የናይጄሪያው ፕሬዚደንት ሙሀማዱ ቡሀሪ ከፍተኛ ውዝግብ ሲያስነሳ የነበረውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸውን የሀገሪቱን የምርጫ ኮሚሽንን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ የተካሄደው የናይጄሪያ አጠቃላይ የምርጫ ውጤት ቡሀሪን ለሁለተኛ የአራት ዓመት የሥልጣን ዘመን የሚያቆያቸው ሆኗል፡፡
የምርጫው ውጤት እንደሚያሳየው ሁለቱን ታላቅ ከተሞች ሌጎስና ካኖን ጨምሮ ቡሀሪ ከአጠቃላይ ሰላሳ ስድስት ግዛቶች በአስራ ዘጠኝ ግዛቶች ያሸነፉ ሲሆን 15 ሚሊዮን አንድ መቶ አሥራ ዘጠኝ ሺ ስምንት መቶ አርባ ስድስት ድምጽ በማግኘት በአጠቃላይ በሃምሳ ስድስት በመቶ ድምጽ ማሸነፋቸው ታውቋል፡፡ ዋና ተቀናቃኛቸው የፒዲፒ ተወካዩ አቡበከር አቲኩ በአሥራ ሰባት ስቴቶች ከፍተኛ ድምጽ ቢያስመዘግቡም በአስራ አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ስልሳ ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ ሰባ ስምንት ድምጽ በአጠቃላይ አርባ አንድ በመቶ ድምጽ ተሸናፊ ሆነዋል፡፡
የምርጫው ውጤት ከመሰማቱ አስቀድመው ደስታቸውን በአቡጃ ጎዳናዎች ላይ ሲገልጹ የነበሩት የኤፒሲ ደጋፊዎች የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላም አቡጃን በአንድ እግሯ አቁመዋታል፡፡ ፕሬዚዳንት ቡሀሪም ዳግም ስለመመረጣቸውም ለደጋፊዎቻቸው የደስታና የምስጋና መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የቡሀሪ ማሸነፍ ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን በዙሪያቸው የሚገኙ ታላላቅ ባለስልጣናትንም ያስፈነጠዘ ነበር ፡፡ ምክትል ፕሬዚደንቱ የሚ ኦሲንባጆ በቪዲዮ በተለቀቀው ምስላቸው ከደስታቸው ብዛት ሲዘፍኑ ታይተዋል፡፡ የቡሀሪ ቃል አቀባይ ጋርባ ሼሁ ፕሬዚዳንቱ የምርጫውን ውጤት ሲከታተሉ የሚያሳይ ምስል በቲውተር ገጻቸው በመልቀቅ ‹‹ቡሀሪ አሸነፈ፤ ምርጫውም በድል ተጠናቀቀ›› የሚል መልዕክት አስቀ ምጠዋል፡፡
አስቀድሞም ቢሆን የምርጫ ኮሚሽኑን በጥርጣሬ የሚመለከቱት አቡበከር አቲኩ በበኩላቸው የምርጫውን ውጤት አምነው እንደተቀበሉ የሚገልጽ መግለጫ እስከ አሁን ድረስ አልሰጡም፡፡ ደጋፊዎቻቸውም የምርጫው ውጤት እንዳጠራጠራቸው እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ በተለያዩ ምክንያቶች ለአንድ ሳምንት ተላልፎ የነበረው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመራጮችና በፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጣን ሲያስነሳ ሰንብቷል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በምርጫ ሜዳው ላይ ሲጋልቡ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ቡሀሪና የቀድሞውን ምክትል ፕሬዚዳንት አቡበከር አቲኩን ያፋጠጠ ነበር፡፡ በምርጫው ሂደት በሁለቱ ተወዳዳሪዎች ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭትም 50 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው፡፡ አሁንም ውጤቱን ተከትሎ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል፡፡
የቡሃሪ ማሸነፍ ደጋፊዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን በዙሪያቸው የሚገኙ ታላላቅ ባለስልጣናትንም ያስፈነጠዘ ነበር፤
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በኢያሱ መሰለ