የጅማ ሰው ለሰው የአረጋውያንና ህፃናት መርጃ ማእከል መስራች ወይዘሮ ዘበናይ አስፋው ይባላሉ። ወይዘሮ ዘበናይ ትውልዳቸውም እድገታቸውም በጅማ ከተማ ሲሆን አባታቸው በአካባቢያቸው በለጋስነታቸው የሚታወቁ ለሰው ደራሽ ነበሩ። ወይዘሮ ዘበናይ በዘጠኝ ዓመታቸው የሶስተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ የተፈጠረው አንድ አጋጣሚ የአባታቸውን ፈለግ በመከተል ዛሬ ለሚሰሩት ሥራ ዋና መነሻ ምክንያት ይሆናቸዋል።
በዛች ቀን ከሁለት ጓደኞቿቸው ጋር ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ቆሻሻ በሚጣልበት ቦታ አሞሮችን ውሾች እያበረሯቸው ያያሉ። ነገሩ ግር ስላላቸው ውሾቹን እየጠበቁ ከሰማይ ወደ ምድር የሚምዘገዘጉት አሞሮች የሚያነሱትን ለማየት ጠጋ ሲሉ አንድ አራስ ህጻን ልጅ እያለቀሰ ያገኛሉ። ወይዘሮ ዘበናይ ጣር ይዞት የሚያለቅሰውን ህጻን ማየት አላስችል ብሏቸው ጓደኞቻቸውን ለሰው እንዲነግሩ ልከው ወደ ክፍል ገብተው ይቀመጣሉ። ትንሽ ቆይተው ሲረጋጉና ልጁ ተነስቶ እንደተወሰደ ሲነገራቸው በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር በመሥራት ህጻናቱን መታደግ እንዳለባቸው በልጅነት አእምሯቸው ለራሳቸው ቃል ይገባሉ። ቃል እንዲገቡ ያስገደዳቸው ግን ያ አጋጣሚ ቢሆንም ነገሩ የሚደጋጋም ስለነበረ ነው።
በዛን ወቅት በጅማ ዞን አቅራቢያ ከነበሩት ወረዳዎች የሚጥል በሽታ የነበረባቸውን ልጆች ከባእድ አምልኮ ጋር በማያያዝ ቤተሰቦቻቸው ከተማ እያመጡ ጥለዋቸው ይሄዱ ነበር። የተዛባው አመለካከት በኅብረተሰቡ ዘንድ በጣም የሰረጸ ስለነበር በሚጥል በሽታ የተያዙ ልጆች በጠጡበት የሚጠጣ በበሉበት የሚበላ በአጠቃላይ እነሱ የነኩትን የሚነካ አልነበረም። በሽታው ይተላለፋል ብቻ ሳይሆን የእርግማን ነው የሚል የተዛባ አመለካከት ስለነበር ቤተክርስቲያን እንዲገቡ አይፈቀድም ሲሞቱም የሚቀበሩት ራቅ ተደርገው ነበር።
በዚህም የተነሳ እነዚህ ህጻናት ያለ ሀጢያታቸው ያለ በደላቸው በቤተክርስቲያን አጥር ስር ሆነው በምጽዋት ለመኖር ይገደዱ ነበር። ወይዘሮ ዘበናይ አስፋው የሰንበት ትምህርት በቤተክርስቲያን ይከታተሉ ስለነበር የሚሆነውን ሁሉ በቅርበት ስለሚያዩ በልጅነት እድሜያቸው የእነዚህ ህጻናት ልጆች እንግልት ያሳቅቃቸው ነበር።
በሰንበት ትምህርት ቤት ቆይታቸው ስለልግስና ሲማሩ ደግሞ ለአእምሯቸው የቸርነትን መዳረሻ እነዚህን ልጆች መታደግን አድርገው ያስቀምጣሉ። በዛም ጊዜ ይህን ነገር በልጆች ላይ አምላክ ሊያደርግ አይችልም በማለት ለሰዎች እየተናገሩ በአቅማቸውም ልጆቹን እያጠቡ እያበሉ ይንከባከቧቸው ነበር። ለልጆቹና ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት ከቻሉም መድሀኒት በአግባቡ ካለመውሰድና ከረሀብ የሚመጣ ነው እያሉ ያስተምሩም ነበር። ነገር ግን ችግሩ ስር የሰደደ ስለነበርና ህመሙ ይተላለፋል የሚል የተዛባ አስተሳሰብ በማኅበረሰቡ ውስጥ ስለነበር በስፋት ለምነው ይኑሩ በማለት የገዛ እናቶች ልጆቻቸውን አሳልፈው ይጥሉ ነበር።
ይህም ሆኖ ወይዘሮ ዘበናይ እነዚህን ልጆች አቅማቸው በፈቀደ መንከባከቡን ይቀጥሉበታል። ከዓመታት በኋላ ግን አግብተው ከጅማ ሚዛን ወደምትባል ከተማ ያቀናሉ፤ እዛው እየኖሩ ሳለም ህጻናት ልጆችን በተመለከተ አንድ ነገር ያስተውላሉ። በአካባቢው ምንም የልጆች ትምህርት ቤት የለም። በመሆኑም ህጻናቱ አቅማቸው የቻለ ሥራ ሲሰሩ፤ ሌሎቹም ከቦታ ቦታ በአቧራና በጭቃ ሲዳክሩ ይውሉ ነበር። እናም ወይዘሮ ዘበናይ የተከራዩት ቤት ትርፍ ቦታ ስለነበረው ባለቤቶቹን አስፈቅደው የአካባቢውን ልጆቹ ማስተማር ይጀምራሉ። በጥቂት ግዜያትም በጣት በሚቆጠሩ ልጆች የተጀመረው ትምህርት እየተስፋፋ ይመጣና የተማሪዎች ቁጥር ሰማኒያ ይደርሳል።
