ኢትዮጵያ ሰፊ የእርሻ መሬት፣ ምቹ የአየር ንብረት፣ ሁሉንም አይነት ምርቶች ለማምረት የሚያስችል የተለያዩ የግብርና ስነ-ምህዳር ቀጣናዎችን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ሃብቶችን ከመታደሏ በተጨማሪ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም የሰለጠነ እና በተመጣጣኝ ክፍያ ሊሰራ የሚችል የሰው ኃይል ተጣምረው ሀገሪቱን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርገውታል።
ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂክ ጂኦግራፊያዊ ቀጠና አንጻር ለመካከለኛ ምስራቅ እና ለአውሮፓ ካላት ቅርበት አንጻር የግብርና ዘርፍ ኢንቨስትመንት እጅግ አዋጭ ነው።ከግብርና ዘርፍ ውስጥም በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ሀገሪቱ ሰፊ እድሎች ያሏት ሲሆን የምግብ ዘይት፣ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶች፣ የስጋ እና የስጋ ምርቶች፣ የዓሳ እና የዓሳ ምርቶችን ፣ የወተት ማቀነባበር እና የወተት ተዋጽኦዎችን ማምረት፣ የሕፃናት ምግብ፣ የእንስሳት መኖ፣ ማካሮኒ እና ፓስታ፣ ሀገሪቱ ካሏት እድሎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በግብርና ዘርፍ በተለይም በምግብ ዘይት እና ፍራፍሬ ዘርፎች ሀገሪቱ በተወሰነ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆነች ቢሆንም በነዚህ ዘርፎች ካሉ እድሎችአንጻር እድሏን አሟጣ ተጠቅማለች ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።በዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶችን በማፍሰስ ከራሷ አልፋ ሌሎች ሀገራትን የመመገብ አቅም እንዳላት ቢታመንም ዛሬም የግብርና ምርቶችን ከውጭ ሀገራት እያስገባች ነው፡፡
“How we made it in Africa” ለተሰኘው ድረ ገጽ አስተያየታቸውን የሰጡት መቀመጫውን ኔዘርላንድስ ያደረገው በአፍሪካ አግሪ ቢዝነስ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው የግሮሶ ፉድስ መስራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ኑራዲን ኡስማን እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ሰፊ እድል ቢኖርም በዘርፉ በሚገባው ልክ መዋዕለ ንዋይ አልፈሰሰም፤ ሀገሪቱም ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን ባለባት ልክም ተጠቃሚ አልሆነችም።
እንደ ኑራዲን ኡስማን ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘይት ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውለው ሱፍ እና ሰማያዊ እንጆሪ የተሰኘውን ለጤና ተስማሚ የሆነው እና በዓለም አቀፍ ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ፍራፍሬ ለማምረት የሚያስችል ሰፊ እድል አለ።ሁለቱ ምርቶች ትርፋማ ሊያደርጉ የሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ቢሆኑም በሚገባው ልክ አልለሙም፡፡
ሰማያዊ እንጆሪ ለጤና ከፍተኛ ጥቅሞች ያሉት መሆኑን የሚያነሱት አቶ ኑራዲን በተለይም ለካንሰር በሽታ የሚያጋልጠውን የዲ ኤን ኤ ጉዳቶችን በመከላከል፣ ኮሌስትሮል በመከላከል እንዲሁም የደም ግፊትን በመቆጣጠር ለጤና ከፍተኛ ፋይዳ የሚያስገኝ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም ይህን ፍራፍሬ በስፋት ማምረት ቢቻል በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምርቱን ወደ ሁሉም የዓለም ጫፍ የማድረስ እድል መኖሩ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰማያዊ እንጆሪ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ትርፋማ ያደርጋል ብለዋል፡፡
አቶ ኑራዲን በተጨማሪ እንዳሉት፤ የሱፍ አበባዎችን ማምረት እና የሱፍ ዘይት ማምረት በኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሃብቶችን ተጠቃሚ ሊያደርጉ ከሚችሉ ኢንቨስትመንቶች መካከል ተጠቃሽ ነው።ምንም እንኳን የሱፍ አበባ ዘይት በመላ የአፍሪካ አህጉር ውስጥ ለምግብነት የሚውል ቢሆንም የሱፍ አበባን በማቀናበር ዘይት በማምረት በአፍሪካ አገሮች መካከል በስፋት አይነገድም።
የኢትዮጵያ መንግስት የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማምረቻው ዘርፍ በትኩረት እንዲሰሩ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያቀረበ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ኑራዲን መንግስት የሚያደርገው ጥረት መልካም ቢሆንም በቂ አይደለም ብለዋል።ጥረቱን አጠናክሮ በመቀጠል በሀገሪቱ ያለውን የሱፍ ሀብት ወደ እድል ሊቀይር እንደሚገባ ጠቁመዋል።ከሀገሪቱ አልፎ
ለአህጉሪቱ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል እድል መኖሩን አንስተዋል።ኢንቨስተሮችም በዚህ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡
ኢንቨስተሮችን ከፍተኛ ጊዜ እና ጉልበት ከሚያስወጣቸው ነገሮች አንዱ ለኢንቨስትመንት የሚቀርብ መሬት በተለያዩ እጽዋቶች የተሸፈነ መሆን እና እነዚያን እጽዋቶች ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት ነው የሚሉት አቶ ኑራዲን ፤ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡
በሌሎች ሀገሮች መዋዕለ ነዋይ ከማፍሰስ ይልቅ በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ በርካታ እድሎችን እንደሚያስገኝ የጠቆሙት አቶ ኑራዲን ኢትዮጵያ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በአንጻራዊ ሁኔታ ብዙ ድካም የማይፈልግ ለእርሻ ዝግጁ የሆነ ሰፋፊ ቦታዎች መኖሩን አንስተዋል፡፡
ስለሆነም በኢትዮጵያ ውስጥ በነዚህ ዘርፎች የሚሰማሩ ባለሀብቶች መሬትን ከእጽዋት ለማፅዳት ከፍተኛ ወጪ ማውጣት እንደማይጠበቅባቸው አብራርተዋል።“በሀገሪቱ በግብርና ዘርፍ በተለይም በሰማያዊ እንጆሪ እና በሱፍ ልማት ዘርፍ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ የሚፈልጉ ባለሃብቶች በአንድ ቀን ውስጥ መሬቱን በማዘጋጀት እና ሰብሎችን መትከል መጀመር ይችላሉ” ብለዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2014