የዩናይትድ ስቴት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ዩን በኒውክለር ምክንያት የገቡበትን ፍጥጫ አስመልክቶ ሁለተኛውን ዙር ውይይት በቬትናም ዋና ከተማ ሀኖይ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ቢቢሲ አልጀዚራንና ሌሎች ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
በፈረንጆቹ የካቲት 27 እና 28 2019 እየተካሄደ የሚገኘው የሁለቱ ሀገሮች ንግግር ቀደም ሲል በሲንጋፖር ከተካሄደው ውይይት ጋር ተያያዥነት አለው፡፡ በውይይቱ ሰሜን ኮሪያ የኒውክለር መሳሪያዎቿን ለማውደም የገባቸውን ቃል የሚያጠናክርና ግልጽ የሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችና አፈጻጸሞች ይካተቱበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይዋ ሳራ ሳንደር ሁለቱ መሪዎች የሚያደርጉት ይህ ውይይት ከዚህ ቀደም በሲንጋፖር በነበራቸው ውይይት የኮሪያን የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ማውደምን በተመለከተ በግልጽ ያላስቀመጧቸውን ዝርዝር ጉዳዮች እንደገና አንድ በአንድ ፈትሸው ጥርት ያለ ነገር ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዋናው አጀንዳ ጎን ለጎን ቀደም ሲል ሲንጋፖር ላይ ተደርጎ በነበረው ውይይት የተደረሰባቸው ስምምነቶች ተግባራዊ ስለመደረጋቸው ይነጋገራሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡ ሁለቱም መሪዎች ጉዳያቸው አስተማማኝ መቋጫ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ ሰንቀዋል፡፡
ውይይቱ በዶናልድ ትራምፕ እንደሚመራ የተገመተ ሲሆን ትራምፕ በበኩላቸው ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያዎቿን እንድታወድም በሚደረገው የሁለትዮሽ ንግግር መስማማት እንጂ ማዋከብና ተገቢ ያልሆነ ጫና ማሳደር እንደማይፈልጉ አስቀድመው ገልጸዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጁንግ በበኩላቸው አራት ሺ ኪሎ ሜትር መንገድን ስልሳ ሰዓታትን በባቡር ተጉዘው ከሥፍራው ደርሰዋል፡፡ ወትሮም አወዛጋቢ የሆኑት እኒህ መሪ በአውሮፕላን በሰዓታት ውስጥ መድረስ የሚያስችላቸውን የተሻለ አማራጭ ትተው ከሁለት ቀን በላይ የሚፈጀውን የባቡር ጉዞ መምረጣቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የተሳፈሩበት ባቡር ጥይትን መከላከል የሚያስችል ብረት ለበስ የሆነ ፣ የመሰብሰቢያ ክፍል ያለው ፣ ዘመናዊ የቆዳ ወንበሮች የተገጠሙለትና ቅንጡም ነው፡፡ ኪም ጆንግ አብረዋቸው ካሉት ሰዎች መካከል እህታቸው ኪም ዮ ጆንግ እና የቀድሞ ጀነራል የነበሩት ከፍተኛ አማካሪያቸው ኪም ዮንግ ኮል ይገኛሉ፡፡ መሪው ጉዟቸው በባቡር እንዲሆን የመረጡት ቀደም ሲል አባታቸው ያደረጉትን ተመሳሳይ ጉዞ ምሳሌ ለማድረግና መዘከር እንደሆነ ተገምቷል፡፡
ባቡሩ የቻይናን ግዛት አቋርጦ ሲያልፍም የቻይና መንግሥት ለኪም ጆንግ ደህንነት ሲል ለስድስት ሰዓታት የተወሰኑ የባቡር ጣቢያዎችን ዘግቷል፡፡ መንገዶች አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጓል፡፡ የባቡር አገልግሎት መስተጓጎሉን ተከትሎ ቻይናውያን በማህበራዊ ሚዲያ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
የኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ሀኖይ ዶንግ ዳንግ ባቡር ጣቢያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላ ቸዋል፡፡ የሀኖይ ከተማ ሆቴሎችና ጎዳናዎች በሁለቱ ሀገር ሰንደቅ አላማዎች ደምቀዋል፡፡ የሀኖይ አካባቢ ባለሥልጣናት በቦታው ተገኝተው የክብር አቀባል አድርገውላቸዋል፡፡
ይህ የትራምፕና የኪም የሀኖይ ውይይት መነሻ ሆኖ ከተማዋ ደምቃለች፡፡ ሳምንቱ በከተማዋ ላሉት ነጋዴዎች ከወትሮው በተለየ ገቢያቸው እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል፡፡ ነጋዴዎች የሁለቱን መሪዎች ምስልና ባንዲራ በቲሸርቶችና በልብሶች ላይ እያሳተሙ በመሸጥ ጥሩ ገቢ እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡ ጸጉር አስተካካዮችም ሁለቱ መሪዎች የሚታወ ቁባቸውን የጸጉር አቆራረጥ በማስተዋወቅ ገቢያቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ይናገራሉ፡፡ ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች በመሪዎቹ ሥም አዳዲስ ስያሜዎችን እየሸጥን ገበያችን ደርቷል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
ሂዩ ዲና በሀኖይ ከተማ የቲሸርት ፋብሪካ ባለቤት ነው፡፡ እርሱ እንደሚለው በሚሸጠው ልብስ ላይ የሁለቱን መሪዎች ምስልና የየሀገራቸውን ሰንደቅ አላማ በማሳተም የሽያጭ ገበያው የደራለት መሆኑን ግን ደግሞ የግብዓት እጥረት እንደገጠመው ይናገራል፡፡ ሌሎች ግለሰቦችም የአሜሪካን፣ የኮሪያና የቬትናምን ታሪካዊ ምስል የሚያሳዩ የፎቶ ኤግዚቢሽኖችን በየጎዳናው በማዘጋጀት ከቱሪስቶችና ከሀገሬው ሰው ጥሩ ገቢ እያገኙ ይገኛሉ፡፡
በአሜሪካና ቬትናም ጦርነት ወቅት ሁለት አጎቶቹን በጦርነቱ ያጣው ዶንግ ሊ የሁለቱን መሪዎች የጸጉር አቆራጥ ለደንበኞቹ በማስተዋወቅ በሳምንት ውስጥ ስድስት መቶ የሚሆኑ ሰዎች የዶናልድ ትራምፕና የኪም ጆንግን የጸጉር አቆራረጥ አይነት ተከትለው እንደተቆረጡ ይናገራል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች ይህን የሰላም ውይይት ለመደገፍ ብቻ ሳይሆን ቬየትናምና አሜሪካን በአንድ ወቅት ባደረጉት ጦርነት ለተፈጠረውና ለነበረው የረዥም ዘመን የሻከረ ግንኙነት እንደ አንድ የእርቅ መድረክ አድርገው በማየት ደስታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
ውይይቱ በቪየትናም ሀኖይ መደረጉ የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ቪየትናም ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርና ሀገራቱ በጠላትነት መተያየታቸውን እንዲያለዝቡ ይረዳቸዋል ተብሏል፡፡ ቪየትናምና ሰሜን ኮሪያ የኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለም ተከታይና አራማጅ ስለሆኑ ግንኙነታቸውን የበለጠ እንደሚያጠናክረው ተገምቷል፡፡
አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ የታጠቀችውን የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ እንድታወድም ካልሆነ ግን እርምጃ ልትወስድባት እንደምትችል ስታስጠነቅቃት መክረሟ፤ ኮሪያም በበኩሏ ለአሜሪካን ማስፈራሪያና ዛቻ ምላሽ እንደምትሰጥ በመግለጽ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ሲዝቱ መክረማቸው ይታወሳል፡፡ ይሁንና ባልተጠበቀ ሁኔታ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ሰላማዊ ድርድር በመምረጣቸው እ.አ.አ በሰኔ 2018 ሁለቱ ሀገራት ሲንጋፖር ላይ የመጀመሪያውን ንግግር ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በኢያሱ መሰለ