በኢትዮጵያ ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው ውድድር ትናንት በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።ሊጉ በሁለት የመክፈቻ መርሀግብሮች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሲጀመርም፤ ሃዋሳ ከተማ ከጅማ አባጅፋር እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከወላይታ ድቻ ጋር ተጫውተዋል።ሊጉ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጉትን አርባ ምንጭ ከተማ፣ መከላከያን እና አዲስ አበባ ከተማን በማካተትም 16ቱ ክለቦች ወደ አዲሱ የውድድር ዓመት ፉክክር ገብተዋል።
ከረጅም ጊዜያት በኋላም እግር ኳስ ወዳዱ ህዝብ በዚህ የውድድር ዓመት ወደ ስታዲየም ሲመለስ፤ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ስታዲየሞች የአቅማቸውን አንድ አራተኛ የሚሆን ተመልካች ብቻ እንዲይዙ ተደርጓል።የስታዲየም መግቢያ ቲኬትም በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ የሚቆረጥ መሆኑን ሊግ ኮሚቴው አስታውቋል።
15 ሳምንታትን የሚሸፍነው ውድድር ከዚህ ቀደም ከተለመደው በተለየ መልኩ ጨዋታዎች ቀትር 8 ሰዓት እና ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይካሄዳሉ። ውድድሩ በርካታ ተመልካቾች እንዲኖረው በማሰብ ሰዓቱ የተመረጠ ሲሆን፤ የሚካሄድባቸው ስታዲየሞችም በምሽት ለሚካሄዱ ጨዋታዎች አመቺ ናቸው።ጨዋታዎቹ ለዘጠኝ ሳምንታት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንዲሁም ከ10ኛው ሳምንት አንስቶ ደግሞ በአዳማ የሚካሄድ ይሆናል።
በክረምቱ ሁሉም ክለቦች ሊባል በሚያደፍር ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለባቸው መቀላቀል ችለዋል።የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግም የተሳተፉ ሲኖሩ፤ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በዚህ ወቅት መንቀሳቀሱ እሙን ነው፡፡
አብዛኛዎቹ ክለቦች በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ እንዲሁም በጎፈሬ ሲዳማ ካፕ ተሳታፊ በመሆን የቅድመ ውድድር ዝግጅት ከማድረግ ባለፈ ክለባቸው ከእረፍት መልስ ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት ችለዋል።የተቀሩት ክለቦች ደግሞ በበጀት ቶሎ አለመለቀቅ ምክንያት በቂ የወዳጅነት ጨዋታ ሳያከናውኑ ወደ ውድድር ይገባሉ።አንዳንድ ክለቦችም በገንዘብ ራሳቸውን ለመቻል በማሰብ የስፖንሰር ሺፕ ፊርማ ከአጋር አካላት ጋር መፈራረማቸውም በቅድመ ውድድር ዓመቱ የታየ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ከመልቲቾይዝ አፍሪካ ሱፐር ስፖርት ጋር በመተባበር ለፕሪምየር ሊጉ አሰልጣኞች አስቀድሞ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን እንዲያገኙም አድርጓል።በመጀመሪያው ዙር ለ16 የሊጉ ተሳታፊ ዋና አሰልጣኞች በንድፈ ሃሳብና ተግባር የተደገፈ ስልጠና ሲሰጥ፤ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 32 ምክትል አሰልጣኞች ስልጠናውን እንዲያገኙ ተደርገዋል።ክለቦች ለውድድር ዓመቱ በተዘጋጀው ደንብ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይም ከሼር ካምፓኒው ጋር ውይይት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በደረጃ ልቆ እና የሌሎች ሃገራት ሊጎች በደረሱበት ልክ የተሻለ ፉክክር የሚደረግበት ውድድር ለማድረግ በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይቷል።ከእነዚህ ተግባራት መካከል አንዱ ለአሸናፊዎች የሚያበረክተው ዋንጫ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ነው።ዲዛይኑ (በመሶብ ቅርጽ) ሃገራዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ የተሞከረው ዋንጫ በውጪ ሃገር የተሰራም ነው።ይህንን ዋንጫም የእግር ኳስ ቤተሰቡ እንዲመለከተው ባለፈው ሳምንት እድል የተመቻቸ ሲሆን፤ የ2013ዓም የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ፋሲል ከተማ በቅድሚያ እንደሚወስደው ታውቋል።መርሀ ግብሩም ረቡዕ ጥቅምት 10/2014ዓ.ም የተዘጋጀ ሲሆን፤ ክለቡ በ9 ሰዓት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ እንደሚረከብም ሶከር ኢትዮጵያ በዘገባው አረጋግጧል።ዋናውን ዋንጫ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ከተረከበ በኋላም ወዲያው በመመለስ ተመሳሳዩ ዋንጫ ተዘጋጅቶ እንዳለቀ በቋሚነት እንደሚሰጠውም ተጠቁሟል፡፡
ሊጉ በዛሬ ውሎውም አዳማ ከተማን ከወልቂጤ ከተማ ሲያገናኝ፤ ወደ ሊጉ ዘንድሮ የተመለሱት አርባ ምንጭ ከተማ እና መከላከያ ይጫወታሉ።ነገ ደግሞ ባህርዳር ከተማ ከአዲስ አበባ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ይጋጠማሉ።ከነገ በስቲያ በሚደረጉ ጨዋታዎችም ቻምፒዮናው ፋሲል ከተማ ሃዲያ ሆሳዕናን ሲያስተናግድ ሰበታ ከተማ ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ይፋለማሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም