ትውልድና እድገቷ ከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ነው። ልጅነቷን እንደማንኛውም የአካባቢው ልጅ አሳልፋለች። ዕድሜዋ ከህጻንነት እንደተሻገረ ከወላጆቿ ልትለይ ግድ ሆነ። አልፎ አልፎ እነሱ ቤት የምትመጣው አክስት አይኖቿ በእሷ ላይ አረፉ።
አክስትዬው ከሌሎች ልጆች መሀል እሷን ብትወዳት የልቧ ምርጫ ሆነች። ይህን ስሜቷን ይዛ ከልጅቷ ወላጆች መከረች። ልጃቸውን አዲስ አበባ ወስዳ ልታኖራትና ልታስተምራት እንደምትሻ ተናገረች። የመሰረት እናት አባት የከተሜዋን እንግዳ ሃሳብ አልጠሉትም።
ልጃቸው ህይወቷ እንዲሻሻል ይወዳሉ። አዲስ አበባ ገብታ ብታምር ደስ ይላቸዋል።ከተማ የብዙዎችን ህይወት ይለውጣል፤ የበርካቶችን ኑሮ ይቀይራ ብለው ያምናሉ። ትንሺቱ መሠረትም ነገን ትልቅ ለመሆን አዲስ አበባ ብትገባ መልካም ነው ብለው አሰቡ። እናም ለእንግዳዋ አክስት የእሺታ ቃላቸውን ከልጃቸው እጅ ጋር ለመስጠት አልዘገዩም። የወላጆችን ይሁንታ ያገኘችው የመሠረት አክስት ትንሸዬዋን ልጅ አስከትላ አዲስ አበባ ተመለሰች።
መሠረትና የከተማ ህይወት በቀላሉ ተግባቡ፤ የሚኖሩበት አካባቢ መርካቶ ዙሪያ በመሆኑ ግርግርና ግብይቱ ይደምቃል። ለእንዲህ አይነቱ ልማድ እንግዳ የሆነችው መሠረት ስፍራውን አልጠላችውም። በቀላሉ ከሌሎች ጋር ተግባብታ በርካቶችን አወቀች። አካባቢውን ለምዳ ክፉን ከ በጎ ለየች።
የመሠረት አክስት ቃሏን አላጠፈችም። አደራዋን አልበላችም። የልጅቷ ዕድሜ ለትምህርት ሲደርሰ ደብተር አስይዛ፣ ልብስ ጫማ ገዝታ ትምህርት ቤት ላከቻት። መሠረት ከእኩዮቿ ጋር የፊደልን ሀሁ ልትለይ፣ ከዕውቀት ማዕድ ተሰየመች።
በአክስት እጅ ማደግ የጀመረችው ልጅ የጎደለባት የለም። የሚያሻትን እያገኘች፣ የጠየቀችው እየተገዛላት ኑሮና ህይወትን ቀጠለች። ጓደኞቿን ለመመስል፣ እንደ አካባቢው ለመሆን አልዘገየችም። ከባልንጀሮቿ ስትውል፣ ጨዋታና ወጉን ለመደች። መውጫ መግቢያውን፣ መሄጃ መመለሻውን አወቀች። አሁን መሠረት የእንግድነት ስሜት የላትም። እንደማንኛውም ተማሪ በነጻነት ውላ ትመለሳለች።ትምህርቷን መማር ለውጤት መትጋት ጀመረች።
ትምህርት ቤት ሲዘጋና ጊዜ ሲኖራት ወላጆቿን ትጠይቃለች።በትውልድ አገሯ በሄደች ቁጥር ልጅነቷን አትረሳም። የአዲስ አበባ ልጅ የሆነችበትን አጋጣሚ አስታውሳ በትዝታ ታወጋለች። ከወላጆቿ፣ ከእህት ወንድሞቿ ጋር የምታሳልፈው ጊዜ እምብዛም አልነበረም። ወደነበረችበት ለመድረስ ወደ ህይወቷ ለመመለስ ትጣደፋለች።
መሠረትና አክስቷ ኑሯቸው ተክለሃይማኖት ከተባለ ሰፈር ነው። ሰፈሩ በርካቶች ለኑሮና ንግድ ይጠቀሙበታል።አብዛኞቹ ለፍቶ አዳሪና በቦታው ዓመታትን የገፉ ናቸው። መሠረት በዚህ አካባቢ ማደጓ ከብዙዎች አግባብቷታል። ስፍራው ለመርካቶ የቀረበ ነውና ለንግድ ሥራ ያመቻል። ይህ እውነታ ንግድን ለሚሹ ሮጠው ለሚያድሩ ባተሌዎች ያመቻል።
