አሜን የበጎ አድራጎት ማህበር በተለያዩ ጊዜያት ኑሯቸውን ከአገር ውጪ አድርገው በነበሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተመሰረተ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ከምስረታው ጀምሮ ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ያጡና ከወላጆቻቸው ተነጥለው የጎዳና ህይወትን ጨምሮ በችግር ወስጥ ያሉ ሕፃናትን እየተንከባከበና እያሳደገ ይገኛል። እኛም የአሜን የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆነውን ወጣት ሰለሞን ሀብቴን አነጋግረን የድርጅቱን ምስረታና ጉዞ እንደሚከተለው አቅርበናል።
አሜን የበጎ አድራጎት ማህበር በአራት ወጣቶች ራዕይ በአንዲት ቤተክርስቲያን በአጋጣሚ በተፈጠረ ግንኙነት የተመሰረተ ነው። ዋናው የሃሳቡ ጠንሳሽ ሱራፌል ወንድሙ ይባላል:: ሱራፌል ትውልዱ ኢትዮጵያ ቢሆንም ወደ አውስትራሊያ በማቅናት ሥራ እየሠራ ቤተሰብ መስርቶ ለረጅም ዓመታት የኖረ ነው። በተመሳሰይ ሰለሞንም ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ቡልጋርያ አካባቢ ሲሆን፤ ቦሌና መርካቶ አካባቢ በኤሌክትሮኒክስ ንግድ ሥራ ተሰማርቶ የሚኖር ነበር:: ነገር ግን በአንድ አጋጣሚ ወደ ቻይና በማቅናቱ ለረጅም ዓመታት ኑሮውን ቻይና አድርጎ ቆይቷል። የሱራፌል እህት ሂሩት ለረጅም ዓመት ውጭ ኖራ የመጣች ሲሆን፤ ልክ እንደ ሲሳይ ተሾመ አሁን ኑሮዋን በአገር ቤት አድርጋለች።
ከአራት ዓመት በፊት ሱራፌል እህቱን ለማየት ለአንድ ወር ወደ አዲስ አበበ በመጣበት ወቅት በተመሳሳይ ሰለሞንም ሙሉ ሥራውን በውጭ አገር ለማድረግ በመወሰኑ አዲስ አበባ በመምጣት ለአንድ ሳምንት ቤተሰቦቹን ጎብኝቶ አሳውቋቸው ሊመለስ መጥቶ ነበር። ሲሳይም ወንድሞቹ በአሜሪካና በዱባይ እየሠሩ የሚኖሩ ሲሆን፤ እሱን ሊወስዱት በዝግጅት ላይ ነበሩ።
ሱራፌል እናቱ በርካታ ሰዎችን ይደግፉ ስለነበር እሱም የተቸገሩ ሕፃናትን ለመታደግ ሁሌም ያስብ ነበር። ነገር ግን በአውስትራሊያ ትዳር መስርቶ ልጅም አፍርቶ ስለነበርና በራሱ መሥራት ስለማይችል በእህቱ በኩል አንድ ልጅ ለማሳደግ ወስኗል:: ነገር ግን ባለቤቱ ሱዳናዊ ስለነበረችና ልጁም የልብ ህመምተኛ ስለነበር ነገሩን በቀላል ማስርዳት አልቻለም። እናም በዚያው ሳምንት ውስጥ ሙሉውን እዛው ቤተክርስቲያን ሲመክሩ ቆይተው መገናኛና ስታዲየም አካባቢ በመሄድ ከጎዳና ልጆቹ ጋር ማሳለፍ ይጀምራሉ። ወዲያውም ጣፎ አባ ኪሮስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ቤት ተከራይተው ልጆችን መሰብሰብ ይጀምራሉ። ይህ ሲሆን ሕጋዊ ፈቃድም ሆነ እውቅና አልነበራቸውም::
