በጣቢያው የተገኙት ሶስቱ ሰዎች በዕለቱ ተረኛ ፖሊስ የሚቀርብላቸውን ጥያቄዎች መመለስ ጀምረዋል። ፖሊሱ የእያንዳንዳቸውን ገጽታና ስሜት በጥንቃቄ እያስተዋለ ነው። መላሾቹ ከሚያሳዩት እንቅስቃሴ የውስጣቸውን እውነታ በቀላሉ መረዳት ይችላል። ይህን ለማድረግ የዓመታት የሙያ ልምዱ ከእሱ ጋር ነው።
መርማሪው ሁሌም ከተናጋሪዎቹ ንግግርና ገጽታ እውነታውን በቀላሉ ማወቅ አይቸግረውም። አንዳንዴ አንዳንዶች ከግምት በላይ ለመሆን ይሞክራሉ። የሆነውን እንዳልሆነ ለማስመሰልም የማይፈጥሩት ዘዴና ብልሀት የለም።
ሌሎች ደግሞ የሰዎችን ስሜት ለመያዝ እውነታ ሀቁን በመረረ ለቅሶ ይሸፍናሉ። እንዲህ አይነቶቹ ውስጣቸው በቀላሉ እንዳይታወቅ የሚፈጥሩት ዘዴ ሊሆን ይችላል። ጥቂት የማይባሉ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በቂ ማስረጃና ምስክር እያለ አይኔን ግንባር ያድርገው፣ ሲሉ ይክዳሉ። እንዲህ አይነቶቹ በየምክንያቱ ምሎ ለመገዘት የሚያህላቸው የለም። ሰበብና ማሳያ እያመጡ ሁኔታውን በመደበቅ ከጉዳዩ ለመራቅ፣ ለማሳሳት ይጥራሉ።
መርማሪ ፖሊሶች ባሳለፏቸው የልምድ ዓመታት በርካታ ባህርያትን ያስተውላሉ። እጅ ከፍንጅ ከተያዙት ጀምሮ ረቂቅ ወንጀል እስከፈጸሙት ድረስ እውነታውን በማስረጃ ለማስደገፍ በውጣ ውረዶች መፈተን የሙያ ግዴታቸው ነው።
ሶስቱን ግለሰቦች ተራ በተራ እየጠየቀ እውነቱን የሚያፈላልገው መርማሪ በሁለቱ ተጠርጣሪዎች ተፈጽሟል የተባለውን የግድያ ወንጀል ከመነሻው ለማወቅ ጥረቱን ቀጥሏል። አጋጣሚ ሆኖ ተጠርጣሪዎቹ ግድያውን ስለመፈጸማቸው አልካዱትም። የእነሱን ምርመራ ለየት ያደረገው ለተፈጸመው ድርጊት ራሳቸውን ፈጽሞ ተጠያቂ ያለማድረጋቸው ነው።
ይህ አይነቱ ምላሽ በፍትህ ሂደቱ ለሚኖረው የፍርድ ማቅለያና ማክበጃ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እውነታውን የሚያውቁ አንዳንድ ተጠርጣሪዎችም ውሳኔው ብዙዎቹ በሚገምቱት መንገድ እንዳይበየን መረጃቸውን ሊያቀርቡና ሊያሳምኑ ይችላሉ። ይህ ይሆን ዘንድም ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ለማሳየት ‹‹አለን›› በሚሉት መከላከያ ይሞግታሉ። አንዳንዴ በለስ ቀንቷቸው ያሰቡት ሊፈጸም፣ ሊሳካ ይችላል።
መርማሪው ሶስተኛውን ሰው በዓይን እማኝነት አቅርቦ እየጠየቀው ነው። ምስክሩ ከእነሱ ቃል በተለየ አየሁት ያለውን ሁሉ ማስረዳት ጀምሯል። የእማኙና የተጠርጣሪዎቹ ሀሳብ መለያየት የመርማሪውን ዓዕምሮ ማንቃት ማጠራጠር ይዟል።
መርማሪ ፖሊሱ የመጀመሪያውን ተጠርጣሪ አስቀምጦ ስለወንጀሉ አፈጻጸም እንዲያስረዳው ጠየቀ። ብዕሩን ከማስታወሻው አዛምዶም ሰውዬው የሚናገረውን ቃል ለማስፈር በተጠንቀቅ ጠበቀ። ተጠያቂው ወደዝርዝር ወንጀሉ ከመዝለቁ በፊት ከህይወት ታሪኩ እንዲነሳ ነገረው። ስሙን መንግስቱ መኮንን ሲል የጀመረው ሰው ስለማንነቱ በዝርዘር ማስረዳቱን ቀጠለ።
