አገራችን ኢትዮጵያ በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ከገባች እነሆ ዓመታት እያስቆጠረች ነው። በነዚህ ዓመታትም ለውጡን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ከውስጥም ከውጪም በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በስፋት እየተስተዋሉ ነው። በዚህም አገርና ሕዝብ ከፍ ባለ ፈተና ውስጥ ይገኛሉ።
በተለይም በሕዝብ የተጸነሰውን የለውጥ መንፈስ በተደራጀና ስልታዊ በሆነ መንገድ ያለ ብዙ ደም መፋሰስ ወደ ውልደት ያመጣው የለውጥ ኃይል፤ ለውጡን የስኬት ታሪክ በማድረግ ሂደት ውስጥ ግምባር ቀደም በመሆን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል። ይህንን የማድረግም ታሪካዊ ኃላፊነትም አለበት።
የለውጥ ኃይሉ አንድም እንደ አንድ አገር ወዳድ፤ ለአገር በጎ አሳቢ ዜጋ በአገር ላይ የተደቀነውን ስጋት ለመቀልበስ በሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ የመሳተፍ የዜግነት ኃላፊነት አለበት ፤ከዚህ በላይ እንደ አንድ የለውጥ ኃይል ለውጡን በስኬት ለማጠናቀቅ በለውጡ ወቅት የተሰዉ ሰማዕታት የአደራ ቃል አለበት።
ይህ ድርብ ኃላፊነት የለውጡ ኃይል ግንባር ቀደም በመሆን እንደ አገር በአሸባሪው ሕወሓት ፣ በታሪካዊ ጠላቶቻችንና የለውጡ አስተሳሰብ ስጋት በፈጠረባቸው ኃይሎች የተቃጣብንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ራስን ለመስዋዕትነት ማዘጋጀት ይኖርበታል።
የትኛውም አይነት የለውጥ አስተሳሰብ ያለ መስዋዕትነት ለስኬት በቅቶ አያውቅምና የለውጥ ጉዞ በመስዋዕትነት የታጀበ ነው። ለውጥ ያለ መስዋዕትነት ይሳካል ብሎ ለማሰብ መሞከርም ራስን ከለውጥ አስተሳሰብ እና ጉዞ ማሰናከል ነው።
ይህ አይነቱ አስተሳሰብ አንድም ከራስ ወዳድነት፤ ለውጡን ለግል ጥቅም እንደ መልካም አጋጣሚ አድርጎ ከመውሰድ፤ ከዚህም ባለፈ ለውጡን በድል አጠናቆ ታሪክ ለመሆን ራስን ከመካድ ጀምሮ ሰማዕት መሆንን የሚጠይቅ የዓላማ ጽናት እንደሚፈልግ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው።
አሁን እንደ አገር ያለንበት ታሪካዊ ወቅት ከመጣንበት የታሪክ አዙሪት ለመውጣት ፤ አገርና ሕዝብን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለማሸጋገር ካለው ከፍ ያለ ፋይዳ አንጻር የለውጥ ኃይሉ በተጨባጭ የሚፈተንበት ነው። ይህንን ፈተና በድል ለመወጣትም ከፍ ያለ የዓላማ ጽናት ይፈልጋል ።
ይህ የዓላማ ጽናት ለአገርና ለሕዝብ መስዋዕት መሆን የቱን ያህል ክብር እንደሆነ፤ በመስዋዕትነት ውስጥ ህያው የሚያደርግ የትግል መንፈስ እንደሚፈጠርና ይህም ትግሉን በድል ለማጠናቀቅ አልፋና ኦሜጋ እንደሆነ ከመረዳት የሚመነጭና የሚጎለብት ነው።
ከዚህ አንጻር የለውጥ ኃይሉ ለውጡንና የለውጡን አስተሳሰብ ለመቀልበስ ሰልፈኛ የሆነውን የውስጥና የውጪ ኃይል ግምባር ቀደም በመሆን ታግሎ ለማሸነፍ ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅበታል። የሰልፉን አደባባይ በመሙላት በርግጥም የሰልፉ መሪ መሆኑን በተግባር ሊያሳይ፤ በዚህም ታሪክ ሰሪነቱን ተጨባጭ ሊያደርግ ይገባል።
ራሱን የለውጥ ኃይል አድርጎ የወሰደ የትኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን በአሁነኛዋ ኢትዮጵያ የሚቆዝምበት ጊዜም ሆነ ቦታ የለውም ፤ ከዚህ ይልቅ ወቅቱ ራሱን ከፍ ላለ አገርና ትውልድ አሻጋሪ ተልዕኮ የሚያዘጋጅበትና ለዚህም ሕይወቱን መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ቁርጠኛ የሚሆንበት ነው።
የለውጥ ኃይሉ ከሁሉም በላይና በፊት ለዘመረለት የለውጥ አስተሳሰብ ፤አስተሳሰቡ ይዞት ለመጣው አገራዊ ትንሳኤ ያለውን ቀናኢነት ከቃላት ባለፈ በተጨባጭ የሕይወት መስዋዕትነት ታሪክ የሚያደርግበት የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ እንደሚገኝ በአግባቡ የሚረዳበትና ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት የሚፈጥርበት ነው።
ወቅቱ ተናጋሪና ተመልካች ፤ ዳር ቋሚና ተቺ የሚበዛበት ሳይሆን፤ ለተቀበለው የለውጥ አስተሳሰብና አስተሳሰቡ ለሚወልደው የሕዝብና አገር ልዕልና ሁሉም በሚችለው እና በሚጠየቀው የመስዋዕትነት መጠን ራሱን አዘጋጅቶ ከፍ ባለ ጽናት ለማይቀረው ድል የሚተምምበት ነው!
አዲስ ዘመን ኅዳር 5/2014