በአንድ ወቅት ነው አሉ ፤ በቅርብ ጊዜ። አንድ ጥቁር እባብ ወደ አንዲት አገር በእንግድነት ይመጣል። የአገሬው ሰው እባብ መሆኑን ቢያይም እንግዳውን በበጎ ተቀብሎ ያስተናግደዋል። ምን አጣህ ? ምንጎደለህ ? ብሎም የልቡን ሃሳብ ይሞላል። እባቡ በሆነለት ሁሉ በእጅጉ ይገረማል። ከልቡ ይደነቃል።
አያ እባቦ ከዚህ ቀድሞ እንዲህ ዓይነቱን ዓለም አይቶት፣ ረግጦት አያውቅም። ተወልዶ ካደገበት ቀዬው ለስደት ያበቃው የእርስ በእርስ ፍጅት ነው። እሱን ጨምሮ የቅርብ ዘመዶቹ ሰላምን ሲናፍቁ፣ ፍቅርን ሲራቡ ኖረዋል። አብዛኞቹ በተፈጠረው ክፉ አጋጣሚ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል። ሌሎች ደግሞ ውድ ሕይወቸው ተነጥቆ በነበር ቀርተዋል።
እንግዳው እባብ ይህ ሁሉ እውነት አልጠፋውም። የትናንቱን ህይወት አሳምሮ ያውቀዋል። በትውልድ ስፍራው በየሰበቡ የሚነሳውን ችግር መቼም አይረሳም። ዘመዶቹ ሲላቸው ተራብን ፣ አልያም ኑሮና ህይወት ጎደለብን ሲሉ ግጭት ያነሳሉ። የሚያስተዳድራቸው መሪ ከስልጣኑ ይወርድ ዘንድም ድንጋይና ጦር ይወረውራሉ።
እንዲህ ዓይነቱን ነውጥ ለመፍጠር ሰበብ ምክንያታቸው፣መነሻ ሃሳባቸው አያሌ ነው። ሲሻቸው የዕለት እንጀራችን የሚሉትን የዳቦ ዋጋ ተንተርሰው በአደባባይ ያምጻሉ። አልያም በመሪያቸው ጥላቻ ናውዘው በቀል ጥላቻን ይሰብካሉ።
እባቡ ግን ዛሬ የትናንት ችግሩ ላይ አይደለም። እንዳሻው በሰላም ወጥቶ ይገባል። ካረፈበት ምድር የፈለገው፣ የወደደውን ይፈጽማል። በተለይ የአገሬው ሰዎች መልካምነት ከአቅሙ በላይ እየሆነበት ነው። እንግድነቱን አይተዉ ጸጉረልውጥ ነው አላሉትም።
የዚህ አገር ሰዎች በጥቁር ግስላ ይመሰላሉ። ጀግንነት፣ አይበገሬነታቸው አይጣል ያሰኛል። ማንነታቸውን ለደፈረ፣ ክፉ አስቦ ለመጣ ክፉ፣ ምህረትን አያውቁም። የጥንት ታሪካቸው አሻራ ከደግነትና ከድንቅ ተጋድሎ ይቀዳል። ምድራቸውን በደምና በአጥንት ፣ በህይወት መስዋዕትነት አስከብረው ኖረዋል። በየዘመናቱ ድንቅ አገራቸውን የሻቱ ባዕዳንን አሳፍረው መልሰዋል። የድንቅ ህዝብና አኩሪ ታሪክ ባለቤት የሆነችውን አበሻዊት አገር ብዙዎች እያደነቁ ይመቀኟታል፣ እየወደዱ ይቀኑባታል።
