ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በቅኝ ግዛትም ይሁን በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በኩል የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለመድፈር የመጡ የውጭ ወራሪዎችንና የአገር ውስጥ ተላላኪዎቻቸውን ቅዠት በማመከን ይታወቃሉ።
በዓድዋ በጣልያን ወራሪ ኃይል ላይ አይቀጡ ቅጣት በማሳረፍ የቅኝ ገዥዎችን ከንቱ ምኞት በማክሸፍ ለአፍሪካውያን ጭምር ታላቅ ገድል ጽፈዋል። ይህ ገድል የፋሽስት ጣልያንን እንዲሁም የተስፋፊውን የሶማሊያ ወረራዎችን በማምከንም ተደጋግሟል። ኢትዮጵያውያን አገራቸው ለቅኝ ገዥዎች ፈጽሞ የማትመች አገር መሆኗን በእነዚህ ታሪካዊ ወቅቶች ለዓለም ጭምር አሳይተዋል።
ቅኝ ገዥዎች ከዚያም ወዲህ ለኢትዮጵያ ጨርሰው አልተኙም። በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሊበቀሏት፣ በጠላቶቿ በኩል ሊወጓት ያልሞከሩበት ጊዜ የለም። የአገሪቱን መዳከም፣ ጠንካራ ሆኖ አለመውጣት ሁሌም ይፈልጋሉ። ይህንንም ለኢትዮጵያ ጠላቶች ድጋፍ በማድረግ አሳይተዋል።
በ1969 እና 1970 ታላቋ ሶማሊያን ለመመስረት በሚል ቅዠት የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ምስራቅ እና ደቡብ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የጦር መሳሪያ ግዥ ማእቀብ በመጣል ለኢትዮጵያ ያለውን ጥላቻ አሳይቷል። በወቅቱ ልክ እንዳሁኑ ሁሉ ግብጽን ጨምሮ በርካታ የአረብ አገሮች ለሶማሊያ ድጋፍ በመስጠት ኢትዮጵያ ላይ ጫና በማሳደር ታሪካዊ ጠላትነታቸውን አስመስክረዋል።
የምዕራባውያኑ እና የአረብ አገሮች ደባና ለሶማሊያ ያደርጉ የነበረው ድጋፍ የዜያድ ባሬን ቅዠት ቅዠት አድርጎ አስቀረው እንጂ እውን ሊያደርገው አልቻለም። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ግን ከዳር እስከ ዳር ተጠራርተው በአንድ ልብ ሆነው፣ በአውደ ውጊያው በመሳተፍ፣ ለጦርነቱ የሚያስፈልገውን ሀብት በማሰባሰብ፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ የዘማች ቤተሰብን በመንከባከብ ታላቅ ገድል በመፈጸም ወራሪውን የዚያድ ባሬን ሠራዊት በመደምሰስ ዳር ድንበራቸውን አስከብረዋል።
እነዚያ ኢትዮጵያውያን ዛሬም በልጆቻቸው ህያው ናቸው። አገራችን በአሁኑ ወቅት የተከፈተባትን ዘርፈ ብዙ ጦርነት እነዚህ ኢትዮጵያውያን በመመከት የአባቶቻቸውን ገድል ከመድገም በተጨማሪ የራሳቸውን የጀግንነት ታሪክ በወርቅ ቀለም እየጻፉ ናቸው።
ከሀዲው ትህነግና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሆኑት የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ሊያፈራርሱ ያልከፈቱት የውጊያ አይነት የለም። ይህን ጦርነት ነው የዘመኑ ትውልድ በድል ለመወጣት መጠነ ሰፊ ተጋድሎ እያደረገ የሚገኘው።
በዚህ ዙሪያ አንድ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ አለ። ይህ ትውልድ የገጠመው አሸባሪውን፣ ከሀዲውንና ተላላኪውን ትህነግ ብቻ አይደለም። እንደ አያት ቅድም አያቶቹ ጣልቃ ገቦችንም እንጂ። አገር የማፍረስ አጀንዳቸውን እንዲያስፈጽም ውክልና የሰጡት ደግሞ ለአሸባሪው ትህነግና ለቡችላው ሸኔ ነው።
ትህነግ የቀበራቸው የጦር መሳሪያዎች ቢኖሩትም ከእነዚህ ኃይሎች ዘመናዊ የመገናኛ መሳሪያ፣ በሰብዓዊ እርዳታ መልክ ስንቅ፣ መድሃኒት፣ የሳተለይት መረጃዎችን እያገኘ ነው። በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ታስቦበት በተቀናጀ መልኩ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ሀሰተኛ መረጃ እየተለቀቀም ነው። ዘመቻው የውጭ አገር ወታደሮች አብረውት ስለመኖራቸውም በግንባር ላይ ተረጋግጧል። እነዚህ ሁሉ ጦርነቱ ከውጭ ኃይሎች ጋር ስለመሆኑ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
