ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት በየትኛውም ዓለም ታይቶ የማይታወቅ ጸያፍ ተግባር ነው።ድርጊቱ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ኩፉኛ አስቆጥቷል፤ አሳዝኗልም።
ወትሮም ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ አጥንታቸውን የከሰከሱት የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት ያችን የክህደት ቀን በቁጭት ያስታውሷታል።አዲስ ዘመን ጋዜጣ ልክ የዛሬ ዓመት በሰራዊቱ ላይ በተፈጸመው ክህደትና በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት እንዴት ይገለጻል?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡- በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጥንታዊ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበርን እንደ አንድ የሀገር ባለውለታ ተመልክቶ በወቅታዊ የሀገር ጉዳዮች ላይ ሀሳብ እንድንሰጥ ስለጋበዘን በማህበሩ ስም ምስጋና አቀርባለሁ።እንደሚታወሰው ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ የህወሓት አሸባሪ ቡድን ጥቃት ፈጽሟል።ይህ ችግር በዚያን እለት በይፋ ይገለጽ እንጂ ከሰላሳ ዓመታት በፊት የነበረ፤ አስቀድሞ የታሰበና የተቦካ ነው።የህወሓት አሸባሪ ቡድን ህዝብን በመደለልና በማታለል፤ የሚነቅፈውን በማስፈራራት በማሰርና ግፍ በመፈጸም እዚህ የደረሰው መከላከያ ሰራዊቱንም ሆነ አጠቃላይ የጸጥታ ኃይሉን በመቆጣጠር ነበር።
ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም ግን ድርጊቱ የፈነዳበት እለት ነው።ለብዙዎቻችን አዲስ ይመስል ይሆናል እንጂ ጉዳዩን ለምንከታተል ግን ስንፈራ የነበረው ነው የሆነው። ለአንድ ዓላማ የቆመ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሀገር አፍራሾች ሴራ ትልቅ ክህደት የተፈጸመበትና ወንድም ወንድሙን በተኛበት ከኋላ በመምታት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እና ሁሌም በመጥፎ ክስተት የሚታወስ ግፍ የተፈጸመበት ነው።አብሮት ሊሰዋ ከጎኑ የቆመ ወንድሙ መሆኑ ሳያንስ የአካባቢውን ማህበራዊ ችግሮች በመፍታት ረገድ በጉልበቱም በገንዘቡም ሲደግፈው የነበረውን አጋሩን በተኛበት ገድሎ ሬሳውን በጠራራ ጸሐይ አስፋልት ላይ የጎተተበትን ቀን ስናስታውስ በቁጭትም ፤ በኀዘንም፤ በአግራሞትም ነው።እንዲህ አይነት ድርጊት ፈጻሚው የአሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያዊ ስለመሆኑ እንጠራጠራለን።
የኢጣሊያን መንግሥት በአድዋ ጦርነት በደረሰበት ሽንፈት ቂም ይዞ ዳግም ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣ ጊዜ እንኳን እንዲህ አይነት ጭቃኔ አልፈጸመም። የእኛ ያልነው ስጋችን፣ ደማችን ፤ የተዋለድን፤ ባህልና ቋንቋችን የተወራረሰ፣ በአንዲት ባንዲራ ሥር የኖርን፤ ስለባንዲራችንና ስለ ሉዓላዊነታችን በጋራ ቆመን ዋጋ የከፈልን፤ በአንድ ጉድጓድ የተቀበርን ሆነን እንዲህ አይነት ክህደት መፈጸሙ የሚያስገርምም የማይታመንም ነው።በተለይም የውጭ ተቀናቃኞቻችን ባሰፈሰፉበትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሊዳፈሩ በሚሯሯጡበት በዚህ ሰዓት በገዛ ወገናችን እንዲህ አይነቱ ክህደት ሲፈጸም ግራ እጅ ቀኝ እጁን እንደቆረጠው የሚቆጠር ነው።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ድርጊት አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ባህሪ ያልሆነ አሰቃቂና የማይረሳ መጥፎ ታሪክ ነው።የኢትዮጵያንም ሆነ የዓለምን ህዝብ ያስደነገጠ ታሪክ ነው።
