በሀዲያ ብሄረሰብ ዘንድ የትኛውም ነገር በዘፈቀደ አይፈጸምም። ባሕላዊ፣ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ክዋኔዎች የሚካሄዱት ባህላዊ ትርጉም ባለው ሂደት ነው። ሰዎች በተፈጥሮ ወይም በሰው ሰራሽ አደጋ ሲሞቱ እና በማህበረሰቡ ውስጥ ያልተለመደ ክስተት ሲፈጠር የብሄረሰቡ ተወላጆች የችግሩን መንስኤና መፍትሄ ትርጉም ባለው መንገድ ፍቺ የሚያገኝበት መንገድ ‹‹ሕራጋ/ hiraaga›› ተብሎ በሚታወቀው ባህላዊ ሥነ-ሥርዓት ነው።
‹‹ሕራጋ›› የሚለው ቃል በአማርኛ ቀጥተኛ ትርጉም ማስቀመጥ ባይቻልም ‹‹ትንቢት›› የሚለው ቃል ተቀራራቢ ትርጉም ሊሰጥ ይችላል። ‹‹ሕራጋንቾ›› ደግሞ ትንቢት ተናጋሪ ሰው ነው። ‹‹ሕራጋኖ›› ደግሞ የሕራጋንቾ ብዙ ቁጥር አመልካች ነው። ሕራጋ በአንዳንድ የሀዲያ አካባቢዎች ‹‹ካልታ›› በመባልም ይታወቃል። የ‹‹ሕራጋ›› ምንነትንና ለብሔሩ የሚሰጠውን ፋይዳ ማስቃኘት የዛሬው የባህልና ቱሪዝም አምድ ጽሑፋችን ዋና ማጠንጠኛ ይሆናል።
የሀዲያ ባህልና ቋንቋ ተመራማሪ እና የሀዲይሳ መጽሃፍት ጻሃፊ አቶ ግርማ ሱልዶሎ እንደሚሉት ‹‹ሕራጋ›› ሁለት ገጽታዎች አሉት። አንደኛው ያልተለመደ ክስተት ወይም ድንገተኛ አደጋ ሲፈጠር ተያያዥ ነገሮችን በመፈተሽ መፍትሄ መፈለጊያ ጥበብ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ካለፈው ነገር ጋር በማስተያየት ለወደፊት በግለሰብ፣ በብሔረሰብ፣ በሀገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊሆን የሚችለውን ነገር መተንበይ ነው።
ሕራጋ ፈጣሪ በመረጠው ሰው/ሕራጋንቾ/ አማካይነት ግሳጼ ወይም ምክር ለግለሰብ፣ ለቤተሰብ፣ ለማሕበረሰብ አሊያም ለአገር የሚያስተላልፍበት መንገድ ነው ተብሎ እንደሚታመን የሚናገሩት አቶ ግርማ ሱልዶሎ፤ ሕራጋ እንደጸጋ የሚታይ ባህላዊ እውቀት መሆኑንም ነው የሚያብራሩት። ሕራጋ ከተለመደው የአኗኗርና የአፈጣጠር ሂደት ወጣ ያለ ነገር ሲያጋጥም፣ በኑሮ ሂደት ውስጥ አለመግባበት ሲፈጠርና በግጭቶች ሕይወት ሲጠፋ የከፋ አደጋ እንዳይደርስ ከማድረግ በተጨማሪ ተበዳይ እና በዳይ ያለ ስጋት በጋራ መኖር እንዲችሉ የሚያደርግ ሥርዓትም እንደሆነ ያብራራሉ።
ሕራጋ ቀደም ሲል የደረሰውን ክስተት መነሻ በማድረግ ወደፊት የሚሆነውን መግለጥ ሲሆን በብሔሩ ውስጥ ሰፊ የሆነ ማሕበራዊ ተቀባይነትና ፋይዳ ኖሮት ለአያሌ ዘመናት ሲተገበር እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረ ሥርዓት ነው።
በሀዲያ ማሕበረሰብ ውስጥ ሕራጋኖ አልፎ አልፎ የሚገኙ ሲሆን፣ ሕራጋ በፈጣሪ ምርጫ ለሕራጋንቾ ብቻ የሚሰጥ ልዩ ጥበብ እንጂ የግለሰብን ፍላጎት ወይም ሃይማኖት የሚነካ አለመሆኑን የሚያብራሩት አቶ ግርማ፤ ሕራጋንቾ የሆነ ግለሰብ የየትኛውም እምነት ተከታይ ቢሆን ሕራጋ ከፈጣሪ ይሰጣል ተብሎ በብሄረሰቡ ዘንድ እንደሚታመን ያስረዳሉ። ያልተለመደ ክስተት አሊያም አደጋ ሲደርስ (‹‹ሕራግሲማ/hiraagsima››) ወደ ሕራጋንቾ ለመሄድ የሚፈልግ ግለሰብም የሃይማኖት ልዩነት አያግደውም።
ሕራጋ በዘር ይተላለፋል አይተላለፍም የሚሉ ሁለት አከራካሪ ሃሳቦች አሉት። በዘር ይተላለፋል የሚሉት ወገኖች እንደአብነት የሚያነሱት አብዛኛውን ጊዜ ሕራጋኖ የሚፈጠርበትን የተወሰነ የሀዲያ ጎሳ በመጥቀስ ነው። በዘር አይተላለፍም የሚሉት ግለሰቦች ደግሞ ሁለት መከራከሪያ ነጥቦችን ያነሳሉ። ሕራጋኖ በተወሰኑ የብሄሩ ጎሳዎች ውስጥ የሚበዙበት ሁኔታ ቢኖርም በሁሉም ጎሳዎች አልፎ አልፎ እንደሚፈጠሩ ይገልጻሉ። በተጨማሪም አንድ ሕራጋንቾ ከወለዳቸው ልጆች ውስጥ የተወሰኑት የሕራጋ ተሰጥኦ ቢኖራቸው እንኳ ተሰጥኦ የሌላቸውም እንደሚኖሩ በመግለጽ ሕራጋ በዘር አይተላለፍም የሚል መከራከሪያ እንደሚያቀርቡም አቶ ግርማ ያስረዳሉ።
ሕራጋኖ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአካባቢ፣ በብሔሩም ሆነ በአገር ደረጃ ያልተለመደ አዲስ ክስተት ሲፈጠር አልያም ግጭት ሲከሰት ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጡ ሲሆን ብሔሩ ከፈጣሪ የተላከ መፍትሄ አድርገው በመቀበል ያለ ምንም ማንገራገር ይተገብራል።
የ‹‹ሕራግማ/hiraagma›› ፀጋ የተሰጠው ግለሰብ ፈጣሪ በነጸ የሰጠውን ጥበብ በአግባቡ እየተረጎመ ለሕብረተሰቡ የመፍትሄ አካል መሆኑን በመዘንጋት ከራሱ የሚጨምር ወይም የሚቀንስ አሊያም ለአገልግሎቱ ክፍያ የሚቀበል ከሆነ እንደሚነጠቅበትም አቶ ግርማ ያብራራሉ።
ሕራጋ ምንም እንኳ በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ ባይኖረውም የሀዲያን ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊ፣ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ያስተሳሰረ ሲሆን ለባሕላዊ ዳኝነት ማስፈጸሚያ ዓይነተኛ መሳሪያ ከመሆኑም ባሻገር በሰዎች መካከል ሰላም ከመፍጠር እና ግጭቶችን ከማስወገድ አንፃርም ሚናው የጎላ መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ግርማ ማብራሪያ፤ ሀዲያ ከጥንት ጀምሮ በራሱ መንግሥት በ ‹‹ገራዳ›› ሥርዓት ሲተዳደርና ሲመራ የኖረ እና የራሱ የሆነ ትውፊት ያለው ህዝብ ነው። አብሮ በሚኖሩ የአንድ ማሕበረሰብ አባላት መካከል በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ግጭቶች መከሰታቸው አይቀሬ ነው። ብዙ ጊዜ የግጭቶች መነሻ የሚሆነው ደግሞ በሀሳብ ያለመግባባት ሲፈጠር እንደሆነ ይታወቃል። ግጭቶች ሲፈጠሩ ደግሞ የሕይወት ማለፍና የአካል መጉደል ሊደርስ ይችላል።
