ጉዳዩ፣ በወታደራዊ ሰልፍ ውስጥ እንዳለው “ባለህበት ሂድ” የሚሉት ዓይነት ነው፤ ወደፊት የለ ወደኋላ፤ ብቻ ባሉበት መርገጥ፤ ትናንት በነበሩበት ቦታና መስመር ላይ ዛሬም እዚያው መርገጥ፡፡ ባሉበት ደጋግሞ መርገጥ ደግሞ ሲያዩት ያምራል፤ ይስባል፡፡ በአንጻሩም ሁነቱን በጥሞና አስተውለው እስኪገነዘቡት በግርማ ሞገስ በኅብረት ሲረግጡት ሁነቱ ያስፈራል፤ ይሁን እንጂ ይህ ባለበት ሆኖ ከሚታየው የግርማ ሞገስ ትዕይንት የዘለለ ወደ ኋላም ወደ ፊትም የሚያደርሰው ተጽዕኖ የለም፡፡ እናም ባሉበት የመሄድ እርምጃ ካልተገነዘቡት ደምስሶ የሚያልፍ ዓይነት ርደትን ይፈጥራል፡፡ ሲገነዘቡት ግን ውበትና ስበትን ከመፍጠር የዘለለ ጉዳት የማያደርስ እንደሆነ ያውቁታል፡፡
የአሸባሪው ሕወሓት እና ጋላቢዎቹ አሁናዊ እውነትም ሁል ጊዜም መልኩን እንደማይቀይረው የ“ባለህበት ሂድ” ዓይነት ነው፡፡ ምክንያቱም ትናንት እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እና ኢትዮጵያውያንን ለመበታተን በሚያደርጉት ጉዞ ውስጥ የሽብር ተግባርን እንደ ዋና ስልትና መሣሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ ይህ አካሄድ በሴራ ታግዞ በወቅቱ ከነበረው አጠቃላይ ሁነት አኳያ ከጫካ አውጥቶ አዲስ አበባ ቤተመንግሥት አድርሷቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ፤ በሽብርና በምዕራባውያን የፕሮፖጋንዳና ሌሎች ድጋፍ ታዝሎ ከደደቢት በረሃ አዲስ አበባ ቤተመንግሥት የደረሰው አሸባሪ ቡድን አገርን የማሻገር ሕዝብን የመምራት ጫንቃም ልብም ስላልነበረው 27 ዓመታትን አገርና ሕዝብን በመበዝበዝ፤ አዝለው ያሻገሩትን ምዕራባውያንን ተልዕኮ ሲያስፈጽም ኖሯል፡፡ በመጨረሻም አፈናና ብዝበዛ ባንገፈገፈው ሕዝብ ማዕበል ተገፍቶ ወደተጸነሰበት ጫካና ዋሻ እንዲገባ ሆነ፡፡
ይህ የዋሻ እና የጫካ ኑሮ ምንም እንኳን አሸባሪ ቡድኑ ተወልዶ ያደገበት ቢሆንም፤ በእርሱ በኩል በሥልጣን ዘመኑ ቅንጦትን ብቻ ሳይሆን ዘረፋና አፈናን በመልመዱ፤ በምዕራባውያን በኩል ደግሞ በእርሱ በኩል የሚያገኙት ጥቅም እና የሚጠመዝዙት እጅ በማጣታቸው ይህ የጫካ እና የዋሻ ኑሮው በሁሉም መልኩ እረፍት አልሰጣቸውም፡፡ እናም ለዳግም ወረራ፣ ለዳግም ግፍ፣ ለዳግም ግድያ፣ ለዳግም ዘረፋ እና ብዝበዛ ከተቀበረበት እንዲወጣ አደረጉት፡፡
