ከሀገራችን ሕዝብ ብዙሃኑን ቁጥር የሚሸፍነው ጾታ ሳይለይ ወጣቱ ትውልድ ነው። ከአምስት ዓመት በፊት ከማእከላዊ ስታስቲክ ማእከል የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው የወጣቱ ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ 55 በመቶ ይሸፍናል። ይሄ የወጣት ቁጥር በሀገር ላይ ማምጣት ለሚፈልግ ሁለንተናዊ የእድገት ለውጥም ሆነ ለሀገር አድን የትግል ተልእኮ ወሳኝ መሆኑን የማህበራዊ ሳይንስ ጠበብቶች ይጠቁማሉ።
ጠበብቶቹ እንደሚናገሩት ታዲያ እንደ እኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ በኢጣሊያ ወረራ ጊዜ ሀገርን በማዳኑ ተግባር የወጣቱ ሚና ጉልህ የነበረ መሆኑን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። በየካቲቱ አብዮትም ቢሆን ለውጥ ፈላጊው ወጣት ግንባር ቀደም ሚና ነበረው። ዛሬም ቢሆን የሀገር ሉዓላዊነቱን ተግባር በማስከበርም ሆነ በተለያዩ መስኮች በመሰለፍ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ያለው ወጣት ሚና ከፍተኛ ነው። ይሄን የወጣቱን ሚና ዛሬ ላይ ከውስጥም ከውጪም ሉአላዊነቷን እየተገዳደረ ባለ ፈተና ውስጥ ያለችው ሀገራችን ከምንጊዜውም በላይ አጥብቃ እንደምትፈልገው ያነጋገርናቸው እናትና አባት አርበኞች እንዲሁም ራሳቸው ወጣቶቹ ይገልፃሉ። ወጣቱ የቀደምት እናትና አባት አርበኞችን ወኔ ሰንቆ፤ የሀገር መውደድና ፍቅርን ስሜት ታጥቆ፣ አደራቸውንም ጠብቆ ኢትዮጵያን ከውስጥም ከውጪም ከከበባት ችግር መታደግ እንዳለበትም ይመክራሉ። ትድግናው ጦርነት ገጥሞ ጥይት በመተኮስ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ በየተሰማራበት የልማት መስክ የየራሱን አሻራ በማሳረፍም መገለፅ ይችላል ባይ ናቸው።
መገናኛ አካባቢ በራይድ ትራንሥፖርት አገልግሎት የተሠማራው ወጣት አማኑኤል አበበ ልኬቱ ዘመኑ እንደደረሠበት ሥልጣኔ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የአሁኑ ትውልድ በልማቱም ሆነ በእናቶቹና በአባቶቹ ፅኑ ተጋድሎ ለረጅም ዓመታት ታፍራና ተከብራ የኖረች ሀገሩን ሠላም በማሥጠበቁ ረገድ የየራሡን አሻራ እያሳረፈ እንደሚገኝ ይናገራል። ይሄ የአባቶቹን አደራ መጠበቁን እንደሚያመላክትም ይገልፃል። ተግባሩ የሀገር ፍቅር ያለው መሆኑን የሚያሳይ መገለጫ ነው ብሎ ማለት እንደሚቻልም ይጠቅሳል። ሆኖም የበለጠ ለመጪው ትውልድ ከድህነትና ከውጪ ጫና ተፅዕኖ ነፃ የሆነች ሀገር ለማሥረከብ መትጋት እንደሚገባውም ያሣሥባል።
‹‹ለዚህ ብዙ መሥዋእትነት ከፍለው ሀገሪቱን ለኛ ያቆዩ የቀደሙ አባትና እናት አርበኞች የሀገር ፍቅር ሥሜትና ወኔ እንዲሁም ተሞክሮ ሥንቅ ይሆነናል›› ይላል።
