በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት በአትሌቲክስ ስፖርት ስኬታማ ጊዜን ያሳለፉና ድንቅ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ አትሌቶች እንዲሁም የስፖርት ባለሙያዎች በዓለም አትሌቲክስና በስፖርት ቤተሰቡ ምርጫ ይሸለማሉ፡፡ በዓለም አትሌቲክስ አዘጋጅነት የሚደረገው ይህ ዓመታዊ የሽልማት መርሃ ግብር በቅድሚያ እጩ አትሌቶችን በማሳወቅ ለአንድ ወር በሚቆየው ድምጽ አሰጣጥ ብልጫ ያገኘው አትሌት አሸናፊ ይሆናል፡፡ ዘንድሮ በሚካሄደው ሽልማትም እጩ የሚሆኑ አትሌቶች ከሰሞኑ ሲታወቁ የወንዶቹ ዛሬ ይለያል፡፡
እአአ ከ1988 ጀምሮ መካሄድ የጀመረው ይህ ሽልማት በሩጫ (በመም፣ በጎዳና እና በሃገር አቋራጭ)፣ በሜዳ ተግባራት እንዲሁም በእርምጃ ስፖርቶች ብልጫ ላሳዩ አትሌቶች ይሰጣል፡፡ ይህ ሽልማት በአትሌቲክስ ስፖርት ወደ ምትታወቀው ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ መጥቶ ያውቃል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸላሚ የሆነው አንጋፋው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እአአ 1998 ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ በተከታታይ ዓመት ሁለቴ (እአአ 2004 እና 2005) ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ መሰረት ደፋር፣ ገንዘቤ ዲባባ እና አልማዝ አያና የዓመቱ ምርጥ አትሌትነት ክብርን ተጎናጽፈዋል፡፡ በምርጥ ተስፈኛ አትሌቶች ዘርፍም አትሌት ሰለሞን ባረጋ ተሸላሚ ነበር፡፡ በዘንድሮው ሽልማት ላይም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ከእጩዎቹ መካከል ይካተታሉ በሚል ይጠበቃል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ ‹‹የዓለም አትሌቲክስ እንደተለመደው በዓመቱ የተሻለ ብቃት ያሳዩ አትሌቶችን ይሸልማል፡፡ እነዚህ አትሌቶች በኦሊምፒክ ባሳዩት ችሎታ ብቻም ሳይሆን በአንድ ቀን ውድድር ላይም የተሻለ ሆነው የታዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡›› ብለዋል፡፡
በእርግጥ በዚህ ዓመት በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ከሌሎች በተለየ አንዳንድ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ አትሌቶች ከባድ ችግሮች ደርሰውባቸዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም ለተሸላሚነት የሚወዳደሩትን አትሌቶች የመለየት ስራውን እንዳወሳሰበው ይናገራሉ። ‹‹እንዲያም ሆኖ በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ እንዲሁም በሌሎች ውድድሮች መድመቅ የቻሉ አትሌቶችን ለመለየት ችለናል፡፡ በዓለም አትሌቲክስ የሚዘጋጁት አምስቱ የዙር ውድድሮች እንዲሁም የአንድ ዕለት ውድድሮችም በአትሌቶች ምርጫው ውስጥ ተካተዋል›› ሲሉ ስለ ምርጫው አብራርተዋል፡፡
ይህ ውድድር አስር ዘርፎች ያሉት ሲሆን፤ የዓመቱ ምርጥ አትሌት ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ውስጥ የሚገቡት አትሌቶች በዓመቱ ምርጥ ብቃታቸውን ማሳየት የቻሉና በስፖርቱም ዕውቅናና ዝናን ያተረፉ አትሌቶች ናቸው፡፡
ምርጫው በቅድሚያ በስፖርቱ ባለሙያዎች በሁለቱም ጾታዎች አስር አስር አትሌቶችን እንዲለዩ በማድረግ በድጋሚ በሚከናወነው ምርጫ በሁለቱም ጾታ አምስት አምስት አትሌቶች ብቻ እንዲቀሩ ይሆናል። እጩዎቹ ከታወቁ በኋላም የዓለም አትሌቲክስ ኮሚቴ፣ የአትሌቲክስ ቤተሰቡ እንዲሁም ስፖርቱን የሚወድ የትኛውም ህዝብ ድምጹን ይሰጣል፡፡ በዚህ መሰረት ዛሬ አምስቱ ወንድ ምርጥ አትሌቶች የሚታወቁ ሲሆን፤ የሴቶቹ ደግሞ ነገ ይፋ ይደረጋሉ፡፡ ከወር በኋላ ደግሞ በሁለቱም ጾታ አሸናፊና ተሸላሚ የሚሆኑት አትሌቶች የሚለዩ ይሆናል፡፡
ሌላኛው በሁለቱም ጾታ የሚደረገው ሽልማት ደግሞ በዓመቱ ምርጥ ተስፈኛ አትሌቶች ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ውድድር እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ እና በስፖርቱ ለወደፊት ትልቅ ደረጃ እንደሚደርሱ ተስፋ ያሳዩ ናቸው የሚታጩት። በተመሳሳይ ለውድድሩ የሚቀርቡት አምስት አምስት አትሌቶች ሲሆኑ፤ ዝርዝራቸውም በመጪው ወር መጀመሪያ ይፋ ይደረጋል። በምርጫው ላይ ተሳታፊ የሚሆኑትም በዓለም አቀፍ የስፖርቱ ባለሙያዎች ነው፡፡
ምርጥ አሰልጣኝም የሽልማቱ ሌላኛው ዘርፍ ነው፡፡ ሌላኛው ግለሰብ፣ ቡድን አሊያም ተቋም የሚሸለምበት ደግሞ በስፖርቱ ጥሩ መነሳሳት እንዲፈጠር በማድረግ የተሳተፉ አካላት ናቸው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ አባል የሆነ ምርጥ ፌዴሬሽን፣ ምርጥ ሴት አትሌት እንዲሁም ባሉበት ፌዴሬሽን በፕሬዚዳንትነት ጥሩ ተሳትፎ ያላቸው የስፖርት አመራሮችም የሽልማቱ አካል ናቸው፡፡ በዓመቱ ምርጥ የአትሌቲክስ ፎቶግራፍ ማንሳት የቻሉም በባለሙያዎች ተወዳድረው ሽልማታቸውን ከዓለም አትሌቲክስ የሚወስዱ ይሆናል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2014