ኢትዮጵያ አሁን እያደረገች ያለው ጦርነት ከአንድ ወገን ጋር ብቻ የሚደረግ ጦርነት አለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለፅ የቆየ እውነታ ነው። በተለይ በሀገር ውስጥ በግልጽ ጦርነት ከከፈቱት አሸባሪዎቹ ሕወሓት እና ሸኔ ባሻገር በስውር የሚሰሩ ሌሎች የውስጥ ባንዳዎችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ሀገሪቱን ለማተራመስ እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል። ከነዚህ መካከል በተለይ በ27 ዓመታት የሕወሓት አገዛዝ ዘመን ከሕወሓት ጋር እጅና ጓንት በመሆን ሲሰሩ የቆዩና በዚህም ሆነ በዚያ አብረው ቃልኪዳን ያሰሩ የውስጥ ባንዳዎች እንዲሁም ከነሱ ጋር በፈጠሩት የጥቅም ትስስር ሲዘርፉ የኖሩ የውስጥ ኃይሎች ተጠቃሽ ናቸው።
ከእነዚህ ኃይሎች ጀርባ ግን ከኋላ ሆነው በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ የሚያደርጉላቸው የውጭ ኃይሎች ዋነኞቹ የችግሩ ምንጭ እንደሆኑ ይታወቃል። በተለይ በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪውን ሕወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማጥፋት ሀገራዊ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ከጫፍ ጫፍ መነቃነቁን ተከትሎ ሕወሓት እንዳይጠፋ የሚፈልጉ ኃይሎች ቡድኑን ለመታደግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል አሜሪካና በሷ የሚዘወሩ ምዕራባውያን ሀገራት፣ ሚዲያዎቻቸው እና በዓለም አቀፍ ተቋማት ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ተቋማት ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ ከዓባይ ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የግብጽና ወዳጆቿ እጅም በዚህ ሀገራዊ ትርምስ ውስጥ ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑን ምሁራን ተጨባጭ ማስረጃዎችና ታሪካዊ ሂደቶችን በማጣቀስ ይገልጻሉ።
በተለይ ምዕራባውያን ሚዲያዎች በኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ በኩል ያለውን እውነታ ለማጣመምና አሸባሪ ቡድኑን ከሞት ለመታደግ የውሸት ዜና ጭምር በመፈብረክ እየሰሩ ያለው እውነታ ሲታይ እነዚህ ኃይሎች ምን ያህል በኢትዮጵያ ላይ ደባ እየሰሩ እንደሆነ ያሳያል። ከዚህ አንጻር ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ ነዋሪ የሆነውና በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ቴክኖሎጂ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆነው ሰለሞን ካሳ ምዕራባውያን ሚዲያዎች በአራት ቀናት ጊዜ ውስጥ ብቻ 72 የሃሰት ዜናዎችን መዘገባቸውን መጥቀሱ ይታወቃል። ከዚህም አልፎ ፋክት ቼክ በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ ላይ ሲወጡ የነበሩ የሃሰት ዜናዎች ሲጋልጥ እንደነበር ተመልክተናል። እነዚህ ሁሉ ከጋዜጠኝነት ያፈነገጡ ዘገባዎች ኢትዮጵያን ለማዳከምና የሽብር ቡድኑን ከሞት አፋፍ ለመመለስ የሚደረጉ ሩጫዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው።
ከዚህም ባሻገር በተለያዩ አጋጣዎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚደረጉ ጥረቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል። ከነዚህም መካከል አንዱ ኢኮኖሚያዊ ጫና ነው። ለዚህ ደግሞ አሜሪካ በአጎዋ ላይ የጣለችው እገዳ አንድ ማሳያ ነው። ከዚህም ባሻገር አሜሪካ፣ እንግሊዝና ጎረቤት ሱዳን ጭምር በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማዛባት እና የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የህብረተሰቡን ስነልቦና ለማዳከም “በኢትዮጵያ ሰላም ስለሌለ ከኢትዮጵያ ውጡ” በሚል ያስተላለፉት መልዕክት እነዚህ ኃይሎች ምን ያህል እንቅልፍ አጥተው ጫና ለማሳደር እየሰሩ እንደሆነ ያሳያል። ከዚህም አልፎ አሸባሪዎቹ ሕወሓት እና ሸኔ አዲስ አበባ ሊገቡ ከጫፍ እንደደረሱ በማስመሰል የሚያሰራጩት ዘገባዎች ኢትዮጵያን የማዳከም ሴራ እንደሆነ ይታወቃል።
በአጠቃላይ እነዚህ ሁሉ ሴራዎችና ሸፍጦች ቢኖሩም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ከህዝቡ ጋር እጅና ጓንት በመሆን አሸባሪቹን ሸኔና ሕወሓት ለመመከትና ሰላሙንም ለማስጠበቅ የጀመረው ጥረት በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል። ከዚህ አንጻር ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መንግሥትን በመደገፍ የተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችና ከተለያዩ የሀገሪቱ ጫፎች ወደሰሜን ለመዝመት የተነሳው የህዝብ ማዕበል ህዝቡ ምን ያህል በአንድነት እንደቆመ ማሳያዎች ናቸው።
ያም ሆኖ ግን ይህንን የህዝብ ማዕበል በአግባቡ ለመጠቀምና የተጀመረውን ሰላምን የማረጋገጥ ተልዕኮ ከዳር ለማድረስ እያንዳንዱ ዜጋ ይበልጥ በአንድነት በመቆም ለድሉ መስራት ይጠበቅበታል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አሁን እያንዳንዱ ዜጋ በአሜሪካ መራሹ የምዕራባውያን ፕሮፓጋንዳ ሳይረበሽ አንድነቱን በማጠናከር ስለሰላሙ ዘብ መቆም አለበት። ለዚህ ደግሞ አንዱና ዋነኛው መንገድ በቅርቡ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለምንም መሸራረፍ ተግባራዊ እንዲሆን ከመንግሥት ጎን መሰለፍ ነው።
በተለይ ኅብረተሰቡ በሽብር ወሬዎች ከመነዳት ይልቅ ከመንግሥት የሚሰጡ መረጃዎችን ብቻ መሰረት በማድረግ የሚሰጡ አቅጣጫዎችን መከተል እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ በህዝቡ ውስጥ ሽብር በመንዛት መንግሥትን ለማዳከም እና የሽብር ቡድኑ የበላይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ከሚሰሩ ኃይሎች ራሱን መጠበቅ ይኖርበታል።
በመሆኑም እያዳንዱ ዜጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ የሚያወጣቸውን መመሪያዎች እና የሚሰጣቸውን ትዕዛዞች በመቀበል ለፀጥታ አካላት መተባበር እና የተለየ እንቅስቃሴ ሲያይ ለሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ወይም ለዚህ ተብሎ በተዘጋጁ ነፃ የስልክ ቁጥሮች በመደወል ራሱንም ሆነ ሀገሩን ከጥፋት ኃይሎች መጠበቅ አለበት።
ከዚህም ጎን ለጎን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዓላማ የሚቃረን፣ የሚቃወም እና ለሽብር ቡድኖች አላማ መሳካት አስተዋፅኦ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጭት የተከለከለ መሆኑን መረዳትና ከዚህ መቆጠብ፤ እንዲሁም በአጠቃላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የወጣውን መመሪያ በአግባቡ በመገንዘብ ለዚህ ተግባራዊነት ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። ይህ ሲሆን ራሳችንን ከሚያጋጥሙ ችግሮች እንከላከላለን፣ ሀገራችንንም ከጥፋት እንታደጋለን!
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/2014