ስለጥቁሩ እባብ ማንነት የዚህች አገር ድንቅ ሰዎች አሳምረው ያውቃሉ። ከጥንት እስከዛሬ ከእሱ ትውልድ አገር ቁርኝት ፣ዝምድና አላቸው። እሱና እነሱ የታላቁን ወንዝ ውሃ ጣዕም የግላቸው ሲያደርጉት ዘመናት አልፈዋል። ውሃው የጋራቸው ስለመሆኑም መካሪና ነጋሪን አይሹም። ሀብቱን ሲጋሩት፣ ሲጠቀሙበት ግን በእኩል ሆኖ አያውቅም። የሚቀዱበት ፣የሚጠልቁበት ጣሳ መጠን የሰማይና ምድር ያህል ይለያያል ።
እነሱ ከምንጫቸው ፈልቆ በደጃቸው የሚያለፈውን ውሃ እስከዛሬ እየዘፈኑ ሲሸኑት ኖረዋል። ለም አፈራቸውን እየዛቀ፣ ውድ ማዕድናቸውን ሲያግዝም መድረሻው ከጥቁሩ እባብ ምድር መሆኑን እነሱን ቀርቶ መላው ዓለም ያውቃል። እስከቅርብ ጊዜ የበይ ተመልካቾች ነበሩ። ሌላውን በቁንጣን ያስጨነቁ፣ በረከታቸውን ያሻገሩ ፣ በረሀብ ታሪክ ከዓለም መዝገብ የሰፈሩ ህዝቦች።
ስለእንግዳው ጥቁር እባብ በእጅጉ የሚውቁት ድንቆች ግን ማግለል ማራቅን አልፈለጉም። ከእሱ በቋንቋ ባይግባቡም፣ በባህርይ ባይመስሉም ስለጉርብትናው፣ በአክብሮት ተቀበሉት። እንደልቡ ይሆን ዘንድም ከልብ ቀረቡት። በተለመደው የሰው አገር ሰውነት አልምደው ፍቅርን ከደስታ ለገሱት፣ አብሮነትን አስተማሩት። ሌሎች ዘመዶቹ ይገቡ ዘንድ በራቸውን ከፈቱ። ቤት ጓዳቸውን ሰጡ።
አያ እባብ ዋል አደር ሲል አካባቢውን ለመደ። ወጣ ገባ እያለም መውጫ መግቢያውን አወቀ። ያለበት ምድርና ፣የሚመለከተው ህዝብ ማንነት ቀልቡን ይይዝ፣ ይገዛው ጀመር። ፍቅር ለጋስነቱን፣ እንግዳ ተቀባይነቱን መደበቅ አልቻለም። ከጥንት እስከዛሬ በእሱና በእነሱ መካከል የዘለቀውን ጥብቅ ቁርኝት ያውቀዋል። በዘፈን ፣በጨዋታቸው ስለአንድነት አዚመዋል። በባህል ማንነታቸው በፍቅር ተጣም ረዋል።
ጥቁሩ እባብ አሁንም ማንነቱን አይዘነጋም። ትናንት ከነበረበት የካብ ለካብ ህይወት ወጥቶ ሰላም እፎይታ ማግኘቱን አይረሳም። ይህን ሲያስብ ትቶት የመጣው ዓለም ትውሰ ይለዋል። አገሬው ፣ወገኖቹ፣ ውል ይሉታል። እነሱ አሁንም በርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ናቸው። ዛሬም በመሪዎቻቸው ያምጻሉ። በድንጋይ ውርወራ ፣በእሳት ነበልባል ይታጀባሉ። አሁንም የሱ ትውልድ አገር በጦርነት እቶን ትነዳለች፣ በተዳፈነ ፍም ትጨሳለች። እሱ ግን… ?
