አንዳንድ ጊዜ አዕምሯችን የተማርነውንና ዓለምን የተረዳንበትን መንገድ አስቶን ያደግንበትን ማህበረሰብ ኋላ ቀር አስተሳሰብ፤ ጎጂ ባህልና ወግ አድንወርስ ያደርገናል። እንደህሊናችን ሳይሆን እንደ አካባቢያችንና እንደ ማህበረሰባችን እንድናድር፤ ምክንያታዊነትን ትተን ዘልማዳዊ እንድንሆን ይጫነናል።
ለምሳሌ፡- የቤት ውስጥ ስራ የሴት ፣ የውጭ ስራ የወንድ ነው የሚለውን ልማዳዊ ፍረጃ እንድንቀበል ያደርገናል። ሊጥ አቅጥኖ እንጀራ የሚጋገርን ወንድ ወይም በሬ ጠምዳ የምታርስን ሴት ያለ ስራ ቦታቸው የተገኙ አድርገን እንፈርጃቸዋለን ማለት ነው። የአዕምሯችን ውቅር /mind set up/ ገና በጠዋቱ ከማህበረሰቡ በወረሰው አስተሳሰብ የተቃኘ በመሆኑ እንዲህ አይነቱን አስተሳሰብ እንድናዳብር ያደርገናል።
ይህን አስተሳሰብ የቀለበሰው የአውራ አምባ ማህበረሰብ ምስጋና ይድረሰውና አሁን ላይ በየአካባቢው ስራ ሳይመርጡ የሚሰሩ ሰዎችን ማየት እየተለመደ መጥቷል። የዛሬዋ እንግዳችን በሌስትሮነት የተሰማራች የልጆች እናት ነች። በእርግጥ ብዙውን ጊዜ ሌስትሮ ሲሰሩ የሚታዩት ወንዶች ቢሆኑም ለእነርሱ ብቻ የተተወ አለመሆኑን በተግባር የሚያሳዩ አንስቶች በርካቶች ናቸው። ባለታሪካችን ከነዚህ አንዷ ነች፤ ኑሯዋን ለማሸነፍ የምታደርገው ጥረት አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው የዚህ አምድ እንግዳ ልናደርጋት ወደናል።
ብርቱካን አብርሃም ትባላለች። ትውልዷና እድገቷ ደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ነው፤ ያደገችበት አካባቢ ልዩ መጠሪያው ኩኑኖ መሆኑን እንጂ የወረዳውን ስም በውል አታውቀውም። እናትና አባቷ በመለያየታቸው ምክንያት እርሷና ታላቅ ወንድሟ ከልጅነታቸው ጀምሮ ያደጉት የእናታቸው እናት (አያታቸው) ቤት ነው። አባቷን ዛሬ ድረስ አታውቀውም። እናቷም ሌላ ባል አግብታ ራቅ ወዳለቦታ ስለምትኖር እምብዛም አይገናኙም።
ብርቱካን በልጅነቷ ከአያቷ ጋር የጉስቁልና ህይወትን እያሳለፈች ለመኖር መገደዷን ትናገራለች። አያቷ የሶስት ወር ህጻን እያለች ደረቅ ጡታቸውን እያጠቡ አሳድገዋታል። ከሚያሳርሷት ቁራሽ መሬት በስተቀር ምንም ገቢ አልነበራቸውም። ያንንም ቢሆን የሚያርሱት የደረሱ ወንዶች ልጆቻቸው ስለሆኑ የእነርሱን እጅ እያዩ የሚኖሩ ነበሩ።
ለብርቱካን ያ የልጅነት እድሜዋ ፊደል መቁጠር የምትጀምርበት ወሳኝ ሰዓት ቢሆንም በልቶ ማደር እንኳ ያልቻለችበት ፈታኝ የህይወት ጊዜ ሆኖ አልፏል። በችግር ያደገችው ብላቴና ገና ከመሬት ብቅ እንዳለች እራሷን ችላ ለማኖር ያስችላል ያለችውን አማራጮች ሁሉ ትቃኝ ጀመር። አንድ ቀን ታዲያ አንዲት እንግድነት ወደ እነርሱ ሰፈር የመጣች የሀገሬው ሰው ልጅ ማጫወት ከቻለች ይዛት መሄድ እንደምትፈልግ ትነግራታለች። ብርቱካን ሰው ቤት ተቀጥሮ መስራትን እንደ ትልቅ እድል ቆጥራ ሳታቅማማ ፈቃደኝነቷን ትገልጻለች። ኋላም እንግዳዋ ሴት ለአያቷ አሳውቃ ይዛት ወደ ወላይታ ሶዶ ከተማ ትሄዳለች።
