ለቀስተኞቹ ከቤተክርስቲያኑ አፀድ ቀድመው ተገኝተዋል። ገሚሶቹ ከቤት የሚነሳውን አስከሬን ለማጀብ በሟች መኖሪያ ቤት የደረሱት ገና በጠዋቱ ነው። አብዛኞቹ የሰውዬውን ስም እያነሱ፣ ደግነት መልካምነቱን ያስታውሳሉ። በድንገቴው ሞት እያዘኑ አምርረው ያለቀሳሉ።
ከለቀስተኞቹ መሀል አንዳንዶቹ የሟችን የቅርብ ዘመዶች ከማጽናናት አልፈው ከኀዘናቸው ለመገሰጽ በየአፍታው ይነሳሉ። እንዲህ በሆነ ጊዜ ለቅሶው ለደቂቃዎች ጋብ ያለ ይመስላል። ጥቂት ቆይቶ ከደጅ የሚመጡ ወዳጅ ዘመዶች ወደግቢው እየጮሁ ይዘልቃሉ። ይሄኔ ለአፍታ ቀዝቀዝ ያለው ለቅሶ እንደ አዲስ ተቀስቅሶ ጩኸት እና ሁካታው ይበራከታል።
የቀብር ሰዓቱን ለመወሰን፣ የሚያስፈልገውን ለመከወን የቅርብ ዘመዶች ዞር ብለው ይመክራሉ። ሁሉም ለእንግዶች መቀበያ ያሻል የሚሉትን እያደረጉ ነው። ዕድረተኞች፣ ድንኳኑን፣ ወንበር ጠረጴዛውን፣ ሰሀን መጠጫውን ለማሟላት ከወዲያ ወዲህ ይላሉ። ሴት ዕድርተኞች በየጥጉ ተቀምጠው ሥራውን ያጣድፋሉ። ንፍሮው የሚቀቀልበት፣ ወጡ የሚሠራበት ብረት ድስትና እንጨት ቀርቧል። አሁንም በሟቹ ግቢ እየቆየ የሚቀሰቀሰው ለቅሶ ጎልቶ መሰማቱን ይዟል።
የቀብር ቦታውንና ሰዓቱን ያላወቁ አንዳንዶች ቤት ባሉ ሰዎች ስልክ እየደወሉ በቂ መረጃ ይወስዳሉ። አሁን የአቶ መኮንን ኃይሉ የቀብር ስነስርዓት የሚፈጸመው በኮዬ ፈጬ አቦ ቤተክርስቲያን ከቀኑ ሰድስት ሰዓት መሆኑን አብዛኞቹ አውቀዋል።
በቤትና በቤተክርስቲያን የተወሰነው ለቀስተኛ የቀብር ሰዓት መድረሱን እየጠበቀ ነው። የሟችን ፎቶግራፍ ተከፋፍለው የያዙ ቤተዘመዶች ማልቀሳቸውን አላቆሙም። እርሙን ከሚያወጣው ለቅሶ ደራሸ ጋር እየተነሱ እዬዬ ማለታቸውን ቀጥለዋል።
አሁን ሰዓቱ እየገፋ ነው። ይህን የሚጠብቁ ውስጥ ያሉትን ኀዘንተኞች ወደ ውጪ አስወጥተው አስከሬኑን ከመኪና ለመጫን ተዘጋጅተዋል። እንዲህ መሆኑን ያወቁ የቅርብ ሰዎች በመጨረሻዋ ሰዓት ለቅሷቸው በርትቷል። ከቀደመው ይበልጥ ጩኸት እሪታው ደምቆ ቤቱ በሰዎች አጀብ ተጨናንቋል። የሟች የመጨረሻ ሽኝት፣ የስንብቱ ጊዜ ደርሷል።
ደሳለኝ ጌጡ – ከዓመታት በፊት
ደሳለኝ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ነው። ወላጆቹ ዕድሜው ከፍ እንዳለ ትምህርትቤት አስገቡት። እንደእኩዮቹ ደብተር ይዞ ቀለም ቆጥሮ ለመመለስ አልተቸገረም። አንደኛ ክፍል ገብቶ መማር ጀመረ። የትምህርት ዘመኑ እንዳለቀ ወደ ሁለተኛ ክፍል ተሻግሮ ቀጣዩን ዓመት ጠበቀ።
የሁለተኛ ክፍል ትምህርት ለደሳለኝ መልካም ሆነለት። ዓመቱን በጥንካሬ ተምሮ ለሦስተኛ ክፍል ተዘጋጀ። ክረምቱን እንደልጆች ሲጫወት ያሳለፈው ታዳጊ በአዲሱ ዓመት አራተኛ ክፍል ለመግባት መማሪያዎቹን ሰነደ፣ ወላጆቹ ያስፈልገዋል የሚሉትን አሟልተው፣ ልብስ ጫማውን ገዝተው ትምህርት ቤት ላኩት።
በአዲሱ ዓመት የተገናኙት ደሳለኝና ትምህርትቤቱ እንደቀድሞው አልሆኑም። እሱን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች በትምህርትቤቱ መማር እንደማይችሉ ተነገራቸው። ወላጆችና ተማሪዎች ለምን? ሲሉ ጠየቁ። ትምህርት ቤቱ ስለመዘጋቱ ምላሽ ተሰጣቸው። በወቅቱ አማራጭ የነበራቸው ተማሪዎች ከአቅራቢያ ትምህርቤት ገቡ። ዕድሉን ያላገኙት ርቀው ለመሄድ ተገደዱ። ደሳለኝን የመሰሉ ጥቂቶች በተስፋ መቁረጥ ቤታቸው ቀሩ።
አሁን ደሳለኝና ትምህርት ተኳርፈው መገናኘት አቁመዋል። ወላጆቹ ስለተቋረጠው ትምህርት ግድ የሰጣቸው አይመስልም። እሱም ቢሆን ሌሎች አማራጮችን ማፈላለግ ይዟል። በዕድሜው ከፍ ማለት የጀመረው ታዳጊ ቤት መዋል ቢከብደው መተዳደሪያ ፈለገ። ያሰበውን አላጣም። በአቅሙ የሚመጥነውን እየተሸከመ፣ ለትንሽ ትልቁ እየተላከ የዕለት ጉርስ ማግኘት ለመደ።
ውሎ ሲያድር ደሳለኝ በቀን ሥራ ውሎ የተሻለ ብር መቁጠር ጀመረ። ሥራው እንጀራው ሆኖም ዓመታትን ዘለቀበት። ከሦስት ዓመት በፊት ከአንዲት ጉብል ተዋወቀ። ወደዳት፣ ወደደችው። አብሮነታቸው ቢሰምር ከእሷ ቁምነገርን ፈለገ። ሃሳቡን በዝርዝር ነገራት። አልተቃወመችም። ትዳር መያዝ ፣ጎጆ መቀለስ የጋራ ዓላማቸው ሆነ።
አሁን ደሳለኝ ከሚወዳት ሴት ጋር ህይወት ጀምሮ ባለትዳር ሆኗል። ከኑሮ አጋሩ ጋር ተሳስበው ያድራሉ። ‹‹አንተ ትብስ እኔ›› የሚሉበት ጎጆም ሰላም ውሎ ያድራል። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ቤታቸውን በፍቅር የሚያሞቅ፣ የትዳራቸውን ገመድ በጽኑ የሚያጠብቅ አጋጣሚ ተፈጠረ።
የደሳለኝ ባለቤት የመጀመሪያዋን ሴት ልጅ ‹‹እነሆ›› አለችው። ጨቅላዋ እንግዳ ህይወታቸውን ልትሞላ፣ ኑሯቸውን ልታሞቅ ታላቅ በረከት ሆነች። በቤቱ የልጅ ሳቅና ለቅሶ ተሰማ። ጥንዶቹ በተሰጣቸው የልጅ ፍሬ ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ። ሁለቱ ሦስት ሆኑ። የቤተሰቡ ቁጥር ጨመረ። ደስታቸው በእጥፍ ተቆጠረ።
አሁን ትንሽዬዋ ልጅ ስድስት ወራት ቆጥራለች። ጥንዶቹ ከዚህ በኋላ የተለየ ትኩረት እንደሚያሻት አሳምረው ያውቃሉ። ተጨማሪ ምግብ ፣ ተጨማሪ እንክብካቤ ትፈልጋለች። ኃላፊነቱ የእናት አባቷ ሆኖ የሚያስፈልገውን እያሟሉ ያሳድጓታል። በተለይ አባወራው የቤቱን ጉድለት ሊሞላ፣ ክፍተቱን ሊደፍን ግድ ይለዋል። ሚስቱን እያገዘ የመጀመሪያ ልጁን ይንከባከባል። ለጎጆው ሰላም፣ ለህይወቱ መለምለም ይህን ሲያደርግ ድካም አያውቅም።
ደሳለኝ ትናንት የተነፈገውን የትምህርት ዕድል ዛሬ በልጁ እንዲደገም አይሻም። ከህይወቱ ተምሮ እሷን ለተሻለ ደረጃ ያበቃል። እሱ ባይማርም ሴት ልጁን ያስተምራል። ይህ ምኞትና ዕቅድ ከልጁ መወለድ ጀምሮ አብሮት ሰነባብቷል። ነገን የተሻለ ለማድረግ፣ ዛሬን መበርታት፣ መጠንከር እንዳለበት ደጋግሞ ያስባል።
ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም – የቀብሩ ዕለት
የጥቅምት ወር ሊጠናቀቅ ሁለት ቀናት ቀርተውታል። ቅዝቃዜው እንደበረታ ነው። ከጠዋት ፀሐይ ጋር ማልዶ የሚከሰተው ውርጭ ዛሬም እስከ ቀትር ዘልቋል። በርካቶች ሙቀትን እንደሻቱ አርፍደዋል። በንፋስ ታጅቦ ሽው የሚለው ቅዝቃዜ ከብዙዎች ጋር ነው።
ደሳለኝ ገና በጠዋቱ የደረሰው መርዶ አስደንግጦታል። ሞተ የተባለውን ሰው ያውቀዋል። የሰፈሩ ልጅ ነው። ከሞቱ አሟሟቱ አሳዝኖታል። ውሃ ጉድጓድ ውስጥ በመግባቱ ህይወቱ እንዳለፈ ተነግሮታል። ድንገቴውን ለቅሶ እንደሰማ ከቀብሩ ለመገኘት ቦታና ሰዓቱን ጠየቀ።
ቀብሩ በዚሁ ዕለት ኮዬፈጬ በሚገኘው አቦ ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ተነገረው። ሰዓቱን አጣራ፣ ከቀኑ ስድስት ሰዓት መሆኑን አወቀ። እሱን ጨምሮ ሌሎች የቅርብ ሰዎች በስፍራው እንደሚገኙ አልጠፋውም። ከተባለው ቦታ በሰዓቱ ለመድረስ ራሱን አዘጋጅቶ ወጣ።
አሁን ለቀስተኞቹ አስከሬን አጅበው ከመኖሪያው ወጥተዋል። የሟች የቅርብ ዘመዶችና ወዳጆቹ አምረረው እያለቀሱ ነው። በሚስትዬው ዙሪያ በርከት ያሉ ሰዎች ይታያሉ። አስከሬኑ ከመኖሪያ ቤት እንደወጣ በእግርና በመኪና ጉዞ ተጀመረ፤ ወደ ቤተክርስቲያን።
የቤተክርስቲያኑ አጸድ በሰዎች ተጨናንቋል። ቀብር ለመፈጸም በስፍራው የተገኙ አንዳንዶች መለስ ቀለስ እያሉ ይጠይቃሉ። ዕለቱን በተመሳሳይ ሰዓት የሚፈጸሙ የቀብር ስርዓቶች ከአንድ በላይ ናቸው። አብዛኞቹ በስህተት ከሌላው ዘንድ እንዳይሄዱ ፎቶግራፎች ያያሉ። ስም እያጣሩ ያረጋግጣሉ። ትክክለኛውን መረጃ ያገኙት ከነበሩበት ተነስተው ወደ ቀብር ያመራሉ።
ደሳለኝ በስፍራው ሲደረስ የመጣበትን ለቅሶ ለይቷል። ሰብሰብ ብለው ከተቀመጡት መሀል አብዛኞቹን ያውቃቸዋል። ሰዓቱ ደርሶ አስከሬኑ እሰኪመጣ አሻግሮ ተመለከተ። ሌሎች ቀባሪዎች ከአጠገቡ እየተነሱ ነው። ከደቂቃዎች በኋላ እሱ የሚጠብቃቸው ለቀስተኞች ታዩት። የአጎቱን ልጅ ደበበንም ከሩቁ አስተዋለው። እሱን ጨምሮ ሌሎች ወደ ግቢው እያለፉ ነው። ከነበረበት ተነስቶ ሊቀላቀላቸው ተጠጋ።
አሁንም የሟች ስም እየተጠራ፣ ደግነቱ እየተወሳ፣ መለቀሱን ቀጥሏል። ለኀዘንተኞች ቀረብን ያሉ አንዳንዶች እያለቀሱ ያጽናናሉ። በግቢው የደረሰው አስከሬን ቤተክርሰቲያኑን ዞሮ ወደቀብር ስፍራው አመራ። ይህን ያዩ ብዙዎች ከኋላ ተከተሉ። ጥቂቶች ሌሎች ቀብረው እሰኪመለሱ በነበሩበት ቆዩ።