አሸባሪው ቡድን ገና ለውጡ ብልጭ እንዳለ ለፌዴራል መንግሥቱ አልታዘዝ በማለት መቀሌ ሄዶ የተሰባሰበ ነው።መንግሥት ከስህተታቸው እንዲታረሙና ለውጡን ደግፈው ኢትዮጵያን በማበልጸግ ሂደት እንዲሳተፉ አስፈላጊውን ሁሉ ጥሪ ቢያደርግላቸውም ፍቃደኛ አልነበሩም፤ ከዚያም አልፎ በሽማግሌ እስከማስመስከር መድረሱን እናስታውሳለን።መጀመሪያም ኢትዮጵያዊነትን በውስጡ የያዘ ስላልነበር እንዲህ አይነቱን ጸያፍ ተግባር ሊፈጽም ችሏል።
አዲስ ዘመን፡- የህወሓት አሸባሪ ቡድን በመከላከያ ውስጥ የነበረውን ፈላጭ ቆራጭነት ሚና እንዴት ይታያል ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡- የመጀመሪያው ጥፋታቸው ደርግ ስልጣን ሲለቅ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት የደርግ ጦር ነው ብለው ማፍረሳቸው ነው።ይህም አንድ ዓላማ ያለው ውሳኔ እንደሆነ ሁኔታዎች አስረድተውናል።የራሳቸውን ጦር ሰራዊት በመከላከያ ሰራዊት ስም የሚተኩበት እድል አገኙ ማለት ነው።በ27 ዓመታት የህወሓት አገዛዝ ሀገሪቱን በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ተቀምጠው እንደፈለጉ ሲዘውሩ የነበሩት የትግራይ ተወላጆች ናቸው።በተለይም በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከፍተኛውን ማዕረግ በመያዝ ሌሎችን ከበታች አድርገው ሲገዙ ነበር።
ለይስሙላህ ከተወሰኑ ብሄረሰቦች ጥቂት ሰዎችን አካተው ከሻንበል ማዕረግ በላይ የትግራይ ተወላጆች እንዲይዙ ሲደረግ ነበር።ከዚያ በፊት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ማዕረግ ለማግኘት ብዙ መድከምን ይጠይቅ ነበር። እነርሱ ግን በዘር እይታ ብቻ ስልጣኑን ለራሳቸው ሰው አከፋፈሉ።ስልጣን ብቻ አይደለም ሀብት እንዲያፈሩም ሁኔታዎችን አመቻቹ።
ባለፉት 27 ዓመታት ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ከበሩ።ሌሎች የሚገዳደሯቸውን የጦር መኮንኖች በየምክንያቱ እያደረጉ ማስወጣት ጀመሩ።እነ ሌተናል ጀነራል አበባው ታደሰ፤ ባጫ ደበሌን የመሳሰሉትን ቀስ በቀስ አሰናበቱ።መከላከያው ውስጥ የሚገኙ ጥቅማጥቅሞችን ቅድሚ እንዲያገኙ የሚደረገው የትግራይ ተወላጆች መሆኑ ይታወቃል።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ወደተለያዩ ሀገራት ከምትልካቸው ውስጥ አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች ነበሩ።በዚህም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መጡ። በኮንትሮባንድ ንግድ እና በተመቻቸላቸው ነገር ሁሉ እየተጠቀሙ ባለፎቅ ሆኑ።በዚህ መልክ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአንድ ብሄረሰብበ የንግድ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል።እንግዲህ ይህ ጥቅማቸው ሲቀርባቸው እንደገና ወደ ስልጣን መመለስ በማሰብ ነው መከላከያውን ያጠቁት።
የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ የመከላከያው የሰው ኃይልም ይሁን የጦር አቅም ከሰማኒያ በመቶ በላይ ትግራይ ውስጥ እንዲቀመጥ አድርገዋል።እነርሱ ሃሳባቸው የፕሬዚዳንት ኢሳያስን አገዛዝ አንስተው ትግራይን ከኤርትራ ጋር አዋህደው ለመግዛት ነው።አስቀድመው የአሰብ ወደብ ያለምንም ድርድር ወደ ኤርትራ እንዲገባ ያደረጉት ይህንን በማሰብ ነው።ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የመዋጋት ፍላጎት አልነበራትም።የአልጀርሱ ውሳኔም ይህን የሚሳይ ነው።ህወሓት ለኤርትራ የተወሰነውን ውሳኔ ሳይቀር ለኢትዮጵያ ተወሰነ ብሎ ህዝብን አስጨፍሯል።
የኤርትራ ጦር ይወረናል የሚል ምክንያት በማስቀመጥ አጠቃላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በክልላቸው አስረው አስቀመጡት።ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ክንፉን የተቆጣጠሩት እነርሱ በመሆናቸው ይህን ጊዜ አስቀድመው በማሰብ ያስፈለጋቸውን ዝግጅት ሲያደርጉ ኖረዋል። ጉምሩክ ፍተሻ ሳያደርግባቸው በቦሌና በጅቡቲ የሚገቡ ኮንቴነሮች ወደትግራይ ይጫኑ እንደነበር ይሰማል።ምን እንደያዙ አይታወቅም።የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ እዚህ አካባቢ ያሉ የመከላከያ ተቋማት ባዶ ሆነው ሁሉም አቅም ያለው ሰሜን እዝ ላይ ነበር። የሀገር ኩራት የሆነው አየር ኃይል ሳይቀር።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተደረገው ሪፎርም ምን ያህል አግዟል ይላሉ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡– ዶክተር ዐቢይ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ባደረጉት ሪፎርም ነው አብዛኛው ችግር የተቃለለው።ውጭ ላለ ሰው ብዙም ላይታየው ይችላል።መከላከያ ላይ አስቀድሞ ሪፎርም ባይሰራበት ኖሮ ምንም የጥይት ድምጽ ሳይሰማ መልሰው ስልጣን የሚይዙበት አጋጣሚም ሊፈጠር ይችል ነበር።ይህንን አሁን ከሚያደርጉት የሞት ሽረት ትግል መረዳት ይቻላል። ሰማኒያ በመቶ የመከላከያ አቅም ትግራይ እያለ የሰሜን እዝ ተጠቅቶ ያ ሁሉ ጉዳት ሲደርስ መቀልበስ የተቻለው አስቀድሞ የተሠራው ሪፎርም ስላገዘ ነው።ሃያ በመቶ በሚሆን አቅም አጥፊዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ከፍተኛ ባለስልጣኖችን እያሳደዱ በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለው ሪፎርም በመሠራቱ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ በለውጥ ጉዞ ውስጥ አትሆንም ነበር።እንደፈለገው እያዘዘ እንቢ ካሉት ግንባር ግንባር የሚመታና የሚያሰቃይ ስርዓት ይቀጥል ነበር።ከዚያ ስርዓት ነው የወጣነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት የትግራይን አርሶ አደር የእርሻ ወቅቱን እንዲጠቀም የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ሲወጣ ወራሪው ቡድን ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ዘልቆ በመግባት እየፈጸመ ያለውን ግፍና ሰቆቃ እንዴት ይገልፁታል?