መንግስቱ መኮንን …
መንግስቱ መኮንን ትውልድና ዕድገቱ ሰሜን ሸዋ ፍቼ ሰላሌ ከተባለ አካባቢ ነው። በልጅነቱ እንደሌሎች ልጆች የትምህርት ዕድል አላገኘም። እኩዮቹ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ወላጆቹ ከቤት አዋሉት። እንደልጅነቱ ከቤተሰቡ ፍቅርን አላጣም። ቤት ያፈራውን እያጎረሱ፣ የአቅማቸውን እያለበሱ አሳደጉት።
መንግስቱ ዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር ዕውቀት የተነፈገ አዕምሮው ከስራ ጫና አላመለጠም። ለቤተሰቡ አሳቢና ደጋፊ ሊሆን ግድ አለው። ጠዋት ማታ ወላጆቹን ማገልገል፣ መርዳት ያዘ።
ጓደኞቹ ትምህርት ቤት ሲሄዱ በአይኖቹ እየሸኘ ከእርሻ ስራው መዋል ጀመረ። በልጅነት ጉልበቱ ከአፈር እየታገለ መሬቱን በበሬዎች አረሰ፣ ዘር በትኖ ቡቃያ ፍሬውን ጠበቀ። ጊዜው ሲደርስ ጎተራ በሚሞላ ምርቱ መልካም ገበሬነቱን አሳየ። ለቤተሰቦቹ መኖር ተስፋ የሆነው ወጣት ደከመኝ፣ ሰለቸኝ አላለም። የታዘዘውን እየፈጸመ ምስጋና ከምርቃት ተቸረ።
መንግስቱ ዓመታትን በዘለቀበት ግብርና ጎተራ ሙሉ እያስገባ ከዛሬ ነገን አሻግሮ አሰበ። ከአምናው ለዘንድሮ አቀደ። አንዳንዴ በሀሳቡ ርቆ ይሄዳል። ካለበት ሕይወት የበለጠ፣ የተሻለውን ያቅዳል። እሱን መሰል እኩዮቹ ከሰፈር ቀዬው ርቀው መሄዳቸውን ያስባል። ከነዚህ መሀል ጥቂቶቹ የልባቸውን ፈጽመዋል። ቆየት ብለው ሲመለሱ እጃቸው ባዶውን አይደለም። ከኪሳቸው ገንዘብ፣ ከሰውነታቸው መልካም ልብስ አይጠፋም።
መንግስቱ እነሱን ባየ ጊዜ ልቡ ይሸፍታል። በቦታቸው ራሱን ተክቶ ህይወታቸውን ይመኛል። ይህ ስሜቱ አብሮት ሲከርም ሀሳቡን ሁሉ ይቀይራል። ትዳር ይዞ፣ ጎጆ ቀልሶ መኖርን ይረሳል። ይህኔ መጪው ጊዜ እንዳአምና ካቻምናው እንዳልሆነ ይገባዋል። ለወደፊቱ አዲስ ህይወትና ኑሮ ራሱን ያዘጋጃል።
የገጠሩ ወጣት በወደፊት ኑሮው ላይ ከራሱ መከረ። ምክሩ ከእሱ ውሎ ሲያድር ለፈጣን ውሳኔ አበቃው። ከተማ ዘልቆ ህይወቱን ማሻሻል፣ መለወጥ ፈለገ። እሱ እንደሌሎች መማር ቀርቶ የፊደል ሀሁን አላየም። ያም ቢሆን ለራሱ ማደሪያ፣ ማስተዳደሪያ እንደማያጣ አውቋል።
እሱን መሰል ያገሩ ልጆች ከተማ ገብተው ኑሯቸው ተለውጧል። የአቅማቸውን ሰርተው ኪሳቸው ገንዘብ ቋጥሯል። መንግስቱ አንድ ማለዳ መንገድ የጀመረው እግሩ መሀል አዲስ አበባ አደረሰው። ስፍራው ሲደርስ የሚያውቁት ተቀብለው አስተናገዱት። ብዙ ቀናትን አልቆጠረም። ጥቂት ቆይቶ ካሰበው ምኞት ተገናኘ። በቀን ስራ ውሎ ኑሮን የጀመረው ወጣት በቂ የደሞዝ ክፍያን አላጣም።
