መጻሕፍት ሃሳብ ናቸው። በውስጣቸው ከተለያየ ልምድ እና ተሞክሮ እንዲሁም ምርምር የተገኘ ሃሳብ ይዘዋል። እንደ ደራሲው ብቃት እና የአተያይ ደረጃ አጻጻፋቸው ቢለያይም ሃሳቦቻቸው ግን በአካባቢያችን ከምናስተውላቸው ሁነቶች፣ ወሎዎች ፣ ንባቦች፣ ምርምሮች ፣ወዘተ የተቀዱ ናቸው።
የፀሐፊው የአጻጻፍ ዘዴ እና አተያይ ደግሞ ይበልጥ እንድንመሰጥ ያደርገናል። በተለይ መጽሐፉ ልቦለድ እና ግጥም ወይም ወግ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ጣፋጭ ያደርገዋል። ታሪክን እና ሳይንስን እንኳን ልክ እንደ ልብወለድ ቀልብ አንጠልጣይ አድርገው የሚጽፉ ደራሲያን ጥቂት አይደሉም።
መጻሕፍትን ስናነብ በውስጣችን ብዙ ጥያቄዎች ይፈጠራሉ። አንዳንዴም ደራሲው ምን አስቦ ይሆን ይህን የሳፈረው እያልን እንጠይቃለን። በሌላ በኩል የሌሎች ሰዎችን አስተያየት እናነባለን። ምክንያቱም የተለያየ አረዳድ ስለሚኖር። ይህን በማድረጋችንም እኛ ካየንበት ዕይታ የተለየ ዕይታ ማግኘት እንችላለን።
እንዳለመታደል ሆኖ በአገራችን መጻሕፍት ላይ የሚደረግ ውይይት እምብዛም አይስተዋልም። በብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ የሚቀርቡ ወርሐዊ እና በየአሥራ አምስት ቀኑ የሚቀርቡ ዝግጅቶች ነበሩ። ዝግጅቶቹ ምንም እንኳን ከኮቪድ-19 መከሰት በፊት አንስቶ መቆራረጥ የጀመሩ ቢሆንም፣ የኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ ተቋረጠዋል።
አሁን ላይ የኮቪድ-19 ስጋት የመጽሐፍ ውይይት መድረክ ማድረግን ባይከለክልም መጽሐፍ ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ግን አይታዩም። ንባብ እና ውይይት የሁሉም ነገር መፍትሔ መሆን ተደርጎ መወሰድ ነበረበት። የሀገራችንን ህልውና ለማስጠበቅ እየተከናወነ ያለው ዘመቻ ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ ልማቱም ተጠናክሮ ቀጥሏል። እንደ እዚህ ዓይነቶቹ መሰል መድረኮችም በስፋት መካሄድ ይኖርባቸዋል።
በዚህ የንባብ ማበረታቻ እና የመጽሐፍ ውይይት በጠፋበት ወቅት አንድ የውይይት መድረክ አጋጠመኝ። ምንም እንኳን ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም ባለፈው ሐምሌ ወር በተካሄደ የመጽሐፍ ሽያጭ እና ዓውደ ርዕይ ወቅት ነው መድረኩ መኖሩን ያወቅኩት።
አራት ኪሎ በሚገኘው ኢክላስ ሕንፃ ላይ የሚደረግ ውይይት ነው። በየሳምንቱ ቅዳሜ ከአራት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ይካሄዳል። አዘጋጆቹ ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ እና ዋሊያ መጻሕፍት ናቸው። ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ ከደራሲዎች፣ ከተለያዩ ለጋሽ ግለሰቦችና ተቋማት የሚያገኛቸውን መጻሕፍት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቤተ መጻሕፍትን በማቋቋም መጻሕፍትን የሚሰጥ ነው። የጽሑፌ ትኩረት መድረኩ ላይ ብቻ ስለሆነ ሌላውን ዝርዝር ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።