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡- ከጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም ጥቃት በኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እራሱን አደራጅቶ አሸባሪው ላይ እርምጃ መውሰድ በጀመረ ሶስት ሳምንት ውስጥ ነው ትግራይን ተቆጣጥሮ ዋና ዋና አጥፊዎችን ለህግ ያቀረበው።ያ ሁሉ ፉከራና ድንፋታ በሶስት ሳምንት ውስጥ የተጠናቀቀበት ምክንያት ሰራዊቱ ቁጭት ውስጥ ስለነበር ነው።መንግሥት ትልቅ አቅም እንዳለውም አሳይቷል።
አሁንም የፈለገውን ማድረግ የሚችል ነው።ግን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በአሸባሪው ወገን የተሰለፈው ሰው የማሰቢያ ጊዜ አግኝቶ ከጥፋት ቡድኑ እራሱን እንዲለይና እንዲያወግዝም እድል ለመስጠት በሚል ነበር።መንግሥት ይህንን በማድረጉ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ለዓለም ህዝብ ያሳየበት ጥሩ አጋጣሚ ነበር።ነጮቹ ግን እውነታውን እያወቁም ጭምር የአሸባሪውን ጥፋት ከማውገዝ ይልቅ ጣታቸውን ወደ መንግሥት መጠቆማቸውን አልተውም ነበር። መንግሥት እርምጃ መውሰድ ሲጀምር ይንጫጫሉ፤ ንጹኃን ሲጨፈጨፉ ግን ደምጻቸውን ያጠፋሉ።
እነዚህ አካላት ቀደም ሲልም ከደርግ ጋር ሲዋጉ የራሳቸውን ጓደኞች እየገደሉ የመጡ፤ አሁንም ታዋቂ ሰዎቻቸው ሲሞቱ ማንነታቸው እንዳይታወቅ አንገት እየቆረጡ የሚደብቁ፤ አረመኔዎች ናቸው። በዚህ ደረጃ ክፋት ያለባቸው ሰዎች በጊዜ መገታት አለባቸው በሚል ነው ማጥቃት የጀመረው።የአፋር፣ የአማራ፣ የሶማሌ፣ የሲዳማ፣ የኦሮሞ፣ የቤኒሻንጉል፣ የደቡብ፣ የሀረሪና ጋምቤላ ክልሎችም ጉዳዩ የእኛም ነው በሚል ተነስተዋል።
ጉዳዩ የማይመለከታቸው አዛውንቶች፣ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ እንስሳት ሳይቀሩ ተረሽነዋል፤ ሴቶች ተደፍረዋል።በአጠቃላይ ቆሞ የሚሄድ እስትንፋስ ያለው በሙሉ በግፍ ተጨፍጭፏል።የሃይማት ተቋማት ወድመዋል ፤ ተዘርፈዋል፤ ህዝቡ የእለት ጉርሱን ተቀምቷል፤ አዝመራው ከማሳው ላይ እየታጨደ ተወስዷል።እነዚህ የአሸባሪው ቡድን ተዋጊዎች እዚህ ምድር ለዚያውም ኢትዮጵያ ላይ የበቀሉ እስከማይመስሉ ድረስ ተሰምተው የማይታወቁ ግፎችን ሁሉ ፈጽመዋል።
ኢትዮጵያውያን ምርኮኛን በክብር የሚይዙ ናቸው። ኢጣሊያኖች ሲማረኩ በእንክብካቤ ነው የሚያዙት፤ መከላከያ ሰራዊት ቀንደኛ የአሸባሪው አመራሮችን እነስብሃት ነጋን በክብር ይዞ ነው ያመጣቸው።አሁንም በክብር ነው ታስረው የሚገኙት።ይህ ከድሮ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን አብሯቸው የኖረ ጨዋነት ነው።
በዚያም ወገን ቢሆን እድሜቸው ያልደረሰ ህጻናትን እየሰበኩና አእምሯቸውን በሀሽሽ እያደነዘዙ ነው ለእልቂት የሚዳርጓቸው።ለምሳሌ ጎቭል የሚባለው የጀርመን የፕሮፓጋንዳ ሰው የሂትለርን ኃይልና አቅም እጅግ በጣም አግዝፎ በመናገሩ ነው ህዝቡን በነቂስ አስወጥቶ ያስጨፈጨፈው።አሁንም በትግራይ እየሆነ ያለው ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ቡድን ኢትዮጵያዊነትን የሚጠላው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡- እነርሱ እኛ የተሻልን ስለሆንን ኢትዮጵያን መምራት አለብን፤ ኢትዮጵያ በእኛ ካልተመራች ትፍረስ የሚል አቋም ይዘው የሚሰሩ ናቸው።ኢትዮጵያን መምራት የሚፈልጉትም ስልጣናቸውን ተጠቅመው ለመመዝበር ፍላጎት ስላላቸው ነው።ህዝቡን አበጣብጠን ኢትዮጵያን መቀመቅ ውስጥ ከከተትን በኋላ ሀገሪቱን እናስተዳድራለን ብለው የመጡ ናቸው።ክፋታቸው ዓለም ላይ ከተደረጉት ክፋቶች ሁሉ የገነነና የሚያሳቅቅ ነው።ኢትዮጵያ በልባቸው የለችም።ከኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅማቸውን የሚያስቡ ናቸው።
