ኢትዮጵያ እየተዋጋች ያለችው አሸባሪነትን ነው። አሸባሪነትን የምትዋጋው ደግሞ የህዝቦቿን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ነው። አሸባሪነት በባህርይው ሀገር አፍራሽ ድርጊት ነው፤ አሸባሪነት የተረጋጋ ሀገርና ሰላሙ የተጠበቀ ህዝብን ማየት አይመኝም። ሀገር የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኗ ዋጋዋ እጅግ ውድ ነው። የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ፣ የህዝቦችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በዘላቂ መልኩ ለማስቀጠል ብዙ መስዋዕቶችን መክፈል የግድ ይላል። ኢትዮጵያም እየተዋጋች ያለችው እነዚህን መሰረታዊ የህልውና ጉዳዮቿን ሊያሳጧት ከሚሯሯጡ ሃይሎች እና ሰላምን ከማይፈልጉ ሽብርተኛ ቡድኖች ጋር ነው።
አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ጦርነት ካወጀ ዓመት ተቆጠረ። መንግስት ሰላምን ለማምጣት የህግ ማስከበር ርምጃ ከወሰደ በኋላ የተናጠል ተኩስ ማቆም ውሳኔ ቢያሳልፍም ሽብርተኛው ሕወሓት ግን የውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ጠላቶችን አለኝታ በመተማመን የሽብር ፍላጎቱን ለማሳካት በጦርነት መቀጠሉን መርጧል። በዚህም የማይወጣውን የሽንፈት ፅዋ እየተጎነጨም ይገኛል። አሸባሪው ሕወሓት በወሎ ግንባር በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ሰሞኑን ራሳቸውን በማደራጀት በከፍተኛ ተጋድሎ አካባቢያቸውን ነጻ እያወጡ ይገኛሉ። ይህም ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ለአሸባሪዎች ቦታ እንደሌላቸው ያረጋገጠ ነው።
አዎ፣ ኢትዮጵያ አሁንም በፊትም የአሸባሪዎች ጥቃት ደርሶባታል፤ አብዛኞቹ የሽብር ጥቃቶች ግን የተነሱትና የተጠነሰሱት በሕወሓት መራሽነት አገር በቀል የሽብር ቡድኖችን በማስተባበር ነው። እነዚህ ሕወሓት መራሽ የጥፋት ቡድኖች ሴራም ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ወደስልጣን የመጡበትን የማጭበርበር መንገድ በመከተል እኩይ ፍላጎታቸውን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለመጫን ነው። እናት ሀገራቸውን ማቁሰል፣ የራሳቸውን ፍላጎት ማርካት፣ መሰረተ ልማቶችን ማፍረስ፣ ተቋማትን ማበላሸት በወረራ በያዟቸው አካባቢዎች የፈፀሟቸው ተግባራት ማሳያ ነው።
ይህ ሁሉ ግፍና በደል በግልፅ የታያቸው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ለዚህ የእናት ጡት ነካሽ ባንዳና ግብረ አበሮቹ የማያዳግም መልስ በመስጠት ላይ ናቸው። የሕወሓት ሂሳብ የማወራረድ የበቀል ብትር ያረፈባቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች ከሌሎች ክልሎች ጋር በአንድነት በመተባበር እና በኅብረት በመደራጀት አካባቢያቸውን ነፃ ማውጣት እየቻሉ ነው። ይህም ሀገር የማተራመስ የውጭ ተልዕኮ በዚህ ትውልድ እንደሚቀለበስ ያረጋገጠ ነው። የአባቶቹን አደራ በተረከበው በዚህ ትውልድ ሀገር አፍራሾች ይፈርሳሉ፤ የሀገራችን ሉዓላዊነትም አይደፈርም።
አዎ፣ ይህ ትውልድ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ከወጣት እስከ አዛውንት፣ በብሄር፣ በፆታ፣ በሃይማኖት ልዩነት ሳይፈጥር በአንድነት በመነሳት የህልውና ዘመቻውን ጥሪ ተቀብሎ ዘምቷል። ለአሸባሪው ሕወሓት እኩይ ዓላማም ተገቢውን መልስ በመስጠት እየተፋለመ ይገኛል። በተለይ ወጣቱ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ዘመኑ አምጦ ከወለዳቸው አርበኞች ጋር በመሆን ህይወቱን፣ አጥንቱንና ደሙን እየገበረ የሀገሩን ሰላምና ደህንነት እያስጠበቀ ይገኛል። ይህ ደግሞ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በአጠቃላይ ጦርነቱ የህልውና ነው እስካልን ድረስ ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ታላቅ ተጋድሎ እየተከፈለለት ያለውን መስዋዕትነት በደጀንነት በማገዝ፤ አቅም በሚፈቅደው መጠን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የኢትዮጵያ እንቅፋት የሆነውን ይህን አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ ግድ ይላል።
እንደጥንቱ ዛሬም ለጠላት የማትንበረከክና ሉዓላዊነቷ የተከበረ ሀገር ህዝቦች መሆናችንን ማሳየት ይጠበቅብናል። ይህ ሲሆን በውጭ ያሉ የአሸባሪው ቡድን ደጋፊዎች የሆኑ የኢትየጵያ ጠላቶች አንገት ይደፋሉ፤ አንድነታችን ሲጠናከር ድል ማድረግ እንደሚቻል ከሕወሓት መደምሰስና ሽንፈቱ መማር ይቻላል። ኢትዮጵያን ከታቀደላት ውድመት ማዳን የምንችለው እኛ ለውጪ ጠላትና ለሀገር ውስጥ ባንዳ ባለመንበርከክ እየተካሄደ ባለው የህልውና ጦርነት ሁላችንም ዘማቾች ስንሆን ብቻ ነው። እንዲህ አይነት ወኔና አይበገሬነት ከተላበስን የጦርነቱ አሸናፊዎች እኛው መሆናችን ምንም አይነት ጥርጥር የለውም!
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2014