በቀጣዩ ዓመት ኳታር (2022) በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ተካፋይ ለመሆን በሚደረገው የማጣሪያ ጨዋታ አፍሪካን ለመወከል የሚችሉ ሀገራት ሊለዩ ከጫፍ ደርሰዋል።ኢትዮጵያን ጨምሮ ከዓለም አቀፉ ታላቅ የእግር ኳስ ውድድር ውጪ የሆኑ ሀገራትም ከሰሞኑ በተካሄዱት የማጣሪያ ጨዋታዎች ለመለየትም ተችሏል።
የዓለም ትልቁ አህጉር እስያ ለሁለተኛ ጊዜ በአረብ ሀገራት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጣዩ ዓመት በኳታር እንደሚካሄድ ይታወቃል።በየአራት ዓመቱ አንዴ በሚካሄደው በዚህ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆንም ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያካሄዱ ይገኛሉ።በየአህጉራቱ የሚገኙ የእግር ኳስ ተቋማት በሚያደርጉት የማጣሪያ ጨዋታ ያለፉ ብሄራዊ ቡድኖች የእግር ኳስ ስፖርትን በበላይነት የሚመራው (ፊፋ) ባስቀመጠው ቁጥር መሰረት በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ ይሆናሉ።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የማጣሪያ ጨዋታዎቹን እያካሄደ ሲሆን፤ ለዓለም ዋንጫው ተሳትፎ የመጨረሻ ፍልሚያቸውን የሚያደርጉና ከምድባቸው ያላለፉ ሀገራትን ከወዲሁ መለየት ተችሏል።በአስር ምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ የቆየው የማጣሪያ ጨዋታው አህጉሪቷን የሚወክሉ አምስት ሀገራትን በመለየት የሚጠናቀቅ ይሆናል።በዚህም መሰረት ከየምድባቸው ባስመዘገቡት ነጥብ ብልጫ የሚያሳዩ ሁለት ቡድኖች እርስ በእርሳቸው በሚያደርጉት ፍልሚያ ወደ ኳታር የሚያመሩበትን ትኬት ይቆርጣሉ።
በምድብ ሰባት ከተደለደሉት አራት ሀገራት (ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ኢትዮጵያ እና ዚምቧቡዌ) መካከልምኢትዮጵያ እና ዚምቧቡዌ መውደቃቸውን ያረጋገጡ ቡድኖች ሆነዋል።ቀጣዮቹ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ከጋና እንዲሁም ዚምቧቡዌ ከጋና የሚያደርጉት የምድቡ የመልስ ጨዋታዎች ይኑሩ እንጂ፤ ባስመዘገቡት ነጥብ የምድቡ መሪዎችና በእግር ኳስ ችሎታቸው በአፍሪካ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን መገንባት የቻሉት ደቡብ አፍሪካ እና ጋና ከምድባቸው አልፈው ወደ ሶስተኛው ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለማለፍ የሚፋለሙ መሆናቸው ከወዲሁ ታውቋል።
በአንድ አቻ እና በሶስት አሸናፊነት ጉዟቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ባፋና ባፋናዎቹ 10 ነጥብ ይዘው በምድብ ሰባት በመሪነት ላይ ተቀምጠዋል።የጋና ብሄራዊ ቡድን (ጥቋቁር ከዋክብት) ደግሞ በአንድ ነጥብ ተበልጦ በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሶስት ነጥብ ያላት ኢትዮጵያ ሶስተኛ ናት።አንድ ጊዜ ብቻ አቻ በመውጣት በተሸናፊነት የምድቡ የመጨረሻ ስፍራ ላይ የሚገኘው የዜምቧቡዌ ብሄራዊ ቡድን አንድ ነጥብ አለው።
በሜዳዋ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተጫውታ ለመጀመሪያ ጊዜ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት የተረታችው ኢትዮጵያ በጆሃንስበርግ በነበረው ግጥሚያም ውጤት ሊቀናት አልቻለም።ኤፍኤንቢ (FNB) በተባለው የደቡብ አፍሪካ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ዋሊያዎቹ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ እንጂ፤ በራሳቸው ስህተት የበላይነቱን ለተቃራኒ ቡድን አስረክበዋል።በ11ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ በራሱ ላይ ያስቆጠረው ግብ፤ በጨዋታ ብልጫ በሜዳው በኢትዮጵያ ላይ ልዩነት ማሳየት ያልቻለውን የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድንን ተጨማሪ ሶስት ነጥብ እንዲያስመዘግብ አድርጎታል።ኢትዮጵያ በምድቡ በተፎካሪነት ለመዝለቅ ቢያንስ ነጥብ ይዛ መውጣት ይጠበቅባትም ነበር።
በጥሩ አጨዋወት አሸናፊ ለመሆን ሲጥሩ የነበሩት ዋሊያዎቹ ግን ኳስን ከመረብ ሳያገናኙ መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ላይ አራት ደቂቃ ተጨምሮ ሊጠናቀቅ ችሏል።በዚህም አንድ ጊዜ አሸናፊነትን ተቀዳጅቶ በተደጋጋሚ ሽንፈትን የተቀበለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ከምድቡ ማለፍ አለመቻሉን አረጋግጧል።በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ሆኖ የታየው የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን በማክሸፍ እንዲሁም በመከላከል በኩል አሁንም ክፍተቶች መኖራቸው የታየበት ጨዋታም ነበር።በመሆኑም ቡድኑ ከወራት በኋላ ለሚሳተፍበት የአፍሪካ ዋንጫ ስህተቶቹን አርሞ የማይገኝ ከሆነ በተመሳሳይ አሳዛኝ ውጤት ናፋቂ ቡድን እንደሚሆን ያንጸባረቀም ሆኗል።
በዕለቱ በተደረገው ሌላ ጨዋታ ዚምባብዌ በሜዳዋ ጋናን ብታስተናግድም እንግዳዋ ጋና በቶማስ ፓርቴ ብቸኛ ግብ የ1 ለምንም ውጤት በማስመዝገብ አሸናፊ ለመሆን ችላለች። ይህን ተከትሎም ጥቋቁር ከዋክብቱ ነጥባቸውን ዘጠኝ ሲያደርሱ ዚምባብዌ ከምድቧ መውደቋን አረጋግጣለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2014