ታሪካችን እንደሚያስረዳን ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ከተመሰረተች በኋላ ህዝቡ በፍቅር የመጡትን የሚቀበል፤ ሲነካ እንደተርብ ተነስቶ አጸፋ የሚሰጥ ህዝብ ነው።አሸባሪው ቡድን ዓላማው በኢትዮጵያዊነት የሚኮራውንና የሚመካውን ህዝብ ጨርሶ ለማጥፋት ነው። ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም የተደረገውም ይሄው ነው።የኢትዮጵያን ክብር ለማዋረድ ነው።መከላከያውን በማፈራረስ ሀገር ዳርድንሯ እንዲደፈርና የውጭ ኃይሎች የሚፈልጉትን እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው።
ዛሬ ለነዚህ አሸባሪዎች የውጭ ኃይሎች የቀኝ እጅ መሆናቸውም ለዚሁ ነው።ኢትዮጵያ በአጼ ቴዎድርስ ጊዜ በትግራይ ተወላጆች እየተመሩ ከመጡ አንግሊዛውያን ጋር ተፋልማለች፤ በአጼ ምኒልክ ዘመንም በትግራይ ባንዳዎች ከሚመራው የኢጣሊያን መንግሥት ጋር ተዋግታ ድል አድርጋለች።በዚያው ልክ ደግሞ ስለኢትዮጵያ ክብርና ሞገስ ሲሉ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ጋር የሞቱ የትግራይ ተወላጆች በርካቶች ናቸው።አሁን የተሰባሰበው ቡድን ግን የጥንቶቹን ባንዳዎች አስተሳሰብ ይዞ የመጣ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለምንድነው በውጭ ኃይሎች እየተደገፈ ያለው?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡- ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ ጋር ባደረገችው ጦርነት ድል ማድረጓ ያኮራው ጥቁር ህዝቦችን እንጂ ፈረንጆችን አይደለም።ነጮቹ ቀደም ብለው ራሳቸውን በሳይንስ፣ በጂኦግራፊ፣ በቴክኖሎጂ አዳብረው ስለነበር ሌላውን ዓለም ቀኝ የመግዛት እድል ስለነበራቸው የኢትዮጵያ ድል አልተመቻቸውም።
በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች በቀኝ ግዛት ስር ስለነበሩ ኢትዮጵያ እራሷን ነጻ ማውጣቷ ለሌሎች አርአያ ሆናለች ብለው ስለሚያስቡ አይወዷትም። የኢትዮጵያ ድል አድራጊነት የቀኝ ገዢ ኢምፔሪያሊስቶችን የበላይነት አንኮታኩቶባቸዋል።የኢትዮጵያ ድል ጥቁሮች ከነጮች ግዞት ነጻ መውጣት እንደሚችሉ አሳይቷል።
በዚህ ሁኔታ ኢትዮጵያ በነጮች አትወደድም፤ በቂም በቀል የተያዘች ሀገር ናት።ለማስመሰል እርዳታ እናደርጋለን፤ የትምህርት እድልና ብድር እንሰጣለን እያሉ ይገባሉ። የሚገቡት ገመናችንን ካዩ በኋላ የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ ነው።እንግዲህ ነጮች ምንም ጊዜ ቢሆን የኢትዮጵያን ትልቅነት አይፈልጉም።ለዚህም ነው ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ያላቸውን የውስጥ ኃይሎች የሚደግፉት።