እንደ አዲስ አበባ ማስፋፊያ ባሉና በፊንፊኔ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ወጣቶች በጫኝና አውራጅነት ሲሰሩ ይታያል፤ ስራው ለበርካታ ነዋሪዎች የስራ እድል የከፈተ ነው፤ ካለው የነዋሪዎች እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይም በቀጣይም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ሊፈጥር የሚችል የስራ አድል ዘርፍ ተደርጎም ሊታይ ይገባዋል።
ዜጎች በዚህ ስራ ውስጥ መስራታቸውን እናደንቃለን፤ ስራው ግን ህግና ስርአት ሊኖረው ይገባል። ስነ ምግባር መኖርም አለበት። በዚህ የስራ ዘርፍ ከተሰማሩት መካከል ጥቂት የማይባሉት ወገኖች ግን በህግ የሚገዙ አይነት አይደሉም። የሠፈር አለቃ፣ አድራጊ ፈጣሪ እየሆኑ ናቸው። እኛ ካላወረድን እና ካልጫንን የሚሉ የመንደር ጉልበተኞች። ድርጊታቸውን ስታስቡት አንዳንድ ጊዜ “አካባቢው የኔስ አይደለም እንዴ? ለካ የጫኝና አውራጅ አውራጃ ወይም ወረዳ ውስጥ ገብቼ ነው የምዋረደው ” ብላችሁ ልታስቡ ሁላ ትችላላችሁ።
በእዚህ ስራ ከተማሩት መካከል አንዳንዶቹ የአንድ መንደር ወጣቶች ናቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌላ አካባቢ ተሳስበው የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። የአገሬ ልጅ፣ የወንዜ ልጅ ሲባል በተኖረበት ሀገር ተሳስበው የተሰባሰቡም አሉበት። በምንም በምንም መልኩ ይሳሳቡ ፤ ዋናው ግን ለህግ ተገዥ መሆን፣ ደንበኞቻቸውን አለማስቀየም ነው የሚኖርባቸው። ከእዚህ አንጻር ግልጽ ችግር ይታይባቸዋል።
ችግሩ የጎጠኝነት አይደለም፤ የዘረፋ ቅሚያ አይነት ነው። እቃው የማያወጣውን ዋጋ ለማስጫኛና ለማውረጃ መጠየቅ ከዚያ ሌላ ስም አያሰጠውም። ችግሩ በማስፋፊያ አካባቢዎች አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል። አንዳንድ አዲስ ገቢዎች ወይም ለቃቂዎች ይህን ፍራቻ በውድቅት ሌሊት እቃቸውን ጭነው መውጣትና መግባት የግድ እየሆነባቸው መሆኑም ይነገራል።
በፊንፊኔ ዙሪያ ወደሚገኙ ከተሞች ቤትተከራይታቸው ወይም ሰርታችሁ ዕቃ ጭናችሁ ስትሄዱ ገና መኪናው ሳይቆም ይሰፍሩበታል። ካላወረድኩ ባዩ ቁጥር ስፍር የለውም። አንዳንዶቹ ደግሞ መኪናው በሚቆምበትና በሚያወርድበት ቦታ ከየት መጡ ሳይበል ከተፍ ብለው ከእኛ ውጪ ማንም ሊያወርድ አይገባም ይላሉ። የሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያ መብዛቱ ደግሞ ከግማሽ ሰዓት ባነሰ ሊወርድ የሚችለውን ዕቃችሁን ቀኑን ሙሉ ሲያወርዱ ይውላሉ ወይ ? ያስብላችኋል። እኛ ራሳችን እናወርዳለን ቢሉ የሚሰማዎት የለም።
