የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከ2012 ዓ.ም አጋማሽ በፊት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወረ የሥነ ፅሁፍ መድረኮችን ያዘጋጅ ነበር። በጉዞዎቹም ደራሲያን እና ሌሎች ታዋቂ ሰዎችን ያሳትፍ ነበር፡፡ እነዚህ ደራሲያን እና ታዋቂ ሰዎች ጉዞው በተዘጋጀበት አካባቢ ሄደው የንባብ ልምዳቸውን ያካፍላሉ፤ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የደራሲያን ማኅበር አመራሮች በየአካባቢው ያሉ አስተዳደራዊ አመራሮችን ይጠይቁ ነበር፡፡
ለምሳሌ፤ በቅርስ አያያዝ፣ በአካባቢው ቤተ መጽሐፍት አለመኖሩን ወይም በቂ መጽሐፍት ከሌለው፣ ታሪኮችን ሰንዶ የማስቀመጥ ልምድ… የመሳሰሉትን የአካባቢውን አመራሮች ይጠይቃሉ፤ ያነሳሳሉ፣ ቃል ያስገባሉ፡፡
ማህበሩ ‹‹ብሌን›› የተሰኘ ወርሐዊ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ነበረው፡፡ በዚህ የሥነ ጽሑፍ ምሽት በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ይቀርባሉ፣ ታዋቂ ሰዎች መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ በአጠቃላይ ወጣቶችን ወደ ሀሳባዊነት የሚወስዱ ዕውቀትን የሚያስይዙ ሥራዎች ይቀርባሉ፡፡
አሁን አገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ፤ እንዲህ አይነት ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች አስፈላጊ ቢሆኑም፣ እነዚያ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችም ሆኑ ጉዞዎች ግን የሉም፤ አዳዲስ መሰል መድረኮችም አይታዩም፡፡
ይህ ለምን ሆነ ስንል የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙን ጠየቅናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የደራሲያን ማኅበር የሥነ ጽሑፍ ምሽት የተቋረጠው ከ2012 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃና በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮቪድ 19- ወረርሽኝ ነው፡፡ በዚያን ወቅት የሥነ ጽሑፍ ምሽት ማካሄድ አይቻልም፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይደረግ የነበረው ጉዞ ደግሞ በፀጥታ ችግሮችና ሥጋቶች ሳይካሄድ ቆይቷል፡፡
ኮቪድ-19 ገና አፍላ በነበረበት ወቅት የሥነ ጽሑፍ ምሽት ተቋማትም ተዘግተው እንደነበር ቢታወስም፤ አሁን ላይ ግን የኮቪድ-19 ሥጋት ያን ያህል መድረክ የሚያስቀር አይደለም፤ በውስን ተሳታፊዎች መድረኮችን ማካሄድ ይቻላል፡፡ በእዚህ አይነት መልኩ ሌሎች በርካታ አይነት መድረኮች እየተካሄዱ ናቸው፡፡
