የወንዶች ስም በጀግንነት የታሪክ መዝገብ ላይ ሲፃፍ ቢኖርም፣ ሴቶች በማንኛውም የነፃነት ተጋድሎ ጉልህ ድርሻ እንደያዙ መኖራቸው እውነትን ለማይፈራ ሰው ግልፅ ሃቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲወሳ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሉዓላዊነትና ነፃነት ያደረጉት ተጋድሎ ሊዘነጋ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ በየዘመናቱ ድንበር ተሻግረው፤ ጦር ሰብቀው የመጡ ወራሪዎች በኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ሕልማቸው የቁም ቅዠት ብቻ ሆኖ ቀርቶባቸዋል። ታዲያ በዚህ የተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ደግሞ ግንባር ቀደም ሆነው የሚጠቀሱ እንስት ኢትዮጵያውያን በርካታ ናቸው፡፡ ከእነዚህ እንስት ጀግኖች መካከል ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩም አንዷ ናቸው፡፡
አርበኛ ከበደች ስዩም ከአባታቸው ከራስ ሥዩም መንገሻና ከእናታቸው ወይዘሮ ጀንበር በርሄ፣ ጥቅምት 17 ቀን 1904 ዓ.ም መቀሌ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። በተወለዱበት አካባቢ ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ቤተሰቦቻቸው ገና በለጋ እድሜያቸው ለደጃዝማች አበራ ካሣ (የራስ ካሣ ኃይሉ ልጅ) ዳሯቸው፡፡ በወቅቱ በልጅነት ጋብቻ መፈፀም የተለመደ ስርዓት ስለነበር ወይዘሮ ከበደች ሥዩምም ከባለቤታቸው ጋር አብረው በመኖር ልጅ በመውለድ ሕይወታቸውን መምራት ቀጠሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀልና ኢትዮጵያን ‹‹የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ የቅኝ ግዛት›› (Italian East Africa Colony) አካል ለማድረግ የነበራትን የረጅም ጊዜ ሕልም ለማሳካት ከዓድዋ ጦርነት 40 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ለመውረር ዝግጅቷን አጠናቅቃ ወረራ ፈፀመች፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ጊዜ ለታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩምና ለቤተሰቦቻቸው የጭንቀት ወቅት ነበር፡፡ ፋሺስቶች ማይጨው ላይ በተደረገው ጦርነት በኢትዮጵያ ጦር ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰው ወደ አዲስ አበባ ገስግሰው የወይዘሮ ከበደች ስዩምን ባለቤት ደጃዝማች አበራ ካሳንና ወንድማቸውን ደጃዝማች አስፋወሰን ካሣን ‹‹… የኢጣሊያን ጦር መውጋታችሁን ካቆማችሁ በሰላም እንድትኖሩ ይፈቀድላችኋል …›› ብሎ በማታለል በጥይት ደብድቦ ገደሏቸው፡፡ የደጃዝማች አበራ እና ወይዘሮ ከበደች ልጅ ዓምደፅዮንም በጠላት እጅ ተይዞ ወደ እስራት ተጋዘ፡፡
ይህ መከራ በሃገራቸውና በቤተሰባቸው ላይ ሲደርስ ወይዘሮ ከበደች ስዩም የሦስት ወር ነፍሰ ጡር ቢሆኑም የስምንት ዓመት ልጃቸውን አምሃን ይዘው የቤተሰባቸውን ደም ለመበቀልና ለሃገራቸው ነፃነት ለመፋለም ወስነው ጥቂት አርበኞችንና አሽከሮችን አስከትለው እያስተባበሩ በእንሳሮ፣ በመርሐ ቤቴ፣ በሚዳና በአካባቢው እየተዘዋወሩ የአርበኝነት ተጋድሏቸውን ጀመሩ፡፡ የጠላት እንቅስቃሴ እያሰጋ በመጣበት ወቅት አርበኛ ከበደች ስዩም በአካባቢው የነበረው ህዝብ በጠላት ስብከት ተደልሎ ትጥቁን በመፍታት ከትግል እንዳይዘናጋ ከፍተኛ ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር፡፡