አንዳንዴ አያ እባቡ ካለበት ምቾት ወጣ ብሎ የአባይ ሸለቆን ያቋርጣል። ሁሌም መንገዱ ቀጥተኛ አይደለም። ውስጥ ውስጡን እየተጓዘ፣ አቅጣጫውን ያሳብራል። ኋላ ቀኙን እያየ በጥርጣሬ ይራመዳል። እንዲህ ባደረገ ጊዜ ኮቴ ትንፋሹ አይሰማም። በዝግታ እየተሳበ ዙሪያ ገባውን ያስተውላል። ከበረሀው እየዘለቀ ፣ ድንቅ ምድሩን ይቃኛል።
ጥቁሩ እባብ ባሻገር የሚያየው የወንዞች ድምፅ ፣የአዕዋፍ ዝማሬ ያስገርመዋል። እየተገረመ ብዙ ያስባል። አሁን የቆመባት ምድር እንደፊቱ አይደለችም፤ የቀድሞ ታሪኳን በተባበረ ክንድ ለውጣለች። ትናንት ከማህጸኗ ተጸንሶ ፣በእናት ክንዷ አድጎ የሰጠችውን በረከት እንደያዘ እብስ የሚል ወንዝ የላትም። አሁን የሰው አገር ሲሳይ የሚሆን፣መንገደኛን አታውቅም። ሁሉን በእጇ ይዛ ከጎረቤቶቿ በአንድ ማዕድ እንቁረሰ፣ በእኩል እንቃመስ እያለች ነው።
ጥቁሩ እባብ ይህ ሃሳብ ከመጣ ወዲህ ሰላም የለውም። እስከዛሬ የእሱ አገር ይህን በረከት ለብቻዋ ስትሰለቅጥ ቆይታለች። እባቡ አሁንም በበረሀው እየዞረ በምናብ ከአገሩ ሲደርስ የታላቁን ወንዝ መነሻ ከራሱ ምድር ያሳርፋል። ይሄኔ የውስጡ ስሜት አገርሽቶ ሌሎች ከጎኑ እንዲቆሙ፣ ከሃሳቡ እንዲጣመሩ ይሻል።
የልቡ መሻት እስኪደርስ ዕንቅልፍ ይሉትን አያውቅም። የቆመባት ምድር የተሸከመችው በረከት እያበገነው ለዓላማው ስኬት እሱን መሰል እባቦችን ያስታውሳል። እነዚህኞቹ እባቦች እንደሱ ዝርያዎች ጥቁሮች አይደሉም። መልካቸው የነጣ፣ ሃሳባቸው የመጠቀ ፣ ኑሯቸው የደረጀ ነው። ለክፉ ሃሳብ በተፈለጉ ጊዜ ፈጥነው ለመድረስ የሚያህላቸው የለም።
ጥቁሩ እባብ አስቀድሞ የፈለጋት አሁን ከሚገኝበት ምድርና እሱ ከፈለቀባት አገር በቅርበት የምትኖረውን ቀይዋን እባብ ነበር። ይህች አጋር እባብ ብዙዎች መልከ ቀና፣ ዕድሜ ጠገብና ታዋቂ ስለመሆኗ ጽፈውላታል። ሁሌም ዙሪያ ገባዋ በአድናቂዎቿ እንደታጠረ ነው። በየሰበቡ ደጇ የሚጎርፉ፣ውበት ታሪኳን የሚያወድሱ ጥቂቶች አይደሉም።
ጥቁሩ እባብና ቀይዋ እባብ ሲገናኙ በራሳቸው ቋንቋ ብዙ አውግተዋል። አሁን በቆመባት ምድር ስለሚገኘው ፈሳሽ ወርቅ ፣ለም አፈርና ድንቅ በረከት ምራቃቸውን እየዋጡ፣ በሃሳብ እየጎመጁ ዕልፍ አቅደዋል። ጥቁሩ እባብ ዛሬ ሰላም ሽቶ እፎይ ባለባት መሬት ላይ ስለተመከረው የየዕለት ውጥን ፈጽሞ አይረሳም።