አሁን ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጎ የሥነ ጽሑፍ መድረክ ማዘጋጀት እንደሚቻል ያመኑት ፕሬዚዳንቱ፣ ማኅበሩም ችግሮች አጋጥመውት እንደነበር ጠቅሰዋል። በቀጣይ ጉዞዎችንም ሆነ የሥነ ጽሑፍ ምሽቱን ለማስጀመር አዲስ ከተቀላቀሉት አመራሮች ጋር በመሆን ውይይት እየተደረገበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አቶ አበረ እንደሚሉት፤ የደራሲያን ማህበር ሰኔ 30 የንባብ ቀን ተብሎ እንዲሰየም ጥረት እያደረገ ነው። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ታላላቅ ሰዎች ተዋናይ እንዲሆኑበትም ይደረጋል፡፡ ንባብ ቢስፋፋ ሁሉም የሀሳብ ሰው ይሆን ነበር፤ ድንጋይ ውርወራና ግጭትም አይኖርም፡፡ እናቶች ልጆቻቸው ተመርቀው እንዲመጡ በጉጉት ሲጠብቁ፣ ልጆች በግጭት ምክንያት ከዩኒቨርሲቲ አቋርጠው ይመለሳሉ፤ ይህ የሚሆነው አንድም ንባብ ባለመኖሩ ነው፡፡
አቶ አበረ እንደሚሉት፤ እንዲህ እንደ አሁኑ አገር ውጥረት ላይ በሆነችበት ወቅት ኪነ ጥበብ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ሆድ የባሰውን ያረጋጋል፣ ጭንቀት ላይ የነበረውን ያነቃቃል፣ ወኔ ይቀሰቅሳል፡፡
ችግሩ ግን ብዙ ሰዎች በእንዲህ አይነት ወቅት የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን ለማቅረብ ይፈራሉ ሲሉ አቶ አበረ ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶቹ ‹‹ይሄ ቀን እስከሚያልፍ›› በሚል ፀጥ ይላሉ፤ አንዳንዶቹም የድል አጥቢያ አርበኛ ለመሆን ቁርጡ ከታወቀ በኋላ ካሸናፊው ወገን እንሆናለን ለማለት ዝምታን ይመርጣሉ ሲሉ ያብራራሉ፡፡
‹‹ኪነ ጥበብ ግን እንደዚህ አይደለም፤ መጋፈጥን ይጠይቃል፤ ኪነ ጥበብ የሚያገለግለው በእንዲህ አይነቱ የውጥረትና የጦርነት ወቅት ነው፡፡›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
አቶ አበረ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በዘመነ መሳፍንትም፣ በጣሊያን ወረራ ወቅትም ፈተና ቢያጋጥማትም እንደ አሁኑ ግን በራሷ ልጆች የተፈተነችበት ወቅት የለም፡፡ ዘመነ መሳፍንት አንድ መስፍን ከሌላ መስፍን ጋር፣ አንድ ባላባት ከሌላ ባላባት ጋር የነበረ መገዳደል እንጂ ዘር እየለየ የሚደረግ አልነበረም፡፡ በዘመነ መሳፍንትም ሆነ አስከፊ በሚባለው የጣሊያን ወረራ ጊዜ እንስሳት ታርደው ይበሉ ከሆነ እንጂ በጥይትና በከባድ መሳሪያ ግን አልተገደሉም፡፡ ሊጥ የተሰረቀበት የጦርነት ታሪክ የለም፡፡
እነዚህ ሁሉ ክስተቶች በኪነ ጥበብ መገለጽ አለባቸው የሚሉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ በሌላ ጊዜ ‹‹አካኪ ዘራፍ›› ይሉ የነበሩ ሰዎች አሁን ደፍረው ሥራዎቻቸውን ሊያቀርቡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በእንዲህ አይነት ወቅት የኪነ ጥበብ ሰዎች ሥራዎቻቸውን በድፍረት ማቅረብ እንዳለባቸው የተናገሩት የደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹እኔ ማንንም ሳልፈራ በድፍረት አቅርቤያለሁ›› ብለዋል። በአንድ መድረክ ላይ ያቀረቡትና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈውን ይህን ግጥማቸውን አገራችን ለምትገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ያለውን ፋይዳ በመመልከት እንዳለ አቅርበነዋል፡፡
‹‹በል በል ሲለኝ››
በል በል በል በል ሲለኝ
ጠይቅ ጠይቅ ጠይቅ
የማን ልጅ መሆንህን ኋላህን ለማወቅ
ጠየቅኩህ ተጠየቅ
አይንና ግንባርህ ከአፍንጫህ ከንፈርህ
ፀጉርህ ራስ ቅልህ
ላይ ላዩ ሁኔታህ የአባትክን ይመስላል
እርግጥ የእሱ ልጅ ነህ?
