አሸባሪው ቡድን በሀገር ማፍረስ እኩይ ተግባር ላይ ከተሰማራ ወዲህ በርካታ ህዝባዊ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ደም ልገሳ፣ የደሞዝ ድጋፍ፣ ስንቅ ዝግጅት እና የመሳሳሉት ተጠቃሽ ናቸው።
የሽብር ቡድኑ የጥፋት አድማሱን እያሰፋ የሚያደርሰው ሰብአዊ ቀውስ እየበረከተ መሄዱን ተከትሎ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ የተነሳ ሲሆን፤ ቁጣውም በአንድነት በመነሳት የኢትዮጵያን ጠላት መደምሰስ ተገቢ መሆኑ ላይ ሁሉም ዜጋ ከስምምነት እንዲደርስ አድርጓል።
ይህ በመደራጀት የአገርና ህዝብን ህልውና የመታደግ ጉዳይ በሰሜኑ፣ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማ መሆን ሊሆን የቻለ ሲሆን ለዚህም የቅርቡን፣ የደሴ ወጣቶችን እንቅስቃሴና ያስመዘገቡትን ድል መጥቀስ ይቻላል።
ይህ በመደራጀት አካባቢንና አገርን ከሽብር ቡድኑ የመከላከል ተግባር ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በአዲስ አበባም ነዋሪው፤ በተለይም ወጣቱ በመደራጀት አካባቢውን በመጠበቅና የጁንታውን ተግባር በማክሸፍ ላይ ይገኛል። ከትናንት በስቲያ፣ እዚሁ አዲስ አበባ ስልጠናቸውን አጠናቅቀው የተመረቁት የህዝባዊ ሰራዊት አባላትም ከከተማው ነዋሪ ጎን በመሆን የሽብር ቡድኑን ተግባር ለማክሸፍና ቡድኑን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት ቃል የገቡ ሲሆን ከትናንትናው እለትም ጀምሮ ስራቸውን ማከናወን መጀመራቸው ተገልፆል።
ስልጠናውም ሆነ በተደራጀ መልኩ የሽብር ኃይሉን ለመምታት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በተለያዩ መልእክቶች የታጀበ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፤
ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!!
አካባቢዎን ይጠብቁ!!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!!
መከላከያን ይደግፉ!!
የሚሉት ዋና ዋናዎቹ መሪ ሀሳቦች ናቸው።
በአሁኑ ሰአት፣ በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ “በሽብር ቡድኑ በጋራ ክንዳችን ይደመሰሳል። አንድነት፣ መተባበር፣ መናበብ፣ መተዛዘን፣ ህብረት፣ መደራጀት፣ መማማር፣ ወታደራዊ ስልጠና መውሰድ፣ አለመፍራት፣ ሞተን ክብራችን ማስጠበቅ እሴት አድርገን መያዝ አለብን።” የሚለውም የጋራ ድምፅ ከሆነ ቆይቷል።
በአዲስ አበባ በሰፈር አደረጃጀት የአካባቢያቸውን ሰላም እና ጸጥታ ለማስጠበቅ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ ህዝባዊ ሰራዊት አባላት የምርቃት ስነስርዓት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተካሄደ ሲሆን፤ ስነስርአቱም “እኔም የሰፈሬ ፖሊስና የሰላም ዘብ ነኝ!” በሚል በከተማው በሁሉም ወረዳዎች ከ200ሺህ በላይ የሰላም ዘቦችና ህዝባዊ ሰራዊት አባላት ያሏቸው ከ32ሺህ በላይ የሰፈር አደረጃጀቶች መኖራቸውም ከከተማው ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
የሰላም ሰራዊቶችን በማደራጀት የሽብር ቡድኑን ለመምታት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ በከተማው የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረን ነዋሪዎች አስተያየታቸውን እንሰዲሰጡን ያነጋገርን ሲሆን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ስሜ አይረዲን ሀሰን ይባላል። የምኖረው ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው። ህዝቡ ተደራጅቶ አካባቢውን መጠበቁ ተገቢ ነው። መንግስትም ይህንን ማድረጉ ትክክል ነው። እስካሁንም መቆየት አልነበረበትም። እኛ አካባቢያችንን በጥንቃቄ መመልከት ከጀመርን ቆይተናል። ሁሉም ነቅቷል። በአገር ቀልድ እንደሌለና ዋናው ጉዳይ ሰላም እንደ ሆነ ሁሉም ሰው ገብቶታል። አሁንም ህዝቡ በንቃት፣ ምንም ሳይዘናጋ አካባቢውን መጠበቅና የማይመስለው ነገር ሲያይም ቶሎ ለህግ አካል ማሳወቅ አለበት። አውሬ ወደ ቤትህ ሲመጣ እኮ ትከላከለዋለህ እንጂ በርህን ከፍተህ ግባ አትለውም። አሁን ያለው ሁኔታ እንደዚህ ነው። ማንም ሰው በሩን ከፍቶ ሽብርተኛን ግባ ብሎ አያስገባም።
ስሜ ሄርሜላ ደሳለኝ (ወይዘሮ) ይባላል። የአዲስ አበባ ነዋሪ ነኝ። ተደራጅቶ አካባቢን መጠበቅ ተገቢ እንደ ሆነ በጣም አምናለሁ። ሁሉም ሰው በመደራጀት፣ አንድ በመሆን፣ ወንድ ሴት ሳይል አካባቢውን ነቅቶ መጠበቅ አለበት። በአሁኑ ሰዓት ከመቸውም ጊዜ በላይ አንድነትና መተባበር አስፈላጊና የግድ ነው። አገራችን እንዲህ አይነት ፈተና ገጥሟት የሚያውቅ አይመስለኝም። በመሆነም ከዚህ አይነቱ ክፉ ተግባር አሸንፈን ልንወጣ የምንችለው በመተባበር፤ በመደራጀትና በጋራ በመሆን ይሄንን ሽብርተኛ ቡድን ማጥፋት ስንችል ነው። አሁን የሚያስፈልገው ይሄ ነው። መንግስትም የማደራጀቱን ስራ አጠናክሮ ሊገፋበት ይገባል። በህዝቡ በኩል ምንም አይነት ችግር የለም። ሁሉም ተደራጅቶ አካባቢውን ለመጠበቅና አሸባሪውን ለመደምሰስ ፍቃደኛ ነው። በአሁኑ ሰአት የአሸባሪውን አገር የማፍረስ ተግባር ቆሞ የሚያይ አንድም ሰው ያለ አይመስለኝም። የለም።
ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው አትክልት መደብር ግብይት ላይ እያሉ አግኝተን ያነጋገርናቸው ወይዘሮ አስቴርም “መንግስት ፀጉረ ልውጥ የምትሏቸውን ሰዎች ንገሩን ባለው መሰረት የተለየ ነገር ካጋጠመን ለህግ እናቀርባለን። በአገርና ህዝብ ጉዳይ በምንም አይነት ወደ ኋላ የሚባል ነገር የለም። አሁንም መንግስት ተደራጅታችሁ አካባቢያችሁን ጠብቁ ማለቱ ተገቢ ነው። ታዲያ እኛ አካባቢያችንን ካልጠበቅን ማን ሊጠብቅልን ነው? አሁን ሰልጥነው አካባቢያቸውን ወደ መጠበቅ ስራ ገብዋል ስለተባለው፤ እኛም አብረናቸው መሆናቸውን ይወቁት። ባጭሩ አሸባሪውን ከመዋጋት አኳያ ከመንግስት ጎን ነን።” በማለት ነው አቋማቸውን ያስረዱን።
ከወይዘሮ አስቴር ጋር ያገኘናቸው ወይዘሮ ዝናሽም ይህንን የወይዘሮ አስቴርን ሀሳብ በሚያጠናክር መልኩ አስተያየታቸውን የሰጡን ሲሆን፤ “መቼም በዚህ ቀን የተኛ ኢትዮጵያን አሳልፎ ከመስጠት የማይተናነስ ስራ ሰርቷል ማለት ነውና ከጁንታ አይተናነስም፤” በሚለው አስተያየታቸውን ያጎለብታሉ።
ከላይ ሀሳባቸውን እንደገለፁልን። እንደ ሁሉም አስተያየት ከሆነ የአሸባሪው ቡድን ምኞት ቅዥት ነው። ኢትዮጵያ በምንም አይነት መንገድ አትፈርስም። አቶ አይረዲን እንዳሉት “ይሄ ሁሉ ጀግና እያለ ኢትዮጵያ አትፈርስም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/2014