ከ1928 እሥከ 33 ዓ.ም የፋሽሥት ኢጣሊያ ወረራ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ኢትዮጵያን አሁን ላለው ትውልድ ማሣለፍ የቻሉት የአባት አርበኛ መኮንን መሸሻ ተሞክሮ ቀዳሚው ነው። ተወልደው ያደጉት እዚህ አዲስ አበባ ውሥጥ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ሲሆን በመጪው ታህሳስ ወር 99 ዓመታቸውን ይይዛሉ። በወረራው ወቅት እሳቸው ቆሥለዋል። አባታቸውና አጎታቸውን ጨምሮ ታላቅ ወንድማቸው ጥላሁን መሸሻ አንድ እለት እስከ አፍንጫቸው ዘመናዊ መሣርያ በታጠቁ በ37 የፋሽሥት ኢጣሊያ ወታደሮች ተከብበው የነበረ መሆናቸውን አይዘነጉትም። መከበብ ብቻ ሳይሆን ጥይት እንደ ዝናብ ያወርዱባቸው የነበረ መሆኑንም ያሥታውሣሉ።
ሆኖም የ37ቱ ፋሽሥት ኢጣሊያ ወታደሮችና የሦሥቱ ኢትዮጵያዊያን የነፃነት ታጋዮች ፍልሚያ በወንድማቸው የአንድ ዓይን መስዋእትነት ብቻ በድል መጠናቀቁንም ያወሳሉ። ፍፃሜው ሊያምር የቻለው መሳርያ ብቻ ሳይሆን ጠንካራ የሀገር ፍቅር ሥሜትና ወኔ በመታጠቃቸው መሆኑንም ይገልፃሉ። እሳቸው ይሄን በውሥጣቸው ይዘው በ1969ኙ የሶማሌ ወረራ እንዲሁም ከ1991 እስከ 1992 በተደረገው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ባድመ፣ ሽራሮና ዛላአንበሳ ግንባር በመሰለፍ ጭምር የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማሥከበር መሠለፋቸውን ይናገራሉ። ሀገርን ጠብቆ ለተተኪው የማሥተላለፍ ትግል ቅብብሎሽ በመሆኑ እሳቸው ለዛሬ ትውልድ በዚህ መልኩ እንዳሥረከቡት የአሁኑ ትውልድም ለነገው በዚህ መልኩ ማሥረከብ እንደሚገባውም ምክራቸውን ይለግሳሉ።
ወሊሶ የተወለዱትና ያደጉት የአባት አርበኛ ወልደሠንበት ጉታ እና የልጃቸው የሻምበል የብርሃነ መሥቀል ወልደሠንበት ታሪክም የዚህ ዓይነቱ የዱላ ቅብብሎሽ ትግል ነጸብራቅ ነው። ጊዜው የፋሽስት ኢጣሊያና የሶማሌ ወረራ በመሆን ይለያይ እንጂ ሁለቱም የተሰለፉበት ሀገርን የማዳን ዓላማ አንድ ያደርጋቸዋል። የ94 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው አባት አርበኛ ወልደሰንበት ጉታ እንዳጫወቱን ከ1928 እስከ 1933 በተደረገው የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ተሳታፊ ናቸው። ከዚህ ቀድሞ በአፄ ምኒልክ ዘመን በነበረው የዚሁ ፋሽስት ወረራ ደግሞ የእሳቸው እናት አባት ተሳትፈዋል።
በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሳትፈው በተደጋጋሚ ቆሥለዋል። በዚህ መልኩ ያቆይዋትን ሀገር ለበኩር ልጃቸው ለሻምበል ብርኃነመስቀል አስተላልፈዋል። ሆኖም ለልጄ አስተላልፊያለሁ ብለው ሦማሌ የምስራቁን የሀገራችንን ክፍል በእብሪት ስትወር በኡጋዴን፣ በቀላፎ፣ በዋርዴርና በሌሎች ግንባሮች ከልጃቸው ጎን በመሰለፍ ሀገራቸውን ተከላከሉ እንጂ ዝም ብለው አልተመለከቱም። አቅም ቢያጥራቸውና ጉልበታቸው ቢደክምም ዛሬም የውሥጥ የጥፋት ኃይሎች በሀገራችን ላይ በከፈቱት ጦርነት ለመሳተፍ ልባቸው ይዳዳል። በ1917 ዓ.ም ነው የተወለዱት አባት አርበኛ ወልደሰንበት ጉታ አባታቸውና ታላቅ ወንድማቸው ከጠላት ሲፋለሙ ማይጮው ላይ ወድቀው የመቅረታቸውን ቁጭት ሰንቀው ነው በ1947 ዓ.ም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ነው ወደ ውትድርናው ዓለም የገቡት።
ለሀገር ፍቅርና ለውትድርና ያላቸው ሥሜት እጅግ ብርቱ ነው። ጨዋታቸው ሁሉ በሀገር ፍቅርና መውደድ የተሞላ፤ የውጊያና ጀግንነት ገድል ጎልቶ የሚንፀባረቅበት መሆኑን የበኩር ልጃቸው ሻምበል ብርኃነመስቀልም ይመሰክሩላቸዋል። አባት አርበኛ ወልደሰንበት በበኩላቸው እንደሚናገሩት ሻምበል ብርኃነመስቀል የመሠለ ሀገር ተረካቢና አደራ ጠባቂ ልጅ ማፍራት ያስቻላቸው እንዲህ ዓይነት የልጅ አስተዳደግና አቀራረፃቸው ነው።
ነፍሥ ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ ይሄ የአባታቸው ወኔ የሰረፀባቸው የበኩር ልጃቸው የዛሬው ሻምበል ብርሃነ መሥቀል ወልደሠንበት በተማሪነት ዘመናቸው ደግሞ እየጎለበተ መምጣቱን ይናገራሉ። የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በአጠናቀቁ ማግሥት የውትድርናን ዓለም ተቀላቀሉ። እንዳወጉን አባታቸው ለሀገራቸው ነፃነት ተጋድሎ ያደረጉበትንና የረገጡትን ቦታ ረግጠዋል። ‹‹አሠብ ላይ አባቴ በፈንጂ የቆሠለባትን አይፋ አይቻታለሁ›› ይላሉ። አክለውም ለ48ኛ ጊዜ እጩ መኮንን ተወዳዳሪ ሆነው ከውርሦ ማሰልጠኛ ተመርቀው ሲወጡም በቀጥታ ወደ ኡጋዴን ነው የዘመቱት።
ዋርዴር፣ ገላዲን፣ ቀለዋ፣ ቦህና በርካታ አካባቢዎች ያሉ ፀረ ሠላም ኃይሎችን ለመፋለም በቅተዋል፤ እስከ 1983 ዓ.ም ድረሥም ከኤርትራ ጋር በነበረው ጦርነት ተሳትፈዋል። ይሄ ዓመት ሊጠናቀቅ አምሥትና አራት ወራቶች ሲቀሩት ሁሉ አሠብ ቤሎል ውሥጥ ቆይተዋል። ይቺ ቦታ በመጨረሻው ሠዓት እጅግ ከፍተኛ መሥዋዕትነት የተከፈለባት እንደነበረች ያሥታውሳሉ። እሳቸው ቢተርፉም በነኝህ ሁሉ አውደ ውጊያዎች ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ አንድነት አብረዋቸው የተሠለፉ ጓዶቻቸው ወድቀው ቀርተዋል። ለሀገር ክብርና ነፃነት እጃችንን ለጠላት አንሠጥም ብለው ራሳቸውን የሠውት ቁጥርም ቀላል እንዳልነበር ይመሰክራሉ።
‹‹እኛ በወጣትነት ዘመናችን ከላብ እስከ ደም ለዚህች ሀገር መክፈል የሚገባንን መሥዋእትነት ከፍለናል›› ሲሉም ለወጣቱ የሚያስተላልፉት መልዕክት ይናገራሉ። በተጨማሪም ወጣቱ ከዚህ መካከል እኛ ዛሬ ላለንበት ህልውና የበቃነው እልፍ አእላፍ ዜጎች የህይወት መስዋእትነት ከፍለውልን ነው ብሎ ማሰብ አለበት። ሰላማዊ ሕይወት መኖር የሚችለው ሀገር ሠላም ሥትሆን መሆኑንም መዘንጋት የለበትም። የመጀመርያውን ትልቅ ኃላፊነት የሚወጣው ወጣቱ ነው። ምክንያቱም ጉልበት ያለው ወጣቱ ነውና ነው። ወጣቶች ናቸው ከፍተኛ መሥዋእትነት ከፍለው ሀገርን ያቆይዋት።