ኢትዮጵያውያን እያካሄዱት የሚገኙት የሕልውና ዘመቻ የአያት ቅደመ አያቶቻቸውን ታሪክ መድገም የሚችሉበትን ዕድል ይዞ መጥቷል። ኢትዮጵውያንም ይህን ታሪክ ለመድገም በሁሉም አቅጣጫ ዘምተዋል። መንግሥት ያቀረበውን የክተት ጥሪ ተከትሎ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ጊዜ አልወሰደባቸውም። በየማሰልጠኛ ተቋማቱ በመግባት ስልጠናውን ተከታትለው በግንባር ዘምተው ድል እያስመዘገቡ ናቸው። ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ከስር ከስር ሠራዊቱን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
ልዩ ኃይሎች፣ ሚሊሺያዎች፣ ፋኖዎች፣ በጡረታ የተገለሉ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ከአገር መከላከያ ጎን ሆነው የተላላኪውን ትህነግ እኩይ ተግባር እያመከኑ ናቸው። የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት፣ ጭምር ጦር ግንባር ድረስ ዘምተው አገርን ለማዳን በተጋድሎ ላይ ናቸው።
ወጣቶች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሁን እንደ ፊቱ በጠላት ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ እየተበገሩ አይደለም፤ በመጡ በመጡ ወሬ ተሸብረው አካባቢያቸውን ጥለው ከመውጣት ተቆጥበው አካባቢያቸውን በንቃት መጠበቁን ተያይዘውታል፤ ይህ ብቻም አይደለም ለሠራዊቱ የመረጃ ምንጭ፣ ስንቅ እና ትጥቅ አቅራቢ ሆነዋል። ዲያስፖራው ምዕራባውያኑ እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ በሰላማዊ ሰልፍ፣ የተለያዩ መድረኮችን በማካሄድና በማህበራዊ ሚዲያው አንድ ሆኖ እየታጋለ ነው። ለሠራዊቱና ለተፈናቃዮች የሚደርገው ድጋፍም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዚህ ጦርነት ትህነግ እና ጋላቢዎቹ ምዕራባውያንና ሌሎች የውጭ ኃይሎች የሚነዙት ሀሰተኛ መረጃ ሌላው ግንባር ነው። በዚህ ግንባር ጥቂት በማይባሉ አካባቢዎች ሕዝብ በትህነግ ሀሰተኛ መረጃ እየተፈታ ቀዬውን እየለቀቀ ወጥቷል። ይህ ሁኔታም ትህነግ ያለምንም ጦርነት ከተሞችን የተቆጣጠረበት ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው የሚባለው እውነት ስለመሆኑ በዚህ ጦርነት ወቅት በግልጽ ታይቷል። አሜሪካን ጨምሮ አውሮፓውያንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ሕዝብን ለማሸበርና አገርን ለማፍረስ እየሰሩ ናቸው።
በዚህ ግንባር የተከፈተብንን ጦርነትም ቢሆን አሁን መመከት ጀምረናል። በአሸባሪው ሕወሓት ሀሰተኛ መረጃ የማይበገር ሕዝብ መፍጠር እየተቻለ ነው። ሕዝቡ በሀሰተኛ መረጃ መረበሹን ትቶ ከጠላቱ ጋር ተናንቆ ለመውደቅ ወስኖ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ሚናውን እየተወጣ ነው።
መንግሥት በቅርቡ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተክትሎም ሕዝቡ የሕልውና ዘመቻውን ሊገዳደሩ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ከመንግሥት ጋር ሆኖ እየሰራ ነው። የጦር መሳሪያ ያላቸው እያስመዘገቡ ናቸው። ሕዝቡ ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩትን፣ ሰርጎቦችንና ጸጉረ ልውጦችን አሳልፎ እየሰጠ ይገኛል።
ይህ ሁሉ ጦርነቱ ሕዝባዊ መሆኑን ያመለክታል። ሕዝብ የተሳተፈበት ጦርነት ደግሞ አሸናፊነቱ አያጠራጥርም። ኢትዮጵያውያን ይህን ጦርነት እንደ ጀግኖች አያቶቻቸውና አባቶቻቸው በድል በማጠናቀቅ የራሳቸውን የጀግንነት ገድል እንደሚጽፉ ጥርጥር የለውም። እየተከናወነ ያለው የተቀናጀ ሥራና በየግንባሩ እየተመዘገበ ያለው ድልም ይህን ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/2014