ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አይረሴ ከሆኑ ታሪካዊ ቀኖች አንዱ ነው::ይህ እለት ትግራይ የሚገኘው የሰሜን ዕዝ ወታደራዊ ኃይል በገዛ ወገኑ ታላቅ ክህደት የተፈጸመበት ቀን ነው::
የትግል አጋሬ በሚላቸው፣ አብረውት ዓመታትን ክፉ ደግ ካሳለፉ ወገኖች የተሰነዘረበት ከባድ ጥቃት ፍጹም የማይታመንና ድንገቴ ነበር ::
በእለቱ የአራተኛ ክፍለጦር ወታደራዊ ኃይል ውሎውን በተለመደው የበጎ ሥራ ላይ አሳልፏል:: ይህ አይነቱ መልካምነት መቼም ብርቁ ያልሆነው ሰራዊት ላለፉት ሃያ ዓመታት ለአካባቢው ነዋሪ ጉልበቱን ሲገብር ፣ላቡን ሲያፈስ ኖሯል ::ለአጨዳው ፣ ለአንበጣ ማባረሩ፣ ለትምህርት ቤት ግንባታው ፣ደከመኝ ፣ ሰለቸኝን አያውቅም::
ይህ ሰራዊት ከኪሱ ደመወዝ እየከፈለ ፣ ከቤት ከጓዳው እየነጠቀ ለሌሎች መስዋዕት መሆኑ አዲስ አልነበረም ::በደምና ላቡ ጠብታ የህዝቦችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ግንባር ቀደም መሆኑ የማንነት መለያው ነው::
ከራስ በፊት የብዙኃንን ጥቅም ማስቀደም ዓላማው ነውና ያችን ዕለትም ይህን ሲተገብር፣ ሲያስመሰክር ውሏል::የህዝቡን ጉልበት ተክቶ ሰብሉን ሲሰበስብ፣ የአንበጣ መንጋውን ሲያባርር ፣በጸሐይና በውሃ ጥም ሲቃጠል አምሽቷል:: ሰራዊቱ ሥራውን አጠናቆ፣ ወደ መኖሪያው ሲመለስም ከታላቅ ድካም ጋር ነበር::
ሃያ ሰባት ዓመታትን በግፍ ሲገዛ የቆየው የወያኔ መንግሥት ከተወገደ ወዲህ ያሰቡት ያልተሳካላቸው ቡድኖች መቀሌ ገብተው መሽገዋል::ይህ ጊዜ ስልጣናቸውን የክብር ጉዳይ ላደረጉ ጥቅመኞች ሁሉ የማኩረፊያ ጊዜ ብቻ አልነበረም::ወቅቱን ለብዙ ሴራዎች ያሰቡት ክፉዎች ያቀዱትን ሊተገብሩ ጠዋት ማታ ማድባት ይዘዋል::
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ህዝቡን በማገልገል ሲደክም የዋለው ሰራዊት ማምሻውን ወደ ማደሪያው መመለስ ጀምሯል::ሌሊቱን ከማረፊያው አሳልፎ ለነገው ግዳጅ መዘጋጀት አለበት::በግቢው ሰራዊቱን ጨምሮ በርካታ የወታደር ቤተሰቦች ህይወትን በአንድነት ይጋራሉ::ዓመታትን በቆጠሩበት በዚህ ስፍራ ህጻናትና ሴቶች፣ ከሌሎች ቤተሰቦቻቸው ጋር መኖራቸው የተለመደ ነው ::
በሌላ አቅጣጫ የክፋት ሴራውን የጎነጎነው የክፋት ቡድን የምሽቱን መቃረብ በጉጉት ሲጠብቀው ቆይቷል:: ይህቺ ቀን የመጀመሪያዋ የጥፋት ደወል የምትሰማበት ቀዳሚ ምዕራፍ ትሆናለች ::እውነታውን አስቀድሞ የሚያውቀው ኃይል ሥራ ውሎ ህዝብ አገልግሎ የተመለሰውን ሰራዊት በዓይነቁራኛ እያስተዋለ የሰዓቱን መድረስ ይጠብቃል::
የተደገሰላቸውን ያላወቁ ፣ የሰራዊቱ አባላት ከወትሮው የተለየ ምልክት አላዩም::በተለመደው መንገድ ምሽቱን ተቀብለው ካሰቡት ደርሰዋል::የክፋት ዓላማን የሰነቁት ቡድኖች የወጠኑትን ለማሳካት ቀድመው የሰገሰጓቸውን ኃይሎች ለዓላማቸው አመቻችተዋል::እነዚህ አካላት ጸጉረ ልውጥ የሚባሉ እንግዶች አይደሉም:: ቀድሞ የነበሩ የሰራዊቱ አባላት ናቸው::ከእነሱ እየዋሉ እያደሩ፣አብረው እየበሉ፣ እየጠጡ ‹‹በሬ ካራጁ›› ለመሆን ተዘጋጅተዋል::
ተልዕኮ ተቀባዮቹ ሶስት ዓላማዎችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተቀብለዋል:: የመጀመሪያውና ዋንኛው ዓላማ ፣- ብዙኃኑን በመምሰል ሰራዊቱን የማፈራረስ ዕቅድን መተግበር ነበር::ሁለተኛው ውጥን ደግሞ ከሰራዊቱ በመነጠል መልሶ ሰራዊቱን የመውጋት ሀሳብ ነው:: ሶስተኛው ዓላማ ደግሞ ሰራዊቱ ያለምንም ማመንታት እጁን ይሰጥ ዘንድ ሽምግልናን ጨምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ዕቅዳቸውን ማሳካት ሆኖ ተነድፏል::
ይህን ሀሳብ ዕውን ለማድረግ ያስቀመጧቸው አካላት ለምሽቱ ዘመቻ አመቺ እንዲሆን የሬዲዮ መገናኛውን በእጃቸው አስገብተዋል::የመከላከያ ዋና መምሪያ ኃላፊው የእነሱ ወገን እንደመሆኑ የሰሜን ዕዝ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የነበረውን ሬዲዮ መገናኛ በራሳቸው ሚስጥርና መዋቅር የግላቸው አድርገዋል::
በሬዲዮ መገናኛ ልማድና አሰራር ሁሉም ሰራዊት ሚስጥሩን በእኩል መረዳቱ የተለመደ ነው:: ይህ እውነታም በወታደሩ መሀል ጥርጣሬና ልዩነት ሳይፈጠር ሥራን ለማወክ የሚያስችል አድርጎታል:: ይህን የሚያውቁት ቡድኖች ለዓላማቸው ስኬት እንደፍላጎታቸው አድርገው አመቻችተውታል:: ያሰቡትን ዳር አስኪያደርሱ ከእነሱና መሰሎቻቸው በቀር የውስጣቸውን የሚያውቅ አልነበረም::
አሁን የሚሰውት በጎች በየተራ ገብተው ስፍራቸውን ይዘዋል::ሁሉንም በዓይነቁራኛ የሚቃኙት ባለ ካራዎች ስለታቸውን ሞርደው እየተዘጋጁ ነው::ደም የጠማቸው አውሬዎች ግዳያቸውን ሊጥሉ ተጎማጅተዋል:: ይህ ያልገባቸው ነፍሶች እንደትናንቱ ዓይነት ህይወትን ቀጥለዋል:: ምሽቱ እየገፋ ሰዓቱ እየነጎደ ነው:: ሁሉም የሠራዊት አባል በሌሎች ታማኞች ጥላ ስር ስለመኖሩ እርግጠኛ ነው :: በእጁ መሳሪያ ይሉትን አልያዘም:: አብዛኛው እንደወጉ ጎኑን ከመኝታ ሊያሳርፍ ለእንቅልፍ መዘጋጀት ጀምሯል::