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ወሳኝ በመሆኑ በቀጠናው የበላይነት እንዲኖራቸው ቦታውን መያዝ ይፈልጋሉ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ አቀማመጥ አብዛኛዎቹን የዓለም ሀገራት ለመቆጣጠር የሚያመች ነው።ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ በልጽጋ በዚህ ቀጠና ላይ የበላይ እንድትሆን አይፈለግም። ሁል ጊዜ እንድትዳከምና የእነርሱ ጥገኛ እንድትሆን ይፈልጋሉ። ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ካላቸው የውስጥ ኃይሎች ጋር የሚሰሩትም ለዚህ ነው።
ለምሳሌ ኦቶማን ኢምፓየር ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ከተባበረች የቀይ ባህርን መተላለፊያ ትዘጋብናለች የሚል ከፍተኛ ፍራቻ ነበር።በወቅቱ የልጅ ኢያሱ መንግሥት ከጀርመን እና ከኦቶማን ኢምፓየር ጋር ጠንካራ ግንኙነት ስለነበረው ከስልጣን እንዲወገድ የተደረገውም በእነርሱ ጣልቃ ገብነት ነው።ለልጅ ኢያሱ ከስልጣን መወገድ አንዱ ምክንያት የውጭ ሴራ ነው።
ኋላም ኢትዮጵያ ዳግም በኢጣሊያን ስትወረር አንድም የአውሮፓ ሀገር አልተቃወመም።ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል ሆና ቤልጄም በተካሄደው ስብሰባ ላይ አጼ ኃይለስላሴ የኢጣሊያን ህገ ወጥ ወረራ ዓለም እንዲያስቆምላቸው ሲጠይቁ ተገቢውን መልስ የመስጠት ፍላጎት አልነበራቸውም።እንደውም እንዴት ጥቁሮች ከእኛ ጋር ማህበር መስረተው እንዲህ ያወራሉ ብለው አላግጠውብናል።
አሁንም ኢትዮጵያ ላይ ይህ ሁሉ ሰው ሲገደል፤ ሲጨፈጨፍ፤ መንግሥት በሀገሩ ውስጥ ያለውን ችግር እራሱ እንዳይፈታ ተጽእኖ እያደረጉ ነው።ይህ ምን ማለት ነው ካልን አንተ መንግሥት የለህም በተዘዋዋሪ የምንመራህ እኛ ነን ማለታቸው ነው።ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይዋጥለትም።
የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በየጊዜው በሚደረጉ ክብረ በዓሎች ላይ የአባቶቻችንን የጀግንነት መንፈስ ለህዝቡ በማስታወስና በማጋባት ግንዛቤ ለማስጨበጥና አዲሱን ትውልድም ለማንቃት ነው። የዛሬው ዘመን ወጣት ከአባቶቹ የበለጠ በሀገሩ ጉዳይ የነቃ ነው።
ነጮች አንድን ነገር የሚመለከቱት በአስር መንገድ ነው።ለነገሮች ጊዜ ሰጥተው፤ ተንትነው በሚያዋጣቸው መንገድ መሄድን የሚመርጡ ናቸው።ያንተን ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም የሚመለከቱ ናቸው።ማጥፋት ለሚፈልጉትም፤ ማዳን ለሚፈልጉትም መፍትሄ ያስቀምጣሉ።የሚመቻቸውን መንግሥት ይደግፋሉ፤ የማይመቻቸውን ግን ያጠፋሉ።እጅ የሚነሳ፣ የሚያጎበድድ፣ የሚገዛ፣ የሚታለል መንግሥት ይፈልጋሉ።ይህን ሀሳባቸውን የሚደግፍ ከሆነ ህዝብን በደለ አልበደለ ምናቸውም አይደለም።የአሸባሪው ህወሓት ቡድንን የሚደግፉትም ከዚህ አንጻር ነው።
አሸባሪዎቹም ፈረንጆች አቅም ሊሆኗቸው እንደሚችሉ ስለሚያውቁ የሆነውንም ያልሆነውንም እያወሩላቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድሩላቸው እየጣሩ መሆኑን እያየን ነው።ቀደም ሲል ኢትዮጵያዊ ናቸው ብለን የምናምናቸው የአሸባሪው ቡድን አባላት ከትምህርት ቤት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማዳከም ሲጠነስሱ የነበሩ ናቸው።የውሸት ፕሮፓጋንዳ እየሰበኩ የትግራይ ህዝብ በተለይም ወጣቱ እንዲከተላቸው አድርገውታል።የህወሓትን አሻጥር የሚያውቀው የተወሰነ ሰው ነው።