ውፍረት ምቾት ሳይሆን በሽታ ነው

በዓለምም ሆነ በሀገር ደረጃ ውፍረትን (obesity) በራሱ በሽታ አድርጎ የመቀበል ሁኔታ እምብዛም ነው። ከዚያ ይልቅ ወደ ሌሎች በሽታዎች የሚመራ አጋላጭ ሁኔታ (risk factor) ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል። ለዚህ አንዱ ክፍተት አሁን ያለው የውፍረት ትርጉምና ግንዛቤ ከነባራዊ ሁኔታው በጣም የራቀ መሆኑ ነው። ይህ እይታ በሕክምና ባለሙያዎች ዘንድም ለመግባባት እና በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ ሕክምናዎችን በበቂ ሁኔታ ለመስጠት ፈታኝ ሆኖ እናገኘዋን።

ስለውፍረት በሽታ መነሻ ጭምር ሳይንሱ የሚያብራራበት ሁኔታ የበሽታውን ውስብስብነት በሚያሳይ መልኩ አይደለም። በቂ ግንዛቤ የሚሰጥም ሆኖ አልተገኘም። ስለዚህም ትርጓሜው ሲሰጥ የተለያየ ተደርጎ ነው። አንዳንዴ ውፍረትን ከመጠን በላይ በመብላትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ የሚያመጣው የስንፍና መገለጫ ተደርጎ ብቻ ይሳላል። ይህ ደግሞ የተሳሳተ ሕክምናም ሆነ የተሳሳተ ግንዛቤ እንድንይዝ ያደርገናል። በመሆኑም ውፍረት ምንድነው፤ እንደ በሽታ ይቆጠራል፤ እንዴት ይከሰታል፤ ሕክምናው ምን ይመስላልና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ከሆኑት ከዶክተር ኤደን ሙላቱ ጋር ቆይታ አድርገናል።

ለውፍረት የሚሰጠው ትርጓሜ አስመልክቶ በዓለም ጤና ድርጅት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት ተጠቂዎች ሆነዋል።

እ.ኤ.አ ሐምሌ 2024 የታተመው አዲሱ ባለ 28 ማሕቀፍ የአውሮፓ ውፍረት ጥናት ማህበር (European Association for the Study of Obesity) መመሪያም ይህንን ነጥብ በተመለከተ እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል። የውፍረት ምርመራ፣ ደረጃ እና ሕክምና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል። ምክንያቱ ደግሞ ስለውፍረት ያለው አረዳድ፣ ትርጓሜ፣ ስያሜና መለኪያዎቹ ገና ያልዳበሩ በመሆናቸው ነው ይላል።

ከዚህ አንጻርም በመነሳት ዶክተር ኤደን ብዙዎች የሚስማሙበትን የውፍረት ትርጓሜ እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል። አንድ ሰው ወፍራም ነው አይደለም የምንለው መጠነ ክብደቱ፤ ከቁመቱ ጋር አካፍለን የምናገኘው ውጤት (Body mass index) ተመጣጣኝ ነው አይደለም የሚለው ላይ ስንደርስ የምንናገረው ነው። ችግሩ ከተፈጠረ ደግሞ ሰውነት ከሚችለው አቅም በላይ እንዲሸከም ያስገድደዋል።

ውፍረት በሽታ ነውን?

ከመጠን ያለፈ ውፍረት በሽታ ነው። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ባለሙያውን ጨምሮ ውፍረትን እንደ ህመም ያለመቁጠር ሁኔታ ይታያል። የጎንዮሽ ችግሮቹን ብቻ ተመልክቶም ጤነኛ እስከ ማድረግ የሚደርስበት ሁኔታ አለ። ወፍራም የሆነ ሰው የመገጣጠሚያ ህመሞች ሲከሰቱበት በብዛት ይታያል። ለዚህ ደግሞ ተያያዥ ምክንያቶች ሳይሆኑ ራሱ ውፍረቱ የፈጠረው ችግር ነው። ስለሆነም ይህንን መቀበል ያስፈልጋል፤ ራሱን የቻለ ሕክምናም መስጠት የግድ ይላል።

