የ12ኛ ከፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና የተማሪዎችን መጪ እጣ ፈንታ የሚወስን ነው። ፈተናው በአንድ የተማሪ ህይወት ላይ ወሳኝ ሚና ያለው እንደመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው። ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ከሰሞኑ የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አፈጻጸም የተሳካ እንዲሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። ፈተናው ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 የሚሰጥ መሆኑም ታውቋል።
የውይይቱ ዋና ዓላማ የ2013 ፈተናን ለመስጠት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መወያየትና አቅጣጫ ማስቀመጥ ሲሆን ለዚህም የ2012 ዓ.ም አፈጻጸምን ተመልክቶ ጠንካራ ተሞክሮዎችን እንደግብዓት መጠቀም፤ ደካሞቹንም ለማረም ያለመ ነው።
የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በኮሮና ወረርሽኝ እና በአንዳንድ አካባቢዎች በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ይሰጥ ከነበረው ጊዜ ዘግይቶ መሰጠቱ እንደ አንድ ችግር ተጠቅሷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፈተናውን በኦን ላይን ለመስጠት የተያዘው እቅድም ቁሳቁስ /ታብሌቶች/ በወቅቱ ባለመድረሳቸው ምክንያት በተለመደው ሁኔታ ለመስጠት አስገድዷል። የፈተና ደንብ መተላለፍ፣ የትግራይ ክልል ተማሪዎችን ለመፈተን ተግዳሮት ማጋጠሙ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ችግሮች የሚባሉት ናቸው።
ያም ሆኖ በየደረጃው ባለ አመራር ሥራው በትኩረት መከናወኑ፤ ክልሎች ለሥራው ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸው ፤ የቴክኒክ ብቃት መኖሩ፤ በተማሪዎች፣ በወላጆችና በመምህራን መካከል የባለቤትነት መንፈስ መኖሩ እና የጸጥታ ኃይሉ ዝግጁነት ለስኬቱ አስተዋጽኦ ያደረጉ ዋና ዋና ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል።
ከዚህ አፈጻጸም በመማር ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 የሚሰጠው የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም የተሳካ እንዲሆን ቅድመ ሥራዎች መሠራታቸው በውይይቱ ተመላክቷል። ኤጀንሲው ባቀረበው የንቅናቄ ሰነድና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ባለድርሻ አካላቱ ተወያይተዋል።
ዶክተር ዲላሞ ኦቴሬ የቀድሞው የሀገር አቀፍ ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ፤ በአሁኑ /በምክትል ርዕሰ መሰተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ/ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት በየዓመቱ የሚደረገውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና በተለይም ከሁለት ዓመት ወዲህ በመደበኛ ፕሮግራም ለመሥጠት ታቅዶ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በወቅቱ መሥጠት አልተቻለም።
በዚህ የተነሳ የ2012ዓ.ም ፈተናን በ2013 ዓ.ም ፤ የ2013 ዓ.ም ፈተናንም በ2014 ዓ.ም ለመሥጠት ሁኔታዎች ማስገደዳቸውን ተናግረዋል። በዚህ ወር መጨረሻ ላይ የሚሠጠውን ፈተና በአግባቡ ለማከናወን ከአለፈው ዓመት የተወሰዱ ተሞክሮዎችን በመቀመር ዝግጅት ሲደረግ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ፈተናው በሀገር አቀፍ ደረጃ ስኬታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን ከኤጀንሲው ዝግጅት ባሻገር የባለድርሻ አካላት ሚናም ወሳኝ ነው። በዚሁ መሠረት ለክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ ለፌዴራልና ክልል ፖሊሶች ፣ ለፖለቲካ አመራሮችና የህዝብ ተወካዮች፤ ለሱፐርቫይዘሮች ፣ ለማህበረሰቡ ተወካዮች አጠቃላይ የፈተናውን አተገባበር በተመለከተ የሥራ አቅጣጫና ሁሉም ባለድርሻ አካል ምን እንደሚጠበቅበት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሠራት ጀምሯል። በእለቱ እየተከናወነ የነበረው ውይይትም የዚሁ አካል መሆኑን የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ፈተናው ላይ የሚቀመጡት ተማሪዎች ብዛትም ስድስት መቶ አሥራ ሰባት ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ እንደሆነ አሳውቀዋል። በኢትዮጵያ ታሪክ በዚህ ደረጃ ለ12ኛ ክፍል ፈተና የተዘጋጁ ተማሪዎችን መመልከት የመጀመሪያ ነው ተብሏል። በመሆኑም በተደራጀ፣ በተቀናጀና በባለቤትነት መንፈስ ለመሥራት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል። ምንም አይነት የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት፣ ኩረጃ እንዳይኖር ሁሉም ኃላፊነት ወስዶ ለመሥራት በሚያስችል ሁኔታ መነጋገር ማስፈለጉን ገልጸዋል።
ጉዳዩ እስከታችኛው የመንግሥት መዋቅርና እስከ ወላጆች ድረስ ትኩረት እንዲያገኝ ተመሳሳይ መድረኮች በማዘጋጀት በቀሩት ጊዜ ሥልጠናዎችና የሥራ መመሪያዎች እንደሚሰጡ ዶክተር ዴላሞ ተናግረዋል።
ኤጀንሲው እስከ አሁን ሁለት ዋና ዋና ተግባራትን እንዳከናወነ ተናግረዋል። እነዚህም በአጠቃላይ የሕትመት ሥራው በደህንነት ካሜራ ቁጥጥር ስር እንዲሆን ማድረግ መቻሉ ተጠቅሷል። የመጀመሪያው አስቀድመው ፈተናዎች ሲዘጋጁ እና በባለሙያዎች እጅ ላይ እያሉ አያያዛቸው በባለሙያዎች ተፈትሾ ደህንነታቸው የተረጋገጠ መሆኑ ታውቋል።
ቀጣዩ የሕትመት ሥራ ነው። በሕትመት ክፍል ብቻ ስድስት ካሜራዎች ተገጥመው 24 ሰዓት ቁጥጥር ሲያደርጉ እንደነበር ተወስቷል። ይህም ከዚህ ቀደም አጋጥሞ የነበረውን የፈተና ደህንነት ችግር ለማስቀረት አጋዥ ነው ተብሏል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከስልሳ በላይ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በእያንዳንዱ ቁልፍ የፈተና ሕትመት ሥራዎችና በማተሚያ ቤቱ ዙሪያ ጠንካራ ጥበቃ ሲያደርጉ መክረማቸውን ተገልጧል። በፈተና ሕትመት ሥራውን የሚሠሩ ሠራተኞችም ሲገቡና ሲወጡ ጥብቅ ፍተሻ ተደርጓል።
በዘንድሮው ዓመት ፈተና የተዘጋጀው በአሥር የትምህርት አይነቶች ሲሆን ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘንድሮ በፈተና ውስጥ ያለተካተተ መሆኑ ታውቋል። በመሆኑም በአሥር የፈተና ዓይነት አራት ሚሊዮን ሦስት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሺህ አምስት መቶ ዘጠና ሁለት የፈተና ወረቀቶች ሕትመት ተጠናቋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የደህንነቱ ጉዳይ ቀደም ሲል በተገለጸው መሠረት ትኩረት ተሠጥቶት በፖስታና በሸራ የማሸጉ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል። በቀጣይም የስርጭት የክምችትና የፈተናው ሂደት በተገቢው መንገድ እንዲከናወን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመሥራቱ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
