አሁን ያለው ወጣት ትውልድ ከአባትና እናቶቹ የተረከባትን ሀገር ሉዓላዊነቷን አስጠብቆና አስከብሮ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ አደራ እንዳለበት ምሁራን ይናገራሉ። ቀዳሚ ተግባራቸው በየተሠማሩበት የሙያ መስክ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት የሚተጋ ዜጋ ማፍራት ነው። ለዚህ ደግሞ እነሱ ራሳቸው በቅድሚያ ይህን ኃላፊነት በአግባቡ የሚወጣ ዜጋ ሆነው መገኘት እንዳለባቸው ያምናሉ። አገርና ሕዝብን የመውደድ፣ የማክበር፣ የማገልገል፣ በአገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ አንድ አቋም የመያዝና በአገርና ህዝብ ጥቅም ላይ ባለመደራደር፣ አርአያነታቸውን ይመሰክራሉ።
እነሱና በዚህ መልክ የቀረፁት ወጣት ትውልድ ስሜትና ምላሽ አሸባሪው ሕ.ወ.ሓ.ት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜኑ ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ምን ይመስል እንደነበር፣ አሁን ላይ ምን እንደሚጠበቅበትም የተለያዩ ባለሙያዎችንና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ወጣቶች ተዘዋውረን ጠይቀናል። የተፈፀመው ጥቃት በሕግ አግባብ እንዴት እንደሚታይና ጥቃቱን ተከትሎ በአገራችን ላይ የበረታውን የውጭ ኃይሎች ጫናም እንዴት እንዳዩትም አነጋግረናቸዋል።
‹‹ይህችን አገር ተረክበን የማስቀጠል ታላቅ አደራና ኃላፊነት አለብን›› ያለን ወጣት ሳሙኤል ጌታቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ሥነ-ምድር ትምህርት ቤት መምህር ነው። ሠራዊቱ በገዛ ወገኑ በተለይም ለብዙ ጊዜ አብሮት በነበረውና በሥጋ ዝምድና ጭምር በተሣሰረው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈፀሙ እጅግ የከበደ ሀዘንና ቅሬታ ተሰምቶታል። ጥቃቱ በባዕዳን ሳይሆን በውስጥ ኃይሎች መሆኑ ሀዘኑን የበለጠ አክብዶበታል። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊና አገሩን እንደሚወድ ዜጋም በብርቱ አስቆጭቶቷል። ድርጊቱን አጥብቆ እንዲቃወመውም አድርጎታል። ከዚህ ውጭ አገርን ለማዳን በሚደረገው ማንኛውም ጉዳይ በሙያውም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ እየተሳተፈና እየተባበረ ይገኛል። ሳሙኤል ሕግ የማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ የውጭ ኃይሎች በአገራችን ላይ እያሳደሩት ያለውን ጫናም አግባብ ነው ብሎ አያምንም።
‹‹በተለይ ለጥፋት ኃይል መወገንና በብዙ መቶ ሺህ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ኑሮ መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ከነበረው የአጎዋ ስምምነት ኢትዮጵያን ማስወጣት ኢ-ዴሞክራሲ ነው›› ይላል ወጣት ሳሙኤል። እንደ እሱ አገላለፅ ዴሞክራሲ የሚባለው ሁለቱንም ወገን እኩል የሚዳኝና የሚያደምጥ አካሄድ ሲኖር ነው። በመሆኑም ኃይላቱ አሁን እየተከተሉት ያለው ለአንድ ቡድን ብቻ ያደላ አካሄድ፣ ያውም ጦርነቱ በጥፋት ኃይሎችና በአንድ ሉዓላዊ ሕዝብ መካከል መሆኑን እያወቁም የጥፋት ኃይሉን በግልጽ መደገፋቸው ተገቢና ጤናማ ነው የሚል ዕምነት የለውም። እነዚህን ኃይሎች መቃወሙና ድርጊታቸውን የዓለም ማኅበረሰብ እንዲያውቀው ማድረጉ ተገቢ ነው ብሎ ያስባል። እንደ ወጣቱ አባባል በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጦርነት በምንም አይነት መልኩ አይፈልግም። የሚፈልግም ካለ አንድም ጤናማ ከሚባለው ኅብረተሰብ ወጣ ያለ አስተሳሰብ ያለው ነው። ሁለትም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ስልጣኔ ያልገባው ወገን ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ከሠራዊቱ ጋር በሥጋና ደም የተጋመዱ አስተያየት ሰጪዎች የሽብር ቡድኑን ተግባር ለማመን የሚቸግር፣ የመጪውን ትውልድ የአገር ፍቅር የሚገዳደር፣ አርአያነት የሌለው፣ አስደንጋጭና አረሜኒያዊ ድርጊት አድርገው ስለውታል።
ዶክተር ቢቂላ ወርቅነህ ጥቃቱ በተጀመረበት ጊዜ በዜና ማሰራጫ ሲሰሙ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ከተሰማቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አንዱ ናቸው። ዶ/ር ቢቂላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዕፅዋት ባዮሎጂና የብዝሐ ሕይወት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ናቸው። ዶክተሩ እንዳወጉን ታዲያ አብዛኞቹ የሥጋ ዘመዶቻቸው በንጉሱ፣ በደርግና በ27ቱ የኢህአዴግ ዘመን የመከላከያ ሠራዊቱ አባል የነበሩና አሁንም በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ እያገለገሉ ያሉ ናቸው። የወጣትነት ዘመናቸውን ያሳለፉት ለአገር መከላከያ ሠራዊት በቃላት ከሚገለፀው በላይ እጅግ ጥልቅ ፍቅርና ክብር በመስጠት ነው። ወጣት ተማሪዎቻቸውንም በዚህ መልኩ ቀርጫለሁ ብለው ያስባሉ። አሁንም በዚህ መልኩ እየቀረፁ እንደሚገኙ በእርግጠኝነት ይናገራሉ። የእሳቸው የልጅነት ዘመን የወደፊት ርዕይ እንደ አብዛኞቹ ቤተሰቦቻቸው ወታደር ሆነው አገራቸውን ማገልገል ነበር። ሆኖም ዕጣ ፈንታቸው ሆኖ በሌላ ሙያ ቢሰማሩም ዛሬም ለሠራዊቱ ያላቸው ክብርና ፍቅር በሕይወት እስካሉ ከልባቸው የሚፋቅ አይደለም።
ዶ/ር ቢቂላ እንደሚሉት ሠራዊቱ በየትኛውም አካል ሲጠቃ ያማቸዋል። ያውም አጥንታቸውን ነው የሚያማቸው። ጽኑው ህመም ውስጣቸው ዘልቆ ይሰማቸዋል። ታዲያ እንዲህ እንደ እሳቸው ላለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የጥፋት ኃይሉ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ያደረሰውን ጥቃት መስማቱ እጅግ ያሳዝናል፤ ይከብዳልም። ዶክተሩ በወቅቱ በዜና ማሰራጫ ሲሰሙ ድንጋጤው ብርክ ነበር ያስያዛቸው። መላ ሰውነታቸው ተንቀጥቅጧል። እጅግም አዝነዋል።
‹‹ማዘን ብቻም ሳይሆን አስቆጥቶኛል። አበሳጭቶኛልም›› ብለውናል። ‹‹አገሩን በሚከላከል ሠራዊት ላይ የትኛውም ኃይል ጥቃት መሰንዘር አለበት ብዬ አላምንም። ውድ ሕይወቱን ለመገበር በቆመ አካል ላይ ጥቃት ሲዘነዘር ያመኛል›› ይላሉ። ዛሬም የሚሰማቸው ያልበረደው ይኸው ዓይነቱ ስሜት እንደሆነም የዶክተር ቢቂላ የፊት ገጽታ አይሸሽግም።
እንደሳቸው መከላከያ ላይ የተፈፀመው ጥቃት በዜጎች በተለይም በሰፊው ወጣት ዘንድ ቁጣን የሚቀሰቅስ ስሜት ፈጥሯል። እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች የወር ደመወዝ ከመለገስ ጀምሮ በተለያየ መንገድ እየደገፉትም የሚገኙት ለዚህ ነው።