ብዙ ጊዜ ሁለቱ እባቦች ለምክርና ለተጨማሪ ሃሳብ የሌሎችን እገዛ ይሻሉ። ይሄኔ የመሀል ዳኛ ሆነው የሚያደራድሯቸው ነጫጭ እባቦች ይበረክታሉ። የእነሱን ፍላጎት ከራሳቸው እያጣመሩ እጅ ለእጅ ባጨባበጧቸው ጊዜም ውስጣቸው ይረካል። ሃሳባቸው በአዲስ ሃሳብ ደምቆ በእኩል ይዛመዳል።
ነጫጮቹ እባቦች ዋንኛ ጉዳያቸው የሁለቱ ፍላጎት አይደለም። የእነሱ ዓላማ ጅምር ቀዳዳዎችን በማስፋት ትላልቅ ጉድጓዶችን መፍጠር ነው። ይህን ሲያደርጉ ለጉድጓዱ ጥልቀት መቆፈሪያውን በማመቻቸት፣ የሚቀድማቸው የለም። እባቦቹ መርዛቸውን ተፍተው መንደፍ እንዲጀምሩም ደጀን ሆነው ያግዛሉ። ከፊት ቀድመው፣ ከኋላ አጅበው እሳቱን ለማንደድ ክብሪት ያቀብላሉ።
በነጮቹ እባቦች ዕውቀት የሚታገዙት ሁለቱ ዝርያዎች በግልጽና በህቡዕ እየተገናኙ የሚጎመጁትን ፈሳሽ ወርቅ ስለመጠቀም፣ ይወያያሉ። ድንቁን ጉዳይ የራሳቸው ብቻ ስለማድረግም አበክረው ያወጋሉ። ወጋቸውን የሚፈልጉት ነጫጭ እባቦች የልባቸው ይደርስ ዘንድ ‹‹አለናችሁ›› ይሏቸዋል። ሁሉም በእባብኛ ቋንቋ ለመግባባት ቸግሯቸው አያውቅም።
ጥቁሩ እባብ ከጎረቤቱ ቀይ እባብ ጋር ዝምድና ማጥበቅ ከጀመረ ሰንበት ብሏል። በተገናኙ ቁጥር የደጊቱን አገር ፈሳሽ ወርቅ ስለመንጠቅ ይመክራሉ። ምክራቸው በነጮቹ እባቦች ታግዞም ሃሳባቸው አንድ ይሆናል።
‹‹ወርቁን ተይልን፣ ለእኛ ብቻ እናጊጥበት›› የምትባለው ድንቅ አገር ‹‹በእኩል እንጋራው›› ማለቷ ተመችቷቸው አያውቅም። ባገኙት አጋጣሚ እየከሰሱ፣ እየወቀሱ ከፍርድ አደባባይ ያቆሟታል። በነጫጮቹ እባቦች እየታገዙ በመርዛቸው ሊነድፏት ገዝግዘው ሊጥሏት ይታገላሉ። አሸንፈዋት አያውቁም።
ስደተኛው ጥቁር እባብ አሁንም በደጋጎቹ መሀል እንደመሸገ ነው። በድብቅ እየቀጠረ ከሚያገኛት ቀይ እባብ ጋር መምከሩን ቀጥሎበታል። እሱ ‹‹በማን ላይ ቆመሽ ምድርን ታሚያለሽ›› ይሉት የአበሾች ተረት አይገባውም። ከካብ ወጥቶ አርካብ በደረሰበት ስፍራ መሽጎ ተንኮሉን ይጠነስሳል። የቋጠረውን መርዝ የሚተፋበትን ቀን እየቀመረም ከወዳጆቹ ይመክራል።
ጥቁሩ እባብ የዘመዶችን የቀደመ ዕጣ ፈንታ ፈጽሞ አይዘነጋም። ከዓመታት በፊት እነሱም ከዚህ ቦታ ተሰደው ተስተናግደው ነበር። የዛኔም ቢሆን የዛሬዎቹ ልበ ቀናዎች ለተራቡ፣ ለተቸገሩት ‹‹ ቤት ለእንግዳ›› ብለዋል። ጥቁር እንግዳው ይህን እውነት መቼም አይረሳም። መቼም።