እስከ አሁን ድረስ ሁለት ሺህ ሰላሳ ስድስት የፈተና ጣቢያዎች እና ስልሳ ሦስት ተጨማሪ ንዑስ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ድርጅቱ አሳውቋል። በነዚህ ፈተና ጣቢያዎች ላይ ከአርባ አንድ ሺህ ስምንት መቶ አሥራ አንድ በላይ አስፈጻሚዎችን ለማሰማራት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል። እነዚህን ስራዎች ለማከናወን ከ188 ሚሊዮን ብር በላይ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተጠቅሷል። ይህም ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ለዚህ ብሄራዊ ፈተና የተያዘው በጀት ምን ያህል ትኩረት እንደተሰጠው የሚያመላክት ነው።
የተጠቀሰው የተፈታኞች ቁጥር የትግራይ ክልልን የማያካትት እንደሆነ ተገልጿል። በትግራይ ክልል አጎራባች ባሉና የጸጥታ ችግር ባለባቸው የአማራና የአፋር ክልል በሚገኙ አንዳንድ ዞኖች በመርሐ ግብሩ መሠረት ለመፈተን የሚያስችል ሁኔታ ካለና ለፈተናው ዝግጁ መሆናቸው በወላጆችና በተማሪዎቹ ከተረጋገጡ ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋል። ካልሆነ ግን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ጊዜው በማያዛባ መልኩ ወደፊት ሌላ የፈተና መርሐ ግብር ወጥቶላቸው እንዲፈተኑ ይደረጋል ተብሏል።
እያንዳንዱን የፈተና ሂደትና አተገባበር የሚከታተል ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን የተናገሩት የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ከትምህርት ሚኒስትር፣ ከሀገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከመረጃ ደህንነት የተውጣጡ አባላት ያሉት ነው።
ዋና ተልእኳቸውም በሀገር አቀፍ ደረጃ አጠቃላይ የፈተና ቅድመ ዝግጅት መደረጉን መገምገም፣ ፈተናውን በበላይነት መምራት እና ተፈጻሚነቱን ማረጋገጥ ነው። ፈተና አጠቃላይ ቅንጅታዊ ሥራን የሚፈልግ እንደመሆኑና ወቅቱም ያን የሚጠይቅ ስለሆነ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል እየተናበበ በመሥራት ለፈተናው ስኬታማነት የራሱን ሚና ይጫወታል። የውይይቱም አስፈላጊነት ለዚህ እንደሆነ ተገልጧል።
ፈተና በአምስት ቦታዎች ላይ ችግር ይገጥሙታል ተብሎ ይታሰባል ያሉት ዳይሬክተሩ እነዚህም ፈተና ሲዘጋጅ፣ ሲታተም፣ ሲጓጓዝ፣ ፈተና ጣቢያ ሲቀመጥ እና ፈተናው ሲሰጥ ነው ብለዋል። እስከ አሁን ከዝግጅትና ህትመት አንጻር በፊዚካልም በቴክኖሎጂም ተደግፎ ደህንነቱ የተጠበቀ ፈተና እንዲሆን ማድረግ ተችሏል። ከዚህ በኋላ በስርጭት በክምችትና በፈተናው ቀን ያሉ ሁኔታዎች ያለምንም ችግር እንዲከናወኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ ነው።
ከእርማትና ውጤት ጋር በተያያዘ ተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ጥያቄ እንደሚቀርቡ የተናገሩት ዶክተር ዴላሞ ይህን ችግር መቅረፍ የሚቻለው መጀመሪያ አድሚሽን ካርዳቸው ላይ ያለው ኢንፎርሜሽን በአግባቡ መሞላቱን ተማሪዎች ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ስማቸውን፣ ፆታቸውን፣ የሚፈተኗቸውን ትምህርቶች ብዛት ካርዱ ላይ ያለው መረጃ በሙሉ እነርሱን የሚገልጻቸው መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። አንድ ጊዜ ከታረመ በኋላ ግን የተሳተ ቢሆን እንኳን መልሶ ለማስተካከል የሚከብድ በመሆኑ ከመፈተናቸው በፊት አድሚሽን ካርዱ ላይ ያለው መረጃ እነርሱን የሚገልጻቸው መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ችግር ካጋጠማቸውም ወዲያውኑ ለድርጅቱ በማሳወቅ እንዲስተካከል ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል። እንዲህ አይነቶቹን ችግሮች አስቀድሞ መፍታት ከተቻለ በዕርማትና በውጤቱ ላይም ችግር ሊኖር እንደማይችል ድርጅቱ አስታውቋል።