እንደ ቀደመው ሁሉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ሳይነፍጉት የመንግሥትነት ህልም አስይዘው በአልሞት ባይ ተጋዳይነት እንዲፍጨረጨር ገፉት፡፡ አሸባሪው ሕወሓትም ዘመኑን በተንኮል፣ በሴራ፣ ዘረፋና አፈና ከማሳለፍ የዘለለ አዲስ ዕውቀትም መንገድም ሳይቀስም በመኖሩ ጉዞው ሁሉ ትናንት በነበረበት ላይ ነው፡፡ ወደፊትም ወደኋላም እልፍ በማያደርገው ባለህበት ሂድ ላይ በመቸንከሩም ዛሬም እንደ ትናንቱ ሽብር የተልዕኮዬ ማስፈጸሚያም መፈጸሚያም ይሆነኛል ብሎ ቀጥሎበታል፡፡
ይሄን ሲያደርግ ያልተረዳው ጉዳይ ግን እሱ ባለበት ቆሞ ሲራመድ፤ የሽብር ወሬና ፕሮፖጋንዳ እንደ ትናንቱ ዛሬ ላይ ለፍሬ የሚያበቃ አለመሆኑን ነው፡፡ ትናንት መጠነ ሰፊ የሽብር ስራ ሰርቶ በተሸበረለት መስመር ወደ በትረ ስልጣኑ እንደወጣ ሁሉ፤ ዛሬም በሽብር በሚያገኛት ኮሪደር ካለች ተጠቅሞ ስልጣን እይዛለሁ ብሎ መቃዠቱ፤ ጋላቢዎቹም በፕሮፖጋንዳ ሽብራቸው አሸባሪውን ለስልጣን እናበቃለን ብለው መመኘታቸው ከትናንት እሳቤ ያለመውጣታቸው ማሳያ ነው፡፡
ምክንያቱም ዛሬ ሽብር መፍጠር ኢትዮጵያውያንን ለህልውናቸው ከመዋደቅ፤ ለነጻነታቸው ከመጋፈጥ፤ ለክብራቸው በአንድ ከመቆም አያግዳቸውምና! ይሄንንም በጎንደር አይተናል፤ በአፋር በኩልም ሕያው ሆኖ ተመልክተናል። በተወሰነ መልኩ ተሳካልን ብለው ሲጨፍሩበት በነበረው በወሎ መስመርም አሁን ላይ ሕዝቡ የሽብር ጉዟቸውን በመገንዘቡ ራሱን በማደራጀት እየተፋለማቸው ይገኛል። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ የእኩይ ተግባር ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች የሽብር ጉዞ ኢትዮጵያውያንን የመበተንና አንበርክኮ ኢትዮጵያን የማፍረስ ኃይሉ ፈጽሞ የከሰመ መሆኑን ነው፡፡
እንዴት ከተባለም፣ ከመቀሌ በአሸባሪው አፈ ቀላጤዎች የሚዘወረው፤ በውስጥ በባንዳዎችና ሰርጎ
ገቦች የሚመራው፤ በውጪ በምዕራባውያን አገራት፣ ግለሰቦች እና መገናኛ ብዙኃኖቻቸው የሚቀጣጠለው ይህ የሽብር ጉዞ፤ እነርሱ እንዳሰቡት ኢትዮጵያውያንን አላራደም፤ ለአሸባሪዎችም አቅም ፈጥሮ አላራመደም፡ ፡ ይልቁኑም በሽብር መንገድ ለሽብር ተግባር አገርን ለማፍረስ እስከሲዖል እንወርዳለን ያለውን ቡድን ከሲዖል ደጃፍ አደረሰው እንጂ፡፡ ሽብርን ለተልዕኮ ማስፈጸሚያ መጠቀም ጊዜው ያለፈበት ነው ስንልም ለዚህ ነው፡፡ በመሆኑም በውስጥም፣ በውጪም ሆናችሁ ኢትዮጵያውያንን በሽብር ለመፍታት የምታደርጉት የተቀናጀ ጥረት ፍሬ አያፈራም እና እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ፤ ድሉ ሁሌም ከኢትዮጵያውያን ላይወጣ ኢትዮጵያውያንንም አትፈታተኑ!
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/2014