በተለይ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በየጊዜው ቤት የሚከራይም ቤት የሚለቅም ሰው ስለሚበዛ የጫኝና አውራጅ ሥራዎች ይኖራሉ። ከጫኝ አውራጆች ጋር ሰፊ ውዝግብ የሚፈጠረውም እዚህ አካባቢ ነው። እኛ ካላወረድን አይወርድም ከማለት አልፎ ለክፍያ የሚጠይቁት ገንዘብ በጣም ይበዛል። ጠብ ቀረሽ ውዝግብ እየተነሳ የመንደሮቹ ሰዎች ሽምግልና እስከ መግባት ይደርሳሉ።
የቤት ዕቃዎች ከአንድ መኪና ለማውረድ ከ5ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ይጠይቃሉ። ለምሳሌ በአንድ መቶ ብር የገዛችሁትን ዕቃ ወጣቶቹ 500 ብር ይጠይቃሉ፤ ይህን ሲሉ ደግሞ ደረታቸውን ልጥጥ አድርገው በትዕቢትና ምን ታመጣለችሁ በሚል ስሜት ነው።በመኪና ተጭኖ ከመጣበት ዋጋ ጋር ስታወዳድሩት ሰማይና ምድር ነው ልዩነቱ። በዚያ ላይ ሲያስጭኑም ከፍለው ነው። በኪሳችሁ ገንዘብ ለመወሰን አትችሉም ፤አይሆንም ብትሉ ግትር ስለሆኑ አይሰሙም።
የሚመክራቸውም ሥርዓት የሚያሲዛቸውም ያለም አይመስለኝም። ብዙ ሰዎች በዚህ ጉዳይ ቅሬታ ያሰማሉ። ጫኝና አውራጆቹን እየፈጠሩ ያሉትን ችግር ሰምቶ በክፍያው ተሳቆ በምሽት ዕቃውን ጭኖ የሚሄድም አንድ ሰሞን እፎይ ብሎ ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተረኛ ጠባቂዎችና አዳሪ ጫኞች ተፈጥረዋል። አዳሪ ነን ባዮቹ ገና መኪናው ሲመጣ ደርሰው አለንልህ አታስብ እናወረድልሃለን ብለው «ደማቅ አቀባበል» ያደርጉለታል።
ጓደኞቻቸውንም ከተኙበት በኪስ ስልክ ይጠራሉ።
በመርካቶ ለጫኝና አውራጅ የሚከፈለው ገንዘብ የብዙ ሰዎችን የእለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ መሸፈን ይችላል። ከአማኑኤል እህል በረንዳ እስከ አንዋር መስኪድ ጎጃም በረንዳ በንግድ ቦታዎች ጫኝና አውራጅ ሲጭንና ሲያወርድ ሥርዓት አለው። ገዥዎች ዕቃቸውን ገዝተው ከጫኝ ጋር ተነጋግረው አወዳድረው በሚስማማቸው ክፍያ ይጭናሉ። ሥርዓት ከሌላቸው ነጋዴው ራሱ ተነጋግሮ ሥርዓት እንዲይዙ አልያም በንግድ አካባቢው ዕቃ እንዳይጭኑነና እንዳያወርዱ ያደርጋቸዋል። በዲፕሎማሲ አነጋገር ማዕቀብ ይጥልባቸዋል።
በመርካቶ አካባቢ ከሚገኙ ንግድ ቦታዎች በቅራቢያው ወደ ሚገኙ መኖሪያ መንደሮች ስትዘልቁ ግን ይህ ሁኔታ የለም። የጫኝና አውራጅ ችግር አፍጦ አግጦ ይጠብቃችኋል። እኛ ነን የምናወርደው ቤት ተከራዮች ወይም አዲስ ቤት ገቢዎች ማውረድ አትችሉም የሚል ክርክር ውስጥ ይገባሉ። በራሳችሁ ዕቃ ክፍያውን ጭምር ይወስኑላችኋል።