ሀዲያ የዚህ አይነት እና ሌሎችም ክስተቶች በሚፈጠሩበት ወቅት የሚፈቱባቸው ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓቶች ያሉት ሲሆን በሥርዓቶቹ መሰረት ችግሮቹን ለመፍታት ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ሲገጥም ወደ ሕራጋኖ በመሄድ የተፈጠረውን ነገር በዝርዝር በማስረዳት መፍትሄ ማገኘት ባሕላዊ ግዴታ ይሆናል። ሕራጋንቾም ያለፈውን ታሪክ ጠይቆ ከተረዳ በኋላ የመፍትሄ ሃሳብ ያስቀምጣል። ውሳኔውም ያለ አንዳች ልዩነት ይጸናል ይላሉ።
በሌላ ጎኑ ደግሞ ብሔሩ በተሽከርካሪ አደጋ፣ በግጭት፣ በቂም በቀል፣ በስህተት እና በሌላም ምክንያት የሰው ነፍስ ካለፈ ያለምንም ተጨማሪ ደም መቃባት እና ካሳ ሳይጠየቅ እርቅ እንዲፈጠር የሚደረግበት የ‹‹ጢግ-ጉላ›› ሥነ-ሥርዓትም አለ። ሽማግሌዎች (ማጋ/maaga) ለጢግ-ጉላ ዳኝነቱን ከጀመሩ በኋላ የጢግ-ጉላ ሥርዓት ለማከናወን ከመካከላቸው አንድ ማጋ በመወከል የተጎጂውንና የጉዳት አድራሹን ቤተ-ዘመዶች ይዘው ወደ ሕራጋንቾ ቤት እንዲሄድ እንደሚደረግ ያብራራሉ።
የተጎጂው ቤተሰብ እና ጉዳት አድራሹ አብረው ወደ ሕራጋንቾ ቤት የሚሄዱበት ምክንያት በዘር ግንዶቻቸው የተደበቀ እና የማያስተውሉት ግፍ ካለ ሕራጋንቾ በዝርዝር አጥርቶ ሲጠይቃቸው በማስታወስ ለመንገር ነው። ለጢግ-ጉላ ሥነ-ሥርዓት ከሁለቱም በኩል የተመረጡ የባሕል ዳኞች የወከሉት ማጋ ከባለጉዳዮቹ እና ከባለጉዳዮቹ ቤተ-ዘመዶች ጋር ወደ ሕራጋንቾ ቤት ሲደርስ በአጋጣሚ ምግብ እየተበላ ወይም ቡና እየተጠጣ ከሆነ አብረው ከተቋደሱ በኋላ ሕራጋንቾ እንደየሁኔታው በቤቱ ወይም በቤቱ ደጃፍ ዛፍ ሥር ተቀምጦ የባሕል ዳኞች ወክለው የላኩትን ማጋ ሁኔታውን በዝርዝር እንዲያስረዳ ይጠይቃል። ሕራጋንቾ ሽማግሌው /ማጋ/ ሲያስረዳ ግልጽ ያልሆነ ነገር ሲገጥመው ደጋግሞ በመጠየቅ ይረዳል። ከዚያም ጉዳት ያደረሰውን ግለሰብ ስለክስተቱ እና ከዚያ በፊት በስውር የሰራው ግፍና ወንጀል ካለ ሳይደብቅ እንዲናገር ያበረታታል።
እንደ አቶ ግርማ ማብራሪያ፤ ለምሳሌ በመኪና ተገጭቶ የሰው ህይወት ጠፍቶ ከሆነ ክስተቱ በስህተት አሊያም ሆን ብሎ የመግደል አደጋ ከሆነም ከዚያ በፊት በራሱ ወይም በቤተ-ዘመዶቹ በስውር የተደረገ ግፍ እንዳለ የማጣራት ስራ ይሰራል። በብሄረሰቡ ባህል፣ ልማድና ወግ መሰረት ሕራጋንቾ ለሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ትክክለኛና እውነተኛ ምላሽ መስጠት ግድ ነው። ከደበቁ አንድም ለሕራጋንቾ ሕራጋ አይታይለትም። እንዲሁም እውነቱን በደበቁት ወገኖች ትውልድ ላይ የከፋ አደጋ ይደርሳል ተብሎ ይፈራል። ጉዳት ካደረሰው ግለሰብ በመቀጠል በቤተሰቦቹ ላይ ያደረሰው ግፍ ስለመኖሩ ተራ በተራ ይጠይቃል። በተመሳሳይም ጉዳት የደረሰበት ቤተሰብ ከአሁን ቀደም ተመሳሳይ አደጋ ደርሶባቸው ካሳ አስከፍለው እንደሆነ ወይም በቤተሰብ ተሰርቶ ያለፈ ግፍ መኖር አለመኖሩን አጥብቆ ይጠይቃል።