ውይይቱ ከዚህ በፊት ከምናውቃቸው መጻሕፍት ላይ ከሚደረጉ ውይይቶች ይለያል። በሌሎች የመጻሕፍት ውይይት መድረኮች የሚታወቀው መጽሐፉ ላይ መነሻ ሃሳብ ቀርቦ መወያየት ነው። ደራሲው ቢገኝ የበለጠ ጥሩ ነው፤ ግን ደራሲው ባይገኝም የውይይቱ ዋና ትኩረት የመጽሐፉ ይዘት ላይ ብቻ ነው።
ይሄኛውን ውይይት ለየት የሚያደርገው ደራሲው የሚገኝበት መሆኑ ነው። አወያዩ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ (ዶክተር) ሲሆን፣ ከደራሲው (በዕለቱ የሚጋበዘው ደራሲ) ሥራዎች በመነሳት ስለአስተዳደጉም ሆነ እንደ ደራሲው ሁኔታ አሁን ካለበት ባህሪ ጋር ተያይዞ ጥያቄዎችን ይቀርባሉ። ለመነሻ ያህል አወያዩ እና ደራሲው ሃሳቦችን ካቀረቡ በኋላ ዕድሉ የሚሰጠው ለተወያዮች ነው።
እንግዲህ የዚህ ውይይት የተለየነት እዚህ ላይ ነው። ብዙ ወጣቶች ወደ ሥነ ጽሑፍም ሆነ ሌሎች የምርምር ሥራዎች የሚገቡት የሌሎችን ሥራዎች አይተው ነው። እነዚህን ሥራዎች ሲያዩ በተረዱበት መንገድ ይረዱታል። በተረዱበት መንገድ ሲረዱት ግን ጥያቄዎች ይፈጠሩባቸዋል። ደራሲው ያንን ጉዳይ ሲጽፍ ከምን ተነስቶ ነው? ዕድሉን እንዴት አገኘው? በትክክል አጋጥሞት ነው ወይ?… የመሳሰሉ ጥያቄዎች ይፈጠሩባቸዋል። ለእነዚህ ጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ደራሲውን ማግኘት ትልቅ ዕድል ነው።
ጥያቄ የሚቀርብበት ሰፊ ሰዓት ያለው መድረክ ማግኘት አንድ ነገር ሆኖ፣ ደራሲውን አግኝቶ ማስፈረም ብቻውን ለአድናቂ ምን ዓይነት ስሜት እንዳለው ይታወቃል።
በዋናነት ግን የደራሲዎች ልምድና ተሞክሮ ለጀማሪ ደራሲዎችም ሆነ ወደፊት ለመጻፍ ለሚያስቡት አርዓያ መሆኑ ነው። በሌላ በኩል የግድ ደራሲ ባይሆኑ እንኳን የደራሲዎችን መጽሐፍ ሲያነቡ ከመጽሐፉ ይዘት በተጨማሪ ስለደራሲዎች ሕይወትም ማወቅ ስለሚፈልጉ እሱንም ለማወቅ ያስችላል።
‹‹ሰው ሥራውን ይመስላል›› ይባላል፤ ስለዚህ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ አንብበው የደራሲውን ባህሪ መጽሐፉ ላይ በተረዱት መንገድ ይቀርጹታል። ወይም ሲባል በሚሰሙት ያምናሉ፤ ለምሳሌ የፍልስፍና መጽሐፍ ከሆነ ደራሲው የተጎሳቆለና በፍልስፍና አካላዊ ገጽታውን የጣለ የሚመስላቸው አሉ።
ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የተገኘው ደራሲ፣ ጋዜጠኛና ተርጓሚ ኃይለጊዮርጊስ ማሞ (ጲላጦስ) ነበር። ደራሲው ‹‹ጥበብ ከጲላጦስ›› በሚል ርዕስ የትርጉም መጻሕፍትን ጽፏል። መጻሕፍቱ ፍልስፍና ላይ የተመሰረቱ ናቸው።