አስከሬኑን የተሸከሙ በሰዎች መሀል አቆራርጠው ወደ መቃብር ቦታው አመሩ። በርካቶች ሀውልቶችን እየታከኩ፣ አንዳንዶች ከላይ ወጥተው እየረገጡ፣ ወደፊት ተጓዙ። እዚህም እዚያም የተቆፈሩ ጉድጓዶች በለቀስተኞች ተከበዋል። ኀዘንተኞቹን የደገፉ ወዳጅ ዘመዶች ሰዎቹ ራሳቸውን እንዳይጎዱ ይጠበቃሉ። ድምፃቸው ጎልቶ የሚሰማ፣ በልባቸው የሚያዝኑ፣ በትካዜ የተዋጡ የመጨረሻውን ስንበት ሊፈጽሙ ተዘጋጅተዋል።
ደሳለኝ ለቀብር ከመጡት መሀል ጥቂቶቹን እየዞረ አስተዋለ። ካያቸው ውስጥ አብዛኞቹን ያውቃቸዋል። ፀሐዩን በእጁ ከልሎ ከዳር እንደቆመ ቆየ። አሁን የቀብር ሰዓቱ ተቃርቧል። ጉድጓዱን ያዘጋጁት ቀባሪዎች በሳጥን የመጣውን አስከሬን ተሸክመው በስፍራው ለማሳረፍ ግራና ቀኝ ይዘዋል።
ድንገቴው ድምፅ…
ደሳለኝ ከኀዘንተኞቹ መሀል እንደቆመ የሚሆነውን ያስተውላል። አስከሬኑ ወደ ጉድጓዱ ለመግባት ጫፍ እንደደረሰ የተሰማው ድንገቴ ድምፅ እሱንም አስደግጦታል። በትክክል ለጆሮው የደረሰው ድምፅ የሽጉጥ መሆኑን አውቋል። እንዴትና ለምን እንደሆነ አልገባውም። ድምፁን ተከትሎ ዓይኖቹን ወረወረ። የሟች ሚስት ወንድም ሽጉጡን በእጁ እንደያዘ በድንጋጤ ክው ማለቱን አስተዋለ።
መሳሪያው ወደ ሰማይ መተኮሱን የጠረጠረው ደሳለኝ ሌሎች ወዳተኮሩበት አንገቱን አስግጎ ተመለከተ። ከቀብሩ አፋፍ ቆሞ ያየው ሰው ወድቋል። ከተኳሹ የቅርብ ርቀት የወደቀውን ወጣት ለመለየት ሞከረ። ዓይኑን ማመን፣ ያየውን መቀበል አልቻለም። ከደቂቃዎች በፊት አሻግሮ ያየው የአክስቱ ልጅ ደበበ ነው።
የደበበ እናት አጠገባቸው የወደቀ ልጃቸውን እንደደገፉ ራሳቸውን ይዘው ይጮኻሉ። ደበበ ከጭንቅላቱ የሚፈሰው ደም ግንባሩን አልፎ ፊቱን ማልበስ ይዟል። ደሳለኝ ራሱን መቆጣጠር ተሳነው። ቦታው በሰው አጀብ ቢጨናነቅም አጠገቡ ያሉትን እየገፋ፣ እየገፈተረ ወደፊት አለፈ።
ከወደቀው አጠገብ ሲቃረብ መክብብ የተባለው ደበበን ቁልቁል እያስተዋለ አጠገቡ መቆሙን ተመለከተ። መክበብ ፊቱ ላይ የሚታየውን ድንጋጤ መደበቅ አልቻለም። በቀኝ እጁ የጨበጠውን ጥቁር ሽጉጥ አጥብቆ እንደያዘ ይንቀጠቀጣል። ደሳለኝ ከወደቀው የአክስቱ ልጅ ተጠግቶ በቅርበት አስተዋለው። ቁስለኛው እየተነፈሰ፣ እየተላወሰ አይደለም።
ደሳለኝ ቀና ብሎ ወደ መክብብ አፈጠጠ። መክበብ በቀኝ እጁ ደበበ የተመታበትን ሽጉጥ አጥብቆ ይዟል። ደሳለኝ መታገስ አልቻለም። በእጁ ያለውን ሽጉጥ ለመንጠቅ አጥብቆ ታገለው። መክብብ በሆነው ሁሉ ድንጋጤ እያብረከረከው ነው። ከደሳለኝ ሊጣላ ሊታገል አልወደደም። ደሳለኝ ስሜቱን ለማስተዋል ጊዜና ትዕግስት አልነበረውም። በእጁ ያለውን ሽጉጥ ለቀም አድርጎ ለግንባሩ አነጣጣረ። ጣቶቹ ቃታውን ለመሳብ አልዘገዩም።
