ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን አስተናግዳለች፤ እያስተናገደችም ትገኛለች። እነዚህ አጋጣሚዎች ደግሞ ዜጎችን ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች የሚያጋልጡ ናቸው። ይህም ሆኖ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ላይ የተመሰረተውና አብሮ የኖረው የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል በርካቶችን ለከፋ ችግር ሲዳረግ ቆይቷል። እየዳረገም ይገኛል። ይህም ሆኖ ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ሀብት ንበረታቸውን ያጡ ጥሪታቸው የወደመባቸው ሁሉ በወገን ድጋፍ እንደ አዲስ ህይወታቸውን ለመጀመር በቅተዋል። ይህ በኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚከወን ለወገን ደራሽነት ከግለሰብ ጀምሮ የሚከናወን ቢሆንም በተባበረ መንገድ ሲሆን ደግሞ ውጤቱ አንጸባራቂ ይሆናል።
በዚህ መንገድ ለተቸገሩት ለመድረስ የሚሰሩ ሥራዎችን ከሚያስተባብሩት መካከል ደግሞ ነጃሺ የበጎ አድራጎት ድርጅት አንዱ ነው። ነጃሺ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሀገሪቱ በበርካታ ውጥረቶች ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ለችግር የተዳረጉ ወገኖችን አቅም በፈቀደ ዜጎችን በማስተባበር በመደገፍ ላይ ይገኛል። እኛም የነጃሺ በጎ አድራጎት ድርጅትን እንቅስቃሴ የድርጅቱን ቦርድ ዋና ጸሐፊ አቶ ኤልያስ ከድርን በማነጋገር እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
ድርጅቱን የመሰረቱት ግለሰቦች እንደ ማህበር ከመቆማቸው በፊት በግላቸው በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ የነበሩ ናቸው። ከመስራቾቹ መካከል ግንባር ቀደም የሆኑት የህክምና ባለሙያው ዶክተር ሰምሀል ነጻ ህክምናዎችን በመስጠት ለአቅመ ደካሞች ቤት ለቤት እየሄዱ በማከም ሲሰሩ ነበር። በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል ላይ ያሉት አቶ አዱኛ ሙጬ የወር ወጪ በማሰባሰብ ጎዳና የወጡ ሰዎችን የመመለስ ሥራ ሲሰሩ ነበር። እነዚህ ለምሳሌ ተነሱ እንጂ ዛሬ በአባልነት የተመዘገቡት በሙሉ በቅርብ ከሚያገኙዋቸው ጎረቤቶቻቸው ጀምሮ ለተቸገረ እጃቻው የማይታጠፍ ናቸው።
እነዚህ ልበ ቅኖችም በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ችግሮች ለመከራ የሚዳረጉ ዜጎችን ለመታደግ የሚደረጉ ድጋፎች ሲሰሩ የተገናኙ እንደመሆናቸው ስለሥራቸው መወያየት ይጀምራሉ። እናም የእነሱም ሆነ የሌሎች እንቅስቃሴ በተናጠል ከመሆን ይልቅ በተቀናጀ መልኩ ቢሆኑ የተሻለ ውጤታማ እንደሆንና ቀጣይነቱም የተረጋጋጠ ሊሆን እንደሚችል ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ። በዚህም መሰረት በ2012 ዓ.ም ነጃሺ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንደተቋም በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለመመስረት ይበቃሉ።
ድርጅቱ ነጃሺ የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚለውን ስያሜ የያዘው ኢትዮጵያ እንደትልቅ ምሳሌ ከምትወስድበት ታሪክ አንዱ ከመቻቻል ጋር በተያያዘ፤ ነቢዩ መሐመድ ባልደረቦችን ወደ ኢትዮጵያ ሲሰዱ ኢትዮጵያ በዘመኑ በነበሩት ንጉስ መቀበሏ ነው። ዛሬም በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለችግር የተዳረጉና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ለእኛ እንግዶቻችን ናቸው። በመሆኑም ያኔ እንደተቀበልናቸው ሁሉ ዛሬም ከጎናችን ሆነው የተቸገሩትን በፍቅርና በርህራሄ ልንቀበል ይገባል በሚል እሳቤ ነው።
በዚህ መልኩ በግለሰብ ደረጃ የጀመሩትን እንቅስቃሴ በተቀናጀ መልኩ በማከናወን ላይ እያሉም የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የታወጀው የቤት ውስጥ ቆይታ በርካቶችን ለከፋ ችግር ሊዳርግ እንደሚችል ይገነዘባሉ። በመሆኑም በወቅቱ የአዲስ አበባ የበጎ ፈቃድ አስተባባሪ የሆኑትን አቶ አብርሃምን ከንቲባ ቢሮ ድረስ በመሄድ ምን ማድረግ እንደሚችሉ በማነጋገር የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። በዚያ የጥድፊያ ወቅትም አርባ ሺ የሚደርሱ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተረጂዎች እንዳሉም ይነገራቸዋል። እነሱም ኡስታዝ አቡበከር አህመድን የፕሮጀክቱ የበላይ ጠባቂ በማድረግ ባደረጉት ጠንካራ እንቅስቃሴ በአስሩም ክፍለ ከተሞች አሉ የተባሉትንና ድጋፉ ያልተዳረሳቸውን የአርባ ሺውንም ዜጎች የአንድ ወር አስቤዛ ድጋፍ ለማቅረብ ይበቃሉ። ይህ ድጋፍም ለአንድ ቤተሰብ ሃያ አምስት ኪሎ ፉርኖ ዱቄት፤ አስር ኪሎ ሩዝ፤ አምስት ሌትር ዘይት፤ አስር ኪሎ መኮሮኒ፤ ሳኒታይዘር፤ ፈሳሽ ሳሙናና ማስክ ማዳረስ የተቻለበት ነበር።
በተመሳሳይ ወቅት በሌላ በኩል የአዋሽ ተፋሰስ ወንዝ ባስከተለው ጎርፍ በአፋር በመተሀራ በኦሮሚያ ዙሪያና እንዲሁም ሌላ ወንዝ ስልጤ አካባቢ በመሙላት በርካታ ጥፋቶችን አስከትሎ ነበር። ይህ ተፈጥሯዊ አደጋም በአካባቢው ያሉ አርሶና አርብቶ አደሮችን ከቀያቸው አፈናቅሏል ማሳዎቻቸውንም አውድሟል። በዚያን ወቅት ነጃሺ የበጎ አድራጎት ድርጅትም በአፋር ለሚገኙት ስድስት ሚሊየን ብር የሚገመት የተለያዩ የእለት ደራሽ ምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች፤ በተመሳሳይ በመተሀራ ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር በላይ የቁሳቁስ ድጋፍ በማቅረብ ያንን አስከፊ ጊዜ ዜጎች እንዲሻገሩት አስችሏል።
በስልጤ ዞንም በተከሰተው ጎርፍ ለተጎዱት ወገኖች ከሶስት ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ከወንዙ የወጣው ውሃ ለከብቶች መኖ የሚውለውን ሳርም ጨምሮ ያወደመ በመሆኑ እንስሳቶች ጊዜ ለማይሰጥ የከፋ ችግር ተዳርገው ነበር። በመሆኑም በአካባቢው ላሉት ከብቶች መኖ የማቅረብ ሥራ በነጃሺ በኩል ተሠርቷል።
በአፋር የነበረው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑና አብዛኛው የጎርፍ ተጠቂ ጥሪቱን አጥቶ ስለነበር ከእለት ጉርስ የዘለለ የመቋቋሚያ ድጋፍ ያስፈልገው ነበር። በመሆኑም ከክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ጋር በመነጋገርና ፕሮጀክት በመቅረጽ መልሶ የማቋቋም ሥራ ተሠርቷል። በዚህም ከሦስት መቶ ሃምሳ በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦችን በጊዚያዊነት ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ አራት ሴትና አንድ ወንድ የርቢ ፍየሎችን ከክልሉ የግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ማዳረስ ተችሏል። ይህ ድጋፍ ለአርብቶ አደሮቹ በቀጥታ ከሚሰጠው ጥቅም በዘለለ ለችግር ደራሽ ወገን አለን ሀገርና ሕዝብ አለን የሚል ስሜት የፈጠረባቸውም ነበር።
ነጃሺ ችግር ሲደርስ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ብቻ ሳይሆን ችግረኞችና ተጎጂዎችንም የሟቋቋም ሥራ እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ኤልያስ፤ በዚህ ረገድ የተሰሩ ሥራዎችንም እንደሚከተለው አብራርተዋል። የውሃ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማስፋፋት አንዱ የድርጅቱ ተግባር ነው። በዚህም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ሃያ ሃያ አንድ ከገባ በኋላ ሃያ አምስት በፓምፕ የሚሰሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በወለጋ፤ በስልጤ፤ በጉራጌና ቡታጅራ እንዲሁም ሲዳማ ላይ ማቅረብ ተችሏል። እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑት የገጠሩ ነዋሪ ተራርቆ የሚኖር እንደመሆኑ ማህበረሰቡም ተማሪዎችም እንዲጠቀሙ በሚያሰባስባቸው የትምህርት ቤቶች አካባቢ ነው።
ለቀጣይም እስካሁን የተሰሩትን ሃያ አምስት የውሃ አቅርቦቶች በተያዘው የፈረንጆች አመት ሃምሳ ለማድረስ እቅድ አለ። የውሃ መቆፈሪያ ማሽንና አምፖላንሶችን ከቀረጥ ነጻ በማስገባት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ፤ የውሃ ወለድ በሽታ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ፈቃደኛ የሕክምና ባለሙያዎችን በማሰማራት የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሀገሪቱ በሰሜኑ ክፍል በአሸባሪዎች በተፈጠረው ጦርነት በርካታ ዜጎች ተፈናቅለው በችግር ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል። በዚህ ጦርነት ስፍር ቁጥር የሌለው ንብረት ወድሟል። በአካባቢው ያሉ ዜጎችም ለቁሳዊ፤ ለሰብአዊና ስነልቦናዊ ቀውስ ተዳርገዋል። በመሆኑም ነጃሺ የበጎ አድራጎት ማህበር በድሬ ሮቃ፤ ገፍራ፤ ፋጂ፤ ጊራና፤ ደሴና ኮምቦልቻ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የከተሙበት ካምፕ ድረስ በመሄድ ሰብአዊ ድጋፍ አድርጓል። በዚህም በመጀመሪያው ዙር ጉዞ ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ብር በላይ በማውጣት ከአስራ አምስት መኪና በላይ እህሎች ለተረጂዎች እንዲዳረሱ ማድረግ ተችሏል። የአካባቢው ማህበረሰብ በስፋት የበቆሎ ዱቄት የሚጠቅም በመሆኑ የቀረበውም ይኸው ነው። ይህም ሆኖ ከተፈናቃዮቹ መካከል እንዲሁም ህጻናት፤ እናቶች፤ እመጫቶችና አረጋውያን የሚበዙ በመሆናቸው ተጠልለው ያሉበት ቦታ ለኑሮ ምቹ አልነበረም።
በተጨማሪ ድጋፉን ለማድረስ የተንቀሳቀሰው አካል በመጀመሪያው ዙር ድጋፍ ከጤና አኳያ ሊደረግላቸው የሚገባ ግን ያልተጀመሩ በርካታ ነገሮች መኖራቸውንም መገንዘብ ችሎ ነበር። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት መሰረታዊ ፍላጎቶችን ጨምሮ ያልተሟሉትንም የሚያሟላ ድጋፍ ለማድረግ ከክልሉና ከዞኑ ጤና ቢሮ ጋር በመነጋገር ሁለተኛውን ጉዞ ለማድረግ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።
ነጃሺ የበጎ አድራጎት ድርጅት የፋይናንስ መሰረቱን በዋናነት ያደረገው የአባላት መዋጮ ላይ ነው። እነዚህ ከአንድ ሺ አምስት መቶ በላይ የሆኑ አባላቶች መነሻውን አምስት መቶ ብር በማድረግ በየወሩ ከዛ መዋጮ የሚከፍሉ ሲሆን እስከ አስር ሺ ብር የሚያዋጡም አሉ። እንዲሁም ለገቢ ማስገኛነት የተለያዩ ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በከተማ ደረጃ በረመዳን ጾም ወቅት በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ ከሀላል ፕሮሞሽን ጋር በመሆን በቅንጅት ተሳትፎበታል። በተጨማሪ ድርጅቱ ሀገር በቀል ለሆኑ ሌሎች ድርጅቶች የበጎ አድራጎት ፕሮጀክቶችን በመስጠት እንዲያስፈጽሙ ይደረጋል። በአጭር የስልክ መልዕክት 7100 ላይ በሚላክ አንድ አንድ ብር የሚሰበሰብ የየእለት ገቢ የሚገኝበትም መስመር አንዱ የገቢ ማስገኛ ነው።
በነጃሺ በጎ አድራጎት ድርጅት ሌሎች ድርጅቶችም ሆነ ግለሰቦች ድጋፋቸውን የሚያደርጉት በተለያየ መንገድ ነው። በዚህ ረገድ የነጃሺ በጎ አድራጎት ድርጅት ቀዳሚ ተግባር የሚሆነው ለእነዚህ በጎ አድራጊዎች ከዚህ ቀደም የተሰሩ ሥራዎችንና ለቀጣይ የተያዙ እቅዶችን ቢቻል በአካል በማስገኘት ካልሆነም ባሉበት ሆነው እንዲረዱ ማድረግ ሲሆን ከዚህ ቀጥሎ አይተው ፈቃደኛ ሲሆኑ በተዘጋጀው ቅጽ ላይ ፎርም እንዲሞሉ ይደረጋል። ይህ ከሆነ በኋላ ሁሉም እንደአቅሙ በገንዘብ በአይነት በእውቀትና በጉልበት በገባው ቃል መሰረት የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል ምክረ ሃሳቦችንም ይሰጣል።
በአሁኑ ወቅት ድርጅቱ ዋና አቅጣጫውን የሰሜኑን ችግር አድርጎ በወሎ እየሠራ ሲሆን በደሴ ለሚገኙ አስር ሺ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች የምግብ አቅርቦት ለማሟላት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይህም ሆኖ የተደረገውም ሆነ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከተፈናቃዩ ቁጥር አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ነው። በተጨማሪ ለህጻናት የአልሚ ምግብ ለሴቶች የንጽህና መጠበቂያ እንዲሁም በህጻናቱ ላይ የተከሰተውን የዝንብ ወረርሽኝና የአይን ህመምን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ትልቅ ስጋት ናቸው። በመሆኑም ከትልልቅ የመድሀኒት አስመጪ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ፈቃደኛ ሆነው ስለተገኙ የእነሱም ድጋፍ በሁለተኛው ዙር ይቀርባል።
ነጃሺ ከዚህም በተጨማሪ በክፍለ ከተሞችና በወረዳዎች ማህበራዊ ዘርፍ ላይ የሚሠሩ የመንግሥት አካላት ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ይህም ሆኖ የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ከነበሩት ኢንጅነር ታከለ ኡማ የተገባ ቃል የነበረ ቢሆንም አስተዳደራዊ ለውጥ በመከሰቱ በተፈለገው ፍጥነት ማከናወን አልተቻለም። በዚህም በአይነት የሚሰበሰቡ ድጋፎች ለተረጂዎች እስከሚከፋፈሉ ድረስ ያለ ብልሽትና ንክኪ ሊቆዩበት የሚያስችል መጋዘን፤ እንዲሁም የቢሮ ሥራ ለማከናወን የህንጻ ችግር አለ። ነገር ግን ወደፊት ይቀረፋል ብለን ተስፋ አለን ሲሉ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል።
ነጃሺ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለሚቀጥሉት ሦስት አመታት የሚዘልቅ ስትራቴጂክ እቅድም አዘጋጅቷል ያሉን አቶ ኤልያስ፤ በዚህም የራሱ ቢሮ እንዲኖረው የማስቻል፤ የአባላት ቁጥሩን ወደ አስር ሺ የማሳደግ፤ እያንዳንዱ አባል የተሠሩ ሥራዎች በአካል በመገኘት እንዲመለከት በማድረግ የባለቤትነት ስሜቱን የመጨመር ሥራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ከክልሎችና ዞን አመራሮች እንዲሁም ከሌሎች ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ማህበራት ጋር በቅንጅት በመተጋገዝ የፈረሱ ቤቶችን በመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቶች አማካኝነት መልሶ የመገንባት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። እንደየውድመቱ የንግድ እቃዎችን በማቅረብና ከብቶች በመግዛት ተጎጂዎችን ጥሪት የማስያዝ ሥራ ለመሥራት እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2014