አቶ ተፈራ ፈይሳ የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር በበኩላቸው እንደተናገሩት ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ያለቅንጅት በኤጀንሲው ብቻ የሚከናወን አለመሆኑን ገልጸዋል።
ያለፈው ዓመት ተሞክሮም ይህንን ያስተማረ በመሆኑ ዘንድሮ የተጠናከረ ቅንጅት በመፍጠር ፈተናውን ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል። በተለይም ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ችግር አንጻር የጸጥታ ሃይሉ ሚና ትልቅ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከፈተናው ዝግጅት ጀምሮ ተማሪዎቹ ተፈትነው ወደ ቤታቸው እስከሚሄዱ ድረስ የጸጥታ አካላት ሚናቸውን የሚወጡበት አሠራር መዘርጋቱን ተናግረዋል። አሁን ላይ ኤጀንሲው አብዛኛውን ሥራውን እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተፈራ ቀሪው ሥራ የጸጥታ ሃይሉ፣ የማህበረሰቡ፣ የተማሪውና የሌሎችም ባለድርሻ አካላት እንደሆነ ጠቅሰዋል። እነዚህ አካላትም ሥራውን በባለቤትነት ተረክበው ተማሪዎች በሰላም እንዲፈተኑ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ከወዲሁ የጋራ መድረኮችን በመፍጠር ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ከሚያረጋግጡ ጉዳዮች አንዱ ደህንነቱ የተጠበቀ ፈተና መስጠት እንዲሁም በዚያው ተከትሎ የተማሪዎችን ብቃት ማረጋገጥ ሲቻል ነው ሲሉ ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ፈተና ዓላማው ሰርተፊኬት ማደል ሳይሆን ቀጣይ ሀገሪቱን የሚመሩ ብቃት ያላቸው ዜጎችን እንደ ችሎታቸው አንጠርጥሮ በማውጣት ተገቢ ቦታቸውን እንዲያገኙ ማስቻል ነው። የተፈታኞቹ ቁጥር ከአምናው በእጥፍ የጨመረ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ አመራሩ ህዝቡና የጸጥታ አካላት ከአምናው በላቀ ሁኔታ ሠርተው ፈተናው ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። አምና ተማሪዎች ፈተናውን በኦን ላይን እንዲፈተኑ ለማድረግ ጥረት ተደርጎ በኮረና ወረርሽኝ ምክንያት ቁሳቁሶች/ ታብሌቶችን/ ማቅረብ ባለመቻሉ ኤጀንሲው በተለመደው መንገድ ለመሥጠት መገደዱን ተናግረዋል። ዘንድሮም ይህ ችግር ባለመቀረፉ ምክንያት የፈተናው አሠጣጥ ከአምናው የተለየ አለመሆኑን ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙ ባለድርሻ አካላትም የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት የሀሳብ ልውውጥ አድርገዋል። ፈተናው የተጠቀሱ ተማሪዎችን በሙሉ ተደራሽ ያደርጋል ወይ? የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች እንዲፈተኑ ይገደዳሉ ወይ? ምን አማራጭ ተዘጋጅቶላቸዋል? የሚሉንና ሌሎች ጥያቄዎችንም ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። ወይይቱ በቀጣይም እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ ባለድርሻ አካላት እንደሚደረግና ከፈተናው እለት በፊት በተለይም በጸጥታው ዘርፍ ጠንካራ ሥራዎች እንደሚሰሩ ተገልጿል። በሚኮራረጁና የፈተና ደንብና ስርዓትን በሚጥሱ ተፈታኞች ላይ ኤጀንሲው ጠንካራ ርምጃ መውሰድ እንደሚገባውም ተወያዮቹ ሀሳብ ሰጥተዋል። የኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን የመቀበያ ጊዜያቸው እንዳይዛባ ኤጀንሲው ፈተናውን በአጭር ጊዜ አርሞ ውጤት የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጿል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2014