ለብዙ ዓመታት ክብደት በኪሎ ግራም ሲካፈል ቁመት በሜትር (BMI) ጤነኛ መሆን አለመሆን ለመገምገም ዋናው መለኪያ ሆኖ አገልግሏል። ለማስላትም ቀላል ስሌት ተመራጭ የጤና መለኪያ ተደርጎ ተወስዷል። ይህ ግን በጡንቻ ፈርጣማ ለሆኑት እና ጠንካራ አጥንት ላላቸው ሰዎች አይሆንም። በስብ ስርጭት (fat distribution) ላይ ያለውን ልዩነትም አያመለክትም። ለአብነት፣ ጡንቻ የገነባና ዝቅተኛ የሰውነት ስብ መጠን ያለው አትሌትና ብዙ ጡንቻ የሌለው ቦርጫም ሰው ተመሳሳይ ወይም እኩል BMI ሊኖራቸው ይችላል። ነገር ግን እነኚህ ሁለቱ ሰዎች እኩል ጤናማ አይደሉም። ቦርጫሙ ሰው BMIዩ መደበኛ ክልል ውስጥ ቢሆንም ቅሉ አደገኛ የሆነ የስብ ክምችት ሊይዝ ይችላል።

ውፍረት ከስያሜው ጀምሮ “ከስብ መብዛት ጋር የተያያዘ ስር የሰደደና የሚያገረሽ ህመም ጭምር (Adiposity Based Chronic Disease) ነውና ቁመትና ክብደትን ብቻ በመለካት የሚመጣውን ውጤት( Body mass index) በማየት የወፍረት በሽታ አለበት የለበትም ማለት አይገባም። ምክንያቱም ውፍረት ሲባል ከክብደትና ከBMI ቁጥር በላይ ውስብስብነት ያለው መልከ ብዙ ህመም ነው። ስለሆነም ሌሎች ተጨማሪ ስልቶችን ተጠቅሞ በሽታውን በትክክል መረዳት ያስፈልጋል። አንዱና ዋነኛው ደግሞ የስብ መጠንን በአግባቡ መለየት ነው።

የስብ መብዛት እንዴት ይለያል?

ቢ ኤም አይ( BMI )ስለ ስብ ስርጭት ምንም መረጃ አይሰጥም። ይህንን ማወቅ ካልተቻለ ደግሞ የውፍረትን ሁኔታ ለማወቅ አዳጋች ነው። እንደሚታወቀው አብዛኛው ስብ የሚያከማችበት ቦታ የት ነው” የሚለው ለጤና ወሳኝ ጉዳይ ነው። በሆድ አካባቢ የተከማቸ ከመጠን በላይ ስብ (“appleshaped” bodies) በተለይም ጉበትና ሌሎች የውስጥ ሰውነት ክፍሎቻችን (visceral fat) ላይ ሲጠራቀም እንደ ስኳር እና የልብ በሽታ ለመሳሰሉት የሜታቦሊክ በሽታዎች የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ነው።

በአንጻሩ ደግሞ በዳሌና ጭን አካባቢ ላይ ያለ ስብ የሚበዛባቸው ሰዎች (“pear-shaped” body) ለሜታቦሊክ በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸውም እንዲሁ ቀላል አይሆንም። BMI ግን ይህንን ስለማያሳየን ሰዎችን ለውፍረት በሽታ በብዙ መልኩ ያጋልጣቸዋል። በተመሳሳይ BMI በእድሜ፣ በጾታና በዘር መካከል ያለውን የበሽታ ተጋላጭነት ልዩነት ግምት ውስጥ አያስገባም። ከእነዚህ አንጻርም የBMI ጉድለቶች በርታ ነውና የውፍረትን በሽታ ለመለየት ተጨማሪ የመለኪያ ዘዴዎችን መጠቀም የግድ ይላል። ውፍረት እና ተዛማጅ የጤና ችግሮችን ለመገምገም አዳዲስ መለኪያዎችን መጠቀምም ያስፈልጋል።

ይህንን ማድረግ ደግሞ እንደ ስኳር፣ የልብ ሕመም እና አንዳንድ የካንሰር በሽታዎች ካሉ ሥር የሰደዱ ገዳይ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድልን ይቀንሳል። ከመጠን በላይ ውፍረትን እና ተጓዳኝ ስጋቶቹን ለመረዳትም ያስችላል። ከዚህ አንጻርም ከ BMI በተጨማሪነት መለኪያ ተደርገው የሚወሰዱት የሚከተሉት ናቸው።

