
በመስኮቱ በኩል እሳታማ ጀምበር ትታየዋለች፤ በአፍላ የጎህ ጸዳል የተከበበች፡፡ ከእንቅልፉ ሲነሳ ደስ እያለው ነበር፤ ኮቱን ሲለብስ፣ ከረቫቱን ሲያደርግ፣ ቁርሱን ሲበላ ደስ እያለው ነበር፡፡ ከቀኖች ሁሉ ጠዋት ደስ ይለዋል፡፡
ቢሮው ሲገባ ሮማን የለችም፤ ዛሬ ገና ቀድሟት መግባቱ ነው፡፡ ጠዋቱን ከሚያሳምሩለት ነገሮች ውስጥ አንዱ ሮማን ናት፡፡ ሳቋ፣ መአዛዋ፡፡ ቢሮው ውስጥ እሷ መኖሯን ሲያስብ፣ ዓለም ላይ እሷ እንዳለች ሲያውቅ ይባረካል፡፡ በምትቀባው ሽቶ፣ በምትለብሳቸው ጽዱ ልብሶቿ ሀሴት ያደርጋል፡፡
አይኖቹን በመስተዋቱ ውስጥ ሲወረውር የአንገት ስከርቧን አየው፡፡ ቀድሟት ሳይሆን ቀድማው እንደ ገባች አሁን ተረዳ፡፡ እምነቷ ይገርመዋል፤ ጽናቷ፣ ለሥራ ያላት ፍቅር ያስደንቀዋል፡፡ ሀገራችን ላይ የእሷን አይነት መቶ ጠንካራ ሰዎች ቢኖሩ ሲል ሁሌ ያስባል፡፡
ጥንካሬዋ ሁሌም እምነቱን ይሽርበታል፡፡ ተነሳሽነቷ ሁሌም እውቀቱን ይንድበታል፡፡ ከሁሉም በኋላ ወንዶች በሀይል ይቺን ዓለም የራሳቸው አደረጉ እንጂ ዓለም የሴቶች ትሆን ነበር ሲል ይደመድማል፡፡ ለምንም ነገር ምስክሩ ናት፡፡ ታስደንቀዋለች…፡፡
በህይወቱ ውስጥ ሶስት ሴቶችን ያውቃል። ከነዚህ ሶስት ሴቶች ጋር እምነትን፣ እውነትን፣ ጽናትን ተቋድሷል፡፡ ሊዲያ የህይወቱ አልፋ ናት። በመጀመሪያነት ውስጥ ያለውን ገናና እውነት፣ ያለውን ነፍሳዊ ስቃይና ደስታ የሰጠችው፣ ከመኝታው ሲነሳ እንደሚያያት የጧት ጣይ ፈክታና ደምቃ የሚያያት የነፍሱ ጠል፡፡ በአሁናዊ የህይወቱ አብራክ ውስጥ እንደሚያየው የሮማን ፈገግታና ሳቅ የሚያስታውሰው፡፡ አስራ ስምንት አመቱን ባከበረ በማግስቱ ነው መንገድ ላይ አግኝታ ካልተዋወኩህ ሞቼ እገኛለሁ ብላ የተዋወቀችው፡፡
ትውውቃቸውን ወደ ፍቅር ለመቀየር ሳምንት ነበር የፈጀባት፡፡ ያኔ እሷ አስራ ስድስት እሱ አስራ ስምንት አመታቸው ነበር፡፡ ከስድስት ወር በኋላ ተለያዩ፡፡ ሊዲያ አባቷ እንግሊዛዊ በመሆኑ ትታው ለንደን ገባች፡፡
ከሊዲያ ጋር ያሳለፋቸው እነዛ ስድስት ወራት በአስራ ስምንት አመታት ውስጥ ከእናቱ እቅፍ ቀጥሎ ያገኛቸው የበረከት ወራቶቹ ነበሩ። እነዛ ስድስት ወራት የህይወቱ ባለቀለም ንጋት ነበሩ፡፡ የሚያፈቅሩትን ሰው እያሰቡ ከእንቅልፍ እንደመንቃትና ወደ መኝታ እንደመሄድ ደስታ እንደሌለ ያወቀው ያኔ ነው፤ በሊዲያ ፍቅር፡፡
ዛሬም ድረስ በነፍሱ ፍኖት ስር አለች፡፡ ዛሬም ድረስ በልቡ ምድጃ ላይ ፍቅሯና ትዝታዋ ይንቦገቦጋል፡፡ ዛሬም ድረስ ያልጠፋ፣ ዛሬም ድረስ ያልረሳውን እውነት ሰጥታው፣ በምንም የማያገኘውን የትዝታ ረመጥ በህይወቱ ላይ ትታ፣ ነፍሱን በፍቅር እሳት ለኩሳ ላትመለስ ለንደን ገባች፡፡ እንደ እሷና እሱ ምድር ላይ ረጅም አመታትን በፍቅር ያሳለፈ ያለ አልመስልህ ብሎት ነበር፡፡
ሁለተኛዋ ሴት ራሄል ናት፡፡ ራሄልን የትዝታው አንድ አካል አድርጎ መጥራቱ ያስቆጨዋል፡፡ ጭራሽ በትናንቱ ውስጥ እሷን ማወቁ ያበሳጨዋል፡፡ ብዙ ነገሯ ሴጣናዊ ነው፡፡ የሊዲያን እውነት፣ የሊዲያን ፍቅር ልታረክስ ወደ ህይወቱ የመጣች እንጂ ልትባርከው የመጣች አልነበረችም፡፡
