ፈጣን፣ አስተማማኝና አቅምን ያገናዘበ ትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት ዛሬም ያልተቀረፈ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ችግር ሆኖ ቀጥሏል። ምክንያቱም በሥራ፣ በትምህርትና በተለያዩ ጉዳዮች ከሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት ወደ ከተማዋ የሚፈልሰው ሕዝብ ብዛት እንደሆነ መረጃዎች ይናገራሉ፡፡ በሁሉም የመዲናዋ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን ሰልፎች በመመልከት ችግሩን መገንዘብ ይቻላል። ሰልፎቹ በፍጥነት ተስተናግደው መቃለል ባለመቻላቸው በተለይ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት መንገዶች ተዘጋግተውና እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለው መመልከትም ተለምዷል።
እንዲህ ዓይነቱ ችግር ጎልቶ ከሚንፀባረቅባቸውና እኛ ከቃኘናቸው የአገልግሎቱ መስጫ አካባቢዎች መካከል ከካዛንቺስ አራት ኪሎና ስድስት ኪሎ፤ ከካዛንቺስ ቦሌ፣ ከአራት ኪሎ ፈረንሳይና ሽሮሜዳ፤ ከሜክሲኮ ፒያሳ፤ ከጊዮርጊስና ከስድስት ኪሎ ጀሞና ሀያት 49፤ እንዲሁም ከአራት ኪሎ መገናኛ፣ ኮተቤና ሌሎች አካባቢዎች የሚወስዱ የትራንስፖርት መስመሮች ይገኙበታል። በእነዚህ አካባቢዎች ያገኘናቸው ተገልጋዮች በምሬትም ተስፋ በመቁረጥም እንደገለፁልን በአካባቢዎቹ ከሚታዩት የትራንስፖርት ችግሮች መካከል የተሽከርካሪ እጥረት መኖር፣ ከእጥረቱ ጋር ተያይዞ የመጡት ተሽከርካሪዎች በመሙላት ሰልፍ የያዘውን ሰው በሙሉ ለማስተናገድ አለመቻል፣ ጭራሽ ሳይመጡ መቅረት እንዲሁም ፌርማታ ዘግቶ መሄድ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
አቶ ነሰርዲን ሁሴንን ያገኘናቸው ከጊዮርጊስ ወደ ጀሞ አንድ፣ ሁለትና ሦስት የምትጓዘውን 103 ቁጥር አንበሳ አውቶቡስ ሲጠብቁ ነው። እርሳቸው እንደነገሩን የሥራ ቦታቸው አምስት ኪሎ አካባቢ ነው። መኖሪያ ቤታቸው ደግሞ ጀሞ አንድ ሲሆን ወደ ጀሞ የሄዱት አሁን አራዳ ክፍለ ከተማ ጀርባ ከሚገኘው ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ በልማት ተነስተው ነው። የትራንስፖርት አገልግሎት መጠቀም በጀመሩበት ጊዜ በርካታ ችግሮች ነበሩ፡፡ ብዙ ሰው ወደ አካባቢው ባለመግባቱና የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ከመሟላታቸው በፊት ቀድመው ወደ ቦታው እንዲዛወሩ በመደረጋቸው አገልግሎቱን ማግኘት አልቻሉም ነበር።
በሂደት አገልግሎቱ ቢኖርም በቂ እልነበረም። የአሁኑ ከፊቱ ሲነፃፀር ቢሻሻልም ችግሩ ሙሉ ለሙሉ አልተቀረፈም። እጥረት በመኖሩ የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችንና መስመሮችን ለመጠቀምና ተጨማሪ ወጪ ለማውጣት ተገደዋል። አዘውትረው የሚጠቀሟት 103 ቁጥር አንበሳ አውቶቡስ ዋጋዋ ኪሳቸውን የሚመጥን (አራት ብር) ብትሆንም እንደ ልብ ባለመገኘቷ ግን ይማረራሉ። አንዳንድ ጊዜ በመንገድ መጨናነቅ ምክንያት በሰዓቷ አትመጣም። ከ30 ደቂቃ እስከ ሁለት ሰዓት ልትዘገይ ትችላለች። በዚህ ጊዜ ሌሎች አማራጮችን ይጠቀማሉ፤ ይህም ለተጨማሪ ወጪ ይዳርጋቸዋል፡፡ እጥረቱ ደግሞ አቆራርጦ በመሄድና ለረጅም ጊዜ ወረፋ በመጠበቅ ለሥራ ሊያውሉት የሚገባ ጊዜያቸውም እንዲባክን አድርጓል። እነዚህን ሁሉ አማራጮች ሞክረው አገልግሎቱን ሳያገኙ ሲቀሩም ከዚህም በበለጠ ክፍያ ከፍለው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።
ከጀሞ ሚካኤል ጀምሮ ጀሞ ሦስት ድረስ ለመንገድ ማስፋፊያ የተተወው ቦታ የመንገዱ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እስኪውል አገልግሎት እንዲሰጥ ቢደረግ፣ የሸገር አውቶቡስና የድጋፍ ሰጪ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ቢጨመር፣ ዘላቂ ተሽከርካሪዎች እንዲመደቡ እንዲሁም፣ አቋራጭና ተለዋጭ መንገዶች እንዲኖሩ ቢደረግ ረጃጅሙን ሰልፍ መቀነስና ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል ይመክራሉ።
ከቅድስተ ማርያም ሰፈር በልማት ምክንያት ተነስተው አያት 49 የሚኖሩት አቶ ብሩክ ወንድአፈራሁም በአገልግሎቱ ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ይናገራሉ። ከሥራ ቦታቸው አራት ኪሎ አራዳ ክፍለ ከተማ ወደ መኖሪያቸው ለመድረስ የሚያወጡት እንደተጠበቀ ሆኖ ከስድስት ኪሎ 83 ቁጥር አውቶቡስን ይጠቀማሉ። ለተማሪ ተብሎ ቆይታዋ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት በመራዘሙ በዚህ ጊዜ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ። ስትቀር መገናኛ ድረስ በመሄድ 61 እና 49 ቁጥር አውቶቡሶችን ይጠቀማሉ። ሁሉም ካልተሳካላቸው ደግሞ ከመገናኛ እስከቤታቸው ድረስ በታክሲ በ11 ብር ይሄዳሉ። በዚህ መካከል የአውቶቡስ፣ የድጋፍ ሰጪ እንዲሁም የሌሎች አማራጭ ትራንስፖርት መዘግየት/ማጣት፤ ረጅም የሰልፍ ወረፋ መጠበቅ፤ ፀሐይ፣ የእግር ህመም እንዲሁም ተጨማሪ ወጪዎች ይገጥሟቸዋል።
ወጣት እህተ አብይ መኖሪያዋ ፈረንሳይ ቦኖ ውሃ፤ የሥራ ቦታዋ አራት ኪሎ ነው። እርሷ እንደምትለው ረጅም ወረፋ ትጠብቃለች፣ አገልግሎቱ ይዘገያል። እጥረትም አለ። የሚቀርበትም ጊዜ አለ። ይሄን ታሳቢ አድርጋ ከቤቷ የምትወጣው ከንጋቱ 12 ሰዓት ነው፤ ከ11 ሰዓት ቀድማም ትራንስፖርት ትጠብቃለች። ወደ ቤቷ የምትገባው አምሽታ ነው። በዚህ ሁኔታ አምስት ዓመታት ማስቆጠሯ አማሯታል። ምሬቷን ‹‹ለውጥ የማያመጣና ችግሩ እየተባባሰ የሚሄድ›› ስትል ትናገራለች።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሪት እፀገነት አበበ በተገልጋዩ የሚነሳውን ችግር ለመፍታት ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ይህን ተከትሎ አገልግሎቱ መሻሻል እያሳየ መጥቷል። ሆኖም በቂ ባለመሆኑ ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም። ስለዚህ ችግሩን የመቅረፍ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል›› ይላሉ። በመሆኑም ‹‹ዘንድሮ 500 የሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶቡሶችን ለማስገባት እንደታቀደ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል። እኛም የትራንስፖርት አገልግሎት እጥረት ትኩረት የሚሻው በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበናል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2014