የሰባት ዓመቷ ታዳጊ በችግር ያደገችበትን ያን የገጠር መንደሯን ትታ፤ ወላይታ ሶዶ ከተማ ትገባለች። ያን ጊዜ እግሯ ጫማ አያውቅም፤ የለበሰችውም የተበጣጠሰ ቀሚስ ነበር። የከተማውን ህይወት ቶሎ ብሎ ለመላመድ ተቸግራ ነበር። በተቀጠረችበት ቤት ልጅ እያጫወተች፣ የመመገቢያ እቃ እያጠበች፣ ቤት እያጸዳችና እየተላላከች ኑሮዋን ቀጠለች።
ብርቱካንን ከገጠሩ የችግር ኑሮ በተጨማሪ ወደ ወላይታ ከተማ ለመምጣት እንድትወስን ያደረጋት ሌላው ጉዳይ የመማር ፍላጎቷ ነበር። ገጠር እያለች በእርሷ እድሜ ያሉ ታዳጊዎች ደብተር ይዘው ከትምህርት ቤት ሲመጡ ባየች ቁጥር ምነው እነርሱን ባደረገኝ ያላለችበት ጊዜ አልነበረም። ይህን ህልሟን ከተማ ገብታ የምታሳካው መስሏት ነበር። አሰሪዋ ግን እንድትማር እድል አልሰጠቻትም። ከአቅሟ በላይ ሃላፊነትን ተሸክማ በአንድ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ተወስና መኖሯ ሆደ ባሻ አድርጓታል።
በሌላ በኩል ደልቷት ባታድግበትም ያ በልጅነቷ የቦረቀችበት መንደር ትዝታና የቤተሰቦቿ ናፍቆት በፊቷ እየተመላለሱ ይረብሿታል። ብርቱካን በዚህ የተነሳ ከአሰሪዋ ጋር መግባባት ያቅታታል፤ ነጋ ጠባ ትጨቃጨቃለች። ለበርካታ ጊዜ በትንሽ በትልቁ እያኮረፈች ከቤት ልትወጣ ሙከራዎችን ስታደርግ አሰሪዋ እያባባለች መልሳታለች።
አንድ ቀን ግን አሰሪዋ ትእግስቷ ያልቅና ሙልጭ አድርጋ ትገርፋታለች። ብርቱካን ብን ብላ ከቤት ትጠፋና የማታውቀው መንደር ሄዳ መንገድ ለመንገድ እየዞረች ታለቅሳለች። ስታለቅስ ያየቻት አንዲት ሴት ቀርባ ታናግራታለች። ብርቱካን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያሳለፈችውን የህይወት መንገድ ታስረዳታለች። በሁኔታው ያዘነችው ሴት ብርቱካንን ወደ ቤቷ ይዛት ትሄድና ታሳድራታለች።
ሀገሯ ከመመለስና ሰው ቤት ተቀጥሮ ከመስራት የትኛውን እንደምትመርጥ ትጠይቃታለች። ብርቱካን ለጊዜው የትውልድ ሀገሯና የቤተሰቦቿ ናፍቆት ቢያስቸግራትም ብትመለስ ምን አይነት ህይወት እንደሚገጥማት ስለምታውቅ ሌላ ሰው ቤት ገብቶ መስራትን ትመርጣለች። ባስኬቶ ከተማ በመምህርነት የምትሰራ እህቷ ጋር እንደትሰራ ትጠይቃታለች። ብርቱካን ፈቃደኛ ሆና ወደ ባስኬቶ ትሄዳለች። ባስኬቶ ከመምህሯ ቤት ልጆችን እያጫወተች መኖር ጀመረች። ብርቱካን ባስኬቶ መምህሯ ቤት ስትገባ የመማር እድል አገኛለሁ ብላ ተስፋ አድርጋ ነበር። ነገር ግን እንዳሰበችው አልሆነም፤ ጭራሽ የቤተሰቦቿን ወሬ እንኳን ሳትሰማ አምስት ዓመት ያህል ተቀመጠች።
በሆነ ወቅት መምህሯ ከባስኬቶ ወደ አረካ ትዛወራለች። ብርቱካን ከአሰሪዋ ጋር ወደ አረካ ከመሄዷ በፊት የናፈቋትን ዘመዶቿን አይቶ የመመለስ ጉጉት ያድርባትና እንድትሸኛት ትጠይቃታለች። አሰሪዋም ፈቃደኛ ሆና ትሸኛታለች።
ከሰባት ዓመት በኋላ የሰራችበትን ትንሽ ገንዘብ ቋጥራ ወደ አደገችብት መንደር በተለይም በችግር ውስጥ ሆነው ያሳደጓትን አያቷን ለመጠየቅ ትመለሳለች። ነገር ግን ያላሰበችው ነገር ይገጥማታል። እኚያ ከሶስት ወር ጀምሮ ደረቅ ጡታቸውን እያጠቡ ያሳደጓት አያቷ አርፈዋል። ብርቱካን እጅግ በጣም አዘነች፤ ከፋት። የአያቷ መሞት ብዙ ነገር አጎደለባት፤ በአያቷ ቤት ውስጥ የእናቷ ወንድም ትዳር መስርቶ መኖር በመጀመሩ ቤቱ ውስጥ የመኖር ፍላጎት አጣች፤ ተስፋዋ ተሟጠጠ። ብርቱካን የአያቷን ሀዘን ሳትጨርስ ወደ መጣችበት መመለስ ፈለገች።