እነዚህን ይዘው እያስተማሩ ለወራት ከቆዩ በኋላ የልጆቹ ወላጆች ያዩት ለውጥ እንዳይቋረጥባቸው በመስጋት በራሳቸው ተነሳሽነት አስር አስር ብር ይከፍሏቸው ይጀምራሉ። እሳቸውም የተማሪዎቹ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና ያላሰቡት ገቢም ስላገኙ አንዲት መምህር ቀጥረው በተደራጀ መልኩ መሥራቱን ይቀጥላሉ። ለራሳቸውም ወደ አዲስ አበባ በማቅናት የህጻናት መምህርነት ስልጠና ወስደው ተመልሰው ሥራቸውን አጠናክረው ይቀጥሉበታል።
በዚህ ሁኔታ እያሉና ትምህርት ቤቱንም ለማስፋፋት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በአካባቢው እንድ ሌላ ሰው ትምህርት ቤት ይከፍታል። አዲስ የተከፈተው ትምህርት ቤት የተደራጀ ቴሌቪዥንም አስገብቶ ስለነበር አብዛኛዎቹ ልጆቹ ወደዛው ይዛወራሉ። በዚህ ወቅት ያጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ባለቤታቸው ስላረፉ ወይዘሮ ዘበናይ የቀሩትን ልጆች በአካባቢው በገዳም ይኖሩ ለነበሩ ሴት መነኮሳት እንዲያስተምሩ አስተላልፈው ወደ ጅማ ይመለሳሉ። እነዛ መነኮሳት የእሳቸውን ፈለግ በማሳደግ ዛሬ ትምህርት ቤቱ አድጎና ተስፋፍቶ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል እያስተማረ ይገኛል።
እሳቸውም ወደ ጅማ ተመልሰው በመምህርነት ተቀጥረው መስራታቸውን ይቀጥላሉ። ከትንሽ ጊዜ ቆይታም በኋላ የራሳቸውን ትምህርት ቤት ከፍተው የተለያዩ የንግድ ሥራዎችንም እየሰሩ እቁብ በመጣል አባታቸው በሰጧቸው ቦታ ላይ ቤት ለመሥራት ይበቃሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ የቤት ኪራዩም እየመጣ ሥራቸውንም እየሰሩ በርከት ያለ ገንዘብ ሲያገኙ በልጅነታቸው ለራሳቸው የገቡትን ቃል ለመተግበር መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። በዛ ወቅት ግን ልጅ ብዙም የሚጣል ስላልመሰላቸው ነገሩ ቀርቷል በሚል እሳቤ በአምስት መቶ ሺህ ብር ቤት ገንብተው አረጋውያን ለመሰብሰብ ይወስናሉ።
አላማቸውም በጎዳና ያሉ አረጋውያንን በማንሳት ገላቸውን አጥበው በቀን አንድ ጊዜ ለማብላት በማሰብ ነበር። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ግን ይህ እንዳያሰናክሉኝ በሚል ስጋት ለማንኛውም የቤተሰባቸው አባል አልተናገሩም ነበር። እናታቸው አልጋና ፍራሽ እየተሰራ ሲገባ ቤቱ ለእንግዳ ማረፊያ ሊከራይ መስሏቸው ነበር።
ወይዘሮ ዘበናይ ግን ነገሩን በድብቅ ይዘው ቆይተው ሥራውን ለመጀመር አምስት ቀን ሲቀራቸው ለእናታቸው ይነግሯቸዋል። እናት ነገሩን ሲሰሙ ከልባቸው በማልቀስ እኔ ላደርገው የሚገባኝን አንቺ ስትሰሪ እንዴት እኔ እንቅፋት ልሆንብሽ እችላለሁ። ከዚህ በኋላ ሌላውም ቤተሰብ ምንም አይልሽም እንዲያውም ከጎንሽ እንቆማለን ብለው አብረዋቸው እንደሚሆኑ ቃል ገብተው መርቀው ያስጀምሯቸዋል።
ወይዘሮ ዘበናይም በነጋታው ወደ ጎዳና በመውጣት አረጋውያንን መሰብሰብ ይጀምራሉ። በዚህ ወቅት አንድ ሆቴል ይቀይር የነበረውን ብርድ ልብስና ትራስ ይሰጣቸዋል የተወሰኑ ሰዎችም አንሶላ ይደግፏቸዋል። የመጀመሪያዎቹን አረጋውያን ካነሱ በኋላ ግን ሌላ አጋጣሚ ይፈጠራል። ከጎዳና ከተነሱት መካከል አንደኛው አረጋዊ ስለታመሙ ለማሳከም ለትብብር የከተማው ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሲሄዱ አንድ አምስት ወር ያልሞላው ህጻን ሲያለቅስ ያገኛሉ። ምን ሆኖ ነው ሲሉ አባቱ ማሳደግ ስላልቻለ አስቀምጦት ሄዶ ነው ይሏቸዋል። ህጻኑ በጣም የተጎዳ ስለነበር ልውሰድና ላሳድገው ሲሉ፤ አይ የልጁ ጤና ትክክል አይደለም አይተርፍም ይሏቸዋል።
እሳቸውም ተቆጥተው ቢፈልግ እጄ ላይ ይሙት እንጂ እንዴት ትቼው እሄዳለሁ ይላሉ። እንግዲያው ለመውሰድ ከወሰኑ መጀመሪያ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ያስመዝግቡ፤ በዛ ላይ አንድ ቀን አባቱ መጥቶ ሊወስደው እንደሚችልም አይዘንጉ ይሏቸዋል። እሳቸውም አባቱ በፈለገ ጊዜ ይምጣና ይውሰደው፤ ለእኔ ዋናው ነገር ልጁን ማዳኔ ነው ብለው የመጣው ይምጣ በማለት አንዲት ጓደኛቸውን ይዘው ጣቢያ በመሄድ አስመዝግበው ህጻኑን ይዘው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ። እግረ መንገዳቸውንም የሚጣሉ ህጻናት ጉዳይ ዛሬም ያልተቀረፈ በመሆኑ መሥራት እንዳለባቸው ለራሳቸው ይነግራሉ።
ወይዘሮ ዘበናይ በዚህች አጋጣሚም የጀመሩትን ልጅ የመሰብሰብ ሥራም አጠናክረው ይቀጥሉበታል። ባለፉት ሶስት ዓመታትም በማእከሉ በአጠቃላይ ከአንድ መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ በላይ ሰዎችን በተለያየ ደረጃ መታደግ የተቻለ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት አምስት የኦቲዝም ተጠቂ ልጆችን ጨምሮ ከአንድ ወር እስከ አስር ዓመት የሚሆናቸው ሃያ አምስት ልጆችና ሃያ ስድስት አረጋውያን እንዲሁም ሌሎች የአእምሮ ህሙማንም ጨምሮ ሰባ ሁለት ችግርተኞች ድጋፍ እያገኙ ናቸው። በሌላ በኩል አካባቢው በጣም ጫት የሚቃምበት በመሆኑ ብዙ የአእምሮ ችግር ያለባቸው ሰዎች አሉ። ወይዘሮ ዘበናይም ከእነዚህ መካከል ችግሩ የሚጸናባችውን ሴቶች መርጠው ማኖር ይጀምራሉ።
ወይዘሮ ዘበናይ እነዚህን ሥራዎች ሲሰሩ በርካታ ችግሮች የሚገጥሟቸው ቢሆንም የጤና እክል ያለባቸውን ልጆች መንከባከቡ በጣም አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥም ሁለት አይኖቹ የማያዩ እጅ እግሩ የማይነቀሳቀስ ኦቲስት ልጅ ራሳቸው መኝታ ቤት ውስጥ አድርገው በመንከባከብ ላይ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ ከግል ክሊኒኮች መካከል ልጆችን በነጻ የሚያክሙላቸው ያሉ ሲሆን ጅማ ሆስፒታልም እስከ አምስት መቶ ብር የነጻ ህክምና አገልግሎት እየሰጣቸው ይገኛል። በተጨማሪ የጤና መድንንም የሚጠቀሙ ሲሆን አንዳንድ ውድ መድኃኒቶችን ለመግዛት ግን ዛሬም ቢሆን በችግር ውስጥ ናቸው።
በእነዚህ ዓመታት ወይዘሮ ዘበናይ በርካታ ውጣውረዶችን ያሳለፉ ቢሆንም አንደኛውን አሳዛኝ አጋጣሚ ግን እንደሚከተለው ያስታውሱታል። አንድ ቀን ወደ ሴቶች ጉዳይ ሲሄዱ ልጅ ያለማቋረጥ ጭንቅላቱ የሚያድግ ልጅ ያገኛሉ። ይህ ልጅ መጀመሪያ እናቱ ጥላው ከሄደች በኋላ ሌላ ሴት አንስታ ለማሳደግ ሞክራ መልሳ ስትጥለው ነው እሳቸው ያገኙት። ልጁ ከጭንቅላቱ ፈጣን እድገት በተጨማሪ ከጀርባው መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ይወጣ ነበር። ወይዘሮ ዘበናይ ይህንን ህጻን ወደ ሆስፒታል ሲወስዱትም አዲስ አበባ ወደ ጥቁር አንበሳ ውሰዱት ይሏቸዋል። እሳቸውም ሌሎቹን ዶክተሮች እንዴት ነው ተስፋ ካለው ይዤው ልሂድ ሲሉ ያማክሯቸዋል።