ዘር ቀለም ሳይለዩ ‹‹ቤትህ ቤታችን›› ያሉቱ ቀናዎች በእሱ ብቻ አልተገደቡም። በጦርነት ለተሰደዱ፣ በችግር ለወደቁ የሰው አገር ሰዎች ፈጥነው ደርሰዋል። ፊት ሳይነሱ እንደዓመል አንደወጋቸው አገር ምድራቸውን ፈቅደዋል። ራሳቸውን ችለው በአንድ ታዛ እንዲያድሩ በጨዋነት ተቀብለዋል። አሁንስ ቢሆን እነማንን ገፉ ? ማንንስ ገፈተሩ ? ማንንም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህች እንግዳ ተቀባይ አገር በገዛ ልጇቿ መፈተን ይዛለች። ሀብት ንብረቷን ግጠው የደግ ልጆቿን ነፍስ የሻቱ ግፈኞች ሰላም ይነሷት ጀምረዋል። አልጠግብ ባይነት፣ ከስልጣን ወዳድነት ተዛምዶ ነፍጥ ያነሱት እኩዮች ቀኝ እጅ በሆኑላቸው ነጫጭ እባቦች እየታገዙ ነው። ሰላም ወዳዱ ህዝብ አሁንም የቀደመ ጀግንነቱ አልበረደም። ቀፎ እንደተነካበት ንብ ‹‹ሆ..›› ብሎ ጠላቱን እያበረየ፣ መከመሩን ቀጥሏል። እውነታውን የማይክዱት ነጫጭ እባቦችም በተከፈተው ቀዳዳ ለመግባት እየተጋሉ ቆይተዋል። ቀዳዳውን ጉድጓድ እንዳይሆን የሚሹት ጀግኖች ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› ማለታቸው አልቀረም።
መግቢያ በሩ የጠበባቸው ነጫጭ እባቦች በየዝርያቸው ተደራጅተው እየመከሩ ነው። ዓላማቸው አልተሳካም። ሃሳባቸው አልሰመረም። ይህ ሲገባቸው ጦርነቱን እየደገፉ ግፈኞችን ማበርታት ያዙ። ግስሎቹን አልቻሏቸውም። ጎረቤቶቻቸውን ማሳደም፣ ጥቅሞቻቸውን መንጠቅ ጀመሩ። በዚህም አልሆነም። አበሻዊቷ አገር ሞተች ሲሏት እየተወለደች፣ ጠፋች ስትባል እየበዛች፣ ፈተነቻቸው።
አሁን በጥቁሩ እባብ እናት ምድር የተለመደው ጠብና ግርግር አገርሽቷል። እንዲህ ለመሆኑ ምክንያቱ የህዝቡና መሪው አለመስማማት መሆኑ ተሰምቷል። በርካቶች በዛች አገር አናት የተለኮሰው እሳት ፈጥኖ እንደማይጠፋ ገምተዋል። አንዳንዶች ደግሞ ህዝቡና መሪው መካረራቸውን አይተው የእሳቱ መጋም ብዙ እንደሚያጠፋ ተናግረዋል። ጥቁሩ እባብ በቆመባት ምድር ሰላም ውሎ ያድራል። በምቾት ተንደላቆ በቸር ውሎ ይገባል። በአገሩ የሚሰማው ነውጥና ረብሻ ያሳስበዋል።
ከነጮቹ እባቦች የአጋፋሪነቱን መንበር ለያዘችው የመርዝ ገንቦ ተገዢ የሆኑት ሌሎች ሁሌም ለምክር ትዕዛዟ አዳሪዎች ናቸው። እሷ በአርጩሜዋ እየገረፈች አበሳ ስታስቆጥራቸው ኖራለች። በትርፍራፊዋ እያታለለች በህይወታቸው ቀልዳለች። እነሱ ደግሞ እንደግስሎች ‹‹እምቢኝ››ን አያውቁም። በምትላቸው እየተስማሙ ‹‹አሜን››ሲሉ፣ ሲንበረከኩ ኖረዋል።