የአባትክን ይመስላል እርግጥ ነው አየሁህ
የእርሱ ልጅ መሆንህን ማወቅ ለሚፈልግ
መረዳት ለሚሻ
እምነት ለጎደለው ሀሳበ ተልካሻ
መቅኖ አሳጥተኸው ካልሆንክበት ግርሻ
ወገቡን ቆርጠኸው እንደ ልውይ ውሻ
ጎን ውጋት ካልሆንከው ካላጣ መድረሻ
ካልሆንክበት ልምሻ
እረፍት አታገኝም እስከ ምፅዓት ድረስ እስከ መጨረሻ።
እንቶኔም ያለ እፍረት ኢትዮጵያን ለማፍረስ
ሲኦል እንገባለን በማለት ፎከረ
ድሮስ የሳጥናኤል ዝንት ዓለም መኖሪያ
ገነት መች ነበረ፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሶኦልን በመሻት ሞቱን ከመረጠው
አንድደው ለብልበው ቆስቁስበትና ይፈንዳ ያበጠው
የማን ልጅ ነህ
በቱልቱላ ብዛት
በቱሪናፋ ቃል በመሰሪ ወሬ
አትበጣጠስም አትፈርስም ሀገሬ፡፡
የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲል የዕውቀት አሳሽ
እዚህ አገር ገንቢ እዚያ ደግሞ አፍራሽ
የአባ ዋጠው ሙሄ የዘርዓያዕቆብ
የአባ ኮስትር በላይ የመይሳው ካሳ
ይቅርና ተኮሶ ፈሪ የሚያርበደብድ
ስሙ እንኳን ሲነሳ
በመልቲ ፋሽስቶች ደባ እና ቅስቀሳ
የማይበገረው
ዑመር ሰመተርን ከቆራሄ አምጣና
እውነቱን ንገረው
የአፋሩ ነበልባል የኤርታሌው ነቢል
ሱልጣን አሊሚራህ ለሰንደቅ ዓላማው
መቼም ቀን የማይወልቅ
የደቡቡ አንበሳ ክንዱ ሳይዝል ቀጥኖ
ዓለም አቀፋዊው የነፃነት ፋኖ
የአብዲሳ አጋ ልጆች በህይወት እያሉ
ሀገር ይደፈራል ኧረ እንደምን ሆኖኧረ እንዴት ተደርጎ አፈር ሳይጫንህ አገርህ ይፈርሳል
እንዲያውም በጠንካራ ክንድህ በጽኑ አንድነትህ
የእነ እንቶኔ ምሽግ ይደረማመሳል
አዎና ይፈርሳል ይነዳል ይጨሳል፡፡
የእሳት አሎሎህን ከእግሮችህ ሥር ወድቆ እንደ ጨው ይልሳል
እንኳንስ ወግተውን ነክተውን በነገር
ትኋን ቁንጫውም አላስተኛን ነበር
አለ ያ አቅራሪ ልቡ ባዘነ ቀን በተከፋ ለታ
አዎና ከፍቶናል
አዝነናል ባዝነናል
በአገር ሲመጡብን እንዲያ ነን ያመናል
የመዩ ልጆች ነን አጥንቱ ህሉዕ ነው ቆሞ ይወቅሰናል
ሲንቁን አንወድም መሞት ይሻለናል
በጠላት ሥር ወድቆ በግፍ ከመረገጥ
ሞት በስንት ጣዕሙ ለማይቀረው ነገር
ሞት ነው የሚመረጥ
እንደነ ካስትሮ እንደነ ቼ ጉቬራ
በነበረ ታሪክ በአባቶችህ ኩራ
እንደ አድዋ ጀግኖች ሌላ ታሪክ ሥራ፡፡
በህይወት እያለህ አገር እንደ ቂጣ አይቆራረስም
አንተም ጋ እሳት አለ ያነዳል አይጨስም
ከተቀጣጠለ እንዲህ በቀላሉ ከቶ አይመለስም
አዎ
የኤርታሌን ነድድ ፍሙን የመሰለ
ሲዖል የሚጨምር አንተም ጋ እሳት አለ
አይጠፋም ይነዳል
ዓለም ጉድ እያለ ወደፊት ይነጉዳል
ቀጥቃጩን ይቀጣል አንዳጁን ያነዳል
ጎርፍ እንደበዛበት እንደሰከረ ዓሳ
ምነው እነ እንቶኔ በድንገት አበዱ ተንቀዠቀዡሳ፡፡
ውቀጠው እንደ ገብስ እንደ በርበሬ አስጣው
ቆስቁስበትና መቅኖውን አሳጣው
እግር እግሩን ሰባብረህ ግንባሩን ፍለጠው
ፍለጠው እንደ እንጨት አንድደው እንደ አጋም
በሀገር ለመጣ ምህረትም አይረጋም፡፡
ለየብቻ ሲያዩህ ሚስማር ትመስላለህ
በወቀሩህ ቁጥር ኃይልህ ይበረታል
አዎ ትጸናለህ!