በመሆኑም አሁን ያለው ወጣት በዚህ በኩል ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት። ከነፃነት በላይ ምንም ነገር አለመኖሩን መገንዘብ ይኖርበታል። የነፃነት ትርጉሙ የሚታወቀው ነፃነትን ሲያጣ መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ባርነት መኖሩን ቆም ብሎ ማሠላሠል ይገባዋል። አይደለም በነፃነት ለመኖር፣ ለመዝናናትና ለመደሠት ወጥቶ ለመግባትና የጠቀለሉትን ለመጉረሥ እንኳን የሚያሥችል ሠላም ላይኖር መቻሉን ማሠቡ አሥፈላጊ ነው። ነፃነት ሲወራ ተራ ነገር ቢመሥልም ከምንም በላይ ትልቅ ነገር ነው። በመሆኑም ወጣቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ቆም ብሎ ሊያሥብ እንደሚገባ ይመክራሉ። ሻምበል ብርኃነመሥቀል አሁን ላይ አፍላ የወጣትነት ዘመናቸውን ለዚህች ሀገር መሥዋእትነት እየከፈሉ ያሉ ወኔ ያላቸው ሀገር ወዳድ ወጣቶችን ያደንቁና ያመሠግናሉ።
‹‹በዚህ ዘመን በነዚህ ወጣቶች ኢትዮጵያዊያኖች እጅግ ልንኮራ ይገባል ›› ይላሉ። ሌሎቹም ዜጎች ሀገር የጋራ መሆኗን ማወቅ እንደሚገባቸውም ያሳስባሉ። ይሄ እየሞተ፣ አንዱ እየቆሰለ ሌላው ላቡን እያፈሰሰ ሌሎቻችን ቁጭ ብለን የምናይበት ሁኔታ መኖር የለበትም ባይ ናቸው። የሚመጣው ሰላም የጋራ እንደመሆኑ ውድቀትም የጋራ ነውና ምንቸገረኝነት አይሰራም። በመሆኑም አሁን ላይ መስዋእትነት እየከፈሉ ያሉ ወጣቶችን እያመሰገንና እያደነቅን አርአያነታቸውንም እየተከተልን ሌሎቻችን እንደ አቅማችን ማገልገል እንደሚገባንም ያሳስባሉ።
‹‹ለዚህች አገር ማገልገል ጠመንጃ መተኮስ ብቻ አይደለም›› የሚሉት ሻምበል ብርኃነመስቀል ብዙ አገልግሎቶች መኖራቸውንም ይጠቁማሉ። የተማረ በዕውቀቱ፣ ሐኪም በሕክምና፣ ፀሐፊ በፀሐፊነቱ፣ የሎጅስቲክ ባለሙያ በሎጅስቲክ ሥራው በተለያየ ሙያ ውትድርና ማገልገል ይቻላል። ሻምበል ብርኃነመስቀል ስለ ውጪ ጠላቶች በተለይም ስለ ምዕራባዊያኑ እንደተናገሩት ቀጥተኛ ቅኝ መግዛት ሳይሆን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ቅኝ አገዛዝ ሀገሪቱንና ሕዝቧን የኢኮኖሚ ባርያ ማድረግ ነው የሚፈልጉት። እነሱ በሚሰጡን የሥንዴ እርዳታ እጃችንን እየጠመዘዙ የእነሡን ጉዳይ እንድናሥፈፅምላቸው ይፈልጋሉ። በተለይ ሁሌም በችግር ጊዜ ፊታቸውን እንደሚያዞሩብን ወጣቱ መዘንጋት የለበትም።
ለዚህ ማሳያነትም በኢጣሊያ ጦርነት ጊዜ አፄ ኃይለሥላሴ የተባበሩት መንግስታት ጽሕፈት ቤት ድረሥ ሄደው ‹‹ኢትዮጵያዊያን በመርዝ ጋዝ እያለቅን ነው›› ሲሏቸው የዝሆን ጆሮ ይሥጠን ማለታቸውን ያነሳሉ።
