የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ዩን በኒውክለር ምክንያት የገቡበትን ፍጥጫ አስመልክቶ ሁለተኛውን ዙር ውይይት በቬትናም ዋና ከተማ ሀኖይ በፈረንጆቹ አቆጣጠር የካቲት 27 እና 28 2019 ያካሄዱ ቢሆንም፤ ትናንት ቢቢሲ በድረገፁ እንዳስነበበው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሰሜን ኮሪያ የኑክሌየር መርሀ ግብሯን መጀመሪያ ሙሉ ለሙሉ ካላወደመች ምንም አይነት ማዕቀብ ለማንሳት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ የሰሜን ኮሪያ አቻቸው ኪም ውይይቱ የሰሜን ኮሪያን ጥቅም ያላስከበረ ነው በማለታቸው ሁለቱ መሪዎች በተነሱት ጉዳዮች ላይ ባለመስማማታቸው ውይይታቸው ያለ እልባት ተጠናቋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ኪም የፈለጉት ሰሜን ኮሪያ የተጣለባት ማዕቀብ ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ ሲሆን፤ ሰሜን ኮሪያ የተጠየቀችውን ቅድመ ሁኔታ ሳታሟላ ማዕቀቡን ማንሳት አንችልም ብለዋል፡፡ ‹‹አቻዬ ኪም ጠብቆ የነበረው ሁሉም ማዕቀብ እንዲነሳለት ነበር›› ያሉት ትራምፕ፤ ድርድሩ በችኮላ ሳይሆን በእርጋታ መካሄድ እንደነበረበትና ከአሁን በኋላ ሶስተኛ ውይይት ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ጋር ለማድረግ እቅድ እንደሌላቸውም ከውይይቱ በኋላ በቬትናሟ ዋና ከተማ ሃኖይ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ውይይቱ ሁለቱ መሪዎች የጋራ ጥቅማቸውን የሚያስከብር ስምምነት አድርገው ለመለያየት የነጩ ቤተመንግስት ‹‹ኋይት ሀውስ›› ቀዳሚና እውነተኛው ፕሮግራም የነበረ ቢሆንም፤ ነገር ግን ሁለቱም መሪዎች ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ውይይታቸውን እንደሰረዙ ከወደ ቬትናም የወጣ መረጃ ያሳያል፡፡
ውይይቱ በተሳካ መንገድ እንዳይደረግ ካደረጉት ነጥቦች መካከል የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም የያዎንግን ውስብስብና የሰሜን ኮሪያ ዋና ዋና የኔክሌየር መርሃ ግብር የልብ ምት የሆነውን የምርምር እና የኑክሌየር ማምረቻ ፋብሪካን ሰሜን ኮሪያ እንድታፈራርስ ትራምፕ መጠየቃቸው ነው፡፡
ኪም በበኩላቸው ሰሜን ኮሪያ የተጣለባትን ሁሉም ማዕቀብ እንዲነሳላት አቋም ቢይዙም፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሰሜን ኮሪያ ቅድመ ሁኔታውን ካልፈጸመች ሁሉንም ማዕቀብ ለማንሳት አልስማማም ብለዋል፡፡
ኪም ሰሜን ኮሪያ ሁሉንም የኑክሌየር ማበልፀጊያ ሳታወድም ሁሉም ማዕቀብ እንዲነሳላቸው ቢፈልጉም ትራምፕ እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ኪም ለማውደም የተስማማው ዮንግብዮን ኑክሌየር ማበልፀጊያ ሰፈርን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የሰሜን ኮሪያ የኑክሌየር ማበልፀጊያ ይህ ብቻ አይደለም›› ሲሉ ተደም ጠዋል።
የሰሜን ኮሪያ ወኪሎች አሜሪካኖች እንዴት ይህን ሊያውቁ ቻሉ ብለው ተደምመዋል። የሁለቱ መሪዎች ውይይት ከዚህ በፊት በሲንጋፖር እ.አ.አ 2018 የተካሄደ ሲሆን፤ እዚህ ግባ የሚባል ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ነበር የተለያዩት። በቬትናም ሃኖይ በሚያደርጉት ውይይት የተሻለ ስምምነት ይኖራል ተብሎ ቢጠበቅም ከመጀመሪያው የባሰ ምንም ስምምነት ሳይኖር ሊለያዩ ችለዋል።
አንዳንዶች የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሁኔታዎች ቀስ በቀስ እየተስተካከሉ ቢሄዱ ይሻላል ብለው ሰሜን ኮሪያን ሊያግባቡ የሞከሩትን ሲያደንቁ፤ የኮሪያው ምሁር ከካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ስቴፈን ሀጋርድ ለሮይተርስ ዜና ወኪል እንደተናገረው ይህ እንደዋነኛ ውድቀት አይደለም፤ ነገሩ ግልጽ ነው የትራምፕ አስተዳደር ከዮንግብዮን የኑክሌየር ጣቢያ በተጨማሪ ሌሎችም እንዳሉ ማረጋገጥ ነው፡፡ ምንም ግልፅነት በሌሌበት ሁሉንም ማዕቀብ ለማንሳት ሰሜን ኮሪያን ማመን በጣም ከባድ ነው ብለዋል።
ዋሽንግተን ሰሜን ኮሪያ ምንም አይነት ማእቀብ ከመነሳቱ በፊት ሁሉንም የኑክሌየር የጦር መሳሪያዎችን ልታስረክብ ይገባታል። እንዲሁም ሁሉንም የኑክሌየር ማበልጸጊያ ቁሳቁሶችንና ኬሚካሎችን ማውደም አለባት ብትልም፤ ይህን ለማድረግ ባለመስማማታቸው ከኪም ጋር ሳይግባቡ ቀርተዋል።
ትራምፕ ለአሜሪካውያን እንደተናገሩት «አንዳንድ አማራጮች አሉን ነገር ግን ምርጫ ቢኖረንም በዚህ ጊዜ ምንም ለማድረግ አልወሰንም። ለኪም መልካም እድል ነው የሰጠነው። ነገር ግን መግባባት ላይ ሳንደርስ ተለያይተናል ፡፡ ቢሆንም ውይይቱ ለወደፊት ጥሩ ውጤት ይዞ ይመጣል ብዬ አስባለሁ»ብለዋል።
አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ የታጠቀችውን የኑክሌየር ጦር መሳሪያ እንድታወድም ካልሆነ ግን እርምጃ ልትወስድባት እንደምትችል ስታስጠነቅቃት መክረሟ፤ ኮሪያም በበኩሏ ለአሜሪካን ማስፈራሪያና ዛቻ ምላሽ እንደምትሰጥ በመግለጽ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ሲዝቱ መክረማቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና ባልተጠበቀ ሁኔታ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ሰላማዊ ድርድር በመምረጣቸው እ.አ.አ በሰኔ 2018 ሁለቱ ሀገራት ሲንጋፖር ላይ የመጀመሪያውን ንግግር ቢያደርጉም ውይይቱ ለስምምነት ሳይበቃ ቀርቷል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት22/2011
በሶሎሞን በየነ