ውብ የሆነው የወጣትነት ጊዜን ፍሬማ የሆነ ተግባር ላይ ካዋሉት ለስኬት መንገድ ያቃርባል። ሮጦ ለመስራት ጉልበት የፈለጉትን ለማድረግ አቅም በዚህ እድሜ የሚታጠቁት ሀብት ነው። ይሄን መመነዘር ደግሞ የባለቤቱ የወጣቱ ተግባርና ኃላፊነት ነው።
ወጣቶች አዲስ ወደሆነው ፋሽን ዘርፍ በመቀላቀል የእራሳቸውን የገቢ ምንጭ ከማሳደጋቸው ባሻገር ለሌሎች ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ ይገኛሉ። በተለይም በልብስ ዲዛይን ሰልጥነው የራሳቸውን ድርጅት አቋቁመው እየሰሩ ያሉ ወጣቶች ተበራክተዋል። ከዚህ ባሻገርም ለማህበረሰቡና ለሌሎች ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ላይ ይገኛሉ፤ አገራቸው በፋሽን ኢንዱስትሪው ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረግ ትልቅ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ ይገኛሉ።
በፋሽን ዲዛይኒግ ሙያ የተሻለ ውጤት ካገኙ ወጣት ሙያተኞች መካከል ዲዛይነር ሚሊዮን ተፈራን ለዛሬ እንግዳችን አድርገን ጋብዘናታል። ገና እያደገ ባለው የፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የራሷን አበርክቶ በመወጣት ላይ ያለችው ወጣቷ ዲዛይነር ሚሊዮን፣ አጠቃላይ የዘርፉ እንቅስቃሴ እንደ አገር ምን እንደሚመስል፣ በግሏ ለዘርፉ እያበረከተች ያለችው አስተዋፅኦ፣ በሙያው ላይ ያላትን አጠቃላይ ምልከታና ስራዎቿን በተመለከተ አውርተናታል።
ለኑሮ ይሆነኛል፤ ለለውጤ ይበጀኛል ያሉት ስራ ላይ ሆነው በድንገት የገጠሞትን ሌላ የተለየ ስራ ወይም አጋጣሚ ተጠቅመው የጀመሩት ስራ ስኬታማ ሊያደርጎት ይችላል። ዲዛይር ሚሊዮን ተፈራ ወደ ዲዛይኒግ ሙያ የገባችው በ2010 ሲሆን፣ በፋሽን ዲዛይኒግ ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ የሆነ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ወጣቶች አንዷ ለመሆን በቅታለች።
ልጅ ሆና ጋዜጠኛ ለመሆን ብርቱ ምኞት የነበራት ቢሆንም፣ ትምህርቷን አጠናቃ በሌላ ሙያ ላይ ቆየች። እንዲያም ሆኖ ግን ሁሌም ለፋሽን ዲዛይን ልዩ ፍላጎት ነበራት፤ አንዳንዴም በራስዋ በተለይ በልብሶች ዲዛይኖችን የመስራት ሙከራ ታደርግ ጀመር። ይሄን ሙከራዋን በአጋጣሚ የተመለከተችው ዝነኛዋ የፋሽን ኔክስት ዲዛይን ባለቤት ሳራ ሙሀመድ፣ ሚሊዮን የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ ሙያውን በእውቀት ደግፋ ትሰራው ዘንድ የትምህርት ዕድል ሰጠቻት።
ቀድሞ በራስዋ ትሞካክረው የነበረውን የፋሽን ዲዛይኒግ ስራ በተሰጣት ዕድል በመጠቀም ፣ በትምህርት አጠነከረችው። ሙሉ ጊዜዋን በስራው ላይ አዋለች። በምትሰራቸው የባህላዊና ዘመናዊ አልባሳት ዲዛይኖች ብዙ ደንበኞችን ማፍራትም ችላለች። ለቋሚና ጊዜያዊ ወጣት ሰራተኞችም የስራ እድል ከፍታለች።
ዲዛይነሯ በራስዋ ዲዛይን የሰራቻቸውን አልባሳትየምትሸጥበት የራስዋ መደብርም አላት። ለሌሎች የዘርፉ ግብአት አቅራቢዎችም የስራ እድል ፈጥራለች።
ሙያውን በሚገባ ተምራ ወደ ስራ ስትገባ ስራዎቿን ማስተዋወቅና ተጠቃሚ ጋ ማድረስ ትልቅ ፈተና እንደሆነባት የምታስታውሰው ዲዛይነር ሚሊዮን፣ የስራው አዲስነት፣ በማህበረሰቡ ዘንድ አለመለመድና መሰል ችግሮች በሌሎችም ባለሙያዎች ላይ በተለይ ወደሙያው ሲቀላቀሉ እንደሚገጥም ታስረዳለች። በእርግጥ በስራዋ ላይ እየጠነከረች ስትሄድ በራስዋ በኩል ተጠቃሚዎችን የማግኘቱ እና ስራዎቿን ለህዝብ የማድረሱ ውስንነት እየቀነሰ ቢሄድም፣ ስራዎችን ለተጠቃሚ በማድረሱና በማስተዋወቁ በኩል ወጣት ዲዛይነሮች ፈተና እንዳለባቸው ትጠቁማለች።
