ኢትዮጵያውያን በዓድዋ የአፍሪካውያንን ጦርነት ተዋግተው በማሸነፍ ለአሀጉሪቱ ህዝቦች የነፃነት ትግል ፋና ወጊ ሆነዋል። እውነታው ለብዙዎች የማይዋጥ መራራ ታሪክ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል የታሪኩ ባለቤት መሆን ችለዋል።
በአንድ በኩል ለዘመናት ከትውልድ ትውልድ ሲወራረስ የመጣው ስለነፃነት ያለው ከፍያለ ሀገራዊ አስተሳሰብ ሁሌም ለነፃነቱ ቀናኢ የሆነ ትውልድ መፍጠር ማስቻሉ ፤ ትውልዱም በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ነፃነቱን ከህይወቱ በላይ መሆኑን መቀበሉ ፤ ነፃነቱን የማህበረሳባዊ ማንነቱ መገለጫ አድርጎ መውሰዱና ለዚህም የጸና ስብእና መፍጠሩ ስለነፃነት የሚደረጉ ተጋድሎዎች ስኬታማ እንዲሆኑ አድርጓል።
በሌላ በኩል በየዘመኑ ስለነፃነት የተከፈሉ የመስዋዕትነት ገድሎች ለቀደሙት አስተሳሰቦች ተጨባጭ አቅም በመሆን እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ኢትዮጵያውያን ስለ ነፃነታቸው ያላቸው ቀናኢነት በህይወት መስዋዕትነት የሚገለጽ ከፍ ያለ ማህበራዊ እሴታቸው መሆን ችሏል። በዚህም ለብዙ አፍሪካውያን ተጨባጭ ተምሳሌት መሆን ችለዋል።
ዛሬም ቢሆን የራሳችንን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የጀመርነው የለውጥ ትግል አፍሪካዊ ወንድሞቻችን እየኖሩበት ካለው የምዕራቡ ዓለም “እኔ አውቅልሀለሁ” አዚህም እንደሚያነቃው ይታመናል። ትግሉም ከፍ ባሉ ተግዳሮቶች የመፈተኑ እውነታም ከዚሁ የመነጨ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል። በዓድዋ አባቶቻችን ከከፈሉት መስዋዕትነት ባልተናነሰ መልኩ መስዋእትነት እንድንከፍል እየተገደድን እንገኛለን።
በአንድ በኩል እንደቀደመው ዘመን የውስጥ ባንዳዎች ባደገ መልኩ ሀገርን እስከ ሲኦል ወርዶ እናፍረስ በሚል ቅዠት ባላቸው አቅም ሁሉ አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የለውጡ እውነታ ያሳሳባቸው ምዕራባውያን ኃይሎችና ታሪካዊ ጠላቶቻችን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ ግልጽ ጦርነት አውጀውብን ባላቸው አቅም ሁል እያሴሩብን ነው።
“እኛ እናውቅላችኋለን “የሚሉት በተጨባጭ ግን ስለኛ የተሻሉ ነገዎች ለማሰብ ፍጥረታዊ ማንነት የሌላቸው ምዕራባውያን ኃይሎች መላውን አፍሪካ ላለፉት 70 ዓመታት በማይጨበጥ ተስፋ በከፋ ድህነትና ኋላ ቀርነት ውስጥ እንዲዳክር ከማድረግ ባለፈ የፈጠሩት አንዳች የሚጨበጥ ነገር እንደሌለ የአሁኗ አፍሪካ ማሳያ ነች።
ባላት የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት የበለጸገች አፍሪካ ተፈጥራ ለማየት ብዙ ትውልዶች በየዘመኑ ከፍያለ መስዋዕትነት ከፍለዋል። መስዋዕትነታቸው ግን በባንዳዎችና እኛ እናውቅልሃለን በሚሉ ምዕራባውያን ኃይሎች ትርጉም አልባ እንዲሆን ተደርጓል። ይባስ ብሎም አህጉሪቱ የከፉ የርስ በርስ ግጭቶች መናኸሪያ እንድትሆን ተደርጋለች።
