ወይዘሮ በላይነሽ ኤልያስን በለገጣፎ- ለገዳዲ ዳሊ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ በተጣለ ድንኳን ውስጥ ናቸው። የሁለት ዓመት ልጃቸውን አቅፈው እንባቸው በጉንጮቻቸው እያፈሰሱ ብሶታቸውን ይናገራሉ። <<የትወደቅሸ፣ ልጆችሽስ በምን ሁኔታ ላይ ናቸው>> ብሎ የጠየቀና አንድም የመንግስት አካል የለም የሚሉት ወየዘሮዋ፤ የልጆቻቸው እጣ ፋንታ ምን ላይ እንደሚወድቅ ስጋት ገንቷቸዋል።
ወይዘሮ በላይነሽ እንደገለጹት፤ የስንምንት ዓመትና የሁለት ዓመት ልጆች አሏቸው። እነዳላቸው ልጅ ወልደው ያሳደጉበት ቤታቸው በህገወጥነት ተፈርጆ በለገጣፎ -ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ትዕዛዝ ያለፈው ቅዳሜ ዕለት እንደፈረሰባቸው የሚናገሩት ወይዘሮ በላይነሽ፤ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ መውደቃቸውን ያስረዳሉ። ልጃቸው ከትምህርትቤት ሲመጣ ቤቱ ፈርሶ ሲያይ የተሰማው መጥፎ ስሜት መቀየር ባይችሉም ህይወታቸውን ለማቆየት ደግሞ ደጀሰላም መውደቃቸውን ያስረዳሉ። አሁንም የበርካቶች ቤት ከፈረሰ በኋላ መጠለያቸው ቤተክርስቲያን ውስጥ መሆኑን ይናገራሉ። አሁንም በርካታ ህጻናት አሁንም ከትምህርት ቤት ቀርተዋል። የሚሄዱትም ቢሆኑ ትምህርት ገበታቸው ላይ ተረጋግተው መማር አልቻሉም።
<<ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለን እስከመቼ እንቆያለን>> የሚል ጥያቄ የሚያነሱት ወይዘሮዋ፤ የዶክተር አብይ መንግስት ችግራችንን አይቶ አፋጣኝ ምላሽ ይስጠን ይላሉ። የአየር ካርታና አስፈላጊው የህጋዊነት መረጃ ቢኖራቸውም በተጨማሪም በአካባቢው ልማት ላይ ከመንገድ እስከ ድልድይ ስራ አስተዋጽኦ ቢያደርጉም በሰባት ቀን ማስጠንቀቂያ ቤታቸው መፍረሱ ሳያንስ የት ደረሳችሁ ብሎ የጠየቀ የመንግስት አካል አለመኖሩ እንዳሳዘናቸው ወይዘሮዋ ብሶታቸውን ይገልጻሉ።
እንደ እርሳቸው ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው ከ150 ሰዎች ጋር ድንኳን ውስጥ ብርድ እየጠበሳቸው ለማደር ተገደዋል። የአካባቢው ህብረተሰብ ግን ከአስተዳደሩ በተለየ የሚበላውንም ሆነ የሚጠጣውን ለተፈናቃዮች እያቀረበ ይገኛል። ልበ ሩህሩህ ሰዎች የዕለት ጉርሳቸውን ቢለግሷቸውም ይህ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም።አሁን ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑንና ልጆችን ጤናም ሆነ ለወላድ እናቶች አሰፈላጊው እንክብካቤ ማድረግ የሚያስችል መጠለያ ያስፈልጋል።
እድሜያቸው በግምት 60ዎቹ ውስጥ የሚገኘው አቶ አበበ ገበረጻዲቅ ደግሞ ሰባት ልጆች እነዳላቸው ይናገራሉ። አንዷ ልጃቸው በአረብ አገር መከራውን ችላ ሰረታ ባገኘችው ገነዘብ የተገነባው ቤታቸው ሲፈርስ ቆመው ማየታቸው እጅጉን ሀዘን ላይ ጥሏቸዋል። ከሰው አገር ዞሮ መገቢያዬ ይሆናል ብላ ልጃቸው ቤት ብታሰራም በህገወጥነት ተፈርጆ በመፍረሱ እንኳነ ለልጃቸው ሊተረፉ እርሳቸውም በቤተክርስቲያን ለመጠለል መገደዳቸውን ያስረዳሉ።
አቶ አበበ ተፈናቃይ በመሆናቸው በቤተክርስቲያን ሲቆዝሙ እና ሲያዝኑ እንዲውሉ ቢያደርጋቸውም የአካባቢው ማህበረሰብን ውለታ ግን ሳያደንቁ አላለፉም። ችግሩን የብሔር መልክ ለመስጠት አሰተዳደሩ ቢጥርም ህብረተሰቡ ግነ የእድሩን ድንኳነ በቤተክርስቲያን በመትከል እየደገፋቸው እንደሚገኝ ይገልጻሉ። ይሁንና አንድም የመንግስት ተወካል ተፈናቃዮች የትደረሱ ብሎ አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለማየት አለመፈለጉ አሳዝኗቸዋል። በርካታ ጡት ጠበተው ያልጨረሱ ህጻናት መሬት ላይ እየተኙና ብርድ እየመታቸው ድድጋፍ ለማድረግ ቀይመስቀል እና የተለያዩ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው አልተዋጠላቸውም። አሁንም መንግስት ካልደረሰላቸው ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ መሆኑን ይናገራሉ።