አንዱ ልኬቱ የወገብ ዙሪያ ከዳሌ ስፋት ጥምርታ (Waistto-Hip Ratio) የመለኪያ ዘዴን መጠቀም ነው። ይህም በእምብርት ልክ ያለው የወገብ ስፋትን ከዳሌ ስፋት ጋር የሚያነጻጽር መለኪያ ነው። የወገብ ከዳሌ ጥምርታ ከፍ ካለ በሆድ አካባቢ የተከማቸ ብዙ ስብን (belly fat) ይጠቁማል። ይህም ከBMI የበለጠ የልብ እና የስኳር ህመም ተጋላጭነትን ይተነብያል።

ሌላኛው ልኬት የወገብ ስፋት (Waist Circumference) ሲሆን፤ አደገኛ የሆድ ውስጥ ስብን ለመገመት ሁነኛ መፍትሔ ነው። በግርድፉ ሲታይ BMI ምንም ይሁን ምን የወገብ ከዳሌ ስፋት ጥምርታ ከአንድ ሜትር በላይ ከሆነ ወይም የወገብ ዙሪያ ስፋት ከ80 ሳንቲ ሜትር በላይ ከለካ ጤናማ ያልሆነና መፍትሔ የሚሻ አደገኛ የስብ ክምችት አለ እንደማለት ነው። ምክንያቱም ቀጭን ሰዎች ሳይቀሩ በዚህ ውስጥ የሚካተቱበት ሁኔታ ይከሰታልና።

ሶስተኛው መለኪያ የሰውነት ስብ መጠን መቶኛ (Body Fat Percentage) ሲሆን፤ ይህ መለኪያ ከሰውነታችን ክብደት ውስጥ ስብ ስንት በመቶውን ይይዛል የሚለውን የሚገምትበት ዘዴ ነው። የስብ መጠን በመቶኛ (Percent) ከሚለካባቸው መንገዶች መካከል የቆዳ እጥፋት መጠን (skinfold measurements)፣ ባዮ-ኤሌክትሪካል ኢምፔዳንስ (bio-electrical impedance) እና ልዩ ኤክስሬይ (DEXA scan) የመሳሰሉ ዘዴዎች ይገኙበታል። ስለሆነም ይህንን አውቆ መሥራት ይገባል።

የውፍረት ምልክቶች

የውፍረት ምልክቶች ልዩ ልዩ ናቸው። የመጀመሪያው የውፍረት መጠናችን ከሚጠበቀው በላይ መሆን መጀመር ነው። ሁኔታው ሙሉ አካልን አለያም የተወሰነ የሰውነት ክፍላችን ላይ ሊሆን ይችላል በስፋት የሚታየው። መገጣጠሚያ አካባቢዎች ላይ የተለየ ስሜት መሰማት፤ ለመራመድ መቸገር፤ የሰውነት መድከም ስሜት መኖር ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

መነሻ ምክንያቶች

ለውፍረት ብዙ ጊዜ መነሻ ምክንያቱ ልዩ ልዩ ተደርጎ ይወሰዳል። የመጀመሪያውና ዋነኛው የሚባለው የምንበላው ምግብና የምናወጣው ጉልበት ያለመመጣጠን ነው። ሌላው ከቤተሰብ ሲወረስ፤ ለተለያዩ የሆሮሞን በሽታዎች የሚወሰዱ መድኃኒቶች፤ እንቅስቃሴ አለማድረግና በቂ እንቅልፍ ያለመተኛት እንዲሁም ከተፈጥሮ ምግቦች ይልቅ የታሸጉና በፋብሪካ የበለጸጉ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ በዋናነት ይጠቀሳሉ።

አሁን ላይ በእነዚህና መሰል ምክንያቶች የተነሳ አብዛኞቹ ሕፃናትና ወጣቶች ለከፋ ችግር እየተጋለጡ ይገኛሉ። የአጥንት እድገት መድከም፤ አጥንት መሸከም ካለበት ክብደት በላይ እንዲሸከምና አጥንት በተፈለገው መንገድ እንዳይጠነክር እየሆነም ነው።