ግንቦት 25 ቀን 1928 ዓ.ም ሚዳ ወረዳ ውስጥ ቀኝ ገደል በተባለው ቦታ ላይ ከፋሺስት ጦር ጋር የመጀመሪያ ጦርነታቸውን አደረጉ፡፡ የፋሺስት ጦር ቁጥሩ ብዛት ያለው ከመሆኑ በተጨማሪ በወታደራዊ ትጥቅም እጅግ የተጠናከረ ነበር፡፡ ጦርነቱ እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ የታየበት ፍልሚያ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በመጨረሻም የኢትዮጵያ አርበኞች ጦር በአርበኛ ከበደች ሥዩም እየተመራ የዘመነ መሳሪያ ከታጠቀውና በቁጥር ከሚልቀው የጠላት ጦር ከበባ ሰብሮ መውጣት ቻለ፡፡ ይህ የአመራር ጥበባቸውና ድል አድራጊነታቸው ዝናቸውን ከፍ አደረገላቸው፡፡
በዚያ አስቸጋሪ የጦርነት ወቅት ሱሪ በመታጠቅ በእንሳሮ፣ በመርሐ ቤቴና በሚዳ ቆላማ ቦታዎች በመውጣትና በመውረድ ለአገራቸው ነፃነት መከበር ከጠላት ጋር ውጊያ አድርገዋል፡፡ ‹‹ጥቁር … በዚያ ላይ ሴት›› ብሎ በድርብ ንቀት የሚመለከታቸውን የፋሺስትን ጦር በቁርጠኝነት እየተፋለሙ እየጠላ እንዲያከብራቸው አድርገውታል፡፡
በዚህም የተነሳ የጀግናዋ አርበኛ ከበደች ስዩም ስምና ዝና ከዳር እስከ ዳር በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ ናኘ። በታላላቅ አርበኞች ሞት ምክንያት ተደናግጠው በስፍራው በዱር በገደሉ ተበታትነው የነበሩት የኢትዮጵያ አርበኞች ሁሉ በጀግናዋ ከበደች ስዩም ወኔ ተማርከው በየጎበዝ አለቃው አማካኝነት እየተፈላለጉ መደራጀት ጀመሩ፡፡
በሰኔ ወር 1929 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ የአርበኝነት ትግላቸውን በተበታተነ መልኩ ይከውኑ የነበሩት አርበኞች እየተገናኙ ይመካከሩ ነበርና አርበኛ ከበደች ስዩምም ስመጥር አርበኞች ከነበሩት ከነራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃዝማች ዘውዴ አስፋው፣ ፊታውራሪ ኃይለማርያም ማሞና ከሌሎች የአርበኞች መሪዎች ጋር እየተገናኙ በጠላት ላይ በጋራ ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይመካከሩ ነበር፡፡
አርበኛ ከበደች ስዩም በአገራቸው መደፈር ተቆጭተው ዱር ቤቴ ብለው ከጠላት ጋር የሚፋለሙ አርበኞችን በማስተባበር ጃርሶ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ላይ የደፈጣ ውጊያ በማድረግ በወሰዱት እርምጃ ከጠላት ጎን ተሰልፈው የነበሩትን ባንዳዎችንና ነጭ የጦር ወታደሮችና አለቆችን በላቀ ወኔና አመራር መደምሰስ ችለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ወልጭ በተባለው ስፍራ ላይ መሽጎ የአርበኛ ከበደች ስዩምን ጦር እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ሙከራ ያደረገው የጠላት ጦር በአርበኛዋ ጦር የሽንፈት ጽዋ ለመጨለጥ ተገዷል።
በሰኔ ወር 1929 ዓ.ም ላይ የአርበኛ ከበደች ስዩም ጦር ወደ ቢሻን ጃሊ በመጓዝ ግንደበረት ላይ ካቺሱ ቦዳ ጤና ከተባለው ቦታ ላይ ሰፍሮ ከነበረው የጠላት ጦር ጋር ውጊያ አድርጎ መጠነኛ ጉዳት ቢደርስበትም የማታ ማታ ግን ድሉን የራሱ ከማድረግ ያገደው ኃይል አልነበረም፡፡
እነዚህ የድል ሰንደቅ የተውለበለበባቸው አውደ ውጊያዎች የአርበኛ ከበደች ሥዩምን ዝና አገነኑት። አርበኛ ከበደች ሥዩም በአርበኝነት ታሪክ ልዩ የሚያደርጋቸው ነገር በውጊያ ላይ ሳሉ እርጉዝ መሆናቸውን እያወቁና የሕመም ስሜት እየተሰማቸው እንኳ ምንም ምክንያት ሳይፈልጉ ጤነኛ መስለው እልህ አስጨራሽ ውጊያዎችን መምራታቸውና ድል መቀዳጀታቸው ነበር፡፡ ሐምሌ 1 ቀን 1929 ዓ.ም ከፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ጦር ጋር ዱላ ቆርቻ በረሃ ውስጥ ውጊያ እያካሄዱበት በነበረበት ወቅት በጥይት እሩምታ መሐል ወንድ ልጅ ተገላገሉ። በዚያ አስጨናቂ የመከራ ወቅት ‹‹የኢትዮጵያ እድል የተገዢነት ወይንስ የነፃነት ይሆን?›› በሚያስብል ሁኔታ ከወራሪው ጦር ጋር በሚፋለሙበት ወቅት የተወለደውን ልጃቸውን ‹‹ታሪክ›› ብለው ስም አወጡለት፡፡