አሁን ላይ ስራዎቿን በመመልከት በርካታ ደንበኞችን ማፍራት መቻሏን የገለጸችው ሚሊዮን፣ ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርና ያሉትን ዕድሎች በትክክል መጠቀም ቢቻል ጥሩ እምርታ ማስመዝገብ እንደምትችል ታስረዳለች።
ሙያውን በአገር ደረጃ ለማሳደግና ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ገቢ ለመጨመር ብዙ መስራት ያስፈልጋል የምትለው ሚሊዮን፣ ያደጉት አገራት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠታቸው ኢኮኖሚያቸውን መደገፍና ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንደቻሉም ትጠቅሳለች። በትምህርት ቤት ደረጃ እየተሰጡ ያሉ ስልጠናዎች ውስን መሆን፣ ትምህርት ቤቶችም ከሚጠበቀው አንፃር ቁጥራቸው አነስተኛ መሆንና በማህበረሰቡም ውስጥ ስለሙያው ያለው ግንዛቤ የተሳሳተና አነስተኛ መሆንን ሙያው እንዳያድግ ምክንያት መሆናቸውን ታብራራለች።
እንደ ዲዛይነሯ ገለጻ፤ ወደ ሙያው ገብተው እየሰሩ ላሉ ዲዛይነሮች የተለያዩ መድረኮች ተዘጋጅተው ስራዎቻቸውን ለህዝብ ማቅረብ የሚችሉበት አጋጣሚ ቢፈጠርላቸው ለሙያው እድገትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ጉልህ ሚና ይኖረዋል። የኢትጵያዊያን ዲዛይነሮች ስራና የፈጠራ ውጤት የሆኑ አዳዲስና ምርጥ የሚባሉ ስራዎችአሉ። እነዚህ ስራዎች ለውጪ ገበያ በስፋት የሚቀርቡበት ሁኔታ ቢፈጠር በዘርፉ ይበልጥ ውጤታማ መሆን ይቻላል።
አሁን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የዲዛይኒግ ትምህርቶች እየተሰጡ መሆናቸውን የጠቀሰችው ዲዛይነር ሚሊዮን፣ ዘርፉ ካለው ሰፊ የገበያ እድልና መጠቀም የሚቻልበት ዕድል ያህል በስፋት ሊሰራበት እንደሚገባም አስገንዝባለች። ለእሷና መሰል ወጣት ባለሙያዎች ለስራቸው ምቹ ሁኔታ በተለይ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች በማመቻቸት ረገድ የሚሰጣቸው ድጋፍ አሁን ጥሩ መሆኑን የገለፀችው ባለሙያዋ፣ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ ቢቀጥል በስራቸው ውጤታማ እንደሚሆኑ እንደሚያደርጋቸው ታስረዳለች።
ማህበረሰቡ በዲዛይኒግ ሙያ ላይ ያለው ምልከታም በደንብ ሊሰራበት እንደሚገባ ነው ያመለከተችው። ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ ማሳደጊያ፣ ለስራ አጥነት መቅረፊያ በመሆንና ለአለም እያበረከተ ያለውን ትልቅ አስተዋፅኦ መገንዘብ እንደሚገባም አስገንዝባ፣ የዲዛይኒግ ሙያ እጅግ በጣም ትልቅና ከሰሩበት አገርንና ማህበረሰብን መለወጥ የሚችል መሆኑን ታስረዳለች።
በትምህርት ባገኘቸው የዲዛይኒግ መሰረታዊ ዕውቀት በመታገዝና የራስዋን ፈጠራ በማከል አዳዲስና ጥሩ ዲዛይኖችን በመስራት ለማህበረሰቡ በማቅረብ ላይ የምትገኘው ሚሊዮን፣ ስራዎችዋን ከእለት ዕለት ለማሻሻልና ጥራትንም ለማሻሻል በምታደርገው ጥረት በርካታ ደንበኞችን ማፍራት መቻልዋን ትናገራለች፤ ወደፊትም በተሻለ መንገድ የመስራት እቅድም አላት።
ወጣቶች ሰፊ በሆነው የፋሽን ዘርፍ ተሳታፊ ሆነው ራሳቸውንና አገራቸውን ቢጠቅሙ ዘርፉን ከማሳደግ ባለፈ አገራዊ ኢኮኖሚን በማነቃቃት በኩል የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ። እኛ ከወጣትዋ ዲዛይነር ሚሊዮን ጋር የነበረንን ቆይታ በዚሁ አበቃን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2014