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ኢትዮጵያን ወክለው ቦታ የሚይዙ የትግራይ ተወላጆች ሁሉ ስለኢትዮጵያ ሳይሆን ስለትግራይ ብቻ የሚያስቡና የሚቆረቆሩ ናቸው።የትግራይ ህዝብም በዚሁ መንፈስ እየተኮተኮተ ከአርባ ዓመታት በላይ ኖሯል።ኢኮኖሚውም ጉልበትም ስላላቸው ማንም ሰው አካኪ ዘራፍ ቢል ጸጥ ለጥ አድርገው የሚገዙበትን ስርዓት ዘርግተው ኖረዋል።አሁን ያ ሲቀርባቸው ከሰውነት ወደ አውሬነት ተቀይረዋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ጥንካሬ እንዴት ያዩታል?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡- የአንድ ሀገር ጥንካሬ የሚገለጸው ከውስጥ ብቻ አይደለም ከጎረቤት ጋር ባለ ጥንካሬም ይለካል።ሱዳን ላይ በነበረው ችግር ቀድሞ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው።እንደውለታ አድርገው ይቆጥሩታል።የሱዳን ህዝብ ለኢትዮጵያ መልካም አመለካከት ያለው ነው።ከኤርትራም ጋር የተደረገው ግንኙነት ቀላል ዋጋ የሚሰጠው አይደለም።ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ ጋር ያለው ግንኙነትም ይሁን ጎረቤት ሀገራት ለምሳሌ ሶማሊያና የኬኒያን፣ ጅቡቲና ኤርትራን ለማግባባት የተሠራው ሥራ የቀጠናውን ሁኔታ የቀየረ ነበር።
ይህ ሲሆን ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጥንካሬ ስጋት የሚሆንባቸው ሀገራት ስላሉ ጉዳዩን በአይነቁራኛ እየተመለከቱ ለማዳከም ይጥራሉ።ሊያንበረክኩን፤ በቁጥጥራቸው ሥር ሊያደርጉን የሚፈልጉ አሉ።አንንበረከክም ባልን ጊዜ ደግሞ እንደሚታየው የተለያየ ጫና ሊያደርጉብን ይሯሯጣሉ።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በውጭም በውስጥም ኃይሎች እየደረሰበት ያለውን ጫና ለመቀልበስ እያደረገ ያለውን ትግል እንዴት ያዩታል።
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡– መንግሥት ማለት ህዝብ ነው። ሀገርን ከጠላት ለመከላከል መንግሥት ጥሪ እስከሚያስተላልፍ መጠበቅ አያስፈልግም።በአንዳንድ ቦታ ወጣቶች እራሳቸውን እያደራጁ የመጣውን ጠላት ሲመክቱ ይታያል።አሁንም ይህንን አጠናክሮ በመቀጠል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሸባሪውን ቡድን ማጥፋት ያስፈልጋል።
ከውጭም ከውስጥም ጫና ቢበዛብንም እስከ አሁን ለጸጥታው ምክርቤት እና ለአሜሪካን እጃችንን አልሰጠንም።በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚያደርጉትን አሻጥሮች አሸንፈናል።ሀገራትን በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ባለማስገባት አሸናፊ ሆነናል። ከዚያም አልፈን ዓለም በተወሰነ መልኩ ምልከታውን እንዲቀይር አድርገናል።የነበረንን አልበገር ባይነት እና ታሪክ በተጠናከረ መልኩ ልንገፋበት ይገባል።አሁን ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ አሸባሪውን ለመደምሰስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴም የሚበረታታ ነው።ሁሉም በሀገሩ ጉዳይ ሊሰለፍ ይገባል እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡ – ለወጣቱ ምን መልእክት ያስተላልፋሉ?
ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፡- የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በተደጋጋሚ ለወጣቱ የሚያቀርበው ጥሪ ወጣቱ ሀገሩን ከገጠማት ችግር እንዲታደጋት ነው።ወጣቱ የሀገሩን ጉዳይ ቆቅ ሆኖ በንቃት መከታተል ይኖርበታል።መጀመሪያ እራሱን ማጽዳትና ለሀገር የሚጠቅመውን፤ ለህዝቦች በሰላም መኖር የሚበጀውን መንገድ መምረጥ አለበት።ከዚያ የሚጠበቅበትን ምላሽም መስጠት አለበት።
የሀገር ፍቅር መስዋእትነት ያስከፍላል።ለሀገር መሞት ክብር ነው። ኢትዮጵያ ክብሯ ተጠብቆ የኖረችው አባቶች በከፈሉት ዋጋ መሆኑን ወጣቱ ሊገነዘብ ይገባል።እርሱም የሀገሩን ዳር ደንበርና ሰላም በማስጠበቅ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለበት።ወጣቱ በወሬ መፈታት የለበትም።የተግባር ሰው መሆን ይጠበቅበታል።ሁልጊዜም በሀገሩ ጉዳይ በተጠንቀቅ መቆም ይኖርበታል።ወጣቱ ሀገሩን ለመከላከል በተጋጋለ ስሜት ሲነሳ መንግሥትም አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠትና ቁሳቁስ በማሟላት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
ከዚሁ ጋር አያይዤ ለትግራይ ህዝብ የማስተላልፈው መልእክት አለ።የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ አንዱና ትልቁ አካል ነው።ኢትዮጵያን ከገነቡት ጉዳዮች አንዱ የአክሱም ስልጣኔና የትግራይ ህዝብ ታሪካዊ ዳራ ነው።
የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ አይደለም።ነገር ግን የተንሸዋረረ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች በሚነዙት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየተታለለ ነው። ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ መግባት፤ ያለፈውን የህዝቦች የእርስ በርስ ትስስርና አንድነት፤ የመጪውን ትውልድ ቅርርብና አብሮነት መርሳት ነው።
የትግራይ እናቶች ወልደው መከራ አይተው ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን ለጥቂት ግለሰቦች ጥቅም ሲሉ ሊገብሩ አይገባም።ወጣቶቹ የያዙትን መሳሪያ አፈሙዝ ኢትዮጵያን ለማጥፋት በተነሱት ላይ ማዞር ይኖርባቸዋል።ሰላሳና ሃምሳ ለማይሞሉና በጥቅም ለተሳሰሩ የአንድ አካባቢ ሰዎች ብለው ከንቱ መስዋእትነት መክፈል የለባቸውም።እጣ ፈንታቸው ከኢትዮጵያ ጋር መቆም ነው።የተለያችሁ ናችሁ እየተባለ የተነገራቸውን መደለያ በመተው በእነርሱ ደም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የፈለጉ ጨካኞችን እንቢ ሊሏቸው ይገባል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014