መሠረት ትምህርቷን መማር ቀጥላለች።እንደእኩዮቿ ከትምህርት ውላ ስትገባ እንደልጅነቷ ከቤት የሚጠብቃት ሥራ አይጠፋም። ሁሉን እንደየሁኔታው የምትቀበለው ወጣት በአክስት ዓይን እየታየች ልጅነቷን ጨረሰች። ወጣትነቷን መያዝ ስትጀምር በዕድሜዋ የሚጠበቁ ምልክቶች ይስተዋሉ ጀመር።
መሠረት የወጣትነት ጊዜዋ ለትምህርት ብቻ አልሆነም። ሃሳቧን የሚጋራ የፍቅር ስሜት ከወንድ ጓደኛዋ አጣመራት። ግንኙነታቸው ጎልብቶ ጊዜያት ሲቆጠር ቁምነገርን አሰቡ። የሁለቱም ልብ በአንድ ጣራ ስር በትዳር አብሮ መኖርን ተመኘ ።ያሰቡት አልቀረም ።ጥንዶቹ ጋብቻ መስርተው ጎጆ ቀለሱ።
መሠረት ባለትዳር ሆናለች። ዛሬ እንደትናንቱ በቤተሰብ ጥላ አታድርም። አሁን ጭንቀቷ ለቤት ለጓዳዋ፣ለትዳሯ ሆኗል። ትዳር ይዞ ቤት መምራት ቀላል አይደለም፤ ኃላፊነትን ይጠይቃል። መታገስና መረጋጋትን ይፈልጋል። መሰረት ከእንግዲህ ልጅነት እንደሌለ አውቃለች። ይህን ማወቋ ትዳሯን ለማክበር ድርሻዋን ለመወጣት አግዟታል።
የቦንጋዋ ልጅ በአዲስ አበባ የጀመረችው ህይወት ከልጅነት እስከወጣትነት አዝልቋታል። ጎጆ ቀልሳ ቤቷን መምራት ከጀመረች በኋላም ተጨማሪ ኃላፊነቶች ሊያገኛት ግድ ብሏል። አራት አመታት ባስቆጠረው የትዳር ዓለም አንዲት ሴት ልጅ አፍርታለች።
መሠረት ልጇን አሳድጋ ለማስተማር፣ ቁምነገር አድርሳ ለመደሰት ታስባለች። እንደእናትነቷ ከእሷ የሚጠበቀውን ለማሟላትም ድካም አታውቅም። ለጎጆዋ መቆም፤ ለትዳሯ መቃናት ለፍቶ ማደር፣ ተግቶ መኖር ልማዷ ነው። እሷን ጨምሮ ቤተሰቦቿን ለማሳደር በሥራ እየደከመች ትገባለች።
የሥራ ዕድል…
አንድ አይነት የሥራ ፍላጎት ያላቸው እናቶች በየጊዜው ይገናኛሉ። በተገናኙ ቁጥር የሚወያዩት በጋራ ሠርቶ ስለማደር ነው። እናቶቹ በቅርቡ ባገኙት የመደራጀት ዕድል እኩል ሠርተው ለመጠቀም ጓጉተዋል። ፍላጎታቸው ተጣምሮ ፍሬ ይኖረው ዘንድ ይበጃል ያሉትን ሃሳብ ያነሳሉ። የተነሳው ሃሳብ በሌሎች ቃል ዳብሮ ሥራና ተግባር የሚሆንበት፣ እንጀራ የሚያስገኝበት ስልት ይቀመጣል። የወደፊቱ ሥራ ህጋዊ ሆኖ እንዲቀጥል ይበጃል የተባለው ሁሉ ተሟልቷል። ትኩረትና የዕለት ድካም በሚያሻው ውሎ የዕቃ አቅርቦትና የሰው ኃይል ተለይቷል። ከሚገኘው ገቢ የሚከፈለው ድርሻ ታውቆም እናቶቹ የሚጠቀሙበትና ነገን በተሻለ የሚቀጥሉበት ዕቅድ ተነድፏል።
መሠረት ባለትዳር ከሆነች ወዲህ ስለ ትምህርት ማሰብ፣ መጨነቅን ትታለች። አሁን ያለችበት ህይወት ጎጆዋን እንድታቀና ባልና ልጇን እንድታስብ የሚያስገድዳት ሆኗል። ቤተሰቦቿን አስተዳድራ በእጇ ገንዘብ ለመያዝም ይበጃል ባለችው አማራጭ ተገኝታለች።
ከምታውቃቸው ሴቶች ጋር በማህበር መደራጀቱን አልጠላችውም። በጋራ ሠርቶ በእኩል መካፈሉን ወዳዋለች። ከተደራጁት መሰሎቿ ጋር የምታገኘው ገቢ ነገን የተሻለ ለማድረግ፣ ልጇንም ለማስተማር ይጠቅማታል። የሴቶቹ ሃሳብ የእሷ ጭምር ሆኖ የሚጠበቅባትን አጠናቃ ከማህበሩ፣ ከመደራጀቱ ተቀላቅላለች።
በጋራ የተቋቋመው የሥራ ዕድል በተማሪዎች ምገባ ላይ ተመስርቷል። እናቶቹ ማልደው ለሚገኙት ተማሪዎች ቁርስና ምሳ ለማድረስ ተግተው ይውላሉ። በዚህ ስፍራ ‹‹የእከሌ ብቻ›› የሚባል ድርሻ የለም። በእኩል ሠርቶ በእኩል ለመጠቀም የጉልበቶች ኃይል በአንድ ይጣመራል።
ወፍ ሲንጫጫ ከትምህርት ቤቱ ግቢ የሚደርሱት እናቶች የሚቀድመውን ቁርስ ለማድረስ መባተላቸው ተለምዷል። የእነሱን እጅ ናፍቀው በባዶ ሆዳቸው የሚመጡ ተማሪዎችን መቅደም ይኖርባቸዋል። ማለዳ ከኩሽናው ገብተው ቁርስ ለማዘጋጀት፣ ትኩስ ሻይ አፍልቶ ለማቅረብ ጥድፊያ ቅልጥፍናው አይቀሬ ነው።
በዚህ ስፍራ በየቀኑ የበዛ እንጀራ ይጋገራል፤ ወጥ በትላልቅ ድስቶች ትኩስ ወጥ ይሰራል፣ ዳቦ ከሻይ ጋር ይቀርባል። ገበያ ሄዶ የጎደለን መሸመት፣ የሚያስፈልገውን ማቅረብ የሁሉም ሴቶች ድርሻ ነው። ምግቡ በጊዜው ተዘጋጅቶ ለሚገባቸው እንዲደርሰ፣ በየቀኑ የጉልበት ዋጋ ይከፈላል።
ይህን የሚያስተውሉ ብዙዎች ትናንት ምግብ ያልነበራቸው፣ ምሳ የማይቋጠርላቸውን ተማሪዎች በምግብ እጦት ራሳቸውን ስተው ይወድቁ ነበር። ዛሬ የልጆቻቸውን ጠግቦ መዋል የሚያውቁ ምስኪን እናቶች ስለምሳ መቋጠር አይጨነቁም። በሆነላቸው በረከት ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ። አሁን የነመሠረት ተደራጅቶ መሥራት መልካም ውጤት አስገኝቷል። ዛሬ ምግብን የሚሹ ተማሪዎች ከእናቶች እጅና ጓዳ ለምለም እንጀራ ይቆረስላቸዋል።
ሁለቱ ሴቶች…
መሠረት በምትኖርበት ሰፈር ማህበራዊ ህይወትን ለምዳለች፤ በአካባቢው ደስታና ሀዘን ሲያጋጥም ተለይታ አታውቅም።ከለቅሶ ከሠርጉ፣ ከዕድር ከማህበሩ ተሳታፊ ናት። ባለቤቷና አንድ ዘመዱ አልፎ አልፎ በነዚህ ቦታዎች ይገናኛሉ። ሚስቶቻቸውም ቢሆኑ ከእነሱ ለመምሰል አብረዋቸው አይጠፉም።
መሠረት ወይዘሮ ህይወት የተባለችው የሰፈሯ ሴት የባሏ ዘመድ ሚስት መሆኗን ታውቃለች። ይህን ማወቋ ለቅርበቷ ምክንያት ሆኖ ትግባባታለች። ሁለቱ ሴቶች በየአጋጣሚው ሲገናኙ ስለቤተሰቦቻቸው ያወጋሉ፣ ስለልጆቻቸው ይወያያሉ፣ ስለ ባሎቻቸው ያወራሉ።
ሴቶቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንጀራ አገናኝቷቸዋል። ህይወት እነመሠረት የሚሰሩበት የመንግሥት ትምህርት ቤት ምገባ ላይ ተሳታፊ መሆን ጀምራለች። መሠረት ካለችበት የሥራ ውሎም ተመድባለች።ኃላፊነት ያለበት የሥራ ክፍፍል ሰዓት ማክበርን፣ በጊዜ ሠርቶ ማጠናቀቅን ይጠይቃል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ክፍተቱ ቢሰፋ ተወቃሽነቱ ይበዛል፤ የሥራ ጫናው ያይላል።
ህዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም
በዚህ ቀን ማለዳ ሁሉም ሴቶች ከሥራ ቦታቸው ተገኝተዋል። ይህ አይነቱ ልማድ በማህበር ለተደራጁት እናቶች አዲስ አይደለም። ሁሌም ተማሪዎች በግቢው ከመድረሳቸው በፊት ቁርሳቸውን ለማቅረብ ይጣደፋሉ። መመገቢያዎችን አሰናድተው ልጆቹን ለምገባው ያዘጋጃሉ።
የአባዶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአንዲህ አይነቱ ትዕይንት ጥቂት አርፍዶ መደበኛ ትምህርቱን ይቀጥላል። መምህራን ከምገባው በኋላ ተማሪዎቻቸውን ለትምህርት ያዘጋጃሉ። ምግብ አቅራቢዎቹ የተበላበትን አንስተው ለምሳው ዝግጅት ኩሽና ይገባሉ።
ወይዘሮ ህይወት ዕለቱን በትምህርት ቤቱ የተገኘችው በማለዳው ሆኗል። ያለባትን የሥራ ጫና ስለምታውቅ ሰዓቷን ማክበር ግድ ብሏታል። በስፍራው ደርሳ ስራዋን ልትጀምር ስትዘጋጅ የሥራ አጋሯን በዓይኗ ፈለገች። አላገኘቻትም። የመሠረትን ስም ጠርታ ሌሎችን ጠየቀች። እንዳልመጣች ነገሯት። ተናደደች።
ህይወት እየበሸቀች፣ መሠረትን አሰበቻት። የመዘግየቷ ምክንያት አልገባሽ፣ አልዋጥልሽ አላት። የአጋጣሚውን መፈጠር ስታሰላው ሆን ብላ እንዳደረገችው ተሰማት። ሥራና ተራዋን እያወቀች ለእሷ ብቻ መተው ግዴለሽነት፣ ራስ ወዳድነት ነው ስትል አሰበች። ንዴቷ ሳይበርድ፣ ኩርፊያው ሳይለቃት መሠረት እሷ ካለችበት ደረሰች። ህይወት በክፉ ዓይን እያየች፣ ከአንገት በላይ ተቀበለቻት።
ጥቂት ቆይቶ ሁለቱ ማውራት ጀመሩ። ንግግራቸው ጤናማ አልሆነም። መተማመን መግባባት አልቻሉም፤ ህይወት ማርፈዷን እያነሳች ወቀሳ ጀመረች። መሠረት ስህተቷን አምና ይቅርታ ጠየቀች። ለህይወት ይህ ቃል ብቻ በቂ አልሆነም። መሠረት ካለችበት ደርሳ ጉዳዩን ደገመችላት። ጥቂት ተ ነጋግረው በዝምታ ቆዩ።
ጊዜው ረፍዶ ሦስት ሰዓት እንዳለፈ ጉዳዩ በድጋሚ ተነሳ። ይህኔ ህይወት በምሬት መሠረት ላይ ጮኸች። መግባባት መስማማት አልቻሉም። ሁኔታቸውን ያስተዋሉ ሌሎች መሀል ገብተው ሊያስማሙ ሊያግባቡ ሞከሩ። የሁለቱም ስሜት በጎ አልሆነም። ክፉ ደግ መነጋገር፣ ስድብ መለዋወጥ ጀመሩ።
ጠባቸው አይሎ ጭቅጭቁ ሲቀጥል መሠረት የህይወትን ወረኛነት እያነሳች መሳደብ ጀመረች። ይህ ባህርይዋ በሰፈር የምትታወቅበት፣ መለያ እንደሆነ በመጥቀስም ሌሎች እንዲሰሙ፣ እንዲታዘቡ ሞከረች። ይህ ድርጊቷ በቦታው 15 ቀናትን ብቻ ላስቆጠረችው ህይወት ውርደት ሆኖ ተሰማት። ከእሷ ስድብ አልፎ ስሟ በክፉ መነሳቱ ይበልጥ አናደዳት፣ አበሸቃት።
ጭቅጭቁን ደጋግመው የሰሙ የሥራ ባልደረቦች ሁለቱንም ለመገሰጽ ካሉበት ተነሱ። በስራ ሰዓት መነጋገር አግባብ ያለመሆኑንም ተናገሩ፤ አስጠነቀቁም። የሰማቸው አልነበረም። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ህይወት ለሰራተኞቹ ቁርስ ለማዘጋጀት ወደ ውስጥ ዘለቀች። መሠረት በበኩሏ የሚከተፈውን ሽንኩርት ይዛ ወደሥራዋ ገባች።
ይህ ከሆነ አፍታ በኋላ ከቀድሞ በባሰ ጭቅጭቁ ጨመረ። ዝምታው መሰበሩን ያዩ ሴቶች እየሮጡ ደረሱ። ህይወት የምትሰራበት የከሰል ማንደጃ ከእነእሳቱ ተገልብጧል። ሁለቱም ይጯጯኻሉ። ህይወት በንዴት ‹‹ተይኝ፣ተይኝ›› እያለች ተጠግታታለች። መሠረት በእጇ ያለውን ቢላዋ ሳትለቅ ቀርባታለች። መሀል ገብተው ማገላገል የሞከሩ አልቻሉም። የሴቶቹ ግጭት ከበፊቱ አይሏል። ስድብ ጩኸቱ በርትቷል።
ጥቂት ቆይቶ መሠረት በህይወት አንገት ላይ የእጇን ቢላዋ ስትሰካው ታየ። ወዲያው ከህይወት አንገት ትኩስ ደም ተንዠቀዠቀ። ሁኔታው ያስደነገጣቸው ሌሎች እንዲመጡላቸው የድረሱልን ጩኸት አሰሙ። ከደቂቃዎች በፊት በግልግል የተለያዩት ሴቶች መጨረሻው አላማረም። አንዷ አጥቂ ሌላዋ ተጠቂ ሆነዋል።
ያዩትን እውነት ያላመኑት እናቶች ከመሬት የወደቀችውን ህይወት በማንሳት ለመርዳት ሞከሩ። ሁኔታው አላማራቸውም። አንገቷ ላይ የደረሰባት ጉዳት እያዳከማት ነው። ሁሉም ተረባርበው ነፍሷን ለማትረፍ ተጣደፉ። ሌሎች የግቢው ሠራተኞች አገዟቸው።
መሠረት በሆነው ሁሉ ተደናግጣለች። በትዕግስት ማጣት በፈጸመችው ድርጊት ጸጸት ገብቷታል። በጭንቀት ከወዲያ ወዲህ ማለቷን ያስተዋሉ የትም እንዳትሄድ ከቦታው እንዳትወጣ አግተዋታል። የታዘዘችውን ከማድረግ ሌላ ምርጫ አልነበራትም።
ተጎጂዋን ደም እየፈሰሳት ከጤና ጣቢያው ያደረሱ የመሠረትን ጉዳይ አልዘነጉም። ካለችበት ይዘው ለፖሊስ ጣቢያ አደረሱ። ተጠርጣሪዋ ከጣቢያው ደርሳ ቃሏን መስጠት ጀመረች። በስፍራው እንዳለች የወይዘሮዋ ሕይወት ማለፉ ተሰማ።
ይህን ያወቀችው መሠረት የቀደመ ግንኙነታቸውን እያሰበች ይበልጥ ተፀፀተች። ቤተሰብ መሆናቸውን እያስታወሰች ተከዘች፣ አንገቷን ደፋች። መርማሪ ረዳት ኢንስፔክተር በለጡ አለነ መዝገብ ቁጥር 695/12 ቃሏን ሲመዘግቡ የሆነውን ሁሉ አልደበቀችም። በንዴት ተነሳስታ ለህይወት ሞት ምክንያት መሆኗ እንዳሳዘናት፣ እንዳስደነገጣት ተናገረች።
ውሳኔ…
ሚያዚያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ መሠረት አበበ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በችሎቱ ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሽዋ ወንጀሉን መፈጸሟን አረጋግጦም ጥፋተኝነቷን አስረድቷል። በዕለቱ በሰጠው የፍርድ ውሳኔም ወይዘሮዋ እጇ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ አንድ ዓመት ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ሲል በይኗል።
መልካም ስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014