‹‹የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነትን መጠበቅ የሚቻለው የእርስ በእርስ ተግባቦት ሲፈጠር ነው›› ይላሉ። በዚህ በኩል ወጣቱ ትውልድ አለመታማቱንም በእርግጠኝነት ይናገራሉ። በፖለቲካው መፈታት ያለባቸውን የፖለቲካ አመራሩ በውይይትም ሆነ በሚቻለው መንገድ መፍታት እንዳለበት ይመክራሉ። አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በመንግሥትም ሆነ በየትኛውም አካል በኩል መሠራት እንዳለበትም ለአገር ተረካቢው ወጣት ያሳስባሉ።
‹‹የአገርን ሉዓላዊነት የማስከበር ጉዳይ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያኖች ብቻ ነው›› የሚሉት ዶክተር ቢቂላ ዕድገታችንን የሚሹ ወዳጆች እንዳሉን ሁሉ ውድቀታችንን የሚፈልጉም አገራት መኖራቸውን ማወቅ ተገቢ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ከተለያዩ ጂኦ-ፖለቲካ እይታዎች አንፃር የዚህችን አገር ማደግ የማይፈልጉ አካላቶች መኖራቸውንም በእርግጠኝነት ይናገራሉ። በመሆኑም እንደ ሕዝብ አገራዊ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን። አገራዊ አንድነታችንን ካላጠናከርን ለውጭ ጥቃት የተጋለጥን እንሆናለን። ከውጭ የሚቃጣብን ጥቃት ከራሳችን ድክመት የተነሳ ነው ብለን ግምገማ ላይ መድረስ እንዳለብንም ይጠቅሳሉ።
እኛ አንድ ብንሆንና ብንጠናከር የውጭውን ኃይል በቀላሉ መቀልበስ እንችላለን። ‹‹ሆኖም አንዳችን ከውጭው ጋር አብረን ሌሎቻችንን ለማዳከም ብለን የምናደርገው ጥረት እንደ አገር ነው የሚጥለን›› ያሉት ዶክተሩ ሁላችንም ቆም ብለን ልንወድቅላት፣ ልንጠብቃትና ልናለማት የሚገባና ለሁላችንም የምትበቃ አንድ አገር እንዳለችን ማሰብ ይኖርብናል እንጂ መባላት የለብንም በማለትም ምክራቸውን ይለግሳሉ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁርና ተመራማሪ ዶክተር ገብረክርስቶስ ኑርዬ እንደገለፁልን ጥቃቱ በቃላት ከሚገለፀው በላይ እጅግ አሳዛኝ ነው። እሳቸውም ሆኑ አደራ ተረካቢው ወጣት በወቅቱ የተሰማቸው ይኸው ዓይነት ጥልቅ ሀዘን ነው። ከገዛ ወገኖቻችን ጋር እርስ በእርስ እንድንዋጋ መንገድ የከፈተ ጥቃት በመሆኑ ባይፈጠር ይመረጥ ነበርም አሰኝቷቸዋል።
‹‹ጥቃቱን ተከትሎ የተወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃም ሆነ ሌሎቹ የዚህ የጥቃት ውጤት ናቸው›› የሚሉት ምሁሩ የሁሉም መነሻ ጥቃቱ ይሄም የግድ ሊወሰድ የሚገባው እንደሆነም ይናገራሉ። እንደ ምሁሩ ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ላይ እያረፈ ያለው የውጭ ኃይሎች ጫና ተረድተውትም ሆነ ሳይረዱት የሚያደርጉት ነው። በተለይ አንዳንድ ኃይሎች ቢረዱትም ከጥቅማቸው አንፃር ሆን ብለው የሚያደርጉት መሆኑ ያሳዝናል። እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ያመጣውን መዘዝ ያለ ውጭ ጫና እንወጣዋለን ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው። ጫናው ሊቀጥል ይችል ይሆናል ብሎ ማሰብና የራስን አማራጭ መውሰዱም እንደማይከፋ ያሳስባሉ። በዚህ በኩል የአገር ተረካቢው ወጣት አስተዋጽኦ የጎላ መሆን እንዳለበትም ጥሪ ያስተላልፋሉ።
‹‹አሁን ያለው ወጣት የአገሩን አንድነትና ሉዓላዊነት አስጠብቆ ለነገው የማስቀጠል ታላቅ ኃላፊነት አለበት›› ያሉን በጠቅላይ አቃቢ ሕግ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ሲሆኑ፤ እንደ እሳቸው ከሆነ ጥቃቱ ኢትዮጵያዊነታችንን የማይወክል በታሪክ እንኳን ተቀባይነት የሌለው ታሪካዊ ስህተት ነው። አፈፃፀሙን እንኳን ትኩስ ስሜት ያለው አገር ተረካቢ ወጣት በየትኛውም ዕድሜ ደረጃ ላይ ያለ ዜጋ ሲሰማው ያስደነግጣል። ወጣቱን ያስቆጣውም ይሄው ነው።
ጥቃቱ በሕግ በኩል አግባብነት የሌለውና በከባድ ወንጀል የሚያስቀጣ በመሆኑ በሕግ መያዙንና በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት የማይቻል በመሆኑ ዝርዝር ውስጥ ገብተው ሰፊ ማብራሪያ ሊሰጡን ባይችሉም በህግ ዓይን ጥቃቱ እጅግ አረመኔያዊ ጥቃት ብቻ ሳይሆን አገር በመክዳት ከባድ ወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሆነ ነግረውናል።
ይህን የሚያስብለው ደግሞ ጥቃቱን የፈፀመው በገዛ ወገኑ ላይ መሆኑንም አስምረውበታል። ከዚህ አንጻር መንግሥት ጥቃቱን ተከትሎ የወሰዳቸው እርምጃዎች ተገቢና ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። ከነዚህ መካከል አገር በመክዳት፣ የመከላከያ ሠራዊቱን መልሶ በማጥቃት ተብሎ የተቀመጠው በከፍተኛ ሁኔታ ያስጠይቃል። የሚያስጠይቀው ከወንጀል ተግባር ባለፈ አፈፃፀሙ አረመኔያዊነት የሆነ ጭምር በመሆኑም ነው። ምክንያቱም ሠራዊቱን የጥቃት ሰለባ ያደረገው ሳይዘጋጅበት የጥቃት ኢላማ ውስጥ በማስገባት ነው። ይሄ በህግ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪም ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ፍፁም ኢ-ሰብዓዊነት የጎደለው አረመኔያዊ ድርጊት ነው ብሎ መግለፅ ይቻላል ሲሉም ዳይሬክተሩ አስተያየታቸውን አካፍለውናል።
‹‹ስለ ጥቃቱ ማውራት ቀርቶ ማሰቡ እጅግ ያሳምማል። ድርጊቱን በደፈናው ወጣቱን የሚያስቆጣ ሰይጣናዊ ሥራ ነው ማለት ይቻላል።›› ያሉን ደግሞ አቶ ተክለፃዲቅ ተክለአረጋይ ናቸው። የፌዴራል መንግሥት ህንፃዎች የግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ተክለፃዲቅ ላለፉት 20 ዓመታት አልጋ ላይ ሳይተኛ የጠበቀውንና በወጣት ኃይል የተገነባውን ሠራዊት መጨፍጨፍ ሰብዓዊነት ካለው ሰው እንደማይጠበቅም አበክረው ያስረዳሉ። ጥቃት አድራሹ ኃይል የከፈተውን ወረራ በመቀልበስና የውጭውን ኃይል ጫና በማርገብ በኩል ከየትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ይልቅ ወጣቱ ክፍል ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅበትም በማከል አስተያየታቸውን ይቋጫሉ።
በአጠቃላይ አሸባሪው ሕወሓት ሰሜን ዕዝ በነበረው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመውን ጥቃት ወጣቶች ተተኪውን ትውልድ የማያስተምር፣ አሣፋሪ፣ ለስነ-ባህል ተመራማሪዎች ከባህል ያፈነገጠ፣ ለስነ-ማህበረሰብ ተመራማሪዎች ደግሞ ለዘመናት የተገነባን የአብሮነት ምሶሶ የሚንድና ባህላዊ እሴትን የሚሸረሽር እኩይ ተግባር፤ እንዲሁም ለስነ-ልቦና ባለሙያዎች ስነ-ልቦናዊ ስብራትን የሚያመጣ፤ የሕግ ሰዎች በፊናቸው ዓለም ከተፈጠረች እስካሁን ተሰርቶ የማያውቅ አረመናዊ ወንጀል ብለውታል። እኛም ሕወሓት የከፈተው ጥቃትና ሽብር በሕዝቦችና በአገር ላይ የሚያሳድረው ኢኮኖሚዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ ስብራት ቀላል አለመሆኑንና በሕዝቦች ዘንድ ቁጣን መቀስቀሱን የቃኘንበትን ጽሑፍ ቋጨን። ቸር ያሰማን!!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2014