ልጃቸው የተወለደው በጦርነት መሐል ለዚያውም የጦር መሪ ሆነው ነበርና ወላድ ሴቶች ከወሊድ በኋላ የሚደረግላቸውን እንክብካቤ አላዩም፡፡ የአራስነት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ አንዲት ደሳሳ ጎጆ ውስጥ እንዲገቡ ቢደረግም የፋሺስት የጦር አውሮፕላኖች ግን እርሳቸው ወዳሉባት ጎጆ ቤት የቦምብ ናዳ ያወርዱ ነበር፡፡ በነዚህ የቦምብ ድብደባዎችም ከእርሳቸው ጋር የነበሩ ብዙ አርበኞች ተሰውተዋል፡፡
አርበኛ ከበደች ሥዩም አራስ ቤት ውስጥ መቆየትን እንደቅንጦት ተመልክተውት የአራስ ወገባቸው ሳይጠና ሕፃን ልጃቸውን ይዘው ከሸዋ በመነሳት ወደ ወለጋ መጓዝ ግድ ሆነባቸው፡፡ ወለጋ ከገቡ በኋላም በሆሮ ጉድሩ፣ በቡያና በሊሙ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ወራሪውን ጦር በመዋጋት ከፍተኛ ጀብዱዎችን ፈፅመዋል፡፡
ድል እንደውሃ መንገድ አይደለምና አርበኛ ከበደች ስዩምና ጦራቸው ለድል የሚበቁት ከባድ መሰናክሎችንና ጋሬጣዎችን እያለፉ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ጎጃም፣ ቡሬ ውስጥ የፋሺስት ጦር አርበኛ ከበደች በሚመሩት ጦር ላይ በወሰደው ድንገተኛ እርምጃ የጠላት ጦር የበላይነቱን በመያዙ የወገን ጦር ማፈግፈግ ጀመረ፡፡ ይህንን የጦራቸውን የማፈግፈግ እንቅስቃሴ የተመለከቱት የአርበኞቹ ጦር መሪ ጀግናዋ አርበኛ ከበደችም ‹‹ወዴት ትሄዳላችሁ፤ እኔ እኮ እዚህ ነኝ›› እያሉ ጦራቸውን ማበረታታትና ማነቃቃት ጀመሩ፡፡ የጠላት ጦርም ይበልጥ ተጠግቶ መዋጋት ቀጠለ። በይበልጥ ደግሞ አርበኛ ከበደችን ለመማረክ ኃይሉን አጠናክሮ መግፋቱን ተያያዘው፡፡ ይህን ሁኔታ የተመለከተ አንድ አርበኛም ወደ አርበኛ ከበደች ስዩም በመጠጋት ‹‹ … ጠላት ደርሶብናል፤ ሊማርክዎት ነው፤ ስለዚህ ይህንን ቦታ በአስቸኳይ መልቀቅ አለብን …›› ብሎ ነገራቸው፡፡ አርበኛ ከበደች ሥዩም ግን ሃሳቡን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ ‹‹ … እኔ ከዚህ ቦታ ንቅንቅ አልልም!›› በማለት ውጊያቸውን ቀጠሉ፡፡ ነገር ግን አርበኞቹ ‹‹እኛ እርስዎን አስማርከን ለጣሊያን መፎከሪያ አንሆንም!›› ብለው በግድ ከቦታው ላይ እዲያፈገፍጉ አደረጓቸው፡፡
የአርበኛ ከበደች ሥዩም የጀግናዋ ገድል እረፍት የነሳቸው ፋሺስቶች አርበኛዋን ለመማረክ ላይ ታች ማለት ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ፋሺስቶቹ አርበኛዋን የመማረክ እቅዳቸው እንዳልተሳካላቸው ሲያውቁ ታርቀውና ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሕዝቡ እንዲገቡ በይፋ መለፈፍ ያዙ። አርበኛ ከበደች ግን የአገራቸውን ጓዳ ይዞ ‹‹እንታረቅ›› ብሎ ጥሪ ያቀረበላቸውን የፋሺስት ጦር ጥሪ ሳይቀበሉና ከቁብ ሳይቆጥሩ ‹‹ባለቤቴ በጠላት እጅ በግፍ ተገድሎ፣ እናት አገራችን በጠላት እጅ ተይዛ፣ ወገናችን በባርነት ቀንበር ተጠምዶና ይህ ሁሉ ግፍ እየተፈፀመ ታርቄ ከጠላት ዘንድ ልገባ አልችልም›› በማለት በተለመደው የአርበኝነት ተጋድሏቸው ጠላትን ማሸበር ቀጠሉ፡፡
አርበኛ ከበደች ስዩም ጎጃም ውስጥ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የነፃነት ትግላቸውን እስከ 1931 ዓ.ም ድረስ ከቀጠሉ በኋላ በወቅቱ የኢትዮጵያ አርበኞችን እየመሩ ያዋጉ ከነበሩት የጦር መሪዎች መካከል ከጥቂቶቹ ጋር በመሆን ወደ ሱዳን ሄዱ፡፡ ካርቱም ከተማ ከደረሱ በኋላም በወቅቱ በስደት እንግሊዝ ከነበሩት ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጋር ተላልከው ወደ ግብጽ እንዲሄዱ በታቀደው መሰረት አርበኛ ከበደች ሥዩም ከልጅ ዐቢይ አበበ (በኋላ ሌተናል ጀኔራል) እና ከልጅ መርዕድ መንገሻ (በኋላ ሌተናል ጀኔራል) ጋር ወደ ካይሮ አቀኑ፡፡