ሕራጋንቾ እውነቱን ለማውጣት ሁለቱንም ወገኖች መርምሮ ጠይቆ ከጨረሱ በኋላ የባሕል ዳኞቹ እንዴት አድርገው መጨረስ እንዳለባቸው የመፍትሄ አቅጣጫ ይነግራቸዋል። ለምሳሌ ለሟቹ ቤተሰብ ጊደር፣ ወይፈን፣ ወይም ፍየል ለማስታወሻነት እንዲሰጥ አሊያም ለሟቹ እናት ሙሉ ልብስ ከነመቀነቱ ተገዝቶ እንዲያለብስ እና የገዳዩ ቤተሰብ ለዕርቅ ሥርዓቱ ማካሄጃ የሚሆኑ ነገሮችን ይዘው ወደ ሟቹ ቤት በመሄድ አርዶ ሁለቱም ወገኖች ተቀላቅለው በጋራ እንዲመገቡና ድሆችን እንዲያበሉ ሊያዝ ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ገዳይ ከሟች ቤተሰብ ጋር አንድ ላይ እንዲተኛ ጭምር ሊያዝ ይችላል።
ሽማግሌዎችን ወክሎ የሄደው ሽማግሌ ሕራጋንቾ የነገረውን ለላኩት የባሕል ደኞች አንድ በአንድ ያስረዳል። የባሕል ሽማግሌዎቹም /ማጋ/ ሕራጋቾ ያስቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል የጢግ-ጉላ ሥነ-ሥርዓት በማካሄድ ጉዳዩን ይጨርሳሉ። ሕራጋንቾ ያስቀመጠውን የመፍትሄ አቅጣጫ በመከተል የባህል ዳኞች በጨረሱት ጉዳይ ቂም መያዝና በክፉ መፈላለግ አይኖርም። ከዚያ ባለፈም ሁለቱም ወገኖች እንደዘመድ ስለሚተያዩ በጋብቻ መተሳሰር እንደማይችሉ አቶ ግርማ ያስረዳሉ።
ድርቅና ዝናብ ከጸና፣ ለተከታታይ ዓመታት ምርት ከቀነሰ፣ ጦርነት ከተከሰተ፣ ድህነትና ሌብነት አንድ የዘር ሀረግ ይዞ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከዘለቀ፣ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ካጋጠመ ፣ ሰውም ሆነ እንስሳ ከተለመደው ወጣ ያለ የአካል ክፍል ያለውን ልጅ ከወለዱ፣ እንስሳት የራሳቸው ወገን ያልሆነውን ከጠቡ ወደ ሕራጋኖ ይኬዳል።
ለአብነት ያህል የሀዲያ ብሄር ዘመን መለወጫ የሆነው ያሆዴ በዓል በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል። የዞኑ መንግሥትም በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብራል። የ2014 ያዴ በዓል ግን እንደሌሎች ዓመታት በዞን ደረጃ በደማቅ ሁኔታ አልተከበረም። በዓሉ ደማቅ ሁኔታ ያልተከበረበት ምክንያት ደግሞ ሕራጋኖ ሀገሪቱ በጦርነት እየታመሰች ባለችበት በዚህ ወቅት በዓሉ በድምቀት መከበር እንደሌለበት ትዕዛዝ በማስተላለፋቸው ነው።