መንግስቱ በአዲስ አበባ ዓመታትን አሳለፈ። ጊዜው እየገፋ ዕድሜው እየጨመረ ሲሄድ ስራው ይከብደው፣ ያስቸግረው ያዘ። የነበረበትን የቀን ስራ ትቶ ከአንድ መዝናኛ በጥበቃ ሙያ ተቀጠረ። የተቀጠረበት ግቢ የሆቴል መስተንግዶና የመናፈሻ አገልግሎት ይሰጣል።
እሱን ጨምሮ ሌሎች ዘቦች ቦታውን በየተራ ይጠብቃሉ። ስፍራውን ለፑል ጨዋታና ለመዝናኛ የሚሹት ደንበኞች ጠዋት ማታ ያዘወትሩታል። መንግስቱ አንዳንዴ ከአንዳንድ ወጣቶች ጋር በየምክንያቱ ይጋጫል። እንዲህ ባጋጠመው ጊዜ ለሆቴሉ ባለቤት ማሳወቅ ልማዱ ነው። ግጭቱ ባስ ሲል ደግሞ ከመጨቃጨቅ አልፎ ለድብድብ ይደርሳል።
ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ሳሙኤል የተባለ ወጣት በግቢው ጠብ ማንሳቱን ብዙዎች አይተዋል። ሳሙኤል ከአንድ ቀን በፊት ከሌላ ጥበቃ ጋር ተጋጭቶ በድንጋይ ፈንክቶታል። ይህን የሚያውቀው መንግስቱ ማግስቱን በግቢው ሲመለከተው አልተደሰተም። በርከት ብለው ከመጡ ጓደኞቹ ጋር ሊፈጽም ያቀደው ተንኮልና ጠብ እንዳለ ጠርጥሯል።
ሳሙኤልና ጓደኖቹ ፑል ለመጫወት ወደውስጥ ሲያልፉ መንግስቱ ከኋላ ተከተላቸው። በስፍራው እንዳይቆዩም ክልከላ አደረገ። ሳሙኤል ይህን ሲያውቅ የመንግስቱን ሸሚዝ እንዳነቀ ዛተበት። አንዳንዶች መሀል ገብተው ገላገሏቸው። በማግስቱ ጠዋት ከጓደኞቹ ጋር ሲመለስ በሆቴሉ የፎቅ በረንዳ ጫት ለመቃም ነበር። መንግስቱ ይህ ይሆን ዘንድ አልወደደም። የእጁን ዱላ እንዳጠበቀ ካለበት ደርሶ ተጋፈጠው።
ሁለቱም ሲተያዩ ዳግም ጠብ ተነሳ። እጅ ለእጅ መያያዛቸውን ያዩ አሁንም ሊገላግሏቸው ሞከሩ። የመንግስቱ ዱላ የሚያስቀርብ አልሆነም። ከታች ሆኖ ድርጊቱን የሚያየው የመንግስቱ ጓደኛ ዱላውን ይዞ መሀላቸው ደረሰ። እንደሌሎች ሊያገላግላቸው አልወደደም። ከጓደኛው ተጣምሮ በሳሙኤል ላይ ዱላ ሰነዘረ።
መንግስቱ የሰነዘረው ቀዳሚ ዱላ ጭንቅላቱን አግኝቶታል። ሳሙኤል ደሙን እያዘራ መንገዳገድ ጀምሯል። ቆይቶ ጠቡን የተቀላቀለው ባልንጀራው ደምሴም ተጎጂው መሬት ከመድረሱ በፊት በያዘው ቆመጥ ተቀብሎታል። ዳግም ፊቱን የተመታው ሳሙኤል ራሱን ስቶ በቁሙ ተዘርሯል።
መርማሪው…
መርማሪ ፖሊሱ ለተጠርጣሪው ‹‹አለኝ›› የሚለውን ጥያቄ ካቀረበ በኋላ በግድያው ስላደረበት ስሜት ጠየቀ። መንግስቱ ድርጊቱን በትክክል ስለመፈጸሙ አመነ። ይህን ያደረገው ግን ሳሙኤል እሱን ሊወጋው በሰነዘረበት ጩቤ ምክንያት መሆኑን ተናገረ። መርማሪው አሁንም የውስጥ ስሜቱን ማወቅ ቢሻ የቀደመውን ጥያቄ ደገመለት። መንግስቱ በድርጊቱ ፈጽሞ ጥፋተኛ አለመሆኑን አስረዳ።
ፖሊሱ አሁንም ለምን? ሲል ጠየቀው። ለወንጀሉ የተዳረገው ራሱን ለመከላከል ባደረገው ሙከራ መሆኑን ደግሞ አረጋገጠለት። መንግስቱ አሁንም የፈጸመው ድርጊት ተገቢና ትክክል መሆኑን እንዳመነ ነው። የተናገረው ቃል እውነት ስለመሆኑ በፊርማ እንዲያረጋግጥ በፖሊሱ ተጠየቀ። ተጠርጣሪው አውራ ጣቱን በቀለም ረግጦ አሻራውን አኖረ።