ይህ ደራሲም የፍልስፍና መጻሕፍትን ስለሚያነብና ስለሚጽፍ ስለባህሪውም ተጠየቀ። ደራሲውም አንድ ገጠመኙን አነሳ፤ አንዲት በአካል ያገኘችው ልጅ ያቀረበችለት ጥያቄ አስቂኝ ነበር። ‹‹እንደ ማንኛውም ሰው ለብሰሃል፤ መኪና ይዘሃል፣ የታሸገ ውሃ ትጠጣለህ…›› አለችኝ ሲል ታዳሚው ሳቅ በሳቅ ሆነ።
ልጅቷ ጠብቃ የነበረው፤ ፈላስፋ ሲባል የተቀዳደደ ልብስ የሚለብስ፣ ውሃ በቅል ይዞ የሚዞር (ምናልባትም ዲዮጋን ያደርጋል ሲባል የምትሰማውን)፣ ሁሌም በእግሩ የሚሄድ…. ይመስላት ነበር ማለት ነው። ብዙ ሰዎች ፍልስፍናን እና ፈላስፋን የሚረዱት እንደዚህ ነው። ከአባባሏ መረዳት እንደሚቻለው ልጅቷ ፈላስፋም አርጋ ሳትመለከተው አልቀረችም። ደራሲው የፍልስፍና ሥራዎችን የሚተረጉም መሆኑን አላየችውም።
ሌላው ለፍልስፍና የተሰጠው የተዛባ አመለካከት ደግሞ ፍልስፍና ማለት የግድ ሃይማኖትን መካድ ተደርጎ መታመኑ ነው። ለእነዚህና መሰል ጥያቄዎች ደራሲውን ማግኘት ብዙ ጥያቄዎችን ይመልሳል ማለት ነው። ስለፍልስፍና ራሱን የቻለ ማብራሪያ ቢያስፈልግም በአጭሩ የሰጠው መልስ፤ ፍልስፍና ማለት የግድ ሃይማኖትን መካድ እንዳልሆነ፣ ሃይማኖትም ራሱ ፍልስፍና መሆኑን ነው።
የእንዲህ ዓይነት ውይይቶች ጥቅም እንዲህ ሃሳቦችን ማጋራት ማስቻላቸው ነው። አንድ ጉዳይ ሲነሳ ሌላ ተያያዥ ነገር ይዞ ይመጣል። በአንድ ጉዳይ ብዙ ማጣቀሻዎች ይጠቀሳሉ፤ እግረ መንገድ ታዳሚው ብዙ ነገር እያወቀ ይሄዳል፤ ምክንያቱም አቅራቢዎቹ ብዙ ልምድ ያላቸው ስለሆኑ።
የእንዲህ ዓይነት መድረኮች ሌላው ጥቅሙ ደግሞ የተለያዩ ዘርፎችን ማስተዋወቁ ነው። ለምሳሌ ኃይለጊዮርጊስ ማሞ በተገኘ ዕለት ስለፍልስፍና ብዙ ይነሳል። ፍልስፍናን የተመለከቱ አተያዮች ይንፀባረቃሉ። ስለፍልስፍና የሰዎች በጎ እና መጥፎ አመለካከት ይነሳል። ይህ በጎ እና መጥፎ አመለካከት መነሳቱ በዕለቱ ለተገኘው ደራሲም ሆነ ወደፊት ለሚጽፉ ሰዎች፤ እንዲሁም ፍልስፍናን ለሚያነቡ ሰዎች ምልከታቸው ላይ የሚጨምረው ይኖረዋል። በተለይም ለፀሐፊዎች መነሻ ሃሳቦችን ያስገኛል። ከታዳሚዎቻቸው (አንባቢዎቻቸው) ጋር ይገናኛሉ።
እንደ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ዓይነት የታሪክ እና የሳይንስ ምሁራን በተገኙበት ቀን ደግሞ ስለታሪካዊና ሳይንሳዊ ምርምሮች ይወራል። በነገራችን ላይ አንዳንድ ምሁራን እንዲህ ናቸው። በአንድ ዘርፍ ብቻ አይወሰኑም። ምንም እንኳን የአገር ታሪክ የእገሌ ነው፣ የዚህ ባለሙያ ነው ባይባልም ብዙ ጊዜ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች ሲሳተፉበት አይታይም። የስነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ በዚህ ውይይት ላይ ተገኝተው ልምዳቸውን አካፍለዋል።