ነገር ግን ሙሉ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከእነሱ ጋር ነበር። በጉዳዩ በደንብ ስላልመከሩበት ባልተስተካከለ የእቃ ግዢ በግል ሆስፒታል በሚደረግ ህክምና ለአስር ወር ሲቆዩ እጃቸው ላይ ያለው ገንዘብ እየተመናመነ መምጣት ይጀምራል። ራሳቸውም በተደጋጋሚም ለመታመም በቅተው ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን በዚህ ሁኔታ የሚቀጥሉበት ነገር ሊኖር እንደማይችል ይረዳሉ። በየግል ሲያደርጉት የነበረውንም እንቅስቃሴ እንደማያዛልቅ ይገነዘቡና በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው ይወስናሉ።
በዚህ መሀል ግን እጅግ ያልተጠበቀ ነገር ይሰማሉ:: ይህም የልብ ችግር የነበረበትና በአውስትራሊያ ይኖር የነበረው የአራት ዓመት ልጁ እዮብ ግብፅ ሆስፒታል ሕይወቱ ማለፉ ይነገራቸዋል። ከቀናት በፊት ደግሞ በህልሜ ልጄ በነጭ ልብስ ተሞሽሮ ሲያገባ አየሁ ብሎ ሲነግራቸው መልካም ዜና አለው ብለውት ስለነበር ነገሩ እጅግ ይወሳሰበባቸዋል። የባለቤቱ ቤተሰቦች ሱዳን እንዲመጣና እንዲመካከሩ ጠይቀውት ከሰለሞን ጋር ለመሄድ ቀጠሮ ይዞም ነበር። ይህ አጋጣሚ ሱራፌልን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የረበሸና የጀመሩትንም ሥራ እርስ በእርስም ሆነ ለራሳቸውም የገቡትን ቃል የሚፈታተን ነበር። በራሱ መርዶውን ለሱራፌል ለመንገር እጅግ አስፈሪ ስለነበር ከሰሙ በኋላ ሦስት ቀናት ወስደው የሰፈር አረጋውያን ሰብስበው ነበር ያደረጉት። ይህም ሆኖ ሁለት ወር ሳይሞላው ባለቤቱ ራሷን ማጥፋቷ ይነገረዋል። ከዚህ በኋላ እንደፈሩትም ነገሮችን መቆጣጠር እስኪያቅትና ዛሬም ድረስ ለጨጓራ በሽተኝነት ለመዳረግ ይበቃል።
ሰለሞንም በተመሳሳይ በአንድ ድንገተኛ ገጠመኝና መልክት ወደዚህ ለመግባት ችሏል:: ነገሩ እንዲህ ነው:: አዲስ አበባ በገባ ሰሞን አንድ ሌሊት በጣም አስፈሪ ህልም ያይና ቤተሰቦቹን ጸበል መጠመቅ እንዳለበት ነግሮ ይወጣል። በዚህ ወቅት ቤተሰቦቹ የልማት ተነሺ ሆነው ኑሯቸውን ያደረጉት መሪ አካባቢ በመሆኑ በጠዋት ወጥቶ እግሩ በመራው ይሄድና ጸበል ጸበል የሚል ታክሲ ተሳፍሮ ይጓዛል:: ታክሲውም መጨረሻ ጸበል የሚባለው አካባቢ የአሁኑ መቄዶንያ አካባቢ በሚገኘው መድሀኒዓለም ቤተክርስቲያን ያደርሰዋል። ከጸበል በኋላ እዛው ቅጽረ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደተቀመጠ በአካባቢው ከነበሩ ሦስት ልጆች ጋር ጨዋታ ይጀምራል። በዚህ መሀል እያሉም አንድ መነኩሴ ወደእነሱ ይጠጉና እንደቀልድ ‹‹ወደመጣችሁበት አትመለሱም፤ የተራቡ የተጠሙን ታበላላችሁ›› ብለዋቸው ይሄዳሉ።