አንዳንዶች ችግሩን ፖሊስ ጭምር ሲያሳስቡ ይሰማል፤ መፍትሄ ግን የለም። አንዳንዴ ፖሊሶች ከጫኝና አውራጆች ጋር ውዝግብ መፈጠሩን ሰምተው ቢመጡም ተስማሙ ከማለት ውጪ መፍትሄ ሳያስቀምጡ ተመልሰው ይሄዳሉ።
ቤት መቀየር ብዙ ወጪን ይጠይቃል። የተቀየረው ቤት ኪራይ ዋጋ የጨመረ ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ላይ የሶስት ወይም የስድስት ወር መክፈልም ይኖራል። ለጫኝና ለመኪና ይከፈላል፤ አሁን ቤቴ ደረስኩ ካሉ በኋላ ደግሞ ጫኝ አውራጅ ሌላ ፈተና እየሆኑ ናቸው። ለጽድቅ እንደማይሰሩ ይታወቃል። የተጋነነ ዋጋ መጠየቅ ግን ከመጯጯህ በተጨማሪ ብዙ ቦታ ሊያደርስ ይችላል። ሰው የሚያሳዝን ተግባር መፈጸምም ተገቢ አይደለም። በዚህ በኩል ጫኝና አውራጆች ቢያስቡበት መልካም ነው። ማህበር ካላቸውም በማህበራቸው በኩል ቢነጋገሩበት ጥሩ ነው።
ወዛደር አንፈልግም ራሳችን እናወርዳለን የሚሉ ካሉም ይህን የሚሉት በእጅ እጥረት ሳቢያ ሊሆን ይችላልና ሊታሰብበትም ይገባል። ከዚህ ውጪ ደግሞ ራሴ አወርዳለሁ ማለት መብታቸው መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
ከዚህ ውጪ በመሆን በየቦታው ደርሰው የጎበዝ አለቃ እየሆኑ እኛ ነን የምናወርደው እኛ ነን የምንጭነው ብለው ዋጋ እንዳሻቸው የሚጭኑትን የሚቆልሉትን ካልከፈላችሁ ብለው ሊማቱ ሊሳደቡ ጥቂት የሚቀራቸውን እነዚህን ጉልበተኞች ባለጉዳዮቹ ብቻ ሳይሆኑ የየአካባቢው ነዋሪዎችም ከፖሊስ ጋር በመሆን ሥርዓት ሊያሲዙዋቸው ይገባል።
ቤት የሚያከራዩ ሰዎች፣ ደላሎች፣ የማኅበረሰብ ፖሊስ አባላትና የወረዳ አስተዳደር አካላት ይህን ሥርዓት አልበኝነት በመልኩ ማስያዝ ይኖርባቸዋል። መጫን ማውረድ የማይቀር ተግባር እንደመሆኑ የሚጫን የሚወርድበት መንገድም ስርአት እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል። የግጭት የአለመግባባት ምንጭ መሆን የለበትም። ሰዎች ቤት ሲቀይሩ ፣ ሰርተው ሲገቡ የጫኝ አውራጅ ነገርን ማሰብ ውስጥ መግባት የለባቸውም።
ከዚህ ሠፋ ባለ መልክ በሸገርም ሆነ በፊንፊኔ ዙሪያ ባሉ ከተሞች የሚታዩ የጫኝና አውራጅ ችግሮችን የሚመለከታቸው አካላት ሊያዩትና ሊፈቱት ይገባል። በማስፋፊያና በመሳሰሉት አካባቢዎች ያለው የጫኝና አውራጅ ሥራ በመርካቶ እና መሳለሚያ እህል በረንዳ አካባቢ ካለው የጫኝ አውራጅ ስራ ስርዓት ትምህርት መቅሰም ይኖርበታል።
እንዳልኩት የጫኝና አውራጅ ስራ አሁን የራሱን አውራጃ የመሰረተ አይነኬ አካባቢ ሆኗል። ህብረተሰቡ በእጅጉ እየተማረረ ይገኛል። ስራው የራሱን ክልል መስርቶ እንዳሻው እየተመራ ካለበት ሁኔታ መውጣት አለበት። ይህ ምንም የማያጠያይቅ በፍጥነት ሊፈጸም የሚገባውም ነው።
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/2014