የውፍረት በሽታ ከጾታ አንጻር በአብዛኛው ሴቶች ላይ የሚያጋጥም ሲሆን፤ ለዚህም የተለያዩ ሕክምናዎች ይሰጣሉ።

ሕክምናው

ብዙ ጊዜ ውፍረትን እንደ በሽታ ባለመቁጠራችን የተነሳ ታካሚዎችን በቀላሉ ለማግኘት ያስቸግራል። ከመጡም በኋላ ቢሆን የመጡበትን በሽታ ቅድሚያ የማየቱና ዋናውን ችግር ያለማከም ክፍተቶች ይታያሉ። በዚህም በውፍረቱ የተነሳ ከመገጣጠሚያዎች ችግር ባለፈ ለተለያዩ ተጨማሪ በሽታዎችም ሰዎች እንዲጋለጡ ይሆናሉ። በዋናነትም እንደ ስኳር፤ ለግፊትና የልብ በሽታ እንዲያጋጥማቸው ያደርጋቸዋል።

ውፍረት እግርን እስከ መቆለፍ ድረስ የሚደርስ የጎንዮሽ ጉዳትን የሚያመጣ በሽታ ነው። የአጥንት የመገጣጠሚያ ችግርን፤ ሰውነት እንደፈለገ እንዳይንቀሳቀስና እንዳይሰራ ያደርጋል፤ የስነልቦና ጉዳትም አለው። ስለዚህም ሰዎች ውፍረት በሽታ አይደለም ከሚለው አስተሳሰብ ሊወጡ ይገባቸዋል። ተያያዝ ችግሮች እስኪገጥማቸውም ድረሰ ከቤታቸው መቆየት የለባቸውም። ወደ ሕክምና ተቋማት በመምጣት ሁኔታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።

በባለሙያዎች ዘንድም ያለው ምልከታ መቀየር ይኖርበታል። ውፍረትን የጎንዮሽ ጉዳቱን ብቻ ከማየት ይልቅ እንደማንኛውም በሽታ ማከም ያስፈልጋል። ለዚህም ሕክምናውን ሰፋ አድርጎ ማየት ይገባል። ውፍረት ሲታከም መነሻ ምክንያቱን ለይቶ ማውጣት ያስፈልጋል። የችግሩ መንስኤ መድኃኒቶች ከሆኑ መድኃኒቶችን መቀየር፤ ሌሎች በሽታዎች ከሆኑ ደግሞ በሽታውን ለይቶ እንዲታከም ማድረግ ወሳኝነት አለው።

በዋናነት ግን ሕክምናው ሊሆን የሚገባው እንቅስቃሴ ማድረግና አመጋገብን ማስተካከል እንዴት እንደሚችሉ መንገር ነው። ታካሚዎችም የተሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይገባቸዋል። ከዚያ ባሻገር የውፍረቱን ሁኔታ ከመደበኛው መለኪያ በተጨማሪ ሌሎች የተጠቀሱትን የመለያ ዘዴዎች መጠቀምም ተገቢ ነው።

መከላከያ ዘዴው

እንደ ሀገር የጤና መርሃ ግብሮች ማዘጋጀትና ስለ ውፍረት በሽታ ያለውን ግንዛቤ ማሻሻል ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ለዚህም ከጤና ኤክስቴንሽኖችና የዘርፉ ባለሙያዎች መጀመር የግድ ይላል። ከዚያ ማኅበረሰቡ እንዲያውቀው በስፋት መሥራት ያስፈልጋል። በተለይም ማኅበረሰቡ ውፍረትን መፋፋትና መመቸት አድርጎ ስለሚወስደው ይህንን ሃሳብ ማስቀየር ላይ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ይሆናል።

‹‹መንገድን ለሰዎች ጤና›› በሚል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል ብዙ መንገዶች ቅዳሜና እሁድ ተዘግተው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ይደረጉ ነበር። ይህ ደግሞ ብዙዎችን ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ ያስቻላቸው ነበር። ሆኖም አሁን ላይ በተለያየ መልኩ እነዚህ ተግባራት ቀንሰዋልና መታየት ይኖርባቸዋል። ችግሮች ተለይተውም ዳግም ሊጀመሩና የሰዎችን የጤና ጉዳት ሊታደጉ ይገባል ሲሉ ዶክተር ኤደን ይመክራሉ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You