አሁን በግስሎቹ ምድር ያለው ችግር ሰበብ ምክንያት ሆኖ ለእባቦቹ አመችቷል። የእጀ ረጅሟ እባብ ተንኮልና ሴራም እንደከሸፈ ቀጥሏል። አሁን የአገሪቷን ግጭት እንደምክንያት ተጠቅማ መሰሎቿን ማሳደሟን ይዛለች። ለክፉ ሃሳቧ የሚገዙ አጋሮቿ የምትለውን ሰምተው ትዕዛዟን እየፈጸሙላት ነው።
አንጋፋዋ እባብ ዜጎቼ የምትላቸውን ከአንበሶቹ አገር ይውጡልኝ እያለች ነው። ይህን የሰሙ ትዕዛዝ አክባሪዎቿ ቃሏን ተክትለው የራሳቸውን ሰዎች ለማስወጣት ጓዛቸውን ሸክፈዋል።
በጣም የሚገርመው የጥቁሩ እባብና የመሰሎቹ ነገር ሆኗል፤ አስከዛሬ እሱና ዘመዶቹ በምቾት ኖረዋል። እንድነታቸውን አክብሮ ማንነታቸውን ተቀብሎ ያኖራቸው ህዝብ መሀል በክብር ዘልቀዋል። ዛሬ በእሱ አገር ምድር የተቀጣጠለው እሳት በየቀኑ እየጋመ ብዙዎችን እያነደደ ነው።
ወዲያ በርካቶች እባቡና ዘመዶቹ በሰላም ምድር መኖራቸው እያስቀናቸው በኑሯቸው እየጎመጁ ነው። እነሱ በከተማቸው በሚነደው እሳት ስደት መፈናቀል ይዘዋል። ወዲህ እሱና ዘመዶቹ ወደእሳቱ ለመግባት መጣደፍ ጀምረዋል። የግስሎቹ፣ የአንበሶቹ አገር ሰላም የለውም ያለቻቸውን አንጋፋዋን ነጭ እባብ ተከትለው የእሳት አራት ለመሆን ተጣድፈዋል።
ይህን ሁሉ በአግራሞት የሚታዘቡት ግስሎቹ በሰላም ቀን የተቀበሉትን ጥቁር እባብ ከደጅ እየሸኑ የጨርቅ መንገድን ተመኝተዋል። አሁን ከነበረበት የእርካብ ምቾት ወደ ካብ ህይወቱ ለተመለሰው እባብ አይጨንቃቸውም። እንደውም ካለበት ዓለም ወጥቶ ወደ እቶን ለተወረወረው ፍጡር ከልብ ያዝናሉ። ሰላም ያለባትን ምድር ትቶ የእሳትን ጫፍ ለሚረግጠው ግዞተኛ ያፍራሉ።
የግስሎቹ እናት ግን በአንጋፋዋ ነጭ እባብ ማንነታቸውን እንደሚነጠቁት ከንቱዎች አይደለችም። ሁሌም ክብሯን ጠብቃ ነፃነቷን ትቀዳጃለች። በጎችን ተቀብላ ተኩላዎችን ትሸኛለች። ከውስጥና ከውጭ የተነሱባትን ጠላቶች ጥግ አስይዛ አክባሪዎቿን ታከብራለች።
ኢትዮጵያ ማለት እንዲህ ናት። በነጭና ቀይ እባቦች በሚመሰሉት አሜሪካና ግብፅ መረብ ፈጽሞ አትጠለፍም። ሱዳንን በመሰሉ ጥቁር እባቦችም ተነድፋ አትወድቅም። ኢትዮጵያ ማለት ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም በጀግንነቷ ትጸናለች። በአንድነቷ ትቆማለች። በቃ!
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/2014