ምሽት አራት ሰዓት ከሰላሳ እያለ ነው:: የአራጆቹ እጆች ለጥፋት ሰልተዋል::በቅርብ ርቀት ዓመታትን በግዳጅ አብረዋቸው የዘለቁ ወንድም እህቶቻቸውን እያስተዋሉ ነው::እነሱ ማለት ለእነሱ የትግል አጋሮች፣የመከራ ጓዶች፣የክፉ ቀናት ምልክቶች ናቸው:: እነሱ ማለት ለእነሱ እንደትናንቱ ነገን በአንድ የሚሻገሩ ፣ በእኩል መስመር የሚራመዱ ወንድሞች ናቸው::
ከሀዲዎቹ ይህን ሁሉ ለማሰብ ጊዜ ያላቸው አይመስልም::ወጥመዳቸውን እያመቻቹ ቀድመው የሚጠልፉትን ያስባሉ::የሚያጠፉትን እየለዩ የሚፈጠረውን ውጤት ይስላሉ::ቀኑ የሰራዊቱ የምግብ ራሽን የገባበትና የወር ደመወዝ የተከፈለበት ዕለት ነው:: እንዲህ በሚሆን ጊዜ አብሮ መብላት መጠጣቱ ተለምዷል::ይህን እውነት አስቀድመው የሚያውቁት ከሀዲዎች ቀን በነበረው የምሳ ግብዣ ከተለያዩ ክፍለጦሮች የሚፈልጓቸውን አዛዦች አግተው ይዘዋል::
የክፋት ዘመቻው የሚጀመርበት ጊዜ ደረሰ :: የሬዲዮ መገናኛው ሂደት ተቋረጠ::ማንም ከማንም እንዳይገናኝ ሆኖ የተዘየደው ስልት ዕውን መሆን ጀመረ::ቀድሞ በከሀዲው አጋራቸው በተመቻቸው ዕቅድ መሰረት የታሰበው ሁሉ መሆኑን ቀጠለ ::ቀድሞ በአንድ ቃልና ትዕዛዝ የሚመራው ሰራዊት መግባቢያ መገናኛ የሚሆነውን የጋራ ቃል ተነጠቀ::መሰማማት ይሉት ጠፋ፣
ቀጣዩ ርምጃ የሰራዊቱን የእለት ራሽንና የተከፈለውን ደመወዝ መንጠቅ ነበር:: አዛዦቹ ፈጥነው ገንዘቡን ለኪሳቸው፣ ቀለቡን ለአጋሮቻቸው አደሉ::ለይተው የመረጧቸውን ኃላፊዎች ከበው ሲጨርሱም በ‹‹እጅ ወደላይ›› ትዕዛዝ የዓላማቸውን ጅማሬ ግልጽ በሆነ ቋንቋ ገለጹት ::
ሶስት ቀናትን ያለእህል ውሃ በማስፈራራትና በእገታ ያቆዩትን ሰራዊት በመከራ ሊፈትኑት ታገሉ:: ሆኖም ይህን ምክንያት አድርጎ እጁን የሚሰጥ አንድ ወታደር አላገኙም ::አራተኛው ቀን እንደጀመረ ያሰቡት ያለመሳካቱን ተረዱት ::ወዲያው መላና ዘዴ ያሉትን ሌላ አማራጭ ተግባራዊ ለማድረግ ተጣደፉ::
አስቀድመው ካገቷቸው አዛዦች መሀል ጄኔራል ኑሩን በመያዝ በሬዲዮ መገናኛው ለሰራዊቱ መልዕክት እንዲተላለፍ አደረጉ:: ጄኔራሉ ከግንባራቸው መሳሪያ ተደግኗል:: የእሳቸውን ሳይሆን የአጋቾቹን ሀሳብ ብቻ እንዲናገሩ ተገደዋል::