በዚህ አጋጣሚ ለረዥም ዓመት የተለያት ወንድሟ መምጣቷን ሰምቶ ከሚኖርበት አዲስ አበባ ከተማ ወደ ወላይታ ሄዶ ያገኛታል። በአያታቸው ሞት ልባቸው የተሰበረው ወንድምና እህት የትውልድ መንደራቸው ሁኔታ አልመቻቸው ሲል ተሰዶ ለመኖር ይመክራሉ።
እርሱ ቀደም ብሎ አዲስ አበባ በመምጣት ሌስትሮ እየሰራ የመኖር ልምምድ አድርጓል። እርሷም አብራው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ሰው ቤት እየሰራች እራሷን የመለወጥ እድል እንደሚኖራት ይነግራትና ይዟት ይመጣል። እንዳለውም ሰው ቤት ያስቀጥራታል። ብቸኝነት እንዳይሰማት በተወሰነ ጊዜ እየሄደ ይጠይቃታል። ብርቱካን የአዲስ አበባን ህይወት ትለማመዳለች። ቦታ እየቀያየረች ለስድስት ዓመት ያህል በቤት ሰራተኝነት ታሳልፋለች። በኋላም ያጠራቀመችውን ገንዘብ ይዛ አንዳንድ ነገሮችን መሸጥ መለወጥ ትጀምራለች።
በዚህ ሁኔታ እያለች ከዛሬው ባለቤቷ ጋር ትተዋወቃለች። እርሷ ሸቀጦችን እየሸጠች እርሱም ሌስትሮ እየሰራ ትዳር መስርተው መኖር ይጀምራሉ። ግንፍሌ አካባቢ አነስተኛ ቤት በስምንት መቶ ብር ተከራይተው ሁለቱም ጠዋት ወደየስራቸው ተሰማርተው ማታ ወደ ቤታቸው ይገባሉ። ያኔ የኑሮ ውድነቱ እንደ አሁኑ አለመወደዱን የምትናገረው ብርቱካን ሰርቶ ለመኖር አይቸገሩም ነበር። የመጀመሪያ ልጇን ወልዳ ያሳደገችውም ያለምንም ችግር ነበር።
ዛሬ የሁለት ልጆች እናት ሆናለች። የመጀመሪያ ልጇ ዘጠኝ ዓመት ሆኗታል። የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ነች። ሁለተኛው ልጇ ገና አንድ ዓመቱ ነው። ብርቱካን ሁለተኛ ልጇን ነፍሰ ጡር በነበረችበት ሰዓት የኮረና ወረርሽኝ በመከሰቱ የእርሷም የባለቤቷም ገቢ አሽቆልቁሎ ነበር። የገጠማቸውን ወቅታዊ ችግር ለመቋቋም ሲሉ ወደ ክፍለ ሀገር ባለቤቷ ወላጆች ጋር ነበር የሄዱት። እርሷም እዚያው ትወልዳለች። እርሱ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ እየሰራ በሚልክላት ገንዘብ እየታረሰች ወራትን ተቀመጠች። የሚልክላት ጥቂት ገንዘብ ቀለቧን የሚሸፍን አልነበረም። እንደምንም እያቻቻለች ያንን መጥፎ ወቅት ካሳለፈች በኋላ ልጆቿን ይዛ ወደ አዲስ አበባ ትመለሳለች።
ከኮረና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ የኑሮ ውድነቱ ተባብሶ ጠብቋታል። ሌስትሮ እየሰራ በሚያገኛት ገቢ ብቻ የአራት ሰው ቀለብና አልባሳት መሸፈን ፣ የቤት ኪራይ መክፈል እንደማይቻል የተረዳችው ብርቱካን በፍጥነት ወደ ስራ ትገባለች። አነስተኛ ሸቀጦችን ገዝታ ልጆቿን አጠገቧ እያስቀመጠች መቸርቸር ትጀምራለች። ብዙም ሳትሰራ ህገ ወጥ የጎዳና ነጋዴ ተብላ እቃዋ በደንብ አስከባሪዎች ይወሰድባታል። በዚህን ጊዜ ኑሯቸው ተቃወሰ፤ በባለቤቷ ገቢ ብቻ ሁሉን ነገር ማድረግ ተሳናቸው። የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው ሰው እስኪከፍልላቸው ድረስ ተቸግረዋል። ብርቱካን ያለስራ መቀመጥ ያስከተለባትን ችግር እያየች እጇን አጣጥፋ መቀመጥ አልፈለገችም።