በኢትዮ ሶማሌ ጦርነት ወቅት ለመሣርያ መግዣ የተቀበሉትን ገንዘብ ክደው ኢትዮጵያውያኖችን ለሶማሌ ወረራ አሳልፈው የሠጡ መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ። ኢትዮጵያ በመካዷና በመወረሯ ሥትጮህ አልደረሱላትም። ነፃነቱን ያሥከበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነውም ይላሉ። በመሆኑም ወጣቱ እንዲህ ሆንክ፣ እንዲህ ተደረክ በማለት ዘለዓለም የእነሱ ሥንዴ ድርጎኛ ሆኖ እንዲኖር የሚፈልጉትን ምእራባዊያንና እንዲሁም ለነዚህ ደጀን የሆኑትን ወያኔ ህወሓትና ሌሎች የጥፋት ኃይሎች በደርግ ዘመነ መንግሥት ‹‹ከዘለዓለም ባርነት የአንድ ቀን ነፃነት›› እንደሚባለው ሁሉ አሸባሪውን ህወሓት በቃህ ማለት እንደሚገባ በማሳሰብ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።
እንዲሁ የቅብብሎሽ ታሪክ ባለቤት የሆኑት እናት አርበኛ ማሚቴ ምህረቱ እንደሚሉት ለሁለተኛ ጊዜ ፋሽስት ኢጣሊያ ሀገራችንን በወረረችበት ጊዜ ከወላጆቻቸው ጋር በቦረና፣ በያቤሎ፣ በሞያሌና በ12 ጠቅላይ ግዛቶች ተዘዋውረው ተዋግተዋል። ‹‹ሞት አንድ ነው። ሁለት አይደለም›› ሲሉ በሀገራቸው ህልውናና በሕዝቧ አንድነት ለመጣ ጠላት ዛሬም በ87 ዓመት እድሜያቸው እንደማይንበረከኩ፣ ገፍቶ ከመጣ ባገኙት ነገር እንደሚፋለሙትም ይገልፃሉ። እኝህ እናት አርበኛ እንደሚያስታውሱት ከላይ ጠላት ቦንብ ሲያዘንብባቸውና መርዝ ሲያርከፈክፍባቸው እነሱ በጦር፣ በጎራዴ፣ ዲሞትፎር ሌቨንና ቆመህ ጠብቀኝ በሚባለው በዱላ ጠላትን ድል ማድረግ ችለዋል። አሁን ላይ ሀገራችን ግን የተዘጋጀና የዘመነም መሣርያ አላት። ወጣቱ የሚያስፈልገው ወኔ ነው።
ይሄን ወኔ ደግሞ ከእናትና አባት አርበኞች በመውሰድ ሀገሩ በጠላት እንዳትጠቃ ሁሉም ዘብ መቆም አለበት። በተለይ የአባትና እናት አርበኛ አደራ ጭምር እንዳለበት ማሥታወሥ ይጠበቅበታል። ወጣቱ ከጥንት አርበኞች የተሠጠውን ወኔና አደራ ተቀብሎ፤ ሀገሩን ከውሥጥና ከውጪ ጠላት መከላከል ይኖርበታል። እነሱ ትላንት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። አሁን ደግሞ ተራው የእሱ ነውና የእናትና የአባት አርበኞችን ወኔ ታጥቆ ከውሥጥና ከውጪ ጠላት በመፋለም ሀገሩ ነፃነት እንድታገኝና የሠላም አየር እንድትተነፍሥ ማድረግ ይኖርበታል።
እናት አርበኛዋ የሀገር ፍቅር ሥሜትና ሥሜቱ ያሳደረባቸው ወኔ ዛሬም ነሸጥ አድርጓቸው በ87 ዓመታቸው የመጣውን ጠላት እንደማይለቁት ቢናገሩም በዕድሜ ጫና ጉልበታቸው ደክሟል። አቅም ቢያጡም ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅርና ሥሜት ዛሬም አፍላ ነው። ከእንግዲህ ወዲህ ወጣቱን በፀሎት እንጂ በአካል ሊያግዙት እንደማይችሉ ያምናሉ። እኛ ከእንግዲህ በፀሎት እንጂ በአካል ልናግዘው እንችልም ጉልበታችንም ሆነ ሁለንተናዊ አቅማችን ወጣቱ ነው ሲሉም ያሳስባሉ። እንደኝህ እናት ወጣት ለሀገሩ፤ ለነፃነቱ ዘብ መቆም አለበት። ነፃነት ሀገር፣ ነፃነት ኩራት፣ ነፃነት ማረፊያ፣ ነፃነት ከምንም ነገር በላይ መሆኑን መገንዘብ ይገባዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2014