አርበኛ ከበደች ካይሮ በነበሩበት ወቅት ስለአርበኝነት ተጋድሏቸውና በወቅቱ በኢትዮጵያ ስለነበረው ሁኔታ ተጠይቀው ለጋዜጠኞች የሰጡት ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር።
‹‹ … ለአገሬ ክብርና ነፃነት ጠላትን እስከመጨረሻው ለመከላከል የነበረኝን እቅድ ወደግቡ ለማድረስ ለሰውነቴ ሙሉ ድፍረት ሰጠሁት፡፡ ከወንዶች ልዩ እንዳልሆን በማለት የጦር ልብስ ለበስኩ፤ መሳሪያም ያዝኩ። አርበኞችም እንደ አንድ ትልቅ የጦር መሪ ያከብሩኝ ነበር፡፡ ከእኔ ጋር የነበረው ጦር ከሌላው ወገን ተዋጊ አርበኛ ጋር በእጅጉ የተባበረ በመሆኑ በጣሊያኖች ላይ የሚያደርገው ፍልሚያ ከቀን ወደ ቀን ይጋጋል ጀመር። በመሆኑም ግዳዩና ምርኮው በጣም ከፍ ያለ ነበር። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በስንቅም ሆነ በትጥቅ ሙሉ ድጋፉን ይሰጠን ነበር፡፡ የነፃነት ፍቅሩንም ይገልፅልን ነበር። ጠላት እኔን ለመማረክና ለመግደል ብዙ እቅድ እንደነበረው አውቃለሁ፡፡ እስከተሰደድኩበትም አገር ድረስ የማስፈራሪያ መልዕክቶችን በመላክ ሁለቱን ልጆቼን ‹እንወስድብሻለን› ይሉኝ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞችም በጠላት ላይ የሚያካሂዱት ጦርነት እየተጠናከረ በመምጣቱ ብዙ ቦታዎችም ከጠላት ቁጥጥር ስር ነፃ መውጣታቸው መረጋገጡ የኢጣሊያ ፋሺስት የሚወድቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ››
ከሁለት ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላም፣ በኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎና በወዳጅ አገራት ድጋፍ ወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ሲሸነፍ፣ አርበኛ ከበደች ሥዩም ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው በሸዋ፣ በወለጋና በጎጃም የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ለአገራቸው ነፃነት ሲታገሉ የነበሩት ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩም በአርበኝነት ዘመናቸው በፈፀሟቸው አኩሪ ተግባራት አምስት ከፍተኛ የክብር ኒሻኖችን ተሸልመዋል፡፡ በመጨረሻም በታኅሳሥ ወር 1971 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
በ2008 ዓ.ም የአርበኞች ድል 75ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲከበር የመታሰቢያ ቴምብር ከታተመላቸው 25 ታላላቅ አርበኞች መካከል አንዷ ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩም ናቸው፡፡
ኢትዮ-ጣሊያናዊቷ ዘፋኝ፣ ጸሐፊና ገጣሚ ጋብርኤላ ጌርማንዲ ስለታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩም የሚከተለውን ጽፋለች፡፡
‹‹ … እርሷ (አርበኛ ከበደች) ከወንዶች የላቀች መሪ እንደሆነች ብዙዎች ይመሰክሩላታል፡፡ ተወዳዳሪ አልነበራትም፡፡ አርበኞች ሁሉ ከማክበር አልፈው ያመልኳታል፡፡ እያንዳንዱ ዘመቻዋ የሚጠናቀቀው በድል ብቻ ነው፡፡ ጣሊያኖች እርሷን ለመያዝ ሞከሩ፣ ሞከሩ … ግን አልቻሉም …››
ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ስዩም በሕይወት ዘመናቸው የፈፀሟቸው ገድሎች ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ እንድትቆይ ከማስቻል አልፈው … ለአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያውያን (በተለይም ለወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች) በአርዓያነት የሚጠቀሱ ናቸው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2014