በቀጣዩ ዓመት 2022 የአፍሪካ ሴቶች አፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ለመሆንም የማጣሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ከኡጋንዳ አቻቸው ጋር ያደርጋል፡፡ ሉሲዎቹ ለሚያከናውኑት የመጀ መሪያ የማጣሪያ ጨዋታ በካምፖላ ይገኛሉ፡፡
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ቡድኑ ከመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ በካፍ የልህቀት ማዕከል ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ሉሲዎቹ ቆይታቸውን በክፍል ውስጥና በመስክ የታገዘ ጠንካራ ልምምድ ሲያከናውኑ ቆይተውም ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ ወደ ዩጋንዳ ጉዟቸውን አድርገዋል፡፡
ዝግጅቱን አስመልክቶም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እና የቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ያለው ጊዜ አጭር ቢሆንም በአካል ብቃት፣ በቴክኒክ እና በታክቲክ ዝግጅት ማድረጋቸውን አሰልጣኙ ጠቁመዋል፡፡ ተጫዋቾቹ ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ አቀባበል ያላቸው፣ ሀገራቸውን ለማስጠራት እና የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስን ከፍ ለማድረግ እጅግ ጥሩ ስሜት እንዳላቸው መግለጻቸውን ፌዴሬሽኑ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
አምበሏ ሎዛ አበራም ቡድኑ ላይ ያለው የመነቃቃት መንፈስ ጥሩ መሆኑን ጠቁማለች። ተግባብቶ በመስራትና ሁሉም የራሱን አስተዋጽኦ በማድረግ ታሪክ ለመጻፍ የሚፈልግ ትውልድ ስለሆነ ጠንክረው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቡድኑ የመልስ ጨዋታውንም ከአስር ቀናት በኋላ ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም የሚያደርግም ይሆናል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2014