የኢትዮጵያ ቤት ኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የ2014 ዓ.ም የውድድር ዓመቱን ከሁለት ቀናት በኋላ በሃዋሳ ከተማ ይጀምራል። በዚህ ውድድር ተፎካካሪ ለመሆንም 16ቱ የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ከዝግጅቶቻቸው መካከልም በአዲስ አበባ እና ሃዋሳ በተካሄዱ የሲቲ ካፕ ጨዋታዎች የተጫዋቾቻቸውን አቅም መፈተሽ ነበር። በዚህ ወቅትም ክለቦቹ ዝግጅታቸውን አጠቃለው ወደ ሊጉ ፍልሚያ በመንደርደር ላይ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም በቅርቡ በሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ተሳትፎ አሸናፊ የሆነው ሰበታ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የዘንድሮው የሊጉ ቅድመ ውድድር ዝግጅቱ ምን ይመስላል በሚለው ላይ ዙሪያ ከክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ምንዳ ጋር ካደረገው ቆይታ መረዳት እንደታቸለው፤ ክለቡ በሲቲ ካፕ ጨዋታው ዘንድሮ ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች የተመለከተበት ከመሆኑም ባለፈ ቻምፒዮን በመሆንም ግቡን ያሳካበት ነበር።
ክለቡ ባለፈው የውድድር ዓመት በኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ መሪነት በደረጃ ሰንጠረዡ አምስተኛ በመሆን ነበር ያጠናቀቀው። ፉክክር ከባድ በመሆኑ ምክንያት ውጤቱም በዚያው ልክ እየዋዠቀ ቢሆንም የተመዘገበው ውጤት ግን ክለቡን የሚመጥን እንደነበር ሥራ አስኪያጁ ይጠቁማሉ። በእርግጥ የተጫዋቾችን ጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ በወቅቱ ካለመክፈል ጋር በተያያዘ ችግሮች ነበሩ። ይህም በተጫዋቾች ሥነልቦና ላይ ጫና አሳድሯል፤ ነገር ግን ይህንን በማረም ወደ ውጤት ማምራት ተችሏል። በተለይ የአሰልጣኞች ቡድን በዚህ ረገድ የነበረው ሚና ከፍተኛ እና የሚያስመሰግነውም ነው ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ለዚህ የውድድር ዓመትም ክለቡ ከነሐሴ 10 አንስቶ መቀመጫውን በሃዋሳ ከተማ በማድረግና አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት ወደ ዝግጅት ገብቷል። አዲስ አሰልጣኝ ክለቡን መቀላቀሉን ተከትሎም ዕቅዱን ያሳወቀ ሲሆን፤ በ2014 የሊግ ዓመት እስከ አምስተኛ ባለው ደረጃ ለማጠናቀቅ ይሰራል። በ2015 ዓ.ም እስከ ሦስት ባለው ደረጃ እንጂሁም በ2016ዓ.ም ዋንጫውን ለማንሳትም ታቅዷል። ነገር ግን ክለቡ የተዋቀረው ልምድ ባላቸው ወጣት ተጫዋቾች በመሆኑ እንዲሁም በሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ያሳዩት ብቃት ምናልባትም እስከ ሦስተኛ ባለው ደረጃ ሊያጠናቅቅ እንደሚችል የሚያመላክት ነው።
በእርግጥ ከክለቡ ተጫዋቾች 80 በመቶ የሚሆኑት በ2013 ዓ.ም ውላቸውን ያጠናቀቁ ናቸው፤ ከተቀሩት ውስጥም ከአሰልጣኙ የአጨዋወት ስልት ጋር የማይሄዱትን በስምምነት ማሰናበት ተችሏል። በመሆኑም ሁለት የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ 14 የሚሆኑ ተጫዋቾች ወደ ክለቡ ተቀላቅለዋል። በሲቲ ካፕ ጨዋታውም በአዲሱ አሰልጣኝ የአጨዋወት ስልት መሠረት ተጫዋቾቹ ምን ያህል እንደተዋሃዱ ለመገንዘብ ተችሏል።
በአዲሱ የውድድር ዓመት እንዳለፈው ጊዜ ተጫዋቾች በደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ምክንያት ሥነ ልቦናቸው እንዳይጎዳ ለማድረግ ክለቡ አስቀድሞ በጠየቀው መሠረት ከከተማ አስተዳደሩ ግማሹ ገንዘብ ተለቆለታል። በመሆኑም የደመወዝ ችግር እንደማይኖርበት ሥራ አስኪያጁ ይጠቁማሉ፤ ነገር ግን የጥቅማ ጥቅምና የውል ገንዘብ ለመክፈል ጊዜ እንደሚያስፈልግ ከተጫቾቹ ጋር መነጋገር ተችሏል። በቀጣይም ከፕሪሚየር ሊጉ አወዳዳሪ እንዲሁም ከሌሎች አካላት በሚገኝ ገንዘብ በመሸፈን ስኬታማ ዓመት ለማሳለፍ ጥረት ይደረጋል። ከዚህ መሰሉ ስጋት በዘላቂነት ለመላቀቅም ክለቡ አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
እንደሚታወቀው የሰበታ ከተማ የኢንዱስትሪ አካባቢ ነው፤ ከ600 በላይ የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች ያሉበት ነው። በመሆኑም እነዚህ ባለሀብቶች ክለብ ውስጥ ገብተው እንዲንቀሳቀሱ ክለቡ በመወያየትና ዕቅድ በማውጣት ክለቡን ከመንግሥት ድጎማ ለማላቀቅ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ይህንን ለማድረግም አደረጃጀቱንና አመሰራረቱን ማስተካከል እንዲሁም ደንቡን በመቀየር ወደ ሕዝባዊነት መውሰድ አስፈላጊ ነው። ከተማ አስተዳደሩ ለማህበረሰቡ ለሚያውለው የመሠረተ ልማት ወጪ ቀንሶ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለክለቡ ያውላል። እንደ ሜታ ያሉ አሁንም በስፖንሰርነት ከክለቡ ጋር እየሰሩ ናቸው። በመሆኑም ክለቡን ከመንግሥት ድጎማ ለማላቀቅ አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
ከዋናው የሰበታ ከተማ ጎን ለጎን በተያዘው ዓመት በታዳጊዎች ላይ መስራት የጀመረ ሲሆን፤ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ 10 የሚሆኑ ከ23ዓመት በታች ተጫዋቾች ተሳትፈዋል። ክለብ በማቋቋም እንዲሁም የሴቶች ክለብን በማጠናከርም ተመጋጋቢና ለሀገርም ግብዓት የሚሆኑ ተጫዋቾችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም