የፈረንጆቹ በጋማው ወቅት ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ በመሆኑ አብዛኛዎቹ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ይካሄዱበታል፡፡ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ከሚካሄዱት ውድድሮች መካከልም በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲንየም ደረጃ ያላቸውን ጨምሮ ዕውቅና የተሰጣቸው በርካታ ውድድሮች በመላው ዓለም እየተደረጉ ነው፡፡ በውድድሮቹ ብዙ አስደናቂ እና አሳዛኝ ነገሮችም ሲገጥሙ ይታያሉ፡፡ በዛሬው የስፖርት ማህደር ገጻችን እጅግ አደገኛ የማራቶን ውድድር የተካሄደበትን ኦሊምፒክ እናስታውሳለን፡፡
እአአ 1904 የበጋው ኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፓን ተሻግሮ በአሜሪካ ሴንት ሉዊስ ከተማ እንዲደረግ ተወሰነ፡፡ በአገሪቷ ሌሎች ታላላቅ ከተሞች እያሉ በሴንት ሉዊስ ውድድሩ የተዘጋጀበት ዋነኛው ምክንያትም በወቅቱ የሬዲዮ እና የኤክስ ሬይ ማሽኖች የተፈለሰፉባት በመሆኗ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጃፓንና ሩሲያ ጦርነት ላይ በመሆናቸው እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የታሰበውን ያህል የኦሊምፒክ ተሳታፊዎችን ማግኘት አልተቻለም ነበር፤ በጥቅሉ በኦሊምፒኩ የተካፈሉት አገራት ከ12 አይበልጡም፡፡ በኦሊምፒኩ 652 አትሌቶች ይገኛሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ የተገኙት 62ቱ ብቻ ናቸው፡፡
ታዲያ በዚህ ኦሊምፒክ በተሳታፊዎቹ ማነስ ውድድሩ ከመቀዛቀዙም ባለፈ የቅድመ ዝግጅት፣ ቅንጅትና የትኩረት ማነስ በግልጽም ታይቶበታል፡፡ በዚህ ምክንያትም ማለዳ ላይ መካሄድ የሚገባው ረጅሙ የአትሌቲክስ ውድድር ከሰዓት በኋላ እንዲካሄድ ተደረገ፡፡
ማራቶን በባህሪው ከ5-10 ዲግሪ ሴልሺየስ በሚሆን የአየር ሁኔታ ውስጥ መካሄድ እንዳለበት የሚመከር ይሁን እንጂ፤ ይህ ውድድር ግን ሙቀቱ አይሎ 30ዲግሪ ሴሊሽየስን ባለፈበት ሁኔታ ነበር የተካሄደው፡፡ እጅግ ጽናት፣ ብርታትና ልምምድ በሚያስፈልገው ሩጫ የአትሌቶችን ህይወት አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል ይታመናል፡፡
32 አትሌቶች ለመሮጥ ሲሰለፉም ከከፊሉ በቀር የተቀሩት ዕድላቸውን ለመሞከር የተቀላቀሉ እንደሆኑ ማወቅ አዳጋች አልነበረም፡፡ ለአብነት ያህልም 42 ኪሎ ሜትሮችን ለመሮጥ ሁለቱ አትሌቶች ባዶ እግራቸውን ሲገኙ፤ 10 የሚሆኑት ግሪካውያን ደግሞ በህይወታቸው አንዴም ማራቶንን ያልሞከሩ ናቸው፡፡ ኩባዊው የመልዕክት ሰራተኛ ደግሞ በስራው ባጠራቀመው ገንዘብ ወደ አሜሪካ ቢያቀናም በቁማር ምክንያት ባዶ እጁን በመቅረቱ በዚህ ውድድር ተሳትፎ ገንዘብ ለማግኘት ነበር ወደ ውድድሩ የገባው፡፡ ይህ ግራ አጋቢ ሰው በመወዳደሪያው ስፍራ ሲገኝም እጅጌው ረጅም የሆነ ሹራብ፣ ከጉልበቱ ዝቅ ተደርጎ የተቆረጠ ሱሪ እንዲሁም የዘወትር ቆዳ ጫማ ተጫምቶም ነበር፡፡
ሰዓቱ ሲደርስም በከተማዋ ጫፍ በሚገኘውና ባረጀውና ቆሻሻ በሚጣልበት ጎዳና ውድድሩ
ተጀመረ፡፡ አስደናቂው ነገር ከጎዳናው ቅርብ ርቀት ላይ ቋጥኞች የሚገኙ ሲሆን፤ የቆሻሻ ማንሻ መኪኖች እንቅስቃሴም ሙሉ ለሙሉ ያልተገደበ በመሆኑ አትሌቶቹ ከሙቀቱ ጋር ተዳምሮ ለመተንፈስም ተቸግረዋል፡፡ አትሌቶች ውሃ የሚያገኙት ከ17 ኪሎ ሜትር በኋላ ከመሆኑም ባለፈ ባለቤት አልባ የሆኑ የጎዳና ውሾች ያሳድዷቸውም ነበር፡፡
በሩጫው አጋማሽም እንደሚጠበቀው አትሌቶቹ የጤና መታወክ ይደርስባቸው ጀመር፤ ጆን ሎርደን የተባለው ሯጭ በማስመለሱ ሩጫውን አቋረጠ፡፡ ዊልያም ጋራሺያ ደግሞ ከሆድ ህመም ጋር በተያያዘ ደም ሲፈሰው፤ የውድድሩ አዘጋጆች ባይደርሱለት ህይወቱ ሊያልፍ ይችል ነበር፡፡ አሜሪካዊው ቶም ሂስክ የተባለው ሯጭም በሩጫው ወቅት በመታመሙ ሃኪም ዘንድ ቀርቦ መርዛማ ነገር በሰውነቱ ውስጥ ተገኝቷል፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ታመው ሩጫውን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡
በአንጻሩ አስቂኝ ነገሮችን ሲያደርግ የቆየው ደግሞ ኩባዊው የመልዕክት ሰራተኛ ነበር፡፡ ይህ ሯጭ በጎዳናው ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ቆሞ ከማውራቱም ባለፈ፤ የቆሻሻ አንሺ መኪኖች ላይ የሚያያቸውንና ጠቃሚ የመሰሉትን ቁሳቁስ ለመውሰድ እሰጣ አገባ ውስጥም ነበር፡፡ በሩጫው መሐል የፖም ዛፍ ሲመለከትም ዳግም ሩጫውን አቁሞ ጥቂቱን ይወስዳል፡፡ በፍሬው ምክንያትም የማስመለስና የሆድ ህመም ሲሰማው ደግሞ አሁንም ሩጫውን አቁሞ ጥቂት ለመተኛት
ይሞክራል፡፡ እንዲያም ሆኖ ሩጫውን ያጠናቀቀው 4ኛ በመሆን ነበር፡፡
ፍሬድ ሎራስ የተሰኘው ሌላው ሯጭ ደግሞ በሩጫው መካከል መኪና ተሳፍሮ ርቀቱን ካጋመሰ በኋላ፤ ወርዶ በሩጫ ውድድሩን ፈጽሟል፡፡ የሩጫው አዘጋጆችም ባለማወቃቸው አንደኛ ሆኖ መግባቱን ማረጋገጫ ቢሰጡትም በድጋሚ አሸናፊነቱን ተነጥቋል፡፡ በመጨረሻም መርዛማ ውህድ በሰውነቱ የተገኘው ሂክስ ከህመሙ እየታገለ ውድድሩ በቀዳሚነት በማጠናቀቁ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን ችሏል፡፡ ውድድሩን እንደፈጸመም አራት ሐኪሞች ህይወቱን ለማትረፍ ተረባርበውለት ወደ ጤናው ቢመለስም፤ ቀድሞ ከነበረው ክብደት 3ነጥብ5 ኪሎ ግራም የሚሆነውን በዚሁ ምክንያት አጥቶ ነበር፡፡
በውድድሩ መነሻ 32 ከነበሩት ሯጮች ከፍጻሜው የደረሱት 14ቱ ብቻ ነበሩ፡፡ ከህመሙ ጋር ታግሎ የወርቅ ሜዳሊያውን በአገሩ ያስቀረውን አትሌት ተከትለውም ፈረንሳዊው አልበርት ኮሬ እንዲሁም አሜሪካዊው አርተር ኒውተን የብር እና የነሃስ ሜዳሊያ አጥልቀዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7/2014