ፍቅርን ሳይሆን ራስ ወዳድነትን ይዛ ነው የመጣችው፡፡ ከራሄል ጋር መከራ እንጂ ትዝታ የለውም፡፡ በህይወቱ እሷን በማወቁ ይቆጫል፡፡ በህይወቱ እሷን በመቅረቡ ይከፋል፡፡ አብረው የቆዩት ለዘጠኝ ወራት ነው፡፡ በነዚህ ወራት ውስጥ ሊዲያዊ ፍቅሩን ገላ አውሬ አድርጋው ነበር፡፡ በአንድ የተባረከ ቀን ተለያዩ፤ ከእሷ ጋር የተለያዩበትን ቀን ሊዲያን እንዳወቀበት ቀን አመት እየጠበቀ ለድሀ በመመጽወት ያከብረዋል፡፡
ከራሄል ጋር በተለያዩ በአመቱ ብስራት ከምትባል ሴት ጋር ተዋወቀ፡፡ ትውውቃቸው ይገርመዋል፤ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ላይ ከራሄል ጋር የተለያዩበትን ቀን አስታውሶ ለአንድ ነዳያን ፍራንክ ሰጥቶ ሲመለስ በእጇ ቡራኬ ይዛ ለመምዕኑ የምታድል አንዲት ሴት ይመለከታል፡፡ ከቡራኬው ሊወስድ ወደእሷ ሲሄድ ቡራኬው አልቋል፤ ከደቂቃዎች በኋላ ይቺው ሴት ቡራኬ ልትሰጠው ወደ እሱ ስትመጣ አየ፡፡ ከምስጋና ጋር ተቀበላት፤ በዛው ተዋወቁ፡፡
የፈጣሪ ሃሳብ ይገርመዋል፡፡ ፈጣሪ የት ጋ፣ ከማን ጋር፣ እንዴትና መቼ እንደጣፈን አናውቅም፤ ብስራት የመጨረሻው እንድትሆን ፈልጎ ነበር ግን አልሆነችም፤ በተዋወቁ በአመቱ ተጋቡ፣ በተጋቡ በሁለት አመታቸው ተለያዩ፤ መጥፎ መለያየት፡፡
የሚሰራበት መስሪያ ቤት ልደት የምትባለዋ ደግሞ ወደደችው፡፡ አሁን ላይ ሲያስብ ልደት ከሳጥናኤልና ከራሄል ቀጥሎ መጥፎዋ ትመስለዋለች፡፡ እሱ ሳያውቅ ስለሁለቱም መጥፎ ነገር ለብስራት ይደርሳት ጀመር። መጨረሻ ላይ ብስራት ሳትነግረው ጥላው ጠፋች፡፡ ከብስራት ጋር የነበረው ታሪክ ይሄ ነው፡፡
ሊዲያ በተነሳች ቁጥር ልጅነቱ፣ ብስራት በተነሳች ቁጥር ልደት ትዝ ይሉታል፤ መጥፎ ትዝታ፡፡ በህይወቱ ውስጥ ሊያስታውሳት የማይፈልጋት አንድ ሴት ልደት ናት፤ ሊረሳቸው የማይችላቸው ሁለት ነፍሶች ደግሞ ሊዲያና ብስራት፡፡
ብስራት እንደ ስሟ ለህይወቱ ብስራት ነበረች፡፡ ከደጀ ሰላም የመለኮት ሀይል ጋር የሚያመሳስላቸው የሆነ ነገር ያላት ይመስለዋል፡፡ በዘላለማት ውስጥ የማይረሱ ዳግማዊ ሊዲያ ይላታል፡፡ አንዳንዴ ሌዲያ በሌላ ሴት ነፍስ ውስጥ ተደብቃ ፍቅረኛው የሆነች ይመስለዋል፡፡ ብዙ ነገሯ መላዕካዊ ነው፡፡
ብስራትን ሳይጨርሳት ሮማንን በመስተዋቱ ውስጥ አያት…፡፡ ከመኝታው ሲነሳ እንደሚያያት የንጋት ጀምበር ተውባ፡፡ በመስተዋቱ ውስጥ ሲያያት ለእይታ ሙዚየም የተቀመጠች ቀይ እንቁ መሰለችው። ወደዳት፤ ከወደዳት በላይ፡፡ አሰባት፤ ካሰባት በላይ፡፡ በህይወቱ ውስጥ አብሮት እንዲቆይ የሚሻው አንድ እውነት የእሷ እውነት ነው፡፡ ፍቅሯና ሴትነቷ፡፡ መልካምነቷና ትህትናዋ፡፡ ሮማንን አፍቅሯታል፤ እንደ ሊዲያና እንደ ብስራት፡፡
የሚገፋውን አያውቅም፤ ከመቀመጫው ተነስቶ ወደ በሩ ተራመደ፡፡ እግሮቹ ወደ እሷ እየወሰዱት ከመንገድ አገኛቸው፡፡
ባቀረቀረበት የሆነ ደስ የሚል ነገር አወደው፡፡ ቀና ሲል ከፊት ለፊቱ አያት፤ ወደ እሱ እየመጣች፡፡ ነፍሱ በደስታ በልቡ ውስጥ ሰከረች፡፡ ወደ ህይወቱ እንድትገባ በሚፈልጋት አራተኛዋ ሴት፤ ሮማን፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2014