ኢትዮጵያ ከውስጥ እና ከውጭ ህልውናዋን የሚገዳደር አደጋ ተጋርጦባታል ። አሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ በሞግዚትነት ከሚያስተዳድሯቸው ከአሜሪካና ምዕራባውያን ጋር በመሆን ሀገራችንን ለማፍረስ እና ዜጎቿን ለስደት ለመዳረግ አልመውና አቅደው እየሰሩ ናቸው።
ሀገርን ለማፈራረስ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን በመደገፍም አሜሪካና ምዕራባውያን በመገናኛ ብዙኃን ጭምር ተናበውና ተደራጅተው የሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እያካሄዱ ናቸው ። በአንድ በኩል ህዝብን ተስፋ ለማስቆረጥ የሀሰት ወሬ መንዛት፤ የኢኮኖሚ ጫና ማድረግ እና መንግሥትን ማስፈራራት ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሸባሪውን ቡድን በማቴሪያልና በሳተላይት ጦርነቱን በማገዝ ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ጭምር እያደረጉ ይገኛሉ ።
በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን አጀንዳው አድርጎ ለ12 ጊዜያት ስብሰባ ተቀምጧል። ይሁን እንጂ በጥቂት እውነትን ባነገቡ ሀገራት ሃሳባቸው ከሃሳብ የዘለለ ሳይሆን ቀርቷል። ባሰቡት መልኩ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አላንበረከኩም።
አሁንም እንቢ ለሀገሬ ያለው በውስጥም በውጪም ያለው ኢትዮጵያዊ ለነፃነቱ በአልበገር ባይነት ትግል እያደረገ ነው። ደሙን እያፈሰሰ፣ አጥንቱን እየከሰከሰና ህይወቱን እየገበረ ጭምር ነው። ባለሀብቱ በገንዘቡ መከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍና የተፈናቀሉትን በመርዳት ላይ ይገኛል። ቀሪው ስንቅ በማቀበልና አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ በየሙያው እገዛ በማድረግ እና በሌሎች ድጋፎች ሁሉ አጋርነቱን እያረጋገጠ ይገኛል ።
የዳያስፖራው ማኅበረሰብም ዓለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሠሩትን ሀሰተኛ መረጃ ከመቃወም ጀምሮ በአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ የውሳኔ አካል ለመሆን የሚሹ የውጭ ኃይሎችን በዲፕሎማሲ ጦርነት በመዋጋት አጋርነቱን በየአቅጣጫው አረጋግጧል፡፡
ሠራዊቱን ለማዳከምና ሕዝቡን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ዘመቻ በሙሉ አቅሙ ተዋግተው ለማሸነፍና ሴራቸውንም ለማጋለጥ ሌት ተቀን እየሰሩ ነው። በሁሉም አቅጣጫ ሀገርን ከብተና ለማዳን እያንዳንዱ ዜጋ በሁሉም መልኩ የአርበኝነት ተጋድሎ በማድረግ ላይ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ድሮም ሆነ ዘንድሮ የጀግኖች ሀገር መሆኗን አረጋግጣለች። የሀገራቸውን ሉአላዊነት ለማስከበር ፣ለነጻነታቸው የማይበገሩ አትንኩኝ ባይ የጀግኖች ሀገር መሆኗን ዳግም አስመስክራለች ።
አሸባሪው ሕወሓት ከምስረታው ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተፈጠረ ቡድን ነው። በስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት ሀገርን ሲዘርፍና ሲያዘርፍ ኖሯል። ዛሬ የሚንጫጩት ምዕራባውያንና ሌሎችም አገራችንን እየፈተኑ ያሉት ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚል ታዛዥ መሪ ማግኘት እንደማይችሉ በማረጋገጣቸው ነው።
ይሄ በሀገር ላይ የተሰራው ሴራ ይበልጥ አጀገነን እንጂ ተስፋ አላስቆረጠንም። ይበልጥ አነቃን እንጂ አላንበረከከንም። ይበልጥ አጠነከረን እንጂ አልተልፈሰፈስንም። ለሀገር ለመሞት ቆረጥን እንጂ አላፈገፈግንም። ይልቁንም ዓለምአቀፉ ጫና በበረታና ማስፈራሪያና የሥነልቦና ዘመቻው ባየለ ቁጥር እኛ ደግሞ አንድነታችንን አጠናክረን፤ ልዩነቶቻችንን ከአጠገባችን አርቀን በፖለቲካ ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት ልዩነት ሳንል በጋራ ቆመን ጠንካራውን ኃይላችንን አሳይተናቸዋል። በቀጣይም ኢትዮጵያ በአንድነቷ ተጠናክራ እንድትቀጥል የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ ይህንን አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በተባበረ ኃይል ሊፋለመውና ግብአተ መሬቱን ሊያፋጥነው ይገባል ።
ሰሞኑን በመላው ሀገሪቱ የተካሄዱ ህዝባዊ ሰልፎች የሀገራዊ ፍቅር ማረጋገጫ አንዱ ምስክር ነው። በዚህም ህዝባችን ለዓለም አቀፉ ጫና የማይንበረከክ መሆኑንና የአሸባሪዎቹ ሕወሓትንና ሸኔ ሀገርን የማፍረስ ውጥን ሜዳ ላይ የፈሰሰ ውሃ መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ‹‹ህዝቡ አሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ ተስፋ ቁረጡ፤ አሜሪካና ምዕራባውያን ጣልቃ እንግባ ስትሉ የሚሰማችሁ የለም፤ ምንም ኃይል ቢመጣ ሀገራችንን አናስደፍርም፤ ለሀገራችን እንሞታለን›› የሚል አንጀት ቆራጭ መልዕክት ነው ያስተላለፈው።
አሁንም ደግመን ደጋግመን እንላለን በውጪም ሆነ በውስጥ በሀገራችን ላይ የዘመታችሁ እኩያን ሁሉ ተስፋ ቁረጡ። በተቀናጀ ህዝባዊ ተሳትፎ ሁለንተናዊ ድላችንን የምናበስርበት ጊዜው ቀርቧል። ሁልጊዜም ሊነጋጋ ሲል ይጨልማል ፤ አሁን ከጨለማው ወደ ጎህ መቅደዱ ደርሰናል። በጋራ ክንዳችንም የኢትዮጵያን ተስፋ እናበስራለን!
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/2014