አሁን ደግሞ ከለገጣፎ- ለገዳዲ እንውጣና አያት ጣፎ መካነ ሕይወት መድሀኒያለም እና ቅድስተ አርሴማ ቤተክርስቲያን ስጥ ስለተጠለሉ ተፈናቃዮች ቅኝት እናድርግ። ቦታው ሜቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ፊት ለፊት ይገኛል። በማዕከሉ በአግባቡ የሚጦሩ አረጋውያንን መመልከት ሲቻል በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ደግሞ 1500 የሚደርሱ ተፈናቃዮች ምግብና ውሃ ሳያገኙ ሜዳ ላይ ይታያሉ። የዚህ አካባቢ ወይም የወረገኑ ተፈናቃዮች በወንዝ ዳር የተሰራው ቤታቸው በመፈረሱ ኑሯቸውን በቤተክርስቲያኑ ገቢ ካደረጉ ሳምንት ተቆጥሯል።
በርካታ ሰዎች ህጻናትንና ሴቶችን እነዲሁም አረጋውያንን ጨምሮ በቤተክርስቲያኑ ጀርባ በሚገኝ ሳር የለበሰ ቦታ ላይ እጭቅ ብለው ጸሐይ ሲመታቸው ይስተዋላል። ይህ ሁኔታ አንድ ወረርሽኝ እንኳነ ቢከሰት በፍጥነት ለመከላከል የማያስችል መሆኑን መታዘብ አይከብድም። በዚህኛው ጊዘያዊ መቆያ ደግሞ ልክ እንደ ገጣፎ እና ለገዳዲዎቹ ሁሉ ምግብ እና ውሃ የሚያቀርብ ማህበረሰብ በብዛት የለም።
ቤተክርስቲያኗ በሰጠቻቸው ድንኳነ ውስጥ ሴቶች ሲያድሩ ወንዶች ደግሞ ግቢው ውስጥ ብርድ ላይ መሆኑን የስድስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ባደግ ተሰማ ይናገራሉ። እንደ አቶ ባደግ ከሆነ፤ የአምስት ቀን መላድ እና እመጫቶች እየተጉላሉ ነው። ህጻናት ከትምህርት ገበታ ከራቁ ቀናት ተቆጥረዋል። እፀድቅ ያለ የተወሰነ የታሸገ ውሃ ቢያመጣ እነጂ የዕለት ምግብ እና ድጋፍ የሚያደርግ የለም። በመሆኑም ምንግስት ህዝቡ ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታ ተመልክቶ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል።
አቶ ባደግ እንደሚያስረዱት፤ የቤት ማፍረሱ ህጋዊነው ህጋዊ አይደለም የሚለው ጉዳይ እንኳን መፍትሄ ባያገኝ በቅድሚያ ግን ስልሰብዓዊነት ማሰብ ይገባል። በሰው ላይ ከነዕቃው ቤት ማፍረስ እና ለጎዳና ተዳዳሪ ማድረግ ከሰብዓዊነት የሚመነጭ አይደለም። ቤተክርስቲያኗ ባትኖር በርካቶች በአውሬ ተበልተው የቀሩ ነበር። አሁንም በርካቶች በምግብ እጦት እና በመጠለያ እጥረት እየተሰቃዩ በመሆኑ መንግስት ድስፍ ማድረጉን ችላ ባይለው የተሻለ ይሆናል።
የብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሮክተሬት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው፤ የአደጋ ተጎጆዎችን ለመርዳት በቅድሚያ ምክንያቱ፣ ሰዎቹ ያሉበት ሁኔታ እና ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በሚሰጡት ጥቆማ መሆኑን ተናግረዋል። ቦታው ላይ የተከሰተው ሁኔታ ምክንያት እና ምን ያህል ሰዎች እንደተፈናቀሉ እኘዱሁም ድጋፍ እነደሚያስፈልጋቸው በጽሁፍ መረጃ መላክ እንዳለባቸው ያስረዳሉ። ስለዚህ ጥያቄው በቀረበ ሰዓት ድጋፍ ለመስጠት ችግር እንደማይኖር ነው የተናገሩት። ይሁንና በጉዳዩ ላይ አስመልክቶ ለኮሚሽኑ የጽሁፍ ጥያቄ ስለመቅረቡ አለማወቃቸውን ይናገራሉ።
ጌትነት ተስፋማርም
ፎቶ፡- ዳኜ አበራ