ሕራጋኖም ክስተቶችን በሁለት መልክ ይተረጉማሉ። አንድ መጥፎ ነገር ከተከሰተ አንደኛ ግለሰቡ (ሕብረተሰቡ) ክፉ ስራ ከመስራቱ የተነሳ የተፈጠረ ክስተት መሆኑን በማስረዳት ሕዝቡ ከፈጣሪ ጋር የሚታረቅበትን የመፍትሄ አቅጣጫ ይናገራሉ። ሌላኛው ደግሞ በቀጣይ ዘመናት ሊሆን ያለውን በመንገር ሕዝቡ ዘመኑን በእውቀትና በጥበብ እንዲያሳልፍ ምክር የሚሰጥበት መንገድ ነው።
ሁል ጊዜ ሕዝቡ ወደ ሕራጋንቾ አይሄድም። አልፎ አልፎ ሕራጋንቾ ለህዝቡ ማስጠንቀቂያዎችን የሚያስተላልፍበት ሁኔታዎች አሉ። ሕዝቡ ያልተለመደ አዲስ ነገር ሲከሰት አሊያም ግጭት ሲፈጠር መላ ፍለጋ ወደ ሕራጋንቾ የሚሄድበት መንገድ እንዳለ ሆኖ ሕራጋንቾ ራሱ ስለ ዘመን እና ትውልድ ከፈጣሪ ያገኘውን ለባሕል ሽማግሌዎች የሚተርክበት ሁኔታም አለ። ሽማግሌዎቹ ደግሞ ከሕራጋንቾ ያገኙትን መረጃ ለቀጣይ ትውልድ በማስተላለፍ ትውልዱ ዘመናትን አውቆ በጥበብ እንዲኖር ምክር ያስተላልፋሉ።
ሕራጋ እና ሀዲያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው የሚሉት አቶ ግርማ ፤ ግለሰብም ሆነ የባሕል ሽማግሌዎች ከሕራጋኖ ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ቀላል ጉዳዮችን ወደ ሕራጋኖ ሳይሄዱ ራሳቸው በመተርጎም የሚጨርሱበት ሁኔታዎች እንዳሉም ይጠቁማሉ። በአንድ ቤተሰብ /ግለሰብ/ ላይ ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሯዊ ክስተቶች ከተደጋገሙ ግለሰቡ /ቤተሰብ/ ቀደምት ሽማግሌዎች ከሕራጋኖ ከቀሰሙት እውቀት ተነስተው ያስተላለፉትን ጥበብ በመጠቀም የችግሩን መንስኤ በማጤን መፍትሄ ያበጃል። የባህል ዳኞችም ምንም አይነት የሚያነጋግርም ሆነ የሚያከራክር ጉዳይ ሲገጥም ውሳኔ ከመስጠታቸው አስቀድሞ የተሳሰተ ውሳኔ በማስተላለፍ ግፍ /በርቼ/ ይዘው ወደ ቤታቸው ላለመሄድ በዘርፈ ብዙ መንገድ የማጣራት ሥራ ይሰራሉ። በመቀጠልም ከልምድ ያገኙትን ሕራጋ በመጠቀም እርቅ እንዲፈጠር ያደርጋሉ።
ለእርቅ የሚመላለሱ ሽማግሌዎች በሚመላለሱበት ወቅት እንደየባለጉዳዮቹ ፍላጎት ቡና ወይም ምግብ አዘጋጅተው ከሚጋብዙት ውጭ ምንም አይነት ካሳ በብርም ሆነ በአይነት መቀበል የተከለከለ መሆኑን የሚያብራሩት አቶ ግርማ፤ በክርክር ወቅት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሰሩት ስህተት ቢኖር እንኳን ምንም ነገር ይዘው ወደቤታቸው ላለመመለስ የያዙት ጉዳይ ባለቀበት ቤት ደጃፍ ላይ ልብሶቻቸውን አራግፈው፣ እግሮቻቸውን ታጥበው ነው የሚሄዱት።
ለብሄረሰቡ ልዩ ጥቅም እየሰጠ አያሌ ዘመናትን የዘለቀው ሕራጋ ቦታ እያጣ እንዳይሄድ እና ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አቶ ግርማ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ኅዳር 5/2014