የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ላይ የተቀዳጀችው የዓድዋ ድል እስከ ዛሬ ድረስ የበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ ድሉ የተገኘበትን መንገድና ለኢትዮጵያ የነበረውን ፋይዳ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ አንድምታውን እየዘረዘሩ ጽፈዋል፡፡
ዝነኛውና አንጋፋው ‹‹ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ (The New York Times)›› ጋዜጣ ‹‹አቢሲኒያውያን ኢጣሊያውያንን አሸነፉ›› በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና፣ ኢትዮጵያን ለመውረር የገሰገሱት የኢጣሊያ ጦር መሪዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ስለመሸነፋቸውና ‹‹አቢሲኒያውያን›› ብሎ የጠቀሳቸው ኢትዮጵያውያን ኃይለኛ የማጥቃት ዘመቻ ከፍተው የኢጣሊያን ጦር ስለማሸነፋቸው ጽፏል፡፡
የኢጣሊያ ጦር አዛዦች ወደ ዓድዋ ሲገሰግሱ ብዙም መከላከል እንዳልገጠማቸውና ዓድዋ ከደረሱ በኋላ ግን ነገሮች ሁሉ ስለመቀያየራቸው ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ የኢጣሊያንን ሽንፈት ‹‹አሰቃቂ ሽንፈት›› ሲል የገለጸው አንጋፋው ጋዜጣ፣ የጀኔራል ባራቲዬሪ ጦር ከባድ መከላከልና ማጥቃት ገጥሞት ብትንትኑ እንደወጣ የጋዜጣው የወቅቱ እትም ያመለክታል፡፡ ‹‹ኳርትዝ (Quartz)›› የተባለው ድረ-ገፅ ‹‹የአፍሪካን ታሪክ ማወቅ ከፈለግን የዓድዋ ድል እውቀቱ ሊኖረን ይገባል›› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ፣ ኢትዮጵያና ኢጣሊያ ያደረጉትና በመጨረሻ በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የዓድዋ ጦርነት የአፍሪካ ታሪክ አካል በመሆኑ የዓድዋ ድል ያልተካተተበት የአህጉሪቱ ታሪክ ሙሉ ታሪክ እንደማይሆን ያትታል፡፡
እንደጽሑፉ፣ ድሉ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቷ አካል ለማድረግ የነበራትን የወቅቱን ምኞት ያከሸፈባት ከመሆኑም በላይ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር የነበሩ አፍሪካውያንን ያነቃቃ ነበር፡፡ ከጦርነቱ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ የተፈረመውና አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት የነደፉት እቅድ አካል የሆነው የውጫሌ ውል (Treaty of Wuchale) ለዓድዋ ጦርነት እንደመነሻ ተደርጎ ቢወሰድም ቅሉ፣ የጦርነቱ መሰረታዊ መንስዔ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቷ አካል ለማድረግ የነበራት የረጅም ጊዜ ፍላጎት ነበር፡፡
ድሉ ኢትዮጵያ ለየትኛውም የአውሮፓ አገር ተገዢ ያልሆነች ሉዓላዊት አገር እንደሆነች ማረጋገጫ የሰጠ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡ የዓድዋ ድል የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የዜና ማድመቂያ ሳይሆን አውሮፓውያንን ያስገረመና ያስደነገጠ ድል ነበር፡፡ አውሮፓውያን መንግሥታት የጦርና የቅኝ ግዛት አስተዳደር ስትራቴጂዎቻቸውን እንዲያጤኑና እንዲከልሱ ምክንያት ሆኗል፡፡
ኢጣሊያ ባላሰበችውና ባልጠበቀችው ሁኔታ በቀላሉ አሸንፋታለሁ ብላ በገመተቻት ኢትዮጵያ መሸነፏ በአውሮፓ አጋሮቿ ዘንድ ዝቅ ተደርጎ የመገመት ጫና አድሮባታል፡፡ ይህን ጫና ለማቃለልና የዓድዋውን ሽንፈት ለመበቀልም በ1928 ዓ.ም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በመውረር ሽንፈቷን ለመበቀልና የረጅም ጊዜ ምኞቷን ለማሳካት ሞክራለች፡፡
የድረ-ገፁ ጽሑፍ ‹‹የዓድዋ ድል በሁሉም መመዘኛ እጅግ አስደናቂ ነበር›› ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን ነፃነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል ያስቻለና መላው ዓለም በድሉ ተደንቆ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክንና የኢትዮጵያን ሕዝብ እንዲያከብር አጋጣሚን የፈጠረ ድል እንደሆነ በጽሑፉ ተመላክቷል፡፡
‹‹ኢንተርናሽናል ኢንተረስት (International Interest)›› የተባለ ድረ-ገፅ ዓድዋን ድል ‹‹አፍሪካን ያስገረመ ታላቅ ድል›› በማለት ገልጾታል፡፡ የድረ-ገፁ ጽሑፍ እንዳተተው፣ ድሉ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እንድትቆይ ከማስቻሉም በተጨማሪ፣ አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት የነደፉት እቅድ ኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህ ባሻገር ድሉ ኢትዮጵያ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ሞዴል ሆና እንድትታይና ሌሎች የአፍሪካ አገራት በቅኝ ገዢዎቻቸው አውሮፓውያን ላይ እንዲያምፁ ተምሳሌት ትሆናለች ተብሎ እንደታሰበም ጽሑፉ ይገልፃል፡፡
ድረ-ገፁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ለጦርነቱ ያደረጉትን ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅትም ጠቅሷል፡፡ ንጉሱ ካደረጉት ጠንቃቃነትና ዝግጅት በተጨማሪም ኢጣሊያ ጦር አዝማቾች በጦርነቱ ላይ የሰሯቸው ስህተቶችም ለድሉ የራሳቸውን አስተዋፅዖ እንዳደረጉ ጽሑፉ ጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2011
በአንተነህ ቸሬ