ምን መስራት እናዳለባት ከባለቤቷ ጋር አወጡ አወረዱ። ኋላም በአንድ የስራ ዘርፍ ላይ መሰማራት እንዳለባት ተስማሙ። የብርቱካን ባለቤት ሌስትሮነትን ለረዥም ዓመታት ሲሰራ ኖሯል። አንደላቆ ባያኖርም ለችግር የሚያጋልጥ አለመሆኑን ተረድቷል። የሁለት ሰው የሌስትሮ ገቢ አንድ ላይ ሲሆን የተሻለ አቅም ይፈጥራል ብሎ በማሰብ ብርቱካን ሌስትሮ እንድትሰራ ይመክራታል። ብዙም ደስተኛ ባትሆንም ፈቃዱን ለመሙላትና እርሱንም ለማገዝ ስትል የሌስትሮ እቃዋን አሟልታ ጫማ በመጥረግ ስራ ላይ ተሰማራች። ባለቤቷ ከእርሷ እራቅ ብሎ ሌስትሮ እየሰራ ጎን ለጎን መኪና ያጥባል።
ለመጀመሪያ ጊዜ አምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ በር ላይ ስራውን ስትጀምር እያፈረች ነበር። በተለይም ሴቶች በዚህ ስራ ላይ እምብዛም አለመሰማራታቸው እራሷን በተለየ ሁኔታ እንድትመለከት አድርጓት ነበር።
ነገር ግን ጫማ የሚያስቀቧት ሰዎች በሚሰጧት ገንቢ አስተያየትና ሞራል እየተበረታታች መጣች። የብርቱካን ገቢ ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ መጣ። ባልና ሚስቶቹ ሌስትሮ እየሰሩ ኑሯቸውን አሸንፈው ለመኖር ይጥሩ ጀመር። አሁን ብርቱካን ስራውን በደንብ ተለማምዳ ህይወቷን እየመራችበት ነው።
ብርቱካን በቀን ከሰማኒያ እስከ መቶ ሃምሳ ብር ታገኛለች። አንድ ኪዊ ቀለም በመቶ ሃያ ብር ገዝታ እስከ ሰባት መቶ ብር እንደተጣራው ትገልጻለች። ይህን ለማግኘት ግን ከሳምንት እስከ አስራ አምስት ቀን ይጠይቃል። ክረምት ከሆነም ከዚያ በላይ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። በክረምት ወቅት ጫማ የሚያስጠርጉ ሰዎች አናሳ ስለሚሆኑ ገቢዋ ይቀንሳል፤ ይህን ለማካካስም ቀለል ያሉ ሸቀጦችን አጠገቧ አድርጋ ትሸጣለች።
አሁን እነብርቱካን እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት የሚፈጥርባቸውን ጫና መቋቋም አቃታቸው እንጂ ሰርቶ የማደር ችግር የለባቸውም። ያም ሆኖ ወጪያቸውን ሸፍነው መኖር እየቻሉ ነው። አንድ ቀን ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ኑሯቸውን እንደሚቀይሩ ታምናለች። ስራን ሳያማርጡ መስራት ከተቻለና ባልና ሚስት የሚረዳዱ ከሆነ ለመቀየር ቀላል መሆኑን ከሁኔታዎች መረዳቷን ትገልጻለች። በተለይም ብድርና አንዳንድ እገዛዎች የሚያደርግላቸው አካል ቢያገኙ በአጭር ጊዜ ህይወታቸውን እንደሚለውጡ እርግጠኛ ሆናለች።
አሁን በወር ከሁለት ሺህ ብር በላይ የቤት ኪራይ እየከፈሉ፤ ሁለት ልጆችን እየተንከባከቡ፣ የምግብና የአልባሳት ችለው እየኖሩ ነው። በዚህ አጋጣሚ ቤት አከራያቸው ከሶስት ሺህ ብር በላይ የሚከራየውን ቤት በሁለት ሺህ ብር እንዲኖሩ ያደረገላቸውን እገዛ መቼም የምትረሳው አይደለም። ለዛሬ በዚህ ተሰናበትን፤ ሳምንት ሌላ ባለታሪክ ይዘንላችሁ እንቀርባለን፤ ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2014