የወጣትነት ዕድሜ ክልል ተብሎ የሚፈረጀው እንደየአገሩ የወጣት ፖሊሲና ተጨባጭ ሁኔታ ይለያያል። የእኛ አገሩ ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ እንደሚያመለክተው የወጣትነት ዕድሜ ክልል ነው የሚባለው ከ15 እስከ 29 ያለ ዕድሜ ነው። ሆኖም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በፈረሙትና አገራችን ባላፀደቀችው የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር መሠረት ወጣት የሚያሰኘው የዕድሜ ክልል ከ15 እስከ 35 ያለው ዕድሜ ነው። ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ኢትዮጵያም በቅርቡ በፈረመችው የአፍሪካ ቻርተር መሠረት የወጣት ዕድሜ ክልል እስከ 35 እንዲሆን ወስናለች።
ይሄን ለመንደርደርያ ያህል አነሣነው እንጂ ዋንኛው የዛሬ አጀንዳችን በዚህ ዕድሜ ክልል የሚገኘው ወጣት በክረምቱ ወራት ሲያደርገው በቆየው፤ በተያዘው በጀት ዓመት በጋ ወራትም እያደረገ ባለውና ሊያደርገው ባቀደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ተሣትፎ ጉዳይ ላይ ነው የሚያጠነጥነው። የዳይሬክቶሬቱ መረጃ ከሦስት ዓመት በፊት የተደረገ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ጥናት ተንተርሶ እንዳመለከተው ታድያ በአገራችን ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ያሉ 32.1 ሚሊዮን ወጣቶች ይገኛሉ። እነዚህ ወጣቶች ዋነኛ የለውጥ ተዋናይ ናቸው።
የትኩስ ጉልበትና ዕምቅ ኃይል ምንጭ በመሆናቸው በአገር ልማትና ዕድገት ላይ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። እናም በዚህ ጽሑፍ ወጣቶቹ አወንታዊ የአገር ልማት ዙሪያ ያበረከቱትንና እያበረከቱት ያለውን እንዲሁም ያበረክቱታል ተብሎ የሚጠበቀውን አስተዋጽኦ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ማቲያስ አሰፋን አነጋግረን ያገኘነውን እናስቃኛችኋለን።
በአንፃሩም ችግር ሲከሰት ቀዳሚ ተጠቂ ወጣቶች ናቸው። በአገር ውስጥ ቀውስ በመፍጠርም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህ አኳያ ሊሰማሩባቸው ከሚችሉ አሉታዊ አፍራሽ ድርጊቶች እንዲታቀቡ የሚያስችል ግንዛቤ በማስጨበጥ፤ በአጠቃላይም አሉታዊውን የወጣቱን ዕምቅ ኃይል ወደ አወንታዊው ለውጦ በመጠቀም እንቅስቃሴ አገራቸውን ከውስጥና ከውጭ ኃይሎች ጫና እንዲታደጉ በማድረግ በኩል እየተሠራ ያለውንም እንዲሁ ልናካፍላችሁ ወድደናል።
ዳይሬክተሩ አቶ ማቲያስ አሰፋ እንደገለፁልን የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደ ተቋም የበጋና የክረምት ተብሎ በመከፈል በሁለት መልኩ ይካሄዳል። የሚካሄደው 70 በ30 በሚል አሠራር (ወንዶችን 70 በመቶ ሴቶችን ደግሞ 30 በመቶ በማሳተፍ) ሲሆን በአሁኑ ወቅት ይሄን አሠራር መሠረት በማድረግ በሁለቱም አገልግሎቶች እንደ አገር በርካታ ወጣቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ። ለአብነት በቅርቡ ተካሂዶ በነበረው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ14 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ተሳትፈዋል። ወጣቶቹ ተሳትፎ ያደረጉት አንድም ከድህነት ቅነሳ፤ ሁለትም ለተቸገሩ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ በሚያስችል የማህበረሰብ እገዛ ነበር።
በተለይ በትልልቅ ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ወጣቶች ሀብት በማሰባሰብና ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማገዝ ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። የአረጋውያንን ቤት በማደስ፣ ችግኝ በመትከል፣ በከተሞች ፅዳትና ውበት በመሳተፍ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በግብርና ሥራዎች፣ የመንገድ ትራፊክ አገልግሎት እንዲሁም በእረፍት ላይ የነበሩ ተማሪዎች ትምህርት ቤት በሚከፈትበት በ2014 ትምህርት ዘመን ትምህርቱ እንዳይከብዳቸውና ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው የማጠናከሪያ ትምህርት በመሥጠት፣ ከሰላምና ደህንነት ጋር ተያይዞ ሰላምን በማስጠበቁ ረገድ፣ በጤናው ዘርፍ በቀይ መስቀል አገልግሎቶች በመሣተፍና ደም በመለገስ ያበረከቱት ይጠቀሳል።
ከእነዚህ አገልግሎቶች አንዳንዶቹ ለምሳሌ ደም ልገሳ፣ የአካባቢን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ፣ በግብርና ሥራው ምርት ስብሰባና በሌሎች እገዛ ማድረግ በበጋው ወቅትም ወጣቶቹ አጠናክረው የቀጠሏቸው ተግባራት መሆናቸውን አቶ ማቲያስ ነግረውናል።
አቶ ማቲያስ እንደገለፁልን ዳይሬክቶሬቱ በበጋ ወራት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በመጠቀም ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን መንከባከብና መደገፍ ነው። በበጀት ዓመቱ በዚህ በኩል ሰፋፊ ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዶም ወደ ሥራ ተገብቷል።
ሁሉም ማህበረሰብ በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች እንደየአቅሙ ድጋፍ እንዲያደርግ የሚያስችሉ ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄዎችን ለማድረግም ታስቦ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል። በተጨማሪም በደም ልገሣ፣ በሰብል መሰብሰብ ሂደት፣ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ባሉ የተለያዩ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ዙሪያም ንቅናቄውን ለማድረግና በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጅት ተደርጓል።
‹‹በብዙ የአገራችን ክፍሎች እንደምናየው ብዙ ወጣቶች አሉ›› የሚሉት አቶ ማቲያስ ከሦስት ዓመት በፊት የተደረገ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ ጥናት እንደሚያመለክተውም በአገራችን ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ያሉ 32 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚገኙም ይናገራሉ። የእነዚህን ወጣቶች ተሳትፎ በተመለከተ ታድያ አቶ ማቲያስ እንዳብራሩልን ወጣቱ የለውጥ ዋንኛ ተዋናይ እንደሆነ ሁሉ ችግር ሲከሰትም ቀዳሚ ተጠቂ መሆኑ ይታወቃል።
አገር በመለወጡም ሆነ በአገር ውስጥ ቀውስ በመፍጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በበጀት ዓመቱ ይሄ ወጣት አቅሙን ተጠቅሞ በአግባቡ በበጎ ተግባራት እንዲሳተፍ የሚያስችሉ ሥራዎችም ይሰራሉ።
ከሕግ ማስከበር ጋር ተያይዞ አገራችን ሳትፈልግ የገባችበት ጦርነት መኖሩን ያስታወሱት አቶ ማቲያስ በዚህ ሂደት በዋናነት ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው በመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ ፋኖ በሚባለውና በሌሎች አደረጃጀቶች የታቀፈው ወጣት መሆኑንም ይናገራሉ። ይሄ ወጣት በአሁኑ ወቅት የአገሩን ዳር ድንበር በማስከበሩ ረገድ ውድ ሕይወቱን ከመገበር ጀምሮ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መገኘቱንም ያወሳሉ።
ከዚሁ ጎን ለጎንም አንዳንድ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ለውጡን ወደ ኋላ ለመመለስና ለመቀልበስ ጥረት በሚያደርጉ የተለያዩ የሽብር ድርጊቶች የሚሳተፉ ወጣቶች መኖራቸውንም ይጠቁማሉ። በመሆኑም ይሄ ለእኩይ የሽብር ተግባር ዓላማ እየዋለ ያለ ዕምቅ የወጣቱ ኃይል ለአገር ልማት እንዲውል የማድረግ ሥራዎችም ይሠራሉ።
ወጣቱ አገርን ከሚጎዱ አሉታዊ አፍራሽ ድርጊቶች ራሱን እንዲያርቅ እና በአገር ግንባታና በትውልድ ቅብብሎሽ ያለበትን የቀደሙ እናትና አባቱን አደራና ኃላፊነት እንዲወጣ እንዲሁም እምቅ ኃይሉን ለአወንታዊ ጉዳዮች እንዲጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችም ይከናወናሉ።
በአጠቃላይ ትልቅ ትኩረት ተደርጎ አወንታዊ የወጣቶች ልማት ላይ ይሰራል። አሉታዊ አፍራሽ ተግባራትን ወደ አዎንታዊው ልማት ቀይሮ የመጠቀሙ ጉዳይ ትኩረት ይሰጠዋል። እንደ አቶ ማቲያስ አሉታዊና አፍራሽ ተግባራትን ወደ አዎንታዊው ለውጦ የመጠቀሙ ጉዳይ አሁን ላይ ምዕራባውያኑና የአገር ውስጥ የጥፋት ኃይሎች በአገራችን ላይ እያደረጉት ካለው ከፍተኛ ጫና አኳያ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ስለሚያስፈልግ ነው። ምክንያቱም አሁን ላይ የውስጥ የጥፋት ኃይሎች በገዛ አገራቸው ላይ በይፋ ጦርነት አውጀው እየወጓት ይገኛሉ።
በዚህ ሳያበቁም በምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም በአፍሪካ ያላትን መልካም ስምና ተደማጭነት የማሳጣት የሠራቻቸውንና እየሠራችው ያለውን በጎ ሥራዎች ከምንም በላይ የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌትነቷን የማጠልሸት፣ በኢኮኖሚ የማዳከም፣ ቀውስን የመፍጠር፤ ቀውስን እየፈጠሩም በአገራችን ላይ አለመረጋጋት እንዲኖር የማድረግ ሥራዎችን እየሠሩ ነው።
በተለይ በማህበራዊና በሌሎች ሚዲያዎች መረጃዎችን በማዛባት፣ መረጃዎች በአላስፈላጊ መንገድ እንዲሄድ እንዲሁም በማህበረሰቡ ዘንድ መጠራጠርና የእርስ በእርስ ግጭት እንዲኖር እያደረጉ ይገኛሉ። አገርን ለማዳከም፣ ኢኮኖሚውን ለመጉዳት፣ ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚያደርጉት ጥረት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ወጣቱ ይሄን በተገቢው መንገድ መገንዘብ አለበት። ይሄን ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ አገራችን ከሕግ ማስከበር ጋር ተያይዞ ተገድዳ የገባችበት ጦርነት መኖሩንም መዘንጋት የለበትም።
የውጭ ኃይሎች ጫና ከዚህ ጋር ሲደመር በአገር ደህንነትና ህልውና ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ከፍተኛ አደጋ ማሰብም ይገባዋል። እንደ አቶ ማቲያስ በእርግጥ በዚህ ሂደት በመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ ፋኖ በሚባለውና በሌሎች አደረጃጀቶች ታቅፎ በዋናነት ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው ወጣቱ ነው። ይሄ ወጣት በአሁኑ ወቅት የአገሩን ዳር ድንበር በማስከበሩ ረገድ ውድ ሕይወቱን ከመገበር ጀምሮ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጎን አንዳንድ ወጣቶች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በጥፋት ኃይሎች የሽብር ተግባራት የሚሳተፉበትና የውጭ ኃይሎችን ጫና የማይረዱበት ሁኔታ አለ። በተለይ በአገራችን ላይ በማህበራዊው ሚዲያ በኩል የውስጥ የጥፋት ኃይሎች የሚፈፅሙትን እኩይ ተግባርና የውጭ ኃይሎች የሚያሳድሩትን ጫና በማራገብ እንዲሁም አገራችንንና ሕዝቦቿን በሚጎዱ ተግባራት የሚሳተፉም አንዳንድ ወጣቶች አሉ።
የውጭዎቹ ኃይሎች (ምዕራባውያኑ) ይሄን የውስጥ ኃይሎች እኩይ ተግባር ሲያበረታቱት በግልፅ እየታየ ነው። ሽብርተኞችን በመደገፍ ተግባር ተሰማርተዋል። ለውስጥ የጥፋት ኃይሎች ደጀንም ሆነዋቸዋል። በአገራችን ላይ ጤናማ እድገት እንዳይኖር፣ አገራችን ወደ ኋላ እንድትቀር፣ የእነሱ ተመጽዋች እንድትሆንና የእነሱን እጅ ብቻ ጠብቃ እንድትኖር የሚያደርጉ የውስጥ ኃይሎች ተግባራት ሁሉ እየደገፉ ይገኛሉ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ከዓለም አቀፍ ሕግና መርህ ባፈነገጠ መንገድ አገራችን ከ20 ዓመታት በፊት ከአሜሪካ ጋር ያደረገችውን ነፃ ንግድ ስምምነት የመሰረዝ ማስፈራሪያ እያደረገ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ መርህ ለዓለም ሰላምና ደህንነት ይሠራል በሚል ብዙዎች ተስፋ የሚጥሉበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር የዚሁ ጣልቃ ገብነት ማስፈፀሚያ የመሆኑ አዝማሚያ ታይቷል። የተመሠረተበትን አላማና የሚገዛበትን ሕግና ሥርዓት በሚፈታተን መልኩ ለ10 ጊዜ ስብሰባዎችን ጠርቷል። የአውሮፓ ኅብረትም በተመሳሳይ መንገድ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ጫናዎች ለመፍጠር በስፋት እየሰራ ይገኛል።
ወጣቶች ይሄን መረዳት አለባቸው። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በሌሎች መንገዶች ተግባሩን ከማበረታታት መቆጠብም ይኖርባቸዋል። ይልቁንም ጫናዎቹ በአገራችን ላይ እየፈጠሩ ያሉትን ቀውሶች ድምፃቸውን በአንድነት በማሰማት ለዓለም ማህበረሰብ ማሳወቅ አለባቸው። ማህበራዊ ሚዲያና ሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ለምን፣ መቼና እንዴት መጠቀም አለብኝ በማለት ራሳቸውን ጠይቀው መጠቀምና አጠቃቀማቸውንም ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን በሚችል መልኩ ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል።
እንደ ቀደሙት አባቶቻችን በአንድነት ቆመው ጫናው ከነፃነታችንና ከሉዓላዊነታችን አይበልጥብንም ሊሏቸው ይገባል። በአንድ ድምፅ በየትኛውም ዓይነት ጫናና ተፅዕኖ ህልውናችንን አንሸጥም ሉዓላዊነታችንን አሳልፈን አንሰጥም ሊሉ ይገባል፤ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማሰማትም ይኖርባቸዋል።
ወጣቶች በአገር ጉዳይ በምንም ነገር የማንደራደር እና አገራችንን አሳልፈን የማንሰጥ መሆናችንንም ከቃላት ባለፈ በተጨባጭ በተግባር ማሳየት መቻል አለብን። በውስጥ ተላላኪዎች አማካኝነት በህልውናችን በሉዓላዊነታችን የሚፈጠሩ ጫናዎችን በተባበረ ክንድ ተቀናጅተን በመንቀሳቀስ መቀልበስ ያስፈልገናል።
አገርን ከሚጎዱ አሉታዊ አፍራሽ ድርጊቶች ራሳችንን ማራቅ ይኖርብናል። ሁላችንም በአገር ግንባታና በትውልድ ቅብብሎሽ ያለብንን ኃላፊነት መወጣትም ግድ ይለናል። የአገር ደህንነት ላይ የተጋረጠው አደጋ ገፍቶ ቢመጣ ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍል ለመመከት ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ አንዱ የቤት ሥራቸው ሊሆን ይገባል።
በመጨረሻም ወጣቱ በክረምት ወራት የሠራቸውን በጎ ተግባራት አጠናክሮ በበጋ ወራትም የሚጠበቅበትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይዞ ከምንም በላይ ለአገሩ ደህንነት፣ ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ተሳትፎ እንዲያደርግ በማሳሰብ ተሰናበትን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2014