አሸባሪው ሕወሓት ከ50 ዓመታት ቀደም ብሎ ባዘጋጀው ማንፌስቶው ጭምር ያሰፈረው አማራ የሚባል ብሄር እንዳይኖር፣ ታላቋን ትግራይ መመስረት የሚል ሀገርን የማፈራረስ ቅዠት ነበር። ይሄንን ዕቅዱን ለማሳካት ደግሞ ሲከተለው የነበረው አካሄድ አንዱን ብሄር በሌላው ላይ በማነሳሳት እሳትና ጭድ አድርጎ መቅረጽና በዚያ መሀል የሚፈልገውን ግብ ማሳካት ነው። ይሄ ጥረቱና ስልቱ ባሰበው ልክ አልተሳካም እንጂ በሠራው ሥራ ብዙ ንጹሐን ተጎድተዋል። የሀገርና የህዝብ ሀብትና ንብረት ወድሟል፤ ተዘርፏል። እንዲሁም የሀገር አንድነት እንዳይጠናከር እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።
በቅርቡም የታየውም መጥፋት አለበት ብሎ ሲሠራ የኖረው የአማራ ብሄር ላይ ሂሳብ የማወራረድ ሃሳቡን በአደባባይ አስታውቆ ወደ አሰቃቂው ተግባሩ ገብቷል። አንድን ብሄር ለማጥፋት ከዚያም ሀገርን ለማፈራረስ በሚል ከሠራው እጅግ ዘግናኝ ጭካኔ የተሞላው እንቅስቃሴው መካከል አንዱ ጥቅምት 24 ቀን 2013 በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት ነው።
ከዚያ በመቀጠልም ጥቅምት 30/2013 በማይካድራ ሳምሪ በሚል ሥያሜ ባደራጀው ገዳይ ቡድን በአማራ ብሄር ላይ የፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ዕርምጃ የሚታወስ ነው። በዚህም ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ንጹሐን መታወቂያቸው እየታየ በአሰቃቂ ሁኔታ የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል። 81 ሰዎች ለአካል ጉዳት 1 ሺህ 644 ሰዎችን ደግሞ ለስነ ልቦና ቀውስ ዳርጓል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በጋራ ባደረጉት ምርመራ የማይካድራ ጭፍጨፋ ላይ ይህ አሸባሪ ቡድን ካሰማራው ሳምሪ ከተባለ ገዳይ ቡድን በተጨማሪ የወራሪው ሕወሓት ልዩ ኃይል ፖሊስ፣ ሚሊሻ እንዲሁም የሽብር ቡድኑ ታችኛው መዋቅር ድረስ የተዘረጋ ተላላኪ ድረስ እንደተሳተፉበት በምርመራ መረጋገጡን አስታውቋል። ይሄ ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምስጢር ነው።
አሸባሪው ሕወሓት በሀገርና በህዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ ይሄ ብቻ አይደለም። በጋሊኮማ፣ አጋምሳ፣ በጭናና ኮምቦልቻ ወዘተ በንጹሐን ዜጎች ፣ በሕፃናትና ሴቶች ላይ ያደረሰው ግፍና መከራ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። በዚህ የጭካኔ ተግባሩ ንጹሐን ሞተዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ሕፃናት ከወላጆች ተለይተው ለስደትና ረሀብ ተዳርገዋል።
አሁንም በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች እያደረገ ያለው ጭካኔ አማራን የማጥፋትና ኢትዮጵያን የማፍረስ ዕቅዱ አካል ነው። ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ በቆቦ፣ አጋምሳ፣ ንፋስ መውጫ፣ ጭና እና ኮምቦልቻ የተፈፀመው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ የአሸባሪውን ሕወሓት የጭካኔና አረመኔነት ጥግ በተግባር ያረጋገጠ ነው።
አስገራሚው ነገር ግን የትኛውም ዓለም አቀፍ ተቋምም ሆነ ሃገር ይሄን ሰብዓዊነት የጎደለው የጭካኔ ተግባር ሲያወግዘው አለመታየቱ ነው። የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን ባይ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም እውነቱን ለማውጣት ሙያው የሚጠይቀውን ዘገባ ለመሥራት ሲደፍሩም አልተስተዋለም። ይልቁንም አይተው እንዳላዩ ነገሩን አድበስብሶ ማለፉን ምርጫቸው ሲያደርጉ ተመልክተን ታዝበናል።
አሸባሪው ቡድን የሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ መኪኖችን ለሽብር ተግባሩ ሲያውላቸው የጠየቀው አንድም አካል አልነበረም ፤ ድርጊቱ በዓለም ላይ ተሰምቶ የማያውቅ በሰብዓዊነት ስም የተሠራ ደባ ቢሆንም አልተወገዘም። እንዲያውም በሰብዓዊ ዕርዳታ ስም አሸባሪውን የመደገፍ የሴራ ተግባር እንደነበር በገሀድ ታይቷል። ይሄንን አሸባሪ ቡድን የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን በሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መደገፍ፣ መንግሥትና ህዝብን በተለያየ መልኩ ማስጨነቅና በሰላማዊ ቦታዎች ላይ ሳይቀር የሰላም እጦት ያለ በማስመሰል ሽብር መንዛት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መገለጫ ሆኖ ከርሟል።
ይሄ ሁሉ ግፍና አሰቃቂ ተግባር በህዝብና በሀገር ላይ እየተፈጠረ ሀገርን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ታጥቀው እየሠሩ በአደባባይ እየታየ ይሄንን አሸባሪ ቡድን አለማውገዝ ፤ የክፋት ሥራውን መደበቅ ፣ተደራደሩ ብሎ የቁም ቅዠት መቃዠት፣ አሜሪካንም ሆነች ምዕራባውያን የተደበቀ አጀንዳቸውን በአሸባሪው ሕወሓት አማካይነት እያስፈጸሙ እንደሆነ በገሀድ የሚያሳይ ነው።
የአሜሪካንንና የምዕራባውያንን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በትኖ ለተነተነና ገጣጥሞ ላነበበ አካል ቁልጭ ብሎ የሚታይ ምስጢር አለ። እንዲህ በገሀድ የሚታይን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አላየሁም ብሎ ማለፍ እና ማድበስበስ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሊባል አይችልም።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይሄን ፀሐይ የሞቀውን ህዝብ የመሰከረውን የአደባባይ ምስጢር እያየ ሊያወግዝ የማይችልበት ሌላ ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም!
አዲስ ዘመን ህዳር 9 ቀን 2014 ዓ.ም