በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና የተሰጣቸው የጎዳና ላይ ሩጫዎች በየሳምንቱ መጨረሻ ይካሄዳሉ። በዚህ ሳምንት መጨረሻም አስር የሚሆኑ ማራቶኖች በተለያዩ ሃገራት ይከናወናሉ። ከእነዚህ ውድድሮች መካከል ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው፣ አትሌቶች ትኩረት የሚያደርጉበት እንዲሁም በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ያገኘው የአምስተርዳም ማራቶን ለ45ኛ ጊዜ ነገ ይካሄዳል።
ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከመም ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች የተሻገረው በአምስተርዳም ማራቶን ሲሆን፣ ወቅቱም እአአ 2005 ነበር። በዚህ ማራቶን ኃይሌ የገባበት 2:06:20 የሆነ ሰዓት በርቀቱ የኢትዮጵያ ክብረወሰን እንዲሁም ሁለት ሰከንዶችን በማሻሻል የቦታው ፈጣን ሰዓት በሚልም ተመዝግቧል። ጌቱ ፈለቀ የተባለ አትሌትም እአአ በ2010 የገባበት 2:05:44 የሆነ ሰዓት የቦታው ክብረወሰን ነበር።
በዚህ ማራቶን በሴቶች ክብረወሰን የተመዘገበው እአአ በ2019 ሲሆን፤ የሰዓቱ ባለቤትም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ደጊቱ አዝመራው ናት። አትሌቷ የገባችበት ሰአትም በ 2:19:26 የሆነ ሰዓት ነው። በወንዶች በኩል ደግሞ እአአ በ2018 ኬንያዊው ላውረንስ ቼሮኖ 2:04:06 የሮጠበት ይህ ሰዓት የቦታው ፈጣን ተብሎለታል።
በዚህ ውድድር ተሳታፊ የሚሆኑት ዝነኛና በርቀቱ ብቃት ያላቸው አትሌቶች እንደመሆናቸው አዲስ ክብረወሰን ይመዘገባል በሚል ይጠበቃል። በተለይ አፍሪካዊያኑ የርቀቱ ሯጮች እንደተለመደው አዲስ ውጤት ያስመዘግባሉ በሚል ቢጠበቅም ቅድመ ግምቱ ግን ወደ ኢትዮጵያ ያደላ ሆኗል።
በዚህ ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ ካረጋገጡት አትሌቶች በብቃታቸው የተመሰከረላቸውና በነገው ውድድር ላይም የበላይነቱን ይይዛሉ በሚል የሚጠበቁ ኢትዮጵያዊያን ስም በስፋት ተዘርዝሯል። በቀዳሚነት አሸናፊ እንደሚሆን የተገመተው ደግሞ በጎዳና ላይ ሩጫዎች የካበተ ልምድ ያለው አትሌት ታምራት ቶላ ነው። እአአ 2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ በ10ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ በማጥለቅ ሃገሩን ያስጠራው አትሌቱ፤ እአአ በ2017 በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በማራቶን ተሳትፎ የብር ሜዳሊያ አስመዝግቧል። በዚያው ዓመት በተካፈለበት የዱባይ ማራቶን ተካፍሎም አሸናፊ በመሆን በርቀቱ ያለውን ብቃት አሳይቷል።
የ30 ዓመቱ ታምራት የለንደን ማራቶንን የገባበት ሰዓት 2.04.11 ሲሆን፤ ከአንድ ዓመት በኋላ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በተካሄደ ሌላ ውድድር ሶስተኛ ደረጃን ቢይዝም ሰዓቱን በማሻሻል (2.04.06) ነበር ያጠናቀቀው። ይህ ሰዓት ደግሞ በአምስተርዳም ማራቶን ክብረወሰን በሚል ከዓመታት በፊት በኬንያዊው አትሌት ከተመዘገበው ጋር ይመሳሰላል። ይህም ማለት ባለፉት ዓመታት ሊሻሻል ያልቻለውን ክብረወሰን ኢትዮጵያዊው አትሌት ልምዱንና ችሎታውን ተጠቅሞ በአዲስ መልክ እንዲጽፍ ከምንጊዜውም በላይ ብቁ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
ታምራት ለቦታው ቀዳሚውን ግምት ያግኝ እንጂ በዚህ ውድድር ላይ ከሚሳተፉት መካከል የተሻለ ሰዓት ያለው ኢትዮጵያዊ አትሌት እንዳለም ተጠቁሟል። ከታምራት ቶላ በአራት ሰከንዶች የፈጠነ ሰዓት (2.04.02) ያለው አትሌት ልኡል ገብረስላሴ ነው። የ29 ዓመቱ አትሌት ይህንን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው እአአ በ2018 የዱባይ ማራቶን ተሳትፎው ነው። ከወራት በፊት በተካሄደው የሚላን ማራቶን ደግሞ 2.04.31 የሆነ ሰዓት አስመዝግቧል።
በማራቶኑ ከኢትዮጵያዊያኑ ባሻገር ኬንያዊያን አትሌቶችም የሚካፈሉ ይሁን እንጂ በተለይ በሁለቱ ኢትትዮጵያዊያን መካከል ፉክክር እንደሚደረግ ይገመታል። አየለ አብሽሮ፣ አበበ ነገዎ፣ አይቼው ባንቲ፣ ሹመት አካልነው እንዲሁም ሌሎች አትሌቶች የዚህ ውድድር አካል ናቸው።
በሴቶች በኩልም በርካታ ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት ይህ ውድድር፤ ባላቸው ፈጣን ሰዓት ለአሸናፊነት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ችሏል። ከተሳታፊ አትሌቶች ዝርዝር የተሻለ ሰዓት ያላት ገበያነሽ አየለ 02: 23፡23 የሆነ ሰዓት አላት። በአምስት ሰንድ ዘግይታ (02፡ 23፡ 28) ተከትላት የተቀመጠችው ደግሞ ሻሾ ኢንሰርሙ ናት፤ 02፡23፡52 የሆነ ሰዓት ያላት ሄቨን ኃይሉ ሶስተኛዋ አትሌት ናት። ወርቅነሽ አለሙ እና መሰረት ጎላም በዚሁ ውድድር የሚካፈሉ ሌሎች አትሌቶች ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2014