የመነኩሲቷ ንግግር የበለጠ እንዲተዋወቁ የወሬ ርእስ ይሆንላቸዋል። ነገር ግን ሁሉም የጀመሯቸው የየራሳቸው እቅዶች ስለነበሯቸው የተባሉትን ነገር ሊያደርጉት እንዳማይችሉ ለራሳቸው እርግጠኞች ነበሩ። ይህም ሆኖ ተዋውቀው ደግመው ለመገናኘት ተቀጣጥረው ይለያየሉ። ነገሩ የሚዘልቅ ባይመስላቸውም እየተገናኙ መነጋገራቸውን ይቀጥላሉ። ነገርግን ራሳቸው ባይሠሩትም የአቅማቸውን አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ይወስኑና ይጀምሩታል። ቀናት ቀናትን እየወለዱ ሲመጡ ግን በአንድ ነገር ይስማማሉ:: ልጆቹን መርዳት ካለብን እዚሁ ሆነን የመጣውን እየተቀበልን ልንቀጥል ይገባል። ካልሆነ በሰው እያሠራነው ውጤታማ ሊሆን አይችልም፤ ሄደን እንመለስ ብንልም አይሆንም ከሚል ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። ወደሥራው የገቡትም ከዚህ በኋላ ነው:: ይሁን እንጂ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈዋል:: የሱራፌል ጉዳይ በተለይ ብዙ የፈተናቸው እንደነበር አይረሳውም::
ቀናት ቀናትን እየተኩ ሲሄዱም ሁሉም በአንድ ቃል በምንም ነገር ከጀመሩት ነገር እንደማይመለሱ ለራሳቸው ቃል ገብተው ሥራቸውን ይቀጥላሉ። በወሳኝ ቁርጥ ሃሳብም ለኔ ለሚሏቸው ሰዎች ይህንኑ ውሳኔያቸውን ማሳወቅ ይጀምራሉ። በጎን ደግሞ ሥራቸው ፍሬ እያፈራ መመጣቱን ይመለከታሉ:: አብዛኞዎቹ ልጆች የእነሱን አርአያ በመከተል ብዙ መሥራት ይጀምራሉ። እርስ በእርስ ይደጋገፋሉ፤ ይመካከራሉም:: ለእነሱም በማሰብ እንዳይጎዱባቸው እንዲያርፉ መምከር ይጀምራሉ። እነሱም ከምንም በላይ የግብረገብ ትምህርትና ትግበራ ላይ ትኩረት በማድረግ ማስተማራቸውን ይቀጥላሉ። ልጆቹ ተረጂ መሆናቸው እንዳይሰማቸው ያደርጉም ነበር። በዚህ ሂደትም ባለራዕዮች ምንም አይነት የራሳቸው ሕይወት እንዳይኖራቸው ይወስናሉ።
የቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ጉትጎታ ቀላል አልነበረም። ለእሱ ደግሞ ለማሳመን የሚከብድ ሁኔታ ነበር። የሰለሞን ቤተሰቦች ነገሩን ትቶ መርዳትም ካለበት ውጭ ሆኖ የራሱን ኑሮ እየኖረ እንዲረዳ ግፊት ያደርጉበታል:: ኑሯቸውን በአውሮፓ ያደረጉት የሲሳይ ወንድምና እህቶችም ስንት ለፍተን ከሀገር ልናውጣህ ስንል በዚህ ሁኔታ መቅረት አይገባህም የሚለውን ውትወታቸውን ቀጥለዋል። ባለራዕዮቹ ግን የተጠራንበት ተግባር ነው ብለው ያመኑበትን ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል:: ሥራቸውንም አጠናክረው ቀጥለዋል:: ይህም ሆኖ ምንም ከማድረጋቸው በፊት እጃቸው ላይ ያለው ገንዘብ እየተጠናቀቀ ሲመጣ የውስጥ ዲዛይን ሥራ በመሥራትና ከቅርብ ሰው ብቻ በሚያገኙት ገንዘብ የተወሰኑትን ማስቀጠል ይጀምራሉ።