መርማሪው የመጀመሪያውን ተጠያቂ አስወጥቶ ሁለተኛውን ተጠርጣሪ አስገባ። በደረሰው ጥቆማ መሰረት በወጣቱ ላይ ወንጀሉን ያደረሱት በአንድነት ተባብረው ነው። ሁለቱም ተቀጥረው በሚሰሩበት ሆቴል በጥበቃ ስራ ያገለግላሉ። ከሌሎች በተለየም የቅርብ ባልንጀሮች ናቸው።
መርማሪው የሁለተኛውን ተጠርጣሪ ማንነት ለማወቅ ከህይወት ታሪኩ እንዲጀምር ጠየቀው። ስሙን ደምሴ በሪሁን ሲል ያስተዋወቀው ወጣት ትውልድና ዕድገቱ ሰሜን ጎንደር ዞን አምባጊዮርጊስ ወረዳ መሆኑን ተናገረ።
ደምሴ መኮንን…
ደምሴ ተወልዶ ባደገበት የገጠር ቀበሌ የትምህርት ዕድል አላገኘም። እሱን ጨምሮ ሌሎች ወንድሞቹ ህይወትና ስራቸው ግብርና ላይ ተመስርቷል። ልጅነቱን እንደጨረሰ ከእርሻ ስራ ሊውል ግድ አለው። በሬ ጠምዶ የሚያርሰው ለም መሬት በየዓመቱ አሳፍሮት አያውቅም። እንደድካም ልፋቱ የጉልበት የላቡን ያሳቅፈዋል።
ደምሴ ወጣትነቱን ባጋመሰበት ቀዬ ጉልምስናውን መቀጠል አልፈለገም። ካገሩ ወጣ ብሎ፣ ከአካባቢው ርቆ ስራ ማግኘት ፈለገ። ፍላጎቱ ይሞላ ዘንድ መተማ ተሻግሮ የፈረስ ጋሪ ጀመረ። ዓመታትን በቆጠረበት ስራ ጥቂት ገንዘብ እንደያዘ አሻግሮ ማሰብ ጀመረ። አሁንም ራቅ ብሎ መሄድ፣ ሌላ ስራ ማግኘት አሰኘው።
አዲስ አበባ የመዝለቅ ምኞቱ ስኬት ሆኖለት ሀና ማርያም ከተባለ ሰፈር ተገኘ። ውሎ ሳያድር በአካባቢው ከሚገኝ ሆቴል በጥበቃ ሙያ ተቀጠረ። ሆቴሉ በርካታ ደንበኖች ይውሉበታል።
የፑል ጨዋታን ከሚሹ ወጣቶች በርካቶቹ ከኪስ ከጉንጫቸው የጫት ቅጠል አይጠፋም። እሱን ይዘው በመጡ ጊዜም ከሌሎች ለመጣላት ለመጋጨት ይፈጥናሉ። ለዚህ ልማድ ትዕግስት የሌላቸው የሆቴሉ ዘቦች ወጣቶቹን በዓይነ ቁራኛ እየቃኙ ይጠብቋቸዋል።
ደምሴ ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ሳሙኤል ከተባለ ወጣት ጋር ተጣልቶ ለድብድብ ደርሰዋል። በወቅቱ በነበረው አለመግባባት ክፉኛ እንዳጠቃውም አይረሳም። በማግስቱ ደግሞ ሲያየው ሁኔታውን አስታውሶ ንዴት ይዞታል። ሳሙኤል በርከት ካሉ ጓደኞቹ ጋር መሆኑን አስተውሎ ጥርሱን ሲነክስ ቆይቷል።
ደምሴ የትናንትናውን ጥቃት እያሰበ ትካዜ ገብቶታል። ሳያስበው የተመታው፣ የተደበደበው እያበሽቀው እያናደደው ነው። ድንገት የሰማው ድምጽ ግን በነበረው ሰሜት እንዲቀጥል አላስቻለውም። የቅርብ ጓደኛውና የስራ ባልደረባው ከእሱ ጠበኛ ጋር ሙግት ጀምሯል። መንግስቱ ዱላውን ከእጁ እንዳጠበቀ ነው።
ሳሙኤል የመንግስቱን ኮሌታ እንደጨመደደ ወደ ውጭ ወጥተው እንዲጋጠሙ ያስገድደዋል። ሌሎች ከዳርቆመው ሁኔታውን ይቃኛሉ። የጓደኛውን ጉልበት ማየል ያስተዋለው ደምሴ ዱላውን አንስቶ አጠገባቸው ሲደርስ መንግስቱ በጠበኛው ጭንቅላት ላይ ምቱን አሳርፎ ነበር።