ልብ አርግልኝ ጓዴ
አርሶ በሌ አባትህ እግሮቹ ቀጫጫ
ልቡ ግን የአንበሳ
ከእሳት ዳር ቁጭ ብሎ የተረከልህን የአባቱን ታሪኮች
ፍጹም እንዳትረሳ
የተሰቀለውን ጋሻ ጦሩን አንሳ
በመንደር ውስጥ ወሬ በተራ አሉቧልታ
መንታ መንገድ ሳትቆም ወኔህ ሳይረታ
የቀረበልህን የጊዜ እንቆቅልሽ በተናጠል ሳይሆን
አንድ ሆነህ ፍታ
ይህን ግጥም በአገሪቱ አፍላ የውጥረት ወቅት ያቀረቡት አቶ አበረ አዳሙ፤ የኪነ ጥበብ ሰዎች በእንዲህ አይነቱ ወቅት ሥራዎቻቸውን ደፈር ብለው ማቅረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር በመጪው ቅዳሜ ከአዳዲሶቹ ሥራ አስፈፃሚዎች ጋር ውይይት እንደሚኖረውና በቀጣይ መድረኮችን ስለማዘጋጀት ቅድመ ሥራዎች እንደሚጀመሩ አመላክተዋል፡፡
የአቶ አበረን አይነት ግጥሞች በዚህ ወቅት በእጅጉ ያስፈልጋሉ፡፡ እንዲህ አይነት ግጥሞች በተለያዩ መድረኮችና ዝግጅቶች ላይ ቢቀርቡ ኢትዮጵያውያንን ይበልጥ አንድ ቃል እንዲናገሩ፣ ስለጠላቶቻቸው በሚገባ እንዲገነዘቡ፣ ለአገራቸው ይበልጥ እንዲነሳሱና እንዲቆሙ ያደርጋሉ፡፡ ወቅቱ ይህን አይነት ግጥሞችን ብቻ ሳይሆኑ ግጥሞቹ የሚቀርቡባቸውን የተለያዩ መድረኮችንም በእጅጉ ይፈልጋል፡፡
እኛም እንደታዘብነው፤ የመድረክ የኪነ ጥበብ ሥራዎች በእርግጥም ተቀዛቅዘዋል፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት መነቃቃት ሲኖርባቸው በመቀዛቀዛቸው መቀጠላቸው ሊያሳስብ ይገባል፡፡
የደራሲያን ማኅበርም ያሉትን ችግሮች ተቋቁሞ አሁን ያለውን አገራዊ ሁኔታ የሚዳስሱ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን / ግጥሞችና ሌሎች የልቦለድ ስራዎችን/ በደራሲያኑ በኩል ይዞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡
እርግጥ ነው የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ፈታኝ መሆኑ ግልጽ ነው፤ በእንዲህ አይነቱ ወቅት ግን ኪነ ጥበብ ገፍቶ መውጣት አለበትና የኪነ ጥበብ ሰዎችም ሆኑ ተቋማት የሥነ ግጥም ስራዎቻቸውን ጭምሮ ሌሎች ድርሰቶቻቸውን የሚያቀርቡባቸውን መድረኮች ሊያዘጋጁ ይገባል፡፡
የአንድን ዘመን ምንነት የሚያንፀባርቀው ኪነ ጥበብ ነውና ይህ እውነታ በተለያዩ የሥነ ጽሁፍ መንገዶች ለሕዝብ እንዲቀርብ እንዲሁም እንዲሰነድ መንግሥትም ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርበታል። ደራሲዎችም ምቹ ሁኔታን ብቻ መጠበቅ የለባቸውም፤ ምቹ ሁኔታን መፍጠርም አለባቸው፤ ይህን በማድረግ ሥራዎችን በድፍረት ማቅረብን መልመድ ይኖርባቸዋል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2014