ለራሳቸው በገቡት ቃል መሰረትም ሠራተኛ መቅጠር አልፈለጉም:: በዚህም ሁሉንም ነገር የሚሠሩት እነሱ ብቻ በመሆኑ ገንዘባቸውንም እየጨረሱ ይመጣሉ። በዛ ላይ አንዳንዶቹ የጎዳና ልጆች የተቀመጠ ብርና አንዳንድ ንብረት ይዘው ይጠፉባቸው ነበር። እነሱ ግን በስምምነታቸው መሠረት በተቻለ አቅም ልጆቹን በመፈለግ እንዲመለሱ ያደርጉ ነበር። በዚህ ሁኔታ ለአስር ወር ያህል ከቆየ በኋላ ቤቱ ለኪራይ ስለሚፈለግ እንዲለቁ ይነገራቸዋል። ይህን ጊዜ ይነቃሉ፤ ሥራችን ከማብላትና ከማጠጣት የዘለለ ፋይዳ ያለው ነገር ሊሆን ይገባልም ይላሉ:: በዚህም በወፍ በረር በሠሩት ጥናት ልጆቹ በጎዳና እያሉ የምግብ ችግር እንደሌለባቸው ወደፊትም እንደማይኖርባቸው በመረዳታቸው ከዚያ ያለፈ ተግባር መከወን እንዳለባቸው ይስማማሉ::
በተደጋሚ በሰበሰቡት መረጃ አብዛኛዎቹ ልጆች የእለት ጭንቃታቸው የምግብና የመጠጠ አልያም የመጠለያ ሳይሆን በየቀኑ በአማካይ እስከ ሰባ ብር የሚያወጡበትን ማስቲሽ መግዣ ነበር። ልጆቹ ማስቲሹን ስበው ከደነዘዙ የምግቡም የመኝታውም ጉዳይ ሁለተኛ ወይንም ትርፍ ነበር። አንዳንዶቹ ለማመን በሚከብድ መልኩ በቀን ከሁለት መቶ እስከ ሦስት መቶ ለማስቲሽ ያወጡ ነበር። በየቀኑ ከአምስት መቶ ጀምሮ በኪራይ የሚለመንባቸውም ነበሩ። አንዳንዶቹ ወላጆችም አፋቸውን አውጥተው ኤት ኤም ማሽኔን አልሰጥም እስከማለት ይደርሱ ነበር። ስለዚህ ልጆቹ ላይ ፍቅር ተስፋ ስለ ሀገርና የወገን ፍቅር፤ ለሰው መኖር ደግነትን መተሳሰብን ማስረጽ የመጀመሪያ ሥራቸው አደረጉም::
ማብላት ማጠጣቱ ማልበሱ ባይቆምም በእያንዳንዷ ቀን በልጆቹ ልብ ውስጥ የምትቀመጥና የምትተገበር ሃሳብ እንድትኖር መሥራትን ቀጠሉ:: ዋናው ነገር ለትውልድ የሚተላላፍ በጎነት ማስረጽ እንዲያውቁት ብቻ ሳይሆን እንዲተገብሩትም ማድረግ ተግባራቸውም ሆነ:: እያንዳንዱ ልጅ ካላው ላይ ለሌሎች በቤት ውስጥም ሆነ በመንገድ ለሚያገኘው በራሱ እጅ እንዲለግስ ያደርጋሉም:: ሁሉም ታላቅን ማክበር የግድ የሚያደርጉት የየቀን ሥራቸው ነው። የሥራ ልምዳቸው እንዲዳብርም በቤት ውስጥ የሚሠሯቸው ነገሮች ያሉ ሲሆን፤ በተለይም በተለያዩ የመልካምነት መገለጫዎች ያዘጋጁት ሰዓት አንዱ ነው። እነዚህ ሰዓታት በቁጥር ፈንታ ደግነት፣ ፍቅር፣ ርህራሄ ወዘተ ምልክት ስለተቀመጠባቸው ማንኛውም የሚጠቀምባቸው ሰው ሰዓቱን ባየ ቁጥር እነዚህን ነገሮች እንዲያስብ የሚያደርግ ነው።
በእነዚህ ጊዜያት ገቢ ማስገኛ የሆነ ነገር ይሠሩ ስላልነበር እጃቸው ላይ ያለው ገንዘብ ሲጠናቀቅ የጣፎውን ሰፊ ግቢ በመልቀቅ በሦስት ሺህ ብር ኮንዶሚኒየም ሀያት አካበቢ በመከራየት ሃያ አምስት ሆነው መኖር የጀመሩት ባለራዕዮቹ፤ የጣፎው ቤት ሰፊና ምቹ ቢሆንም በየጊዜው ገንዘብ ይጨመርባቸው ነበር:: በዚህም ከዘጠኝ ሺህ ወደ ሃያ ሺህ አድጓል:: በዚያ ላይ በኮንዶሚንየም የሚኖረው ሰው ተረበሽን ይላቸዋል:: ይህም ሆኖ ገንዘባቸው አለቀ:: የሚበላ ማጣት ሲጀምሩ ግን ወደ ገንዘብ ማሰባሰቡ መግባት ግድ እንደሆነ አመኑ:: በዚህም የጀመሩትን ፈቃድ በማውጣት በሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስን ቀጠሉ::