በየወቅቱ ይህንን እውነታ ተረድተው ችግሩን ለመቀልበስ ወደ አደባባይ ብቅ ያሉ የአህጉሪቱ የቁርጥ ቀን ልጆች በተቀናጁ ዘመቻዎች፤ በሀገር ውስጥ ለሆዳቸው እና ለስልጣን ባደሩ ባንዳዎች፣ ከሀገር ውጪ በዓለምአቀፍ ደረጃ በተቀናጀ የፕሮፓጋንዳ፣ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ አሻጥር ዘመቻዎች የብልጭታ ያህል ታይተው እንዲጠፉ ተደርገዋል።
ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች በተመሳሳይ መልኩ ድምፃቸው እንዳይሰማ፤ ሕዝባቸውን አነሳስተው የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ መወሰን እንዳይችሉ ሲደረጉ ቆይተዋል። በዚህም አፍሪካ ብዙ ተስፈኛ ልጇቿን እንድታጣ ተደርጓል። ብዙ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ንቅናቄዎች በተለመዱ ሴራዎች ከፍ ወዳሉ የርስ በርስ ግጭቶች እንዲለወጡም ሆነዋል። በዚህም አፍሪካውያን ብዙ ዋጋ ለመክፈል ተገደዋል።
ዛሬ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውም እውነታ የዚሁ የምዕራቡ ዓለም የቀደመ ሴራ ቀጣይ ምዕራፍ ነው። አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዳይወስኑ ሲከናወኑ የነበሩት ደባዎችም አካል ነው። የአፍሪካውያንን የተስፋ ዜማ የማምከን ኢ-ሰብዓዊ ተልዕኮዎች ሌላ ማሳያም ነው።
ልዩ የሚሆነው የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ትግል ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያውያን መሆናቸው፤ ትግሉን የጀመሩት ደግሞ እውነታውን በሚገባ ተረድተውና ለዚሁ የሚሆን ጽናት አንግበው መሆኑ ነው። ከዚህም በላይ የትግላቸው ተልዕኮ እንደ ቀደመው ዘመን የዓድዋ ጦርነት ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ጎህ ቀዳጅ እንደሚሆንም ተረድተው መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያውያን የጀመሩት ብልጽግና አብሳሪ ታሪካዊ የለውጥ ጉዞ ከራሳቸው አልፎ የአፍሪካውያንን የትግል ታሪክ ወደ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የሚለውጥ፤ የመጪውን አፍሪካዊ ዕጣ ፈንታ በተጨባጭ መለወጥ የሚስችልና ለአፍሪካውያን አዲስ ዓለም አቀፍ ስብዕና መገንባት የሚያስችል ነው።
ለዚህም ነው እኛ ኢትዮጵያውያን አሁን በሁለንተናዊ መልኩ የተከፈተብንን ጦርነት ለመመከት እያደረግነው ያለው እልህ አስጨራሽ ትግል ስለ አፍሪካና አፍሪካውያን የምናካሄደው ጦርነት ነው ብለን የምናምነው። በጦርነቱ የምናስመዘገበው ድልም የነገይቱን አፍሪካ ገጽታ የሚለውጥና አፍሪካዊና አዲስ ዓለም አቀፋዊ ስብዕና የሚገነባ እንደሆኑም የምናምነው።
ይህንን ታሪካዊ እውነታ ሁሉም አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በአግባቡ ሊረዱትና አፍሪካዊ ተልዕኮውን ሊያጤኑት ይገባል። ብዙዎች ተስፋ አድርገው ዋጋ የከፈሉለትን የነገይቱን አፍሪካ እውን በማድረግ ሂደት ውስጥ አዲስ የታሪክ ጅማሬ መሆኑንም አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ሊያስተውሉና ለትግሉ ስኬትም የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ኅዳር 7/2014