ዶክተሮቹም ይዘሽው አትሂጂ ጭንቅላቱ በየቀኑ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ስለሆነ ሊተርፍ አይችልም። እዚሁ በህይወት እስካለ የምንችለውን ድጋፍ እናደርግለታለን ይሏቸዋል። የልጁ ጭንቅላት በየቀኑ በጣም ይጨምር ስለነበር ጭንቅላቱን ብቻ ለማንቀሳቀስ አንድ ሰው ያስፈልግ ነበር። ይህም ሆኖ ልጁ የሚቻለው ሁሉ ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገለት ሶስት ወር ከኖረ በኋላ አረፈ።
ሰው ለሰው የበጎ አድራጎት ማእከል ከሰኔ አንድ ሁለት ሺህ አስር ጀምሮ ሕጋዊ እወቅና አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። አምስት የቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን ከበጎ ፈቃደኞች ውጭ በተጨናነቀ ሁኔታ የሚሰሩ አስራ ሁለት ሠራተኞች አሉ። ከሀምሳ ብር ጀምሮ የሚከፍሉ ሁለት መቶ የሚደርሱ አባላት አሉት። አንድ የማዕከሉን ልጆችና ሌሎችንም የሚያስተምር አጸደ ህጻናትም አለው። በጅማ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ እስካሁን የዶሮ እርባታ ሲያረቡና ሲደግፉ የነበረ ቢሆንም ከሶስት ወር በፊት በመኖ መወደድ አቁመዋል።
ወይዘሮ ዘበናይ የጀመሩትን ሥራ ለማስፋፋት እቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም ሁለት መቶ ካሬ ሜትር የሚሆን ጎረቤታቸው የነበረ የቀበሌ ቤት ሰዎቹ ሊለቁ ሲሉ ጠቁመዋቸው በብዙ ውጣ ውረድ መንግሥት ሰጥቷቸዋል። ራሳቸው በገዙት ሌላ ቦታ ላይም ባለሁለት ወለል ፎቅ ቤት በመሥራት ለማስፋፋት እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ከተሳካላቸው ለአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ገቢ ማስገኛ፤ መኖሪያ፤ ሥራ መሥሪያና መንሸራሸሪያ የሚሆን አሥራ አምስት ሺህ ካሬ ቦታ ከመንግሥት ጠይቀው ምላሹን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። በተጨማሪ ለሀያ ዓመት ያለሥራ የቆመ ቤት በአቅራቢያቸው በመኖሩም ለጊዜውም ቢሆን እንዲጠቀሙበት ጥያቄ አቅርበው በተመሳሳይ ምላሽ በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ። ለማእከሉ አገልግሎትና ለገቢ ማስገኛ ለሽያጭ የሚውል ፈሳሽ ሳሙናና ሻማ ለማምረት እንዲሁም ዳቦ ለመጋጋርና ለማቅረብም እቅድ አላቸው።
ወይዘሮ ዘበናይ የሁለት ወንድ ልጆች እናት ሲሆኑ አንዱ የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሲሆን አንደኛው የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ነው። እነዚህ ልጆችም የደከመ ከመንከባከብ የሞተ እስከመገነዝ አብረዋቸው ይሰራሉ። የአካባቢው ነዋሪም አቅሙ በፈቀደ በሞራልም ከሚበላውና ከሚጠጣው ከሚለብሰውም እየቀነሰ እየደገፋቸው ሲሆን በቅርቡም የተደጋፊዎችን ቁጥር ለመጨመር ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ይገኛል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2014