ፈቃድ ለማውጣት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አስር ሴቶችና ሕፃናት በኃላፊነት የሚሠራ ሮቤል የሚባል ልጅን ያነጋግረሉ። ልጁ ደግሞ እነሱ አያስታውሱትም እንጂ ዘብር ገብርኤል ጸበል አግኝቷቸው እንደሚያውቅና ሥራቸውንም እንደሚያውቅ ይነግራቸዋል። ቀጥሎም በጥያቄያቸው መሠረት ፈቃዱንም እንዲያገኙ እንዴት እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ይነግራቸዋል:: እነርሱም በተባሉት መሰረት ሥራቸውን ይጀምራሉ::
ይህ ጊዜ ለድርጅቱ መጠሪያ የሆነው አሜን የሚለውን ስያሜ የፈጠሩበት ነው:: እስከዚያ ቀን ድረስ ስያሜው ፈቃድ ባያገኝም የመድኀኒዓለም ብርሃን የበጎ አድራጎት የሚል ነበር። ታሪኩም አንዲት በጎዳና ላይ ትኖር የነበረች እናት አራት ልጆቿን እንደያዘች ሕይወቷ ያልፋል። ሮቤል እነዚህን ልጆች ማንሳት እንዳለባቸው ይነግራቸዋል:: ሴትየዋ አምስተኛ የሁለት ወር ልጅ ነበራት። ትንሹ ለክበበ ፀሐይ እንዲሰጥ ይደረግና ዓመት ያልሞላውን የዛሬውን አሜንን ጨምሮ አራቱን ይዘው ይሄዳሉ። ልጆቹ የእናታቸውን ህልፈት በአባታቸው እጅ ሲፈጸም በዓይናቸው በማየታቸውና ሲረበሹ ስለነበር የተወሰነ ጊዜ በሌላ ሰው እጅ እንዲኖሩ እስከማድረግ ተገደው ነበር። የተለያዩ የጤና እክሎችም ስለነበሩባቸው ድርጅቱ ከምንም በላይ ለእነሱ ብዙ ትኩረት ይሰጥና የተለየየ ክትትልም ያደርግ ነበር።
በአሁኑ ወቅት አሜን የበጎ አድራጎት ድርጅት በትኬት ሽያጭ በወር ለቤት ኪራይ የሚከፍለውን ስልሳ ሺህ ጨምሮ እስከ ሦስት መቶ ሺህ ብር በማወጣት ሃምሳ ልጆችን ይዞ እየተንከባከበና እያሳደገ ይገኛል። በየወሩ የሚከፍሉት ስልሳ ሺህ ብር መሰናክል ሆነባቸው እንጂ በየክፍለከተማው በመክፈት በርካቶችን ለመታደግም እቅድ አላቸው። በተለይም ያቀረቡት የቦታ ጥያቄ ከመንግሥት ምላሽ ካገኘላቸው ሁሉን ያሟላ የሕፃናት መንደር ለመመስረትና ብዙ ለመሥራት እቅድ አላቸው። ዋናው ነገር ከፍተኛ የገቢ ማስገኛ መፍጠር ነው:: ልጆቹ ተረጂነኝ ከሚለው ስነልቦና እንዲላቀቁ ለማድረግም ይህ ያግዛል ብለው ያምናሉ:: የተወሰኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ስም በደግ አይነሳም የሚለው ሰለሞን ሰዎች ያለውን ነገር በአካል በመገኘት እያዩ ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራል። ኢትዮ ቴኬኮም ባመቻቸላቸው የቴሌ ብር የገንዘብ ማሰባሰቢያም ሕብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያዳረግ ጥሪውን ያቀርባል::
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2014