የአንድ ጥይት ድምፅ ደምቆ ተሰማ። ወዲያው መክብብ በቁመቱ ልክ በጀርባው ተዘረጋ። ለቀስተኛው በሚያየው እውነት መረበሽ፣ መደናገጥ ያዘ። ጩኸት ግርግሩ፣ ሩጫ ትርምሱ አየለ። በደቂቃዎች ልዩነት የሁለቱን ሰዎች አስከሬን ያዩ በፈርሀት ራዱ። የቀደመውን ሰው ጨምሮ ሦስት ሙታን በመቃብሩ ዙሪያ ተጋድመዋል። ጥይቱን የሰሙ፣ የሆነውን የተመለከቱ ሁሉ ኀዘናቸው በረታ።
ደሳለኝ የአክስቱን ልጅ ህይወት ያጠፋውን ገዳይ መልሶ በመግደሉ ለጊዜው እፎይ ያለ ይመስላል። ጥቂት ቆይቶ ግን ድንጋጤና ግራ መጋባት ያዘው። የሁለቱ ሟቾች አወዳደቅና ገጽታ በፊቱ ተመላለሰ፤ጨነቀው። እየተደናገረ ሽጉጡን ይዞ በፍጥነት ተራመደ፤ የለቀስተኛው ግራ መጋባትና ግርግር አገዘው። በሰዎች መሀል ተሹሎክሉኮ ከግቢው ሲወጣ የተከተለው፣ ያሰቆመው አልነበረም።
የፖሊስ ምርመራ…
የወንጀል ድርጊቱ ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ በስፍራው ተገኝቶ የሟቾችን አስከሬን አነሳ። ተገቢውን ምርመራ አጠናቅቆም ለጥያቄ የሚሻቸውን ምስክሮች አቅርቦ ጠየቀ። ምስክሮቹ የመጀመሪያው ተኳሽ አቶ መክበብ የሟቹ የቅርብ ሰው መሆኑን ተናገሩ። ድርጊቱን የፈጸመው ሆን ብሎ አለመሆኑንና ወደሰማይ ያለመው ጥይት ወደጎን አልፎ ደበበን እንደገደለው ቃላቸውን ሰጡ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ መርማሪ ዋና ሳጂን መብራቱ በአቶ ደበበ ሞት ምክንያት አቶ መክብብን ገድሎ ስላመለጠው ተጠርጣሪ ማንነት የሚያውቁትን እንዲያስረዱ ጠየቃቸው። ምስክሮቹ ተጠርጣሪው ደሳለኝ እንደሚባል፣ ለደበበ የአክስቱ ልጅ መሆኑንና በጥይት ተመቶ መሞቱን እንዳየ የገዳዩን ሽጉጥ ነጥቆ እንደገደለው ማየታቸውን አረጋገጡ።
መርማሪው መረጃዎቹን ሰንዶ ተጠርጣሪውን ለመያዝ የሚያስችሉትን ዝግጅቶች አጠናቀቀ። ከቀናት በኋላ የፖሊስ ጣቢያው ቢሮ በድንገት ተንኳኳ። በእጁ ስታር ሽጉጥ አጥብቆ የያዘ፣ ፊቱ በፍርሐትና ድንጋጤ የገረጣ አንድ ሰው ወደውስጥ ዘለቀ። ደሳለኝ ነበር።
ማንነቱን የተረዳው መርማሪ የሆነውን ሁሉ አንድ በአንድ እንዲያስረዳው ጠየቀው። ደሳለኝ በቀብሩ ቀን በለቀስተኞች መሀል የተፈጸመውን አጋጣሚ አስታውሶ መናገር ጀመረ። በድንገት በጥይት ተመቶ የወደቀውን የአክስቱን ልጅ ሞት ለመበቀል ሲል መክብብ የተባለውን ሰው በያዘው ሽጉጥ ተኩሶ እንደገደለው አመነ። መርማሪው የተጠርጣሪውን ቃል በወንጀል መዝገብ ቁጥር 572/ 12 ላይ በጥንቃቄ አሰፈረ።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014