ደምሴ ድንገት ደርሶ ከጓደኛው ተመሳሳለ። አብረው ተባብረው ሳሙኤልን በያዙት ዱላ አጣደፉት። ድብደባው የበረታበት ወጣት የባልንጀሮቹን የዱላ ውርጅብኝ መቋቋም አልቻለም። በደም እንደተነከረ በቁመናው ተዘረረ።
መርማሪ ፖሊሱ የደምሴን ቃል ተቀብሎ እንዳጠናቀቀ የመንግስቱን ጥያቁ ደገመለት። በወንጀሉ ምክንያት ሰለጠፋው ህይወት እያስታወሰ ምን እንደሚሰማው ጠየቀ። ደምሴ ከመንግስቱ የተለየ ምላሽ አልሰጠም። ወንጀሉን የፈጸመው ራሱን ለመከላከል ሲል እንደሆነ ገለፀለት። የተናገርው ቃል አውነት ስለመሆኑም በተዘጋጀለት የቀለም መርገጫ በአውራጣቱ አትሞ አረጋገጠ።
ምስክሩ….
መርማሪው ፖሊስ ለጥያቄ ከጠራቸው ሰዎች መሀል ሶስተኛ ሆኖ የቀረበው የዓይን እማኙ ካሳ ቢሆነኝ ነው። በዕለቱ ወንጀሉ ሲፈጸምና ነፍስ ሲጠፋ በስፍራው ነበር። ዋና ሳጂን ደጉ ዓለም አቡዬ ቃሉን ሲቀበል ያየውን ሁሉ አንድ በአንድ እንዲያስረዳ ዕድል ሰጥቶታል።
ምስክሩ ሁለቱ ባልንጀሮች ሟችን እያንገላቱ ተባብረው እንዳጠቁት ተናገረ። ሁለቱም በያዙት ዱላ ሳሙኤልን መቀጥቀጣቸውም ለህልፈት እንዳበቃው አስረዳ። እማኙ ሳሙኤል ከመሬት ከወደቀ በኋላ ጓደኞቹ ከግቢው ይዘውት እንዲወጡ ማስገደዳቸውን መናገሩን አልዘነጋም።
መርማሪው በጠቡ ላይ ሟች ይዞት ነበር ስለተባለው ጩቤ ምስክሩ ያውቅ እንደሆነ ጠየቀው። ምስክር ካሳ በሟች እጅ ላይ ምንም አይነት ዱላ፣ ድንጋይና ጩቤ ያለማየቱን በእርግጠኝነት ተናገረ። መርማሪው ግለሰቡ የሰጠውን ምላሽ በጥንቃቄ መዝግቦ የዓይን እማኙን በምስጋና አሰናበተ።
አሁን መርማሪው ፖሊስ የወንጀሉን መነሻና የድርጊቱን እውነታ በተለያዩ ማስረጃዎች አረጋግጧል። በህክምና የተገኘው ውጤትም ሟችን ለህልፈት ያበቃው በጭንቅላትና ማጅራቱ ላይ በደረሰበት ከባድ ድብደባና የደም መፍሰስ ስለመሆኑ አስረድቷል። መርማሪው ያገኛቸውን መረጃዎች በማስረጃዎች አረጋግጦም የክስ መዝገቡን ወደ ዓቃቤ ህግ አስተላልፏል።
ውሳኔ…
ነሀሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሁለቱ ግለሰቦች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮ ተገኝቷል። ሁለቱ ባልንጀሮች በጭካኔ አንድን ግለሰብ ተባብረው መግደላቸውን በበቂ ማስረጃዎች ያረጋገጠው ፍርድ ቤት በሁለቱም ግለሰቦች ላይ የጥፋተኝነት ብይንን አስተላልፏል። በዕለቱ በሰጠው ፍርድም ግለሰቦቹ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ስድስት ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ በማለት ውሳኔውን አስተላልፏል።
መልካም ስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014