸው።
በዚሁ ስም አያሌ ሥራዎችን እንዳከናወኑ ሆነው መገለጣቸው ነው። ይሁን እንጂ እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ፤ የአሜሪካም ሆነች አጋሮቿ የሽብርተኝነት ጠላትነታቸው፤ የሰብዓዊነትና ዴሞክራሲ ተቆርቋሪነታቸው የማስመሰል እንጂ የእውነት መገለጫቸው አለመሆኑን እነሆ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አረጋግጠዋል።
ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያ ሕወሓት የሚባል አሸባሪ ኃይል ከማህጸኗ ወጥቶ ሲወጋት እና ሊያፈርሳት እንቅልፍ አጥቶ ሲሰራ፤ የሽብርተኝነት አምካኝ አድርገው ራሳቸውን የሳሉት እነ አሜሪካ ከአሸባሪ ጎን ቆመው ሲዋደቁና ኃይል ሊሆኑላቸው ሲታትሩ ታይተዋልና።
በሕወሓት የሽብር ቡድን የዴሞክራሲ ጭላንጭል ጠፍቶ የትግራይ ሕዝብ በግዳጅ ወደጦርነት ሲማገድ፤ አያሌ ንጹሃን በአማራ እና በአፋር ክልሎች ወረራ ተፈጽሞባቸው ሰብዓዊ ክብራቸውን ተገፍፎ ጭፍጨፋ ሲፈጸምባቸው ለእርዳታ የሄደ መኪናን እንዳይመለስ አድርገው የትግራይን ሕዝብ ሲያስርቡ የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ነን ባዮች ይሄን የሚመለከት ዓይን እንደሌላቸው ለዓለም ተገለጠ።
ይህ ግን ያለምክንያት አልነበረም፤ ይልቁንም የነዚህ አገራት ሁሉንም የሚያደርጉት ከራሳቸው ትርፍና ኪሳራ አኳያ አስልተው በመሆኑ ነው። ትናንት በእነ አፍጋኒስታን እና ሊቢያ ያደረጉትም ይሄንኑ ታሳቢ አድርገው እንደሆነው ሁሉ ዛሬም በኢትዮጵያ እያደረጉ ያሉት የእውር ድንብር ጉዞም የዚሁ ስሌታቸው ውጤት ነው።
ምክንያቱም በኢትዮጵያ ተክለውት የነበረው ታዛዥ መንግሥት መወገድ እና የኢትዮጵያ ቀና ማለት እረፍት ነስቷቸዋል። ኢትዮጵያ ደግሞ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ጭቁን ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲል እንደመሆኗ፤ ዛሬ ላይ እያሳየች ያለችው መቃናት ከራሷ አልፎ ለመላው አፍሪካውያን ከፍታ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት፤ ለአሜሪካና አጋሮቿ ደግሞ አፍሪካ ላይ ያላቸውን የዘመናዊ ቅኝ ግዛት ግስጋሴ የሚገታ መሆኑን መገንዘባቸው የበለጠ እረፍት ነስቷቸዋል። ለዚህም ነው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞ ገትቶ የትናንቱን አሻንጉሊት፣ የዛሬውን አሸባሪ ባንዳ ኃይል ወደስልጣን ለመመለስ ያለማቋረጥ የሚታትሩት።
ለዚህ ምኞታቸው ደግሞ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፤ ያልሞከሩት መንገድ የለም። እስከ ፀጥታው ምክር ቤት የዘለቀው የተባበረ ዓለም አቀፍ ጫና የማሳደር ሕልማቸው አልሰምር ሲላቸውም ነው ወደተናጠል ጫና የተሸጋገሩት። በዚህም አጎዋን የኢኮኖሚ፤ ኤምባሲዎቻቸውንና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶቻቸውን የዲፕሎማሲ ጫና ማሳደሪያ አድርገው መጠቀምን ተያያዙት። ለፕሮፖጋንዳውን ጦርነት ደግሞ የመገናኛ ብዙሃኖቻቸውን ዋና የሀሰት ወሬ መፈልፈያ ማሽን አድርገው እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ከሚፈጽሙት የገጽታን ማጠልሸት ያልተሳካ ሙከራ ጀምሮ፤ የአሸባሪው ቡድን አዲስ አበባን ከብቦ ያለ እና ከተማዋን መቆጣጠሩም የማይቀር ስለመሆኑ ያሰራጩት የበሬ ወለደ ወሬ ማሳያዎች ናቸው። ይህ ደግሞ በተለይ አሜሪካ እና ተከታዮቿ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎቻቸውን ስጋት ውስጥ በመክተት ከአዲስ አበባ እንዲወጡ በማድረግ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል የስነልቡና ጫና ውስጥ የመክተት የቆየ አቅጣጫና ስልት በአሜሪካ ፊት አውራሪነት (በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷና በአዲስ አበባ ኤምባሲዋ አማካኝነት) በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ላይ ያተኮረ ሽብር የመም ራት ተግባር ነው።
እውነታው ግን ኢትዮጵያ በምንም መልኩ መፍረስ የማትችል፤ ሕዝቦቿም አሻንጉሊት መንግሥት ተቀምጦላት ማየት የማይሹ መሆናቸው ነው። ለዚህም ነው ሕዝቦቿ በጽናት ቆመው ከዳር ዳር ከግንባር እስከ ደጀን ማንኛውንም መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉት። ይልቁንም የአሜሪካም ሆነ አጋሮቿ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ሕልም እውን ለማድረግ የበለጠ ጫናን ባሳደሩ ቁጥር፤ በተቃራኒው ኢትዮጵያውያን የበለጠ አንድነታቸው እየጠነከረ፣ አፍሪካውያን ወንድሞቻቸውም አጋርነት እየታየ እንዲሄድ እያደረገ ነው። ለዚህም ነው የአሜሪካና አጋሮቿ የተዛባ ጉዞ ሊታረም ይገባዋል የምንለው።
አዲስ ዘመን ኅዳር 11/2014