በየካ ጋራ ስር በሚገኘው የሚሊኒየም ፓርክ ዳርቻ የሚገኘው ሰፊና ጽዱ ግቢ ከሩቅ ላየው የሰፈነበት ጸጥታ አንዳች ምርምር የሚካሄድበት ማእከል አስመስሎታል። በአስጎብኚያችን መሪነት ግቢው ውስጥ በመዝለቅ ወደ አንደኛው ክፍል ስንገባ በርካታ ህጻናት በኩባያ የተሞላ ወተትና ዳቦ ይዘው በሰልፍ ተቀምጠው አገኘናቸው። መግባታችንን የተመለከቱት ህጻናት ለአክብሮት ከወንበራቸው ተነሱና የሰነዘርንላቸውን ሰላምታ ተቀብለው ደህና እግዚአብሄር ይመስገን ብለውን በአንድ ድምጽ መልሰውልን እንደአነሳሳቸው በስርአት ተቀመጡ።
በመመገቢያ ክፍሉ አንድ ጥግ ራሷን ችላ መመገብ የማትችል አንዲት አካል ጉዳተኛ ልጅ በሞግዚቷ እየተመገበች በፈገግታ ትመለከተን ነበር። ከደቂቃዎች በኋላ ህጻናቱ ገበታቸውን ጨርሰው ሲወጡ ግቢው በጸሀይ ፍጥነት በህጻናቱ ጨዋታ መድመቅ ጀመረ።
ያለነው በኢምፓ (ትምህርት ለተቸገሩ በጎ አድራጎት ማህበር) ነው። እኛም ለዛሬው ሀገርኛ አምዳችን የኢምፓ ምስረታና ጉዞ እንዴት ነበር ስንል ዋና ስራ አስኪያጁን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ወጣት ካሌብ ጸጋዬ ከኢምፓ መስራቾች መካከል አንዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ በመሆን እያገለገለ ይገኛል። ካሌብና ጓደኞቹ ያደጉት ዝዋይ በሚገኘው አምባ የህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ነው። የዝዋዩ አምባ የህጻናት ማሳደጊያ በአስራ ዘጠኝ ሰባዎቹ መጀመሪያ በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን በጦርነትና በተለያዩ ችግሮች ከቤተሰባቸው የተለዩ ህጻናት ልጆች የሚያድጉበት፤ በማእከሉ የነበሩት አብዛኛዎቹ ህጻናትም ወላጆቻቸው የሶማሊያን ወረራ ለመቀልበስ በተደረገው ጦርነት የተሰው ነበሩ።
ህጻናቱ በማእከሉ ይደረግላቸው የነበረው እንቅስቃሴ በወቅቱ ሀገሪቱ ከነበራት የኢኮኖሚ ደረጃ አንጻር በጣም ከፍተኛ ነበር። የዝዋይ ህጻናት አምባ ከምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛው የህጻናት ማሳደጊያ አንዱ ሲሆን እስከ ሰባት ሺ ህጻናትን በአንድ ግዜ ማስተናገድ የሚችልም ነበር።
አምባው አምስት መንደሮች የነበሩት ሲሆን ከዜሮ እስከ ስድስት ዓመት ያሉ ልጆች የሚቆዩበት ዘርአይ የሚባለው በስሩ ሰብለ፣ አብዮት፣ መስከረም ሁለትን የያዘ። ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ ኦጋዴን የሚባለው ከአንደኛ አስከ ስምንተኛ ክፍል የሚማሩበት ነው። እንዲሁም በቀድሞ የኢህዴሪ ፕሬዚዳንት ጓድ መንግስቱ ሀይለማርያም ስም የተሰየመውና ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የሚማሩ የሚኖሩበት ነው።
የአምባው ልጆች በእረፍት ግዜያቸው ወላጅ ያላቸው በመላው ሀገሪቱ የአሁኗን ኤርትራ ጨምሮ በአውሮፕላን ይላኩ ነበር። ወላጅ የሌላቸው ደግሞ እንደ ሶደሬ ላንጋኖ ባሉ መዝናኛዎች ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።
የመንግስት ለውጥ ከተደረገ ጀምሮ ግን አዲሱ መንግስት ለአምባ ልጆች እንጀራ እናት ሆኖባቸው ቆይቷል። ይብስ ብሎ በ1989 ዓ.ም ሳይታሰብ ግማሹ ወላጅ ለመጠየቅ ለእረፍት እንደወጣ በቴሌቪዥን የመዘጋቱ መርዶ ይደርሳቸዋል። እንደነ ካሌብ ወላጅ ያልነበራቸው ደግሞ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሚኪሊላንድ ማቆያ እንዲሰነብቱ ይደረጋል።
በወቅቱ ማእከሉ የራሱ የሆነ ከብት፤ ዶሮና አሳማ ማርቢያም የነበረው ሲሆን ራሱን እያስተዳደረ ለአምስት አመት መቀጠል እንደሚችል በጥናት ተረጋግጦ ነበር። ካሌብና ጓደኞቹ ደግሞ በዚህ ሁኔታ ከቤታቸው ቢሰናበቱም ሁሌም ለኢትዮጵያ ሀገራቸውና ለህዝባቸው አንዳች ውለታ መዋል አንዳለባቸው ለራሳቸው ይነግሩ ነበር።
ከአመታት በኋላ ከአብሮ አደጎቹ መካከል ሄኖክ አለሙ፤ ጸጋ በርሲሳ፤ ይታገሱ ጌትነት፤ ህላዌ ቦጋለና ሌሎችም በርካቶች ኮተቤ አካባቢ መኖር ሲጀምሩ በአካባቢው ያለውን ህብረተሰብ የኑሮ ደረጃ በቅርበት ለመረዳት እድሉን ያገኛሉ። በእነሱ ምልከታም እዛ አካባቢ የከተማዋ ዳርቻ እንደመሆኑ አብዛኛው ነዋሪ በኢኮኖሚ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ነበር።
ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ቀርቶ በቀን ሶስት ጊዜ ለማብላትም የሚገዳቸው ነበሩ። እናም እነ ካሌብ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አንድ ነገር መስራት እንዳለባቸው ከስምምነት ደርሰው ወደ ስራ ይገባሉ። ለስራቸው ቀዳሚ ያደረጉት ደግሞ በየሜዳው ይውሉ የነበሩትን ህጻናት ልጆች ማስተማር ነበር። ለዚህ ደግሞ አነሰም በዛ ገንዘብ የሚያስፈልግ በመሆኑ እንደ አማራጭ በአካባቢው ያሉትን እድሮች ለማነጋገር ይወስናሉ።
እናም የአድዋ እድር የሚባለው ጋር ሄደው ያላቸውን ቦታ ተመጣጣኝ ክፍያ በመክፈል ለልጆች ማስተማሪያነት ለመጠቀም እንደሚፈልጉ ይነግሯቸዋል። ሃላፊውም ነገሩ የምትዘልቁበት አይደለም እናንተ እንደምታስቡት ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አይሆንላችሁም። ለልጆች ቀለብ ሰፍራችሁ ዩኒፎርም አልብሳችሁ አይሆንላችሁም የሆነ ሆኖ እንሞክረው ካላችሁ እሺ ብለው ይፈቅዱላቸዋል።
በዚህም መሰረት በ2001 ዓ.ም በጣም በዝቅተኛ ደረጃ የነበሩትንና የትምህርት እድል ያላገኙትን የአካባቢውን ህጻናት እንዲሰበሰቡ ያደርጋሉ። በዚህም ወላጆቻቸው በቤት ኪራይ የሚኖሩና ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ያለባቸው ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ከአባቶቻቸው ጋር ያልሆኑ ከአንድ መቶ ሀምሳ በላይ ህጻናት መኖራቸው ይነገራቸዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ በመስጠት መቶውን ብቻ በመያዝ ስራቸውን ይጀምራሉ። በወቅቱ የመነሻ ካፒታላቸውም ከራሳቸው ገቢና እውቀታቸውን ለመጠቀም ነበር። ያገኙት የጭቃ ቤት ውሃና መጸዳጃ ቤት አልነበረውም። ነገር ግን ወላጆች ሃሳባቸውን ስለተረዱ ውሃ በጄሪካን እየቀዱና በሚፈልጉት እየተባበሯቸውና የሞራል ስንቅ እየሆኗቸው ስራቸውን ይቀጥላሉ። ይህም ሆኖ አብዛኛዎቹ ልጆች በቂ ምግብ ማግኘት ስለማይችሉ ክፍል ቢመጡም በአግባቡ ትምህርታቸውን መከታተል አይችሉም ነበር።
የተወሰኑት ዳቦና ቆሎ ይዘው የሚመጡ ሲሆን ቀሪዎቹ ግን ባዶ እጃቸውን ነበር። በወቅቱ የነበራቸው ዋናው ገቢ የጓደኛማቾቹ መዋጮ ብቻ ስለነበር በእነሱ አቅም የሚደፈር ባይሆንም በችግሩ ውስጥ ሆነው ለአንድ ዓመት ይቆያሉ። እናም ይህ ችግር መቀረፍ ስለነበረበት ለወረዳው ሴቶችና ህጻናትና ቢሮ ለኤምባሲዎች፤ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለሌሎችም ትብብር ለማግኘት ደብዳቤ መጻፍ ይጀምራሉ።
በወቅቱ ምላሽ ባያገኙም ከጊዜ በኋላ ጣሊያን ትምህርት ቤት ደውለው የሚወገዱ የመማሪያ ወንበሮች ስላሉ መውሰድ እንደሚችሉ ይነግሯቸዋል። እነሱም ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው እቃውን ተቀብለው ሲወጡ ሁለት መምህራኖች ያላችሁበትን ሁኔታ እንይ ብለው ይከተላሉ። ሁለቱም መምህራን ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ቅርብ ጊዚያቸው ነበር። እናም በቦታው ተገኝተው ልጆቹ ያሉበትን ሁኔታ ሲያዩ በጣም በማዘንና በመገረም ማን እንደሚደግፋቸው ይጠይቃሉ። ማንም እንደሌለ ሲነገራቸው እስካለን እንደግፋችኋለን ብለው ቃል በመግባት አንዷ ዩኒፎርም አንዷ ጫማ ለልጆቹ መግዛት ይጀምራሉ።
ይህ ድጋፍም ለሶስት ዓመት ከቆየ በኋላ መምህራኖቹ ኮንትራታቸው ስላለቀ እንዲሄዱ ይወሰናል። ነገር ግን የእነሱም ፍላጎት ስለነበርና እነካሌብም የሰሩትን ስራ በደብዳቤ በማሳወቃቸው ሌላ ሶስት አመት ድጋፋቸውን እያደረጉ የሚቀጥሉበት እድል ይፈጠራል። እነዚህ ጣሊያናዊት መምህራን ለቀጣዩም ሶስት ዓመት በየሳምንቱ አንዷ ሙዝ አንዷም እንቁላል ይልኩ ነበር።
ከሶስት ዓመት በኋላ ለቀው ሲሄዱ ግን ተቋሙ ሌላ ችግር ይጋረጥበታል። በአንድ ወገን ቋሚዎቹ ደጋፊዎች መሄዳቸው ሲሆን በሌለ በኩል ትምህርት ቤቱ ያለበት ቦታ አስፋልት በመሰራቱ የቤት ኪራይ መጨመሩ ነበር። ነገሩ ከአቅማቸው በላይ እየሆነ በመምጣቱም ከመበተናቸው በፊት ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ አለብን ብለው መንቀሳቀስ ይጀምራሉ።
መጀመሪያም ለወላጆች ትምህርት ቤቱ ሊዘጋ በመሆኑ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉና እስከዛውም ለምገባ ፕሮግራም የሚወጣው ወጪ ወደ ቤት ኪራይ ስለሚዛወር ምግቡ እንደሚቋረጥም ያሳውቋቸዋል። ወላጆችም ትምህርት ቤቱ አይዘጋም ገና ለእኛም ትተርፋላችሁ ብለን እየጠበቅን ነው። ካስፈለገ አደራጁንና እኛም የሚመለከተው ጋር ሰላማዊ ሰልፍ እናደርጋለን በማለት አብረዋቸው መንቀሳቀስ ይጀምራሉ።
ወቅቱ የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፉ አይሆንም እነካሌብ እናቶቹን በጸሎት ብቻ እንዲረዷቸው በማሳሰብ እነሱም ለጸሎት ወደ ቤተክርስቲያን ያቀናሉ። ይህ ከሆነ ከሰባት ቀን በኋላ አንድ ወጣት ይመጣና ይጎበኛቸዋል እናም ያለባቸውን ችግር ተመልክቶ ይሄዳል። ለካስ ወጣቱ የመጣው ከሀበሻ ቢራ ፋብሪካ ነበር። እናም በሶስተኛው ቀን ደውሎ ይጠራቸውና ስምንት ኩንታል ጤፍ፤ ሁለት ኩንታል መኮሮኒ፤ ሁለት ኩንታል ፉርኖ ዱቄትና አንድ ኩንታል ስኳር አድርጎ ይሰጣቸዋል።
በተመሳሳይ ወቅት ተማሪዎቹ ደግሞ ኮተቤ ኪዳነምህረትና መድሀኒአለም ቤተክርስቲያን በመገኘት ትምህርት ቤታችን እንዳይዘጋ እያሉ ከምእመናኑ ገንዘብ ያሰባስቡ ነበር። በዚህም አምፕሊፋየርና ጄነሬተር ገዝተው ይህንን እያከራያችሁ ትንሽ ብር አግኙ ይሏቸዋል። እነካሌብም አሁን ከሁለት መቶ በላይ አባላት መያዝ የቻሉበትን አባላት በመመዝገብ ሌሎችም ፍላጎት ያላቸውን ጨምሮ ከሀምሳ ብር ጀምሮ በዓመት እንዲያወጡ ለማግባባት መንቀሳቀሳቸውን ይቀጥላሉ። የህጻናት አምባ አብሮ አደግ እድርንም በመጠቀም ሁለት መቶ ሀምሳ ሰዎች የተሳተፉበት የእግር ጉዞ «ጸሀዩ ደመቀችን» እየዘመሩ ለገቢ ማስገኛው ያደርጋሉ። በዛ ቀን ብቻ ሰባ አምስት ሺ ብር ገቢ ለማሰባሰብም ይበቃሉ። እነዚህ ነገሮች የወቅቱን ችግር በመቅረፍ ለቀጣይ ጉዞ መንደርደሪያ ሆኗቸዋል።
በዚህ መካከል ልጆቹ ከትምህርት ውጪ ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በዕረፍት ጊዜያቸው እንደ ሙዚቃ ስእል እርሻ እግር ኳስና የተለያዩ ክህሎቶችን እንዲጨብጡ ይደረግ ነበር። በዚህ ወቅት የማህበሩ አምባሳደር የነበረችው ጋዜጠኛ አዜብ ወርቁ ያለውን ነገር በመመልከቷ ሁኔታዎችን አመቻችታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬን ትጋብዝላቸዋለች።
እሱ ሲገኝም የዝዋዩ ህጻናት አምባ ሲዘምራቸው ከነበሩ ከስልሳ በላይ መዝሙሮች መካከል «ጸሀዩ ደመቀች» የሚለውን ህጻናቱ እንዲያቀርቡለት ይደረጋል። ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩም በዛ ሰሞን ከጎዳና ላይ ልጆችን የማንሳት መርሃ ግብር ስለነበር እዛ ላይ ልጆቹ ዝማሬ እንዲያቀርቡ ይጋብዟቸዋል። በዛ ፕሮግራምም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የነበሩትን አቶ ታከለ ኡማን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች ተገኝተው ስለነበር በጣም ተደስተው ባይሳካላቸውም መጥተው እንደሚጎበኟቸው ቃል ገብተው ይሄዳሉ።
ከስድስት ወር በኋላ ለቡሄ በአል በድጋሚ በጋዜጠኛ አዜብ ወርቁ በኩል ህጻናቱ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ለነበሩት አቶ ታከለ ኡማ ዝማሬ እንዲያቀርቡ ይደረጋል። ከንቲባውም የቀደመውንም ስራ አስታውሰው ደብተርና እርሳስ እንደሚሰጧቸው ቃል ይገቡላቸዋል። ልጆቹም ይሄ በኢምፓ ስለተሟላልን ለምን መጥተው አይጎበኙንም ይሏቸዋል። እሳቸውም በማድነቅ ሄደው እንደሚጎበኙ ቃል ገብተው ያሰናብቷቸውና በቃላቸው መሰረት ተገኝተው ይጎበኛሉ።
በወቅቱ ባዩት ነገር በጣም በማዘናቸው አልቅሰው አብረዋቸው ከመጡት ሀላፊዎች መካከል የሚመለከታቸውን መርጠው ቤት እንዲመቻችላቸው ነግረው ይሄዳሉ። የተነገራቸውም ሃላፊዎች በአካባቢው ለሀይል ማእከል ተብሎ የተሰራና ለረጅም ዓመታት ካለ አገልግሎት የተቀመጠና እየፈራረሰ ያለ ቤት በመኖሩ እንዲገቡበት ይደረጋል። እነካሌብም በየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ፈቃድ ቤቱን አስተካክለው አጥር አጥረው ስራቸውን ይቀጥላሉ።
ማእከሉ እስካሁን አስራ ሁለተኛ ክፍል የደረሱትን የመጀመሪያ ገቢዎች ጨምሮ ሰባት መቶ የሚደርሱ ህጻናት በማእከሉ አገልግሎት አግኝተዋል። በአሁኑ ወቅትም በሁለቱ ግቢዎች ሁለት መቶ ልጆች አስፈላጊው ነገር በሙሉ ተሟልቶላቸው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛል። ላለፉት ሶስት አመታትም በጣላናውያኑ መምህራን በየአመቱ አስር አስር ዊልቸሮችን እያስመጡ ለአካል ጉዳተኞች ያስረከቡ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ስድስት ለማምጣት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።
ባለፈው ዓመት አርባ ልጆችን ወደ መንግስት ትምህርት ቤት አንደኛ ክፍል እንዲገቡ በማድረጋቸው አርባ የሚሆኑ አዲስ ተቀብለዋል። ተማሪዎቹ በመንግስት ትምህርት ቤት በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርግላቸውም ኢምፓ ነው። ትምህርት ቤቱ በክረምትም የማይዘጋ ሲሆን ከየሀገራቱ የሚመጡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረትም እየመጣ ከቋንቋ ጀምሮ በበጎ ፈቃድ ድጋፍ ያደርጋሉ።
በተጨማሪ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ሀምሳ በጎ ፈቃደኞችም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣሉ። ማእከሉ ከህጻናቱ በተጨማሪ ለወላጆችም የልጅ አስተዳደግ ቁጠባና ሌሎች ማህበራዊ ከህሎቶችን እንዲሁም እንደ ጸጉር ስራ፣ ልብስ ስፌት፣ ምግብ ዝግጅት ያሉ የእጅ ሞያዎችንም እያሰለጠነ ይገኛል።
ከቆርኪ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ስምንት መቶ ብር በየወሩ እየተሰጣቸው በነጻ በሰላም የህጻናት መንደር ስልጠና እየወሰዱ ይገኛል። በዚህም እስካሁን አንድ መቶ ሀምሳ እናቶችን ማብቃት የቻሉ ሲሆን በተቋሙ ምግብ የሚያበስሉትም በዚህ መንገድ የመጡ ናቸው። ማእከሉ በርካታ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ ሲሆን ከብት እርባታና ዶሮ እርባታ ለመጀመር የሚያስችለው ዝግጅት እየተጠናቀቀ ይገኛል።
በርካታ የአካል ጉዳተኞች በመኖራቸውም ፊዚዮ ቴራፒና የጎልማሳና አረጋውያን ማስተማሪያ እንዲሁም የአዳሪ ትምህርት ቤት ለመመስረት እቅድ አለው። በተለይም ልጆቻቸውን የሚጥሉ እናቶችን ለመታደግ ችግሩ እስከሚያልፍ ህጻናትን መያዝ ለማይችሉት ማቆያ ለማዘጋጀትም እቅድ አላቸው።
ይህም ሆኖ ቦታውን ሲረከቡ ካርታም ሆነ ደብተር አልተሰጣቸውም ነበር። እናም በአሁኑ ወቅት የአካባቢ ጥበቃ ባለ ስልጣን ቦታውን እንዲለቁ ጥያቄ በደብዳቤ አቅርቦላቸዋል።
በተደጋገሚ ለሚመለከተው አካል ጥያቂያቸውን ሲያቀርቡ በቂ ምላሽ ያላገኙት እነካሌብ ይህ ነገር ለቀጣይ ስራቸውም ሆነ አሁን ያሉት ልጆች ላይ መሰናክል እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ። ዛሬም በአካባቢው ያለው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖረው መደገፍ ያለበት ህዝብ በርካታ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጧቸው እንደሚገባም ያሳስባሉ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2014