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ሳይንሱንም፣ ታሪኩንም፣ ፍልስፍናውንም፣ ፖለቲካውንም፣ ልብወለዱንም… በተመለከተ ሃሳቦች ይነሳሉ ማለት ነው።
በዚህ አጋጣሚ ግን ከዚህ በፊት በነበሩ ውይይቶች ላይ በሳይንስ መጻሕፍት ላይ ብዙም ውይይት አለመካሄዱን ታዝቤያለሁ። ውይይትና ገለጻ የሚደረገው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በሌሎች የምርምር ተቋማት አዘጋጅነት ነው። ምንም እንኳን ከባህሪው አንፃር ሳይንሳዊ ገለጻና ውይይት መዘጋጀት ያለበት በእነዚህ አካላት ቢሆንም፣ በሌሎች የውይይት መድረኮችም መለመድ አለበት።
መድረኩ ብዙ አድናቂዎች ያሏቸው እንደነ ዓለማየሁ ገላጋይና ታገል ሰይፉ ዓይነት ገጣሚዎችና ልቦለድ ፀሐፊዎችም የተገኙበት ነው። በተለይም በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅ የሆኑ ሰዎች መገኘታቸው ለንባብ መነሳሳት ብቻ ሳይሆን ለመጻፍ መነሳሳትም ይሆናል።
ወደ መድረኩ ድባብ እንሂድ። ምናልባት የተጋባዦች ባህሪ ይሆናል፤ በዚህ መድረክ ላይ የተመለከትኳቸው ታዳሚዎች በብዛት ወጣቶች ናቸው። ትልልቅ ሰዎች ታሪክ፣ ፖለቲካ እና ሳይንሳዊ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩር መድረክ ነው የሚበዙት። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በሚያዘጋጀው ወርሃዊ የውይይት መድረክ ላይ በብዛት የሚታዩት ትልልቅ ሰዎች ናቸው። ወጣቶች የሉም ባይባልም ጥቂት ናቸው። በአንፃሩ በዚህኛው መድረክ ደግሞ በብዛት የሚታዩት ወጣቶች ሲሆኑ አዋቂዎች ጥቂት ናቸው።
ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ (ዶክተር) የመጀመሪያው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት (2005 ዓ.ም) ‹‹የወጣቱን የንባብ ባህል በማሳደግ›› በሚል ዘርፍ ተሸላሚ ነው። እነሆ ከስንት ዓመታት በኋላ (በ2013 ዓ.ም ነው የተጀመረ) ይህን መድረክ በማዘጋጀት የወጣቱን የንባብ ብቻ ሳይሆን የመጻፍም ባህል እንዲዳብር እያደረገ ነው።
በመድረኩ ላይ ደጋግሞ እንደሚናገረው፤ ይህን በጎ ሥራ ለመደገፍ የኢክላስ ሕንፃ ባለቤት አቶ ፋድል ሀሰን ቦታውን በነፃ ፈቅደዋል። በዚህ ዘመን ብዙ ሺህ ብር የሚከራይን ክፍል ለእንዲህ ዓይነት የተቀደሰ ዓላማ በነፃ መስጠት የአገር ውለታ ጭምር ነው። እኚህ ሰው ለወጣቱ ትውልድ አዕምሮ መዳበር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
እንዲህ ዓይነት ስለመጽሐፍ እና ንባብ የሚወራባቸው መድረኮች በብዛት ሊኖሩ ይገባል። መድረክ የለም እያሉ የሚወቅሱ ሰዎችም ያለውን መድረክ መታደም ይኖርባቸዋል። ንባብ እና ውይይት ሃሳባዊ ስለሚያደርግ አገራዊ ዋጋ ስላለው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/2014