ጄኔራሉ የተባሉትን ለመፈጸም አንደበታቸውን ከፈቱ::ባስተላለፉት መልዕክትም የጦርነትን አስከፊነት ጠቅሰው፣ እጃቸውን መስጠታቸውን ተናገሩ:: ሰራዊቱ እጁን እንዲሰጥ ሲመክሩ ግን በመጨረሻዋ ደቂቃ ያስተላለፉት መልዕክት የብዙዎችን ስሜት ተቆጣጠረ::
ጄኔራል ኑሩ ‹‹ከእንግዲህ አታገኙኝም ሲሉ የተናገሩትን ቃል ብዙዎች በብዙ ተረጎሙት::ቅኔው የገባቸው በርካቶችም እንዴትና ለምን ሲሉ ተመራመሩ:: ሚስጥሩን የደረሱበት ጀግኖች ትጥቅ አስረክበው እጅ መስጠትን ከሞት ቆጠሩት::ይህን ስሜት የተረዱት ጨካኞች ድርድሩ እንደማያዋጣ ሲረዱ አፈሙዛቸውን ወደሩ:: ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመለዮ፣ በባንዲራ ምለው የገቡትን ቃል ፈጥነው በክህደት ጀመሩት::
ሚሊሻና ልዩ ኃይል በሚል የተደራጀው ቡድን ወንድሙን ሊወጋ ካሰፈሰፈው ጋር ጦረኛ ሆኖ ተሰለፈ::ዛሬ ከሕወሓት ጋር ጋብቻውን የፈጸመው የኦነግ ርዝራዥም ባንዲራውን ይዞ በእኩል መዋጋቱን ያዘ::ትናንት አጋር ወንድሜ ያለው መከታ እጁን ሲያነሳበት፣ በግንባሩ ሲተኩስበት ያየው ሰራዊት ከጥይቱ ቀድሞ ልቡን ኀዘን ገባው:: ከጀርባው የሚወጋውን የቅርብ ሰው ጭካኔና ማንነት አምኖ ለመቀበል ተቸገረ::
ትናንት የወንድሙን አካል ለአሞራና ጅብ ሲሳይ ያደረገው ከሀዲ ቡድን ጭካኔውን ለመግለጽ እልፍ ቃላቶች አይበቁም::ዓመታትን በምሽግና በጉድጓድ የተፈተነ ፣ደሙን ቀድሞ የጠረገ፣ ቁስሉን ፈጥኖ ያከመ ወገን ዛሬ ጠላት ሆኖ ሲገድል፣ ሲያሳደድ ማየት ከአእምሮ በላይ ነው:: የአንድ ኮዳን ውሃ በአንድ ጉንጭ የተቃመሰ የክፉ ቀን አጋር ጥይት ለማጠጣት፣ ነፍስን ለመንጠቅ ሲጣደፍ ማስተዋል ከሞት በላይ ሞት ነው::
ይህ እኩይ ተግባር የኢትዮጵያውያንን ልብ ክፉኛ ሰበረ::ድርጊቱ በየትኛውም ታሪክ ተፈጽሞ አያውቅምና የጭካኔው ጥግ ትርጉም ታጣለት:: ፈታኝ የጦርነት ዓመታትን በቀበሮ ጉድጓድ በአብሮነት ያሳለፈ ወገንን ማሰቃየትና በግፍ መግደል በማንም አልተሞከረም::ትናንት ከጎኑ ተሰልፎ ለሀገር ህልውና የተዋደቀን ጀግና ሳያስበው መሰዋትም ታይቶ ተሰምቶ አይታወቅም:: ክፋት ጠንሳሾቹ ግን ይህን ታሪክ በትክክል ፈጽመውታል::
አረመኔው የሕወሓት ቡድን እያሰቃየ የገደላቸውን ወታደሮች ልብስ አውልቆ፣ በአስከሬናቸው ተሳልቋል:: ክቡር በሆነው አካላቸው ላይ እየጨፈረ ቀልዷል:: ሬሳቸውን እየጎተተም ስለማንነቱ አስመስክሯል :: ይህ እውነታ ገሀድ በሆነ ጊዜ ብዙዎች በተሰበረ ልብ አንብተዋል::በርካቶች ባደመጡት ታሪክ ተሳቀዋል:: የአረመኔው ቡድን ደጋፊ ነን ባዮችና አፈቀላጤዎች አንደበት የተሰማው ምላሽ ግን በተቃራኒው ሆነ::
የዛሬን አያድርገውና ሴኮ ቱሬ ጌታቸው የተባለው ቀላጤ በወቅቱ ስለጥቃቱ የሰጠው ማብራሪያ አሳፋሪ ነበር:: የንፁሀን ደም በግፍ የፈሰሰበትን ፣በርካቶች በገዛ ወንድማቸው ከጀርባ የተወጉበትን፣ክፉ ቁርሾ መብረቃዊ ጥቃት ሲል ተሳለቀበት::ድርጊቱን ከጀግንነትና ድል አዛምዶም በወታደራዊ ቃል ሊያሽሞነሙን፣ ሊያሳምረው ሞከረ::
ሴኮ ቱሬ በወቅቱ በነበረው መተማመን እንደቆራጥ ጀግና ሆኖ ነበር:: ሀሳብ እየመዘዘ፣ታሪክ እያጣቀሰ ሲያብራራም ድርጊቱ ትክክል ነበር ብሎ በመመስከር ሆነ::ይህን እውነታ ሲናገርም አንደበቱ ፈጽሞ አልተያዘም::ለእሱ በከንቱ የፈሰሰው የንፁህን ደም ከጅረት ወንዝ ያነሰ፣ ከብርጭቆ ውሀ የቀለለ ሆኗል ::
ሴኮ ቃሉን ሰምተው ለሚያምኑት ሁሉ ‹‹ይድረሰ›› ባለው መልዕክቱ የጥቃቱን መፈጸም ሚዛናዊ ነው ለማለት ፈጽሞ አልተሳቀቀም::እየደጋገመ ‹‹መብረቃዊ በሚለው›› አጸያፊ ቃላቱ ድርጊቱን የሚያሞካሸው ያለምንም መሸማቀቅ ነበር:: በእሱ ሀሳብና አገላለጽም ይህ መብረቃዊ የተባለ ጥቃት አገሩን ለዓመታት ላገለገለው ጦር ሰራዊት ተገቢ የሚባል ክፍያ ነው::
ሴኮ ቱሬ ኣይኑን በጨው አጥቦ በሰጠው ማብራሪያ የትግራይን ህዝብ በደል ዋቢ አድርጎ ይጠቅሳል:: ህዝብን ለህዝብ ለማናቆር በቀየሰው ዘዴም ብዙሀኑን ማሳመን የሚችሉ ቃላቶችን ደርድሯል:: የአንበጣውንና የኮቪድ ወረርሽኙን በምክንያት እያጣቀሰም ለተከሰቱት ክፉ አጋጣሚዎች ሁሉ መንግሥትን በተጠያቂነት ፈርጇል::
ከሴኮ ቱሬ አንደበት የሚወጡ ቃላቶች በሰራዊቱ ላይ ከዘነቡ ጥይቶች ባልተናነሰ መርዝ የሚረጩ ነበሩ:: በእሱ አገለላጽ መብረቃዊ የተባለው ጥቃት ለአገር አፍራሹ ኃይል የመጨረሻ አማራጭና የመጀመሪያው የድል ምዕራፍ ነበር ::
የትግራይ መንግሥት የወሰደው ፈጣን እርምጃ አይቀሬና ትክክለኛ ነው ሲል ያረጋገጠው የዛኔው ቀላጤ የሰሜን ዕዝን ከትግራይ መንግሥት ጎን ለማሰለፍ የተደረጉ ማግባባቶች ነበሩ ሲልም በማስረጃ ለማጣቀስ ሞክሯል::
የተፈጸመውን እውነታ ፈጽሞ ያልሸሸገው ሴኮ በወቅቱ የነበሩት አመራሮች በትግራይ ህዝብ ላይ አፈሙዝ የማንሳት ፍላጎት እንደሌላቸው ማሳወቃቸውን በራሱ አንደበት አረጋግጧል ::‹‹ሌባ እናት ልጇን አታምነውም›› እንዲሉ ሆኖ ቃሉን ያልጠበቀው የክፋት ቡድን ግን በእነሱ አንገት ላይ ቀድሞ የማረጃ ሳንጃውን አሳረፈ ::ደም በማፍሰስ ህይወት ማጥፋት መፍትሄ ሆኖትም የጭካኔ ተግባሩን አንድ… ሲል ጀመረ ::
በሴኮ ቱሬ ዋሾ አንደበት እንደተገለጸው ትግራይን ለመጨፍለቅ የተነሱ ኃይሎችን ለማጥፋት የተደረገው የግድያ ዘመቻ በሰራዊቱ መሀል በተሰገሰጉ ሰርጎገቦች ዕውን መሆን ችሏል::በእሱ ቀለል ያለ አባባል እንደዋዛ የተጠቀሰው አስከፊ ጭፍጨፋም እጅግ ፈጣንና ደቂቃዎችን ብቻ የወሰደ ነበር::
በሴኮ ቱሬ ‹‹መብረቃዊ›› ተብሎ የተገለጸው የአርባ አምስት ደቂቃው አሰቃቂ ድርጊት ከእስራኤልና አረቦች ጥቃት የተወሰደ ተሞክሮ ነው::ራሱን እንደ አገረ እስራኤል የሰየመው የሕወሓት ቡድንም ይህን ድርጊት ሲፈጽመው በምክንያትና አስቀድሞ በታሰበ ዕቅድ ነበር::
ሴኮ በወቅቱ አበክሮ እንደገለጸው ደግሞ የሕወሓትን እኩይ ዓላማ ለመደገፍ ያልተባበሩ የሰራዊቱ አባላትና አመራሮች ላይ ፈጣን የሚባል እርምጃ ሊወሰድ የግድ ነበር :: ይህን ዕውን ለማድረግና የልቡን ሀሳብ ለመፈጸም የተጣደፉ ከሀዲዎችም ከጎኑ ለመሰለፍ የቀደማቸው አልተገኘም:: የጭካኔውን ተግባር እንደታላቅ ገድል የተጠቀመበት የወቅቱ አፈቀላጤ እርምጃው ራስን የመከላከል ዓለም አቀፍ ተሞክሮን የተጋራ እንደነበር በድፍረት ሲዘረዝር ተሰምቷል::
የሴኮ መብረቃዊ የተሰኘ ጥቃት ሰራዊቱን ለማተራመስና ለማፈራረስ የሚጠቅም ስልት እንደነበር ተጠቅሷል:: ይህ እውነታ መሰረት ሆኖም ዛሬ ድፍን አንድ ዓመት ለሞላው አገር አፍራሽ ጦርነት የመነሻ እርሾ መሆኑን አስመስክሯል:: ትናንት ሴኮ ቱሬን የመሰሉ አገር በታኞች የቀመሩት ሴራ የሚበጃቸው አልሆነም:: ይህን ለወጠኑ ሴረኞች መጥፊያና መቀበሪያ ሆኖ በነበር እንዲታሰቡ አስገድዷል::
አምና ይህን ጊዜ በተለየ አድናቆት ድርጊቱን ሲያወድስ የነበረው ሴኮ ቱሬ ጌታቸው አሁን ዳግም ሀሳቡን ላያስታውስ ከሞት መንደር ተሸኝቷል:: ተደጋግሞ እንደሚነገረው በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን የሚሰነዝሩ ክፉዎች መጨረሻ አምሮና ሰምሮ አያውቅም::
እነሆ! ዛሬም እናት ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጇቿ ህብረት ህልውናዋ ይከበራል::ጠላቶቿ የክፉ ድርጊት ታሪካቸው ተቀብሮም ማንነታቸው ከምድር በታች መዋሉን ይቀጥላል:: ዘመንና ትውልድ የማይዘነጋው የሰሜን ዕዝ ወታደራዊ ጥቃትም በታሪክ ምዕራፍ ሲወሳና ሲዘከር ይኖራል ::
ከአትጠገብ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2014