እውነት አቧራ ትለብስ ይሆናል እንጂ ተቀብራ አትቀርም። ሐሰት ግን የቀን ጉዳይ ይሆናል እንጂ ይጋለጣል። በሐሰተኛ መረጃ እና በጥቅም ተጋሪነት ላይ በመመስረት እውነታን እየሸፈኑ መዝለቅ አይቻልም። በኢትዮጵያ እየታየ ያለውም ይሄው ነው!
አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን እያደማ፣ ሀብትና ንብረታቸውን እየዘረፈና እያወደመ ተበዳይ መስሎ የሐሰት መረጃ እየፈበረከ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እያጭበረበረ ዕድሜውን አራዝሟል። ውሸትን ዋና መሳሪያው አድርጎ የተፈጸመው እንዳልተፈጸመ ፣ ያልተፈጸመውን እንደ ተፈጸመ አድርጎ ያቀርባል።
አንዳንድ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አካላት በኢትዮጵያ ላይ የራሳቸውን ተልዕኮ በመያዝ በአሸባሪው ሕወሓት ሐሰተኛ መረጃ ተሞልቶ የተለያዩ ጫናዎችን በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ነው። በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እያካሄደ የሚገኘውን አሸባሪውን ሕወሓት እየደገፉም ነው። የኢትዮጵያ መንግስት እውነታውን ሊያስረዳ ቢሞክርምና የኢትዮጵያ እውነታ እንዲታይ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ቢሰራም፣ ከወዲያኛው ወገን ያለው ዘመቻና የእነዚሁ አካላት እውነታውን ለመስማት ያለመፈለግ የሚፈለገውን ያህል እንዲታይ ለማድረግ አላስቻለም። በዚህ የተነሳም አገርና ሕዝብ ክፉኛ እየተጎዱ ናቸው።
እውነት ትዘገይ ይሆናል እንጂ ተዳፍና አትቀርም እንደሚለው ብሂል የኢትዮጵያ እውነታዎች በዓለም አደባባይ እየወጡ ናቸው። በሐሰተኛ መረጃ ላይ በመመስረት ዘመቻዎች ቢከፈቱባትም ፣ እውነት እና ንጋት እያደር ይጠራል እንደሚባለው እውነታዎቿ አንድ በአንድ እየወጡ ናቸው። ለዚህም የተመድ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ቢሮና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ በጋራ ያወጡት ሪፖርት ግኝት ያመላከታቸው እውነታዎች ማሳያዎች ናቸው። በዚህ ሪፖርት አሸባሪው ሕወሓት የዚህ ሁሉ ቀውስ መሰረት የሆነውን ጦርነት የከፈተ መሆኑ ተረጋግጧል፤ በማይካድራ ንጹሐን ዜጎችን የጨፈጨፈውና ያስጨፈጨፈው ይሄው አሸባሪ ኃይል ራሱ መሆኑም ተረጋግጧል።
ይህ ሪፖርት ውስንነቶች ቢኖሩትም የኢትዮጵያን እውነት ቁልጭ አርጎ አሳይቷል፤ የአሸባሪውን ሕወሓት፣ የደጋፊዎቹን ምዕራባውያንና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ቅሌትንም ገላልጦ አሳይቷል። ሪፖርቱ በሸፈናቸው ክሶች ላይ ሐሰተኛ መረጃ ጭምር እያጠናቀሩ አሸባሪው ሕወሓትና ምዕራባውያኑ መንግሥታት እንዲሁም የነሱ ወሬ አናፋሽ የሆኑ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሲነዙት የነበረው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑ ተጋልጧል። እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ከዚህ በላይ ምን ማሳያ ሊቀርብለት ይችላል።
የኢትዮጵያ እውነታ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የትናንት በስቲያ ሪፖርትም ፍንትው ብሎ ወጥቷል። አሸባሪው ሕወሓት፣ ደጋፊዎቹ ምዕራባውያንና መገናኛ ብዙኃኖቻቸው እንደ ዋዛ ያለፉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአምነስቲ ሪፖርት ተጋልጧል። አምነስቲ አሸባሪው ሕወሓት የአማራ ክልልን ወርሮ በንፋስ መውጫ ከነሐሴ 6 እስከ 21 ቀን 2013 ዓ/ም ባደረገው ቆይታ በሴቶች ላይ የቡድን አስገድዶ መድፈር ፣ ዘረፋና የአካልና የህሊና ቁስል ያስከተለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን አጋልጧል።
የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶችን በማነጋገር ያካሄደው ጥናት የደረሰበት ውጤት እንዳመለከተው፤፣ ጥያቄ ከቀረባላቸው 16 ሴቶች 14ቱ በአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች የቡድን አስገድዶ መደፈር ተፈጽሞባቸዋል። ልጆቻቸው ጭምር እየተመለከቱ አስገድዶ መደፈሩ የተፈጸመባቸውም አሉ። ድርጅቱ የንፋስ መውጫ አካባቢ የመንግስት አካላት ያረጋገጡለትን ጠቅሶ በ71 ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር ድርጊት ተፈጽሟል ሲል በሪፖርቱ አመልክቷል። የፍትሕ ሚኒስቴር በበኩሉ ይህን አኃዝ 73 ያደረሰው መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቁሟል።
አምነስቲ በተጎጂዎቹ ላይ ያካሄደው ምርመራና ጥናት ውጤት የአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች የጦር ወንጀል እንዲሁም በሰው ዘር ላይ የማይፈጸም ወንጀል መፈጸሙንም አጋልጧል። ሪፖርቱ ታጣቂዎቹ በንፋስ መውጫ የሚገኙ የጤና ተቋማትን መዝረፋቸውንና እንዲወድሙ ማድረጋቸውንም አመልክቷል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሐፊ አግኔስ ከላማርድ የሕወሓት ታጣቂዎች ወሲባዊና ፆታዊ ጥቃቶችን ጨምሮ ሁሉንም አይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎች ጥሰቶችን መፈጸማቸውን አስታውቀው፣ ይህ ጥሰት ሊቆም አንደሚገባም አስገንዝበዋል። የአምነስቲ ሪፖርት ይህን የምዕራባውያኑን እና አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ተግባር ያጋለጠ ነው። በአንጻሩ ደግሞ የኢትዮጵያን እውነታ ቁልጭ አርጎ ያመለከተ ነው።
የአምነስቲ ሪፖርት በንፋስ መውጫ ላይ ተፈጽሟል በተባለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ነፋስ መውጫ ማሳያ ናት። አሸባሪው ቡድን በአማራ ክልል ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር ፣ በሰሜን ወሎ አሁን ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞኖች ተመሳሳይ ጥቃት እየፈጸመ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች ላይም ተመሳሳይ ጥናት ከምዕራባውያኑ ተጽዕኖ ነጻ በሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቢካሄድ ቡድኑ የፈጸመው ግፍ ምን ያህል ግዙፍ ስለመሆኑ ማሳየት ያስችላል፤ ቡድኑን በፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ ማድረግም ያስችላል።
አዎን ኢትዮጵያ በአሸባሪው ሕወሓት የተፈጸመባት ግፍ ተዘርዝሮ አያልቅም። ገና የሚወጣ በርካታ እውነታ አላት። ያለስሟ ስም በተሰጣት፣ ስም በሐሰተኛ መረጃ ብዙ የተፈተነችና በመፈተን ላይ ያለች አገር ናት። የጊዜ ጉዳይ ነው፤ እውነታው አሁንም ይወጣል። ለዚህ ደግሞ አምነስቲ፣ የተመድ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ቢሮና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መሰል ተቋማት በአሸባሪው ቡድንና በተባባሪዎቹ የተሸፈኑ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን እውነታዎች ለማውጣት ይበልጥ ተጠናክረው መስራት ይኖርባቸዋል።
በቀናነት ለሚመለከተው አካል የአምነስቲ ሪፖርት እንደ ተመድ የሰብዓዊ መብት ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ሪፖርት የአሸባሪውን ቡድን ማንነት ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው። ይህን የተመለከተ ማንም ሰው አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጠላት መሆኑን በቀላሉ ይረዳል።
አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም ሆኖ እንጂ በአሸባሪው ሕወሓት የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በሌሎች ወንጀሎች ላይ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያወጡት ሪፖርቶች ለቡድኑ ድጋፍ የሚያደርጉትን ምዕራባውያን አንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶ ለቡድኑ በሚያደርጉት ድጋፍ ላይ ቆም ብለው ማሰብ በጀመሩ ነበር !
አዲስ ዘመን ህዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም