የሥነ ጥበብ ሰዎች አንድ የሚሉት ነገር አለ። ‹‹አርቲስት›› የሚለው ቃል የሚያገለግለው ለሠዓሊ ነው። ‹‹አርት›› የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የቅርጻቅርጽና የሥዕል የፈጠራ ሥራዎችን የሚገልጽ ነው። እርግጥ ነው ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎችም የፈጠራ ውጤቶች ናቸው። ምንም እንኳን የዘርፉ ባለሙያዎችንም የሚያከራክር ቢሆንም ‹‹አርቲስት›› የሚለው ቃል ግን ለሠዓሊዎች የሚሆን ነው። በኢትዮጵያ ግን ዘፋኝም ይሁን ደራሲ፣ ሠዓሊም ይሁን ተዋናይ በጥቅሉ ‹‹አርቲስት›› ተብሎ ነው የሚጠራው። ይሄ ጥቅል ስም ሲሆን በተናጠል ግን ሠዓሊ፣ ድምጻዊ፣ ገጣሚ፣ ተዋናይ… እያልን መግለጽ እንችላለን።
እንግዲህ የዘርፉ ሰዎች እስከሚስማሙበት ድረስ ‹‹ሠዓሊ›› በሚለው የአማርኛ ቃል እንጠቀምና ስለ ሥዕል እናውራ። ሥዕል ከጥበብ ሥራዎች ሁሉ የመጀመሪያው ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም የሥዕል ጥበብ ከሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ ጋር አብሮ የቆየ ነው። የሰው ልጅ ሥዕልን የጀመረው ዋሻ ውስጥ ይኖር በነበረበት ዘመን ነው። ይሄ ማለት እንግዲህ ከሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች ሁሉ ይቀድማል ማለት ነው። የጥበብ ሁሉ መጀመሪያው ሥዕል ነው ለማለትም ያስችላል። ለዚህም ነው ሥዕል ልክ እንደ ዘፈን እና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሥራዎች ባህላዊ እና ዘመናዊ የሚል ምድብ የለውም። የእጅ ጥበብ ብቻ ስለሆነ ከቴክኖሎጂ ዕቃዎች መቀያየር ጋር አብሮ አይቀያየርም።
ይህ ዋሻ ውስጥ የተጀመረ ጥበብ የሰው ልጅ ከዋሻ ሲወጣም አብሮት ወጥቷል። ይልቁንም እየረቀቀና የበለጠ ተወዳጅ እየሆነ መጣ። የሰው ልጅ የፈጠራ ሥራውን በሥዕል ጀመረና ወደ ቴክኖሎጂና የማሽን ውጤቶች አደገ። ያየውን ነገር ብቻ ይስል የነበረው የሰው ልጅ በምናቡ እየፈጠረም መሳል ጀመረ። በሰማይ ላይ የሚበር (አውሮፕላን)፣ በመሬት ላይ የሚሽከረከር (መኪና) አይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ከመኖራቸው በፊት የሰው ልጅ ሰርቶ ማሳያቸውን (ሞዴላቸውን) የሰራው በሥዕል ነው። በጂኦሜትር የሒሳብና ፊዚክስ ውስጥ ያለው ቀመርም ከመሳል የዳበረ ነው። አንድ ሕንጻ ከመሰራቱ በፊት ንድፉ የሚሰራው ወረቀት ላይ ነው። ሥዕል ረቂቁን የሳይንስ ጥበብ አስጀምሯል ማለት ነው።
ሥዕል በተለያየ መንገድ ይሰራል። በዋሻ ግድግዳ ላይ መሰራት የጀመረው ሥዕል፣ በወረቀት፣ በሸራ፣ በቆዳ፣ በመስታወትና በሌሎች አካላትም ላይ ይሳላል።
አገራችንም በተለያዩ የስዕል ሥራዎቻቸው በዓለምም በአገር ደረጃም የሚታወቁ ታላላቅ ሠዓሊዎች እናት ናት። ለአብነትም የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በመስታወት ላይ የሰሩትን ሥዕል እንዲሁም የክብር ዶክተር ሎሬት ለማ ጉያ ደግሞ በቆዳ ላይ የሰሯቸውን ሥዕሎች መጥቀስ ይቻላል።
የዛሬ ትኩረታችን በክብር ዶክተር ሎሬት ለማ ጉያ የስዕል አንድ የስዕል ቱሩፋት ላይ ነው፤ የሥዕል ትምህርት ቤት ነው። የዛሬ ዓመት በዚህ ወር በዚህ ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የክቡር ዶክተር ሎሬት ሰአሊ ለማ በአሥራ አምስት ዓመታቸው ከሚኖሩበት ቀበሌ በአሥር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አጼ ልብነ ድንግል ትምህርት ቤት ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩ የተደረገው በልጅነታቸው ባሳዩት የቅርጻቅርጽና ሥዕል ችሎታ ሳቢያ ነው።
ከዚያም ናዝሬት በሚገኘው አጼ ገላዲዎስ የመምህራን ኮሌጅ ገብተው በትምህርት ሰልጥነው ወደ ሥራ ተሰማርተዋል። የአየር ሃይል ባልደረባም ነበሩ፤ በኋላም ሙሉ በሙሉ ወደሚወዱት የሥዕል ሙያ ገብተው ሕይወታቸው አደረጉት።
ሰዓሊው ሥዕልን የተራቀቁበት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እንዲራቀቁበት ያደረጉ ናቸው። የሠዓሊው ቤተሰቦች ሁሉ ሠዓሊ ናቸው። በአትሌቲክሱ ዘርፍ ‹‹የዲባባ ቤተሰብ›› እንደሚባለው ሁሉ፤ በሥዕል ደግሞ ‹‹የለማ ጉያ ቤተሰብ›› እየተባለ ይጠራል። ከቤተሰቦቻቸው ውስጥ ልጆቻቸው ዳዊት ለማ ጉያ፤ ነፃነት ለማ ጉያ እና ሰላም ለማ ጉያ ሠዓሊዎች ናቸው። ወንድሞቻቸው ቱሉ ጉያና፣ አሰፋ ጉያም ሠዓሊዎች ናቸው።
ሠዓሊ ለማ ጉያ በአንድ ወቅት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ እናታቸውም አመዱን፣ ጭቃውን፣ ከሰሉን እየተጠቀሙ በቤቱ ግድግዳ ላይ የተለያዩ ዕቃዎችንና እንስሳትን ይስሉ ነበር። እናታቸው የስፌትና የጌጣጌጥ ዕቃዎችን፣ የሸክላ ሥራዎችን አሳምረው ይሰሩ ነበር። ዕቃዎቻቸውም ተፈልገው ነው የሚገዙት። አርቲስት ለማ ጉያም ከዚያ ከእናታቸው የስዕል ህይወት ተነስተው ነው ስዕልን የተራቀቁበት።
የሠዓሊ ለማ ጉያ ልጅ ሠዓሊ ዳዊት ለማ ሰዓሊ ብቻ አይደለም፤ በቢሾፍቱ ከተማ የሥዕል ትምህርት ቤት ባለቤትም ነው። ይህ የሥዕል ትምህርት ቤት ብርቅዬ የስዕል ትምህርት ቤት ነው፤ ምክንያቱም በአገራችን እንኳን ራሱን የቻለ የሥዕል ትምህርት ቤት ይቅርና ሥዕል እንደ አንድ የትምህርት አይነት እንኳን የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩ ያጠራጥራል፤ ያጠራጥራል ማለቴ በአንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ትምህርቱ ሲሰጥ ስለተመለከትኩ እንጂ ትምህርቱ ጨርሶ አይሰጥም ማለት የሚያስችል ሁኔታ ስለመኖሩ ማንም አይጠራጠረውም። በሠዓሊ ዳዊት ለማ የሥዕልና የበገና ትምህርት ቤት ግን ሥዕል ራሱን የቻለ የትምህርት ክፍል ነው።
የሠዓሊ ዳዊት ለማ ልጅ (የሠዓሊ ለማ ጉያ የልጅ ልጅ) ወጣት አቤል ለማ የዳዊት ለማ የሥዕል ትምህርት ቤት ተማሪ ነው። በ2011 ዓ.ም ወጣት አቤል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገረው፤ ይህ ትምህርት ቤት ባይኖር ኖሮ የሥዕል ፍላጎቱ ፍላጎት ብቻ ሆኖበት ይቀር ነበር፤ እንዲያውም ፍላጎቱ ራሱ እየቆየ ሊጠፋ ይችል ነበር። ከሕጻንነቱ ጀምሮ ነው ሥዕል መሳል የሚወደው።
‹‹ሥዕል የተፈጥሮ ችሎታ ብቻ አይደለም›› የሚለው አቤል በትምህርት ሲታገዝ ሙያው እንደሚያድግ ነው የሚናገረው። ሥዕል የብዙ ነገር መነሻ ነው። በትምህርቱ ውስጥ ደግሞ ብዙ ‹‹ዲሲፕሊን›› አለው፤ ከሥርዓተ ትምህርቱም ጋር የሚያገናኘው ነገር አለ።
አቤል የኪነ ሕንጻ (አርክቴክት) ባለሙያ ይፈልግ ነበር። እሱ አንዳለው የሥዕል ትምህርት ቤት መማሩ በተፈጥሮ ተሰጥኦው መሳል ከሚችለው በላይ ብዙ ቴክኒካል ነገሮችን ይጨምርለታል፤ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር ያቀራርበዋል። ትምህርቱ የሚሰጠው በተግባር ብቻ ሳይሆን በንድፈ ሃሳብም ጭምር ነው። ምንም እንኳን ሥዕል ተግባር ቢበዛውም በንድፈ ሃሳብ መታወቅ ያለባቸው ብዙ ሙያዊ ቃላትም አሉት።
የዳዊት ለማ ጉያ የሥዕል ትምህርት ቤት ሥዕል የሚያስተምረው በተለያየ መንገድ ነው። ይሄውም የበጋ፣ የክረምት፣ የአዋቂዎችና የህጻናት እየተባለ የተከፋፈለ ነው። ይህ ምድብ አንድ ጥሩ ነገር አለው። የመደበኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሥዕልን በክረምት መማር ይችላሉ፤ ሥዕልን ብቻ መማር የሚፈልጉም በፈለጉት ወቅት ይማራሉ። ህጻናትም እንደዚያው፤ ህጻናትን ታሳቢ ያደረገ ትምህርት ይሰጣል።
በ2011 ዓ.ም ‹‹የሥዕል ትምህርት ቤቱ ትምህርት ቤት ብቻ አይደለም›› ብለውን ነበር የዳዊት ለማ ጉያ አርት ጋለሪ አስተዳዳሪ ዳዊት ለማ ጉያ። ትምህርት ቤቱ የአርት ጋለሪም ጭምር ነው። አርት ጋለሪ ማለት የሥዕል ሥራዎች የሚቀመጡበትና የሚታዩበት ማለት ነው። እናም የዳዊት ለማ ጉያ አርት ጋለሪ እንደ ሥዕል ማስቀመጫና ማሳያም እንደ ትምህርት ቤትም ያገለግላል። በዚያው ዓመት እንኳን መስከረም 2 ቀን 2011 ዓ.ም 250 የሥዕል ተማሪዎችን አስመርቋል። እነዚያ 250 የሥዕል ተመራቂዎች የበጋውም የክረምቱም የአዋቂዎችም የሕጻናትም ጭምር ናቸው።
በብዛት የሚማሩት የተግባር ትምህርቱን ነው። በንድፈ ሃሳብ ትምህርቱ ደግሞ የፍልስፍና ትምህርትም ይሰጣል፤ ይህ የሚሰጠው ግን ለአዋቂዎች ነው። ለሕጻናት አብዛኛውን ጊዜ የተግባር ልምምድና ቀለል ቀለል ያሉ የንድፈ ሃሳብ ትምህርቶችን ነው። እንዴት መሳል እንዳለባቸው፣ የማስመሪያና የቀለም አጠቃቀም ለሕጻናት የሚሰጥ ትምህርት ነው።
የሥዕል ትምህርት እንደሚታወቀው ፤ ራሱን ችሎ እንደ አንድ ትምህርት የሚሰጥበት ሁኔታ አናሳ ነው። የዳዊት ለማ ጉያ የሥዕል ጋለሪና ትምህርት ቤት ልጆችን ማስተማር ብቻ ሳይሆን የሥዕል ትምህርት በትምህርት ቤትም እንዲሰጥ ሲሰራ የቆየ ነው። ለዚህም ከቢሾፍቱ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ጋር እንደተነጋሩ ነው የጋለሪው ባለቤት በወቅቱ የተናገሩት። የሥዕል ትምህርት ራሱን ችሎ መሰጠት እንዳለበት ማለት ነው።
ሥዕል እንደ ኬሚስትሪና ፊዚክስ ሁሉ ራሱን የቻለ የትምህርት አይነት ተደርጎ በመደበኛው ትምህርት ቤት ቢሰጥ አሁን ባለው ሁኔታ ውጤታማ እንደማይሆን ነው ሠዓሊው የሚያምኑት። ምክንያት አላቸው። በትምህርት ቤት ውስጥ ሥዕል የሚሰጠው የጥበብ ፍቅር ባለው መምህር አይደለም። ለሥዕል ተብሎ የተቀጠረ መምህር የለም፤ ለሥዕል ተብሎ ቢቀጠርም በሥዕል የተመረቀና ሥዕል የሚወድ የለም። በተደራቢነት ቢሰጥ ደግሞ ውጤታማ አይሆንም።
እንደ ሌላው ትምህርት ከኢንተርኔት ላይ በማውረድ የሚሰጥም አይደለም። ሥዕል የተፈጥሮ ችሎታንና ልዩ የጥበብ ፍቅርን ይፈልጋል። ራሱ ያልተማረውን ሊያስተምር አይችልም፤ የሚያስተምረው ተማሪ ተሰጥዖው ይኑረው አይኑረው አያውቅም። ስለዚህ መሰጠት አለበት ተብሎ ቢሰጥ እንኳን ውጤታማ ትምህርት አይሆንም።
የሥዕል ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። እንደ አጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ የኪነ ጥበብ ዘርፍ በቂ ትኩረት ያላገኘ ቢሆንም፤ ሥዕል ግን ከሌላውም የከፋ ነው። የሚገርመው ደግሞ መንግስት ሁሌም ‹‹ሳይንስና ቴክኖሎጂ›› እያለ ከሚጠቅሰው ጋር የሚገናኘው ሥዕል ነው።
እዚህ ጋ የኪነ ሕንጻ ባለሙያዎች የሉንም የሚል እሮሮ አለ፤ እዚህ ጋ ደግሞ ሥዕልና ቅርጻቅርጽ የሰነፍ ተማሪ ተደርጎ ይታያል። ሥዕል ማለት እኮ ጂኦሜትሪ የሚባለው የሂሳብ ክፍል ነው። ፊዚክስ ነው፤ ኪነ ሕንጻ ነው። እንዴት ይሄ ጥበብ ትኩረት ይነፈገዋል? የግለሰብ ጥረት ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ለኪነ ጥበብ ትኩረት መስጠት አለበት። አለበለዚያ ሥዕልና ሠዓሊው ተለያይተው ቀሩ ማለት ነው።
ለዚህም እንደ ሠዓሊ ለማ ጉያ እናት አይነት ያልተማሩ ግን ችሎታ ያላቸው እናቶች ምስክሮቻችን ናቸው። ሞፈርና ቀንበርን ገጣጥመው የሚሰሩ አርሶ አደሮች ምስክሮቻችን ናቸው። ድንቅ የባህል ቤቶችን የሚሰሩ የገጠር ሰዎች ምስክሮቻችን ናቸው። ታዲያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማለት ምን ይሆን? የግድ ከአውሮፓ የመጣ ማሽን ብቻ መሆን የለበትም።
ከአንድ ወር በፊት የዚህ ትምህርት ቤትና የሠዓሊያን ቤተሰብ አባት የሠዓሊ ለማ ጉያ ፋውንዴሽን ተመስርቷል። በፋውንዴሽኑ እና በሌሎች የሥዕል ሥራዎቻቸው ላይ